>

የግዞት ደጆችን ለአንዱ ከፍቶ ለሌላው የመጠርቀም አካሄድ የፍትሕን ሚዛን ያዛባል!!!  (ግዮን መጽሄት)

የግዞት ደጆችን ለአንዱ ከፍቶ ለሌላው የመጠርቀም አካሄድ የፍትሕን ሚዛን ያዛባል!!! 

ግዮን መጽሄት
*  “መለያዬ ኢትዮጵያዊነቴ ነው” ብሎ ለኢትዮጵያዊያን መብትና የዴሞክራሲ ፍላጎት እውን መሆን ሲደክም ኖሮ በህወሓት/ኢህአዴግ የፈጠራ ክስ ለግዞት የተዳረገው ፍቃዱ ማኅተመወርቅ ግን የሚጮህለት ብሔረሰብና የፖለቲካ ድርጅት ስለሌለ በዕሥር እንዲማቅቅ ተፈርዶበታል፡፡
 
* ምልዓትነት የጎደለው ፍቺ ዜጎች ዋጋ ለከፈሉበት ለውጥ በቂ አይደለም!
…ነገር ግን “መርጦና ለይቶ አንድ ወገንን አስሯል” ተብሎ የትችት መርግ ሲወረወርበት ለቆየው መንግሥት፣ መርጦና ለይቶ መፍታቱ ደግሞ በጎ ተግባሩን በምልዓት እንዳንቀበለው ሳንካ መፍጠሩ አልቀረም፡፡ ለዚህ አብነት ማቅረብ ካስፈለገ ደግሞ ሩቅ ሳንሄድ ዛሬም በግፍ እስር ላይ እየማቀቀ የሚገኘውን የመጽሔታችን [ግዮን] ማኔጂንግ ዳይሬክተር ፍቃዱ ማኅተመወርቅን መጥቀስ እንችላለን፡፡ መንግሥት ለሀቀኛ ዴሞክራሲና ሠብዓዊ ልማት ቦታና ዋጋ የሰጠ ከሆነ ደግሞ “ፈታኋቸው” ከሚላቸው አመራሮችም ሆነ “የፖለቲካ ግድያዎች ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ አላቸው” ካላቸው የድርጅት አመራሮች “ወንጀል” ጋዜጠኛ ፍቃዱ ማኅተመወርቅ “ፈጽሟል” ተብሎ የታሰረበት “ወንጀል” አይበልጥምና በተፈጠረው አጋጣሚ ሊለቀቅ ይገባው ነበር፡፡
 በኢትዮጵያ ፖለቲካ ወቅታዊ አሰላለፍ ትርጉማቸው ግዝፍ ነስቶ የሚታዩት በቡድን (ብሔር) ፖለቲካ ውስጥ ተሳትፎ ያላቸው ግለሰቦች የሚጮህላቸውም ሆነ ድምጹን በጉልህ የሚያሠማላቸው አያሌ ወገን እንዳላቸው እሙን ነው፡፡ መዋቅሩ፣ አደረጃጀቱና ሚዲያው ደግሞ ለነዚህ ወገኖች አቋምና ትግል የሚያመች በመሆኑ የመንግሥትን እጅ ለመጠምዘዝ እጅጉን ቀላል ነው፡፡ ነፍስ ካወቀበት ጊዜ አንስቶ አሁን እስካለበት ዕድሜ ደረጃ ድረስ “መለያዬ ኢትዮጵያዊነቴ ነው” ብሎ ለኢትዮጵያዊያን መብትና የዴሞክራሲ ፍላጎት እውን መሆን ሲደክም ኖሮ በህወሓት/ኢህአዴግ የፈጠራ ክስ ለግዞት የተዳረገው ፍቃዱ ማኅተመወርቅ ግን የሚጮህለት ብሔረሰብና የፖለቲካ ድርጅት ስለሌለ በዕሥር እንዲማቅቅ ተፈርዶበታል፡፡
ይኼ ዓይነቱ የመንግሥት የግዞት ደጆችን ለአንዱ ከፍቶ ለሌላው የመጠርቀም አካሄድን ታዲያ የወሰዳቸውን ዕርምጃዎች ኹሉ “ቀናዒነትን፣ እውነትን፣ ፍትሕንና ርትዕን የተከተሉ ናቸውን?” የሚለው መሠረታዊ ጉዳይ ላይ የበዙ ጥያቄዎችን እንድንደረድር የሚጋብዝ ነው፡፡ አሁንም ግን እንላለን፡፡ መንግሥት ሆይ ሁሉንም በሠብዓዊነትና በሀቀኝነት ተመልከት፣ የቀሩ የግፍ እስረኞችንም ያለአግባብ ከታጎሩበት ግዞት በአስቸኳይ ልቀቅ፡፡ ያን ጊዜ ዜጎች ዘመናትን በደም ሚንዳ ዋጋ የከፈሉለት ጥያቄ በርግጥም ትርጉም ማስገኘቱን በደማቁ ማስመር እንጀምራለን!
ፍትሕ ለፍቃዱ ማኅተመወርቅ!!!
Filed in: Amharic