>

ዳንኤል ገዛኸኝ:- ሞትን የተጋፈጠ ጋዜጠኛ... (ታምሩ ገዳ)

ዳንኤል ገዛኸኝ:- ሞትን የተጋፈጠ ጋዜጠኛ…

(ታምሩ ገዳ)

ስደት ሲባል ስሙ አንድ አይነት ነው። በአውሮፕላን የተጓዘውም፣በእግሩ የኳተነውም፣በግመል ጀርባ ላይ ተፈናጦ በረሃ ያቆራረጠውም ፣ከተሰባበረ እንጨት በተሰራ ጀልባ አማካኝነት የባህር አውሬዎችን እና ማዕበለን ተቋቁሞ ካሰበው ስፍራ የደረሰው፣ ሁሉም ስደተኛ ነው።

ዳንኤል ገዛኸኝ ወንድሙ በአስቸጋሪው የኢትዮጵያ ነጻ ፕሬስ ታሪክ ውስጥ ሙያቸውን በመተግበራቸው ፣ህገመንግስታዊ እና ሰብአዊ መብታቸው የሆነው ሀሳብን በነጻ የመግለጽ መብትን እውን ለማድረግ ሲሉ ከአገዛዙ ብርቱ መከራ እና እስራት ከገጠማቸው ፣ በስተመጨረሻም ለስደት ከተዳረጉ በርካታ የነጻ ፕሬስ ጋዜጠኞች መካከል አንዱ ነው።

በህወሐት /ኢህአዲግ አገዛዝ ለስድስት ጊዜያት ወደ እስር ቤት የተወረወረው፣በዋስትና እጦት እና በተንዛዛ ቀጠሮ ለእንግልት የተዳረገው ጋዜጠኛ ዳንኤል ገዛኸኝ ምርጫ ግንቦት 97ዓም( 2005 እኤአ) ተከትሎ በኢትዮጵያ ውስጥ ተፈጠሮ በነበረው እስራት፣ወከባ እና ሞት የተነሳ በሶማሊላንድ (ቦሳሶ ) በኩል ወደ የመን ተስዷል።

የዳንኤል የስደት ጉዞው ደግሞ አልጋ በአልጋ አልነበረም።የዘመኑ ምድራዊ ሲኦል ከሆነችው የመን ለመድረስ ሰባ ሁለት ሰአታት የፈጀ የየበስ እና አርባ አንድ ሰአታት በባህር ላይ ለመጓዝ ተገዷል። በጉዞው ላይም ንጹሃኖች እንደ ቅጠል ሲረግፉ፣ሴት ልጃገረዶች ሲደፈሩ፣ዜጎች በረሀብ፣ በጥማትእና በእርዛት ሲቆራመዱ አይቷል፣እርሱም ቢሆን አብዛኛው ገፈቱን ቀምሷል።

በ እርስ በርስ ጦርነት ከምትታመሰው የባህረሰላጤዋ አገር የመን ለአራት አመታት ከስድስት ወራት በችግር አረንቋ ውስጥ ቆይቶ የአትላንቲክ ውቅያኖስን በመሻገር ወደ አሜሪካ ያቀናው ጋዜጠኛ ዳንኤል እነዚያ አሳዛኝ ገጠመኞቹን የግንቦቱን ምርጫ ሰማእታቶችን እና ከእናት አገሩ የተሰደደበት ወረሃ ግንቦትን ለማስታወስ ሲል እኤአ 2012 ሲዋን/ሲቫን በተሰኝ ባለ 279 ገጽ፣ በአማሪኛ ቋንቋ የተጻፈ መጽሐፉ አማካኝነት ከልጅነት እስከ ስደቱ የገጠመው ውጣ ውረድን ለአንባቢዎቹ አቅርቧል።

ገመና፣ሞገድ በተባሉ እና መሰል የፕሬስ ውጤቶች ላይ በዋና አዘጋጅነት የሰራው ጋዜጠኛ ዳንኤል ገዛኸኝ አስቸጋሪ እና አስገራሚው የህይወት ጉዞው በዚህ ብቻ አላበቃም ። በ ሁለቱ ኩላሊቶቹ ላይ በደረሰበት ከባድ የኩላሊት ህመም ጋር እየታገለ የሚገኘው ጋዜጠኛ ዳንኤል ባለፈው የካቲት/ፌበርዋሪ 10,2020 እኤአ ወደ ሞት ጉዞ(Journey to Death) የተሰኘ 248 ገጾች ያሉት መጽሐፉን በእንግሊዘኛ ቋንቋ ለእንባቢዎች አቅርቧል።ለብዙዎች አስተማሪ ሊሆን የሚችለው አዲሱ መጽሐፉ በአሁኑ ወቅት በአማዞን፣ ራአኩተን ኬቦ ፣ባርናስ እና ኖብል በተባሉት ዘመናዊዬቹ የኤሌክትሮኒክስ መጽሐፍት አከፋፋዬች እና ሻጮዎች አማካኝነት በማዳረስ ላይ ይገኛል።

ታሪካችንን በሲኒማ ብናቀርበውስ?:-

ሰሞኑን ከጤንነቱ እና ከሙያው ጋር በተያያዘ ከህብር ራዲዮ ጋር አጭር የስልክ ቃለምልልስ ያደረገው ጋዜጠኛ ዳንኤል ገዛኸኝ ምንም እንኳን ጤንነቱ ሙሉ በሙሉ ወደ ነበረበት ባይመለስም ከፊቱ የሚጠብቁት የህክምና ውጣ ውረዶች መኖራቸውን የጠቆመ ሲሆን በቅርብ በሩቅም የሚገኙ ወገኖቹ እና አድናቂዎቹ ላደረጉለት እገዛ በፈጣሪ ስም አመስግኗል።

ሙያውን በተመለከተ በተለይ ወደ ሞት ጉዞ/Journey to Death መጽሐፉን እንደ ሆቴል ሩዋንዳ፣ ሊሚቴሽን ጌም ፣ ኢን ቱ ዘ ዋይልድ፣ ላዋረንስ ኦፍ አረቢያ፣ አሜሪካን ስናይፐር የመሳሰሉት በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመረኮዙ ሲኒማዎች ወደ ስኒማነት ለመቀየር ጽነ ምኞት እንዳለው ገልጾ በእርሱ እና በብዙ ጓደኞቹ ላይ ከደርሰው ችግር ፣ መከራ እና እሸናፊነት ትውልድን ለማስተማር ካለው ጉጉት አኳያ ፣ ህልሙንም እውን ለማድረግ በሲኒማ ሙያ የተካኑ ወይም ለሆሊውድ እና መሰል የሲኒማ ኢንዱስትሪዎች ቀረቤታ ያላቸው ኢትዮጵያኖች በጋራ እንዴት መስራት እንደሚቻል፣ የምክር አገልግሎታቸውን እንዲለግሱት ተማጽኗል።
(ታምሩ ገዳ)

Filed in: Amharic