>
5:18 pm - Saturday June 15, 7799

አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ የአድዋን ድል ታሪክ ለመመረዝ ያደረገው ጥረት!!! (አምሳሉ ገ/ኪዳን)

አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ የአድዋን ድል ታሪክ ለመመረዝ ያደረገው ጥረት!!!

አምሳሉ ገ/ኪዳን
አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ አዛኝ ቅቤ አንጓቹ አሳቢ መስሎ “ልዩነት የፈጠሩ ሕመሞቻችንን ለማከም በታሪክ የተፈጸሙ ዕንከኖችን በሙሉ አውጥተን ዳግመኛ ወደኋላ ላንመለስባቸው ተነጋግረን አንዳች መፍትሔ ላይ ለመድረስ!” በሚል ሸፍጠኛ ምክንያት ሽፋን የኢትዮጵያን ታሪክ መርዞ በማስጣል ለጥፋት ኃይሎች ምቹ ሁኔታን መፍጠር ወይም የኢትዮጵያ ሕዝብ መቸም ቢሆን እንዳይግባባና እንዳይስማማ አድርጎ ማስቀረትን ዋነኛ ዓላማው አድርጎ “ትውልድ አይደናገር እኛም እንናገር!” በሚል ርእስ መጽሐፍ ማሳተሙ ይታወሳል!!!
ያለ የሌለ እያወሩ ይሄንን ችግር ለመፍጠር የመሥራት ስልት የሸአቢያው የተስፋዬ ገብረእባብ መሆኑን ታውቃላቹህ፡፡ አቶ አንዳርጋቸው “እታገላለሁ!” ብሎ ኤርትራ በገባ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ገና ከድሮው ወያኔ ሥልጣን ሲጨብጥ ከለንደን መጥቶ ወያኔን ከተቀላቀለበት ጊዜ ጀምሮ ከተስፋዬ ገብረእባብ ጋር የልብ ጓደኞች ነበሩ!!!
አቶ አንዳርጋቸው አዛኝና ለሕዝብና ለሀገር የሚታገል መስሎ በመተወን ሥልጣን ለመያዝ ጥረት ሲያደርግ የኖረው ቢሳካለትና ሥልጣን ቢይዝ ኖሮ ምኞቱ ምን ማድረግ እንደነበር ይሄ መጽሐፉ ቁልጭ አድርጎ አሳይቶናል፡፡ ሰውየው በዚህ ፀረ አማራና ፀረ የኢትዮጵያ ታሪክ ዕኩይ አስተሳሰቡ ምኞቱ ተሳክቶለት ሥልጣን ቢይዝ ኖሮ ምን ሊያደርግ ይችል እንደነበር መገመት ለማንም የሚያቅት አይመስለኝም!!!
ጉድና ጅራት ከወደኋላ ነው እንዲሉ እኛ ይሄንን ሰይጣናዊ ገጽታውን አናውቅም “ለእኛ ብሎ በረሃ ገባልን፣ ለእኛ ብሎ የጅቦች የጭራቆች እራት ሆነልን!” እያልን ስናለቅስ ከረምን!!! በተለይ እኔማ በዚያ ክፉ ዘመን ሰው ሁሉ “አብዷል ወይ!” እስኪለኝ ድረስ እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ እየኖርኩ ትክክለኛ ፎቶየንና ትክክለኛ ስሜን ተጠቅሜ በምገለገልበት የፌስቡክ አካውንቴ አቶ አንዳርጋቸውና ዶ/ር ብርሃኑ የአግ7ን ቲሸርት ለብሰው አብረው የተነሡትን ፎቶ የባክ ግራውንድ ፒክቸር አድርጌ የተጠቀምኩ ብቸኛው ኢትዮጵያዊ ነበርኩ፡፡ ከዚህም በላይ በዚሁ የፌስቡክ አካውንቴና በታላላቅ ድረገጾች ላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ የአግ7ን ትግል እንዲደግፍ በየጊዜው ያለማሰለስ ጽሑፎችን እጽፍ ነበር!!!
ሀገር ውስጥ እዚሁ አዲስ አበባ ሆኘ ሳልደበቅ በይፋ እየታየሁ ይሄንን ሳደርግ እራሴን ለሞት ሰጥቸ ይሄንን አደርግ እንደነበር ለማናችሁም ግልጽ ይመስለኛል!!! ዓላማየ ሕዝቡ ከታሰረበት የፍርሐት ቆፈን ወጥቶ አገዛዙን በድፍረት እንዲጋፈጥ ለማበረታታት ለማጀገን ምሳሌ አርዓያ መሆን ነበር፡፡ ሙሉ ለሙሉም ተሳክቶልኛል!!! እነ ብርሃኑ በሠሯቸው ስሕተቶች ግ7ን እስከተለየንበት ጊዜ ድረስ ብዙ ዋጋ እያስከፈለንም ይሄንን ያህል ደፍረን እራሳችንን ለሞት አጋልጠን ሰጥተን ድጋፍ ስንሰጣቸውና ስናጀግናቸው የነበሩ ሰዎች ዛሬ ላይ ፀረ አማራና ፀረ ኢትዮጵያ ሆነው እንደማየት ልብን የሚያደማ ነገር ይኖራል ብየ አልገምትም!!!
ይሄው ሰው መሳይ በሸንጎ አቶ አንዳርጋቸው የተባለ ለሀገርና ለሕዝብ አዛኝ መስሎ ሲተውንብን የኖረ አስመሳይ ባንዳ በመጽሐፉ ከላይ በገለጽኩት ዕኩይ ዓላማው ምክንያት ከጠላትም አፍ ከራሱም ፈጠራ በርካታ የማይታወቁ “በታሪክ ተፈጽሟል!” ብሎ ከጠቀሳቸው መርዘኛ ወሬዎች አንዱ “በአድዋ ጦርነት ሙስሊሞች በሃይማኖታቸው ምክንያት ሳይቀበሩ ቀርተዋል!” የሚለው አንዱ ነው!!!
አቶ አንዳርጋቸው ለዚህ መርዘኛ ወሬው ዋቢ ያደረገው ሬመንድ ጆናስ የተባለ ጸሐፊ እንደፈረንጆች አቆጣጠር በ2011ዓ.ም. ያሳተመውን መጽሐፍ ነው፡፡ ጆናስ መረጃውን አገኘሁት ብሎ የጻፈው ደግሞ እ.ኤ.አ. በ1901ዓ.ም. አካባቢ አውግስቶስ ዋይሌድ ካሳተመው መጽሐፍ እንደሆነ ተገልጿል!!!
ጣሊያን ገና ሀገራችንን ለመውረር ሲያስብ ከጦርነቱ ዓመታት በፊት ጀምሮ መሳፍንቱን እርስበርስ በማናቆርና በመከፋፈል አንድ ሆነው ሀገራቸውን ከወረራ እንዳይከላከሉ ለማድረግ ከመጣር ጀምሮ ሕዝቡና መንግሥቷ ወረራውን መመከት እንዳይችሉ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት የሆነውን ግብርናውን ለማንኮታኮት፣ ሕዝቡንም በረሃብ ለመፍጀት የከብት በሽታ አስገብቶ የሀገሪቱን ከብት እስከመፍጀት የደረሰ ሸፍጥና ሴራ ሲፈጽም እንደቆየ የሚታወቅ ሆኖ እያለ አቶ አንዳርጋቸው እንዴት ይሄንን ወሬ ትክክለኛ ምንጭ አድርጎ ሊወስደው እንደቻለ የሚገርም ነው!!!
ዶ/ር መሰለ ተሬቻ ስለ አቶ አንዳርጋቸው ምንጮች ሲናገሩ “ዋይሌድ የተባለው ጸሐፊ ተናገረ የተባለው ስለአጠቃላይ እስላሞች ሳይሆን ስለአንድ ፈረሰኛ የጦር ክንፍ ነው፡፡ ጆናስ የተባለው ጸሐፊ ደግሞ በበኩሉ ይህችን ጫፍ ይይዝና እስላሞች ሁሉ እንዳልተቀበሩ አስመስሎ ጻፈ፡፡ ይህ የፈረሰኛ ክንፍ አልተቀበረም የሚለውም የዋይሌድ ድምዳሜም ቢሆን ትክክል አይመስልም፡፡ ምክንያቱም ዋይሌድ በአድዋ ጦርነት ወቅት ከቦታው አልነበረም፡፡ ከጦርነቱ ስፍራ ደረስኩ ያለው ጦርነቱ ከተጠናቀቀ ከ4 ወራት በኋላ ነው!” ብለዋል፡፡
እንግዲህ ልብ በሉ ዋይሌድ የዓይን ምስክር አይደለም፡፡ ከአራት ወራት በኋላ ነው ከቦታው የተገኘው፡፡ ከአራት ወራት በኋላ ከቦታው ሲገኝ የአጽም ክምችት ሊመለከት እንደሚችል መገመት ቀላል ነው፡፡ በርካታ የመቃብር ስፍራም አብሮ እንደሚመለከት መገመት ይቻላል፡፡ ተዘርቶ ያለው አጽም የማን እንደሆነ በዩኒፎርማቸው ወይም በደንብ ልብሳቸው መለየት የሚችል ይመስለኛል፡፡ ሰውየው ከዚያ መሀል በደንብ ልብሳቸው እየለየ ለመመልከት ሲሞክር የጣሊያን ነጭ ወታደሮችን አስከሬን ከተዘራው አጽም መሀል ሲፈልግ ሊያገኝ አልቻለም፡፡ ምክንያቱን ሲጠይቅ እንደተቀበሩ ይነገረዋል፡፡ ይሄ የኔ ግምት ነው፡፡ ምክንያቱም የእኛ ሠራዊት “ምንም ጠላት ቢሆኑም የክርስቲያን አስከሬን ክቡር ነውና፣ የክርስቲያንን አስከሬን ሳይቀብሩ ጥሎ መሆድ በሃይማኖታችን ክልክል ነውና!” በሚል ቀብረዋቸው ነበርና!!!
ከሊቢያ፣ ከሶማሊያ፣ ከኤርትራ የመጡ ለጣሊያን የሚዋጉ የባንዳ ሠራዊት አስከሬን ግን አልተቀበረም ነበረ፡፡ እስላም በመሆናቸው ሳይሆን ከጊዜ እጥረት አንጻር፡፡ ማለትም ሠራዊቱ ለቀናት እዚያው ሰንብቶ ያንን ሁሉ አስከሬን ቆፍሮ ለመቅበር መሞከር እንዲህ ዓይነት የአስከሬን ክምችት ባለበት ስፍራ መቆየት ለወረርሽኝ በሽታ ስለሚዳርግ ይሄንን አደገኛ በሽታ በመፍራት ሊያደርጉት አልቻሉም፡፡ በተቻላቸው መጠን ቦታውን ፈጥነው መልቀቅ ይኖርባቸዋል፡፡ በመሆኑም የሊቢያና የሶማሊያ እስላም የባንዳ ሠራዊት ወታደሮችን ሳይቀብሯቸው ለመሔድ ተገደዋል፡፡ ሠራዊቱም ስንቅ አልቆበት ተርቦ ስለነበረ ይሄም ለወረርሽኙ መቀስቀስ ምቹ ሁኔታ በመሆኑ ያንን ሁሉ አስከሬን ቆፍሮ መቅበር የማይቻል ሆኖበታል!!!
ዋይሌድ ግን ጣሊያኖች ከጦርነቱ ቀደም ሲል እንዳደረጉት ከአርባ ዓመት በኋላም እንደገና ሊወሩን ሲመጡ እንዳደረጉት ኢትዮጵያውያኑን በዘር በሃይማኖት በሞያ ሳይቀር ከፋፍለው ለማናቆርና አንድነት ጥንካሬ እንዳይኖራቸው ለማድረግ እንደጣሩት ለዚህ ይጠቅመኛል ብሎ በማሰቡ ይህችን ሁኔታ ለተንኮል ሥራው ሊጠቀምበት ፈለገና ጠምዝዞ ፈረሰኛ የኦሮሞ እስላሞች እንዳይቀበሩ እንደተደረጉ አድርጎ አወራ፡፡ የመንፈስ ልጁ አቶ አንዳርጋቸውም ተቀብሎ ናኘው፡፡ ይሄው ነው የሆነው!!!
ኢትዮጵያውያን እስላሞች ከዚህ ከአድዋው ጦርነት ዐሥራ አራት ዓመት በፊት ከደርቡሽ ጋር በተደረገው ጦርነት ከደርቡሽ ጎን ተሰልፈው የገዛ ሀገራቸውንና ሕዝባቸውን ወግተው ስለነበረ፡፡ እንዲሁም ቀደም ባለው ታሪክም አውዳሚው የግራኝ ወረራ ታሪክ በመኖሩ የሰውየው ወሬ በእስላሞች ላይ በቂም በቀል የተፈጸመባቸው መስሎ እንዲታይለት አድርጎታል፡፡ ይሄ የሚመስለው ግን እንደ አቶ አንዳርጋቸው ላለ ድፍን ጭንቅላት ላለው ለማይመረምርና ለማያገናዝብ ዕኩይ ዓላማ ላለው ሰው ብቻ ነው!!!
ምክንያቱም እነ ሸህ ኦጀሌንና እስላም ሠራዊታቸውን በአዲስ አበባ አቀማጥለውና ተንከባክበው የያዙ ዐፄ ምኒልክ፣ ቤተመንግሥታቸውንና መናገሻ ከተማቸውን ለእስላሞቹ ለእነ ጅማ አባጅፋርና ለእነ ሸህ ኦጀሌ አደራ ሰጥተው ለጦርነት አድዋ የዘመቱ ዐፄ ምኒልክ፣ እነኝህን ሰዎች “እስላም ሆናቹህ ባለሟሌ ልትሆኑ አትችሉም!” ያላሉና በየአካባቢያቸው የሾሙ ዐፄ ምኒልክ፣ “ሁሉም እንደእየምነቱ ይደር!” የሚል አስተሳሰብ ያላቸው ዐፄ ምኒልክ፣ ከወሎ እስላሞች ጋር ወዳጅነት ያላቸው ዐፄ ምኒልክ፣ በብስለታቸው በአስተዋይነታቸውና በትዕግሥታቸው የላቁት ዐፄ ምኒልክ፣ በርሕራሔያቸው እምዬ እስከመባል የደረሱት ዐፄ ምኒልክ “የሀገሬ ሰው ሆይ ከዚህ ቀደም የበደልኩህ አይመስለኝም….!” ብለው ባስነገሩት አዋጃቸው መሠረት ለሀገራቸው ሊሞቱ ሊሠው የዘመቱና የተሠው አርበኞችን “እስላም ስለሆኑ አትቅበሯቸው!” ሊሉ ፈጽሞ አይችሉምና ነው!!!
አንድ ፊደል የቆጠረ ሰው እንዴት ይሄንን አመዛዝኖ አገናዝቦ ወሬው ፈጠራና ለዕኩይ ዓላማ የተነገረ መሆኑን መገንዘብ ይሳነዋል??? ሲጀመር ከአድዋው ጦርነት 14 ዓመት ቀደም ብሎ ከደርቡሽ ጎን ተሰልፈው በፈጸሙት ጥፋትና በሀገር ላይ የእምነት ማጉደል ተግባር ምክንያት እፍረት ተሰምቷቸው በአድዋው ጦርነት ወቅት እዚህ ግባ ሊባል በሚችል ቁጥር ደረጃ እስላሞች አልተሳተፉም ነበር፡፡ የእነ ሸህ ኡጀሌና የእነ ጅማ አባጅፋር ጦር ደግሞ ቤተመንግሥት እንዲጠብቅ አዲስ አበባ ቀርቶ ስለነበር አልዘመተም!!!
በመሆኑም ወሬው በዘመናችን ተስፋዬ ገብረእባብ በአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ለዕኩይ ዓላማ የተነዛ የፈጠራ ወሬ መሆኑን ልናውቅ ይገባናል ነው ማሰሪያው!!!
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
Filed in: Amharic