>

ምእራባውያን "አምባገነን" የሚል ስያሜ የሰጡት የሊቢያውያን ደግ አባት!!! (ዋሲሁን ተስፋየ) 

ምእራባውያን “አምባገነን” የሚል ስያሜ የሰጡት የሊቢያውያን ደግ አባት!!!

 

 

ዋሲሁን ተስፋየ 
ከጥቂት አመታት በፊት ደብረዘይት የሚገኘው ኩሪፍቱ ሪዞርት አልፎ አልፎ  በድንገት ብቅ የሚል አንድ እንግዳ ነበር ። ይህ ታላቅ እንግዳ ወደ ሪዞርቱ ሲመጣ አካባቢው ከመቅፅበት ይቀየራል ። አስተናጋጆች ከወትሮው የበልጥ ዝግጁና ቀልጣፋ ሆነው ያን ታላቅ ሰው ለማስተናገድ ይሯሯጣሉ ።
ከዚያም በልዩ ሁኔታ ከተዘጋጀው ፕሬዝደንሺያል ፓላስ ግቢ ውስጥ ጥይትና እሳት የማይበግረው አንድ አነስተኛ ድንኳን ይጣላል ። ይህ ድንኳን ለስሙ ድንኳን ይባል እንጂ በቅንጡ እቃዎች የተሞላ በሃር ጨርቅ የተለበጠ አረቢያን መጅሊስ እና በላባ ትራሶች የተሞላ ዘመናዊ ተንቀሳቃሽ ቤት ነው ።
ከዚያም ከድንኳኑ አጠገብ አንድ ችካል ይተከልና የግመል ግልገል ይታሰርበታል ። ይህ ድባብ ከድንኳኑና አጠገቡ ከታሰረችው ግመል ጋር እኚህ ታላቅ ሰው የተወለዱበትን ትንሿን የሲርጥ አረባዊ  መንደር ያስታውሳቸዋል ተብሎ ስለሚታሰብ ነው ።
በፕሬዝደሽያል ፓላሱ ግቢ የጋዳፊ ሴት ቦዲ ጋርዶች ቦታ ቦታቸውን ይይዙና የፕሬዝደንታቸውን ደህንነት ይጠብቃሉ ። ጋዳፊ በዚህ መልኩ በተደጋጋሚ ወደ ኢትዮጵያ እየመጡ ዘና ይሉ ነበር ። እሳቸው መጡ ሲባል ሪዞርቱ ብቻ ሳይሆን ከጥበቃ ጀምሮ ያሉ ሰራተኞች የወራት ገቢያቸውን እንደሚዘጉ እርግጠኞች ናቸው ።
ጋዳፊ ህይወታቸውን በዚህ መልኩ ከምቾት ጋር ቢያስማሙም የሚመሩትን ሃገር ህዝብም ረስተው አያውቁም ። ከጥቂት አመት በፊት ማንኛውም የሊቢያ ዜጋ ወደ ወደ ፓሪስ ለንደን ኒውዮርክ ወይም ለኑሮ  ውድ ወደሆነችው ሞስኮ የሚሄደው በስደተኝነት ሳይሆን በትላልቅ ሞሎች ተገኝቶ ሾፕ ለማድረግ ነበር ።
ዛሬ ግን ታሪክ ተቀይሯል ። .ሊቢያውያን ዛሬ ጋዳፊ ማረን ቢሉ ማንም አይሰማቸውም። ያ ወርቃማ ዘመን ዳግም ላይመጣ ቁጭትን አውርሷቸው አልፏል ተከብሮና አስከብሯቸው የኖረውን መሪ በህዝባዊ አብዮት ሽፋን እንደ ውሻ ገድለውታል። ልክ መጥፎ ቅዠት በሚመስል መልኩ ያ በቤንጋዚ ቤተመንግስት ተንደላቆ እና አንደላቋቸው የኖረውን መሪ ሸሽቷቸው ከተደበቀበት ኩይሳ ውስጥ አውጥተው ምራቅ እየተፉ ተሳልቀውበታል። ምክንያቱም ለነሱ አብዮት ማለት ያ ነበርና ! ለነሱ አብዮት ማለት የዚህን  አያታቸው የሚሆን ደግ መሪ ግንባር በጥይት በስተው ሲያጣጥር በሞባይል መቅረጽ ነበር ..
በ 1951 እ.ኤ.አ . ሊቢያ ከዋናዎቹ የአፍሪካ ድሃ ሃገራት ተርታ የምትመደብ ምስኪን ሃገር ነበረች። ይህችን ሃገር አንድ ሙአመር ጋዳፊ የተባለ ባለ ራእይ መሪ ከስር መሰረትዋ ለውጦ ታሪክዋን ገለበጠው። ወደ ስልጣን እንደመጣ የጦር ሰፈራቸውን ነጥቆ  ከሃገሩ ባባረራቸው በአሜሪካን ፈረንሳይ እና እንግሊዝ የሚዘወሩት የምእራባውያኑ ሚዲያዎች በሙአመር ጋዳፊ ላይ በለጠፉለት የአምባገነንነት ስያሜ አለም የሚያውቀው ጋዳፊ ድሃ ህዝቡን ከድህነት ማጥ ውስጥ ስቦ በቅንጦት ማኖር ቻለ። እናም በዚህ መሪ የአገዛዝ ዘመን ከንግዲህ በሊቢያ ምድር እንኳን ሊሆኑ ሊታሰቡ የማይችሉ ነገሮች ለዜጋው ይደረጉ ነበር ። ጥቂቶቹን ብንጠቅስ
አሁን በየደቂቃው የሊቢያ ዜጎች እየሞቱበት ያለውን መሬት ለማረስ የፈለገ አንድ የሊቢያ ዜጋ ማድረግ ያለበት እጅ እና እግሩን ብቻ ይዞ … ጉዳዩ ወደሚመለከተው የግብርና ቢሮ መሄድ ብቻ ነው። ከዛ ምን ያህል መሬት ማልማት እንደሚፈልግ ተጠይቆ ለእርሻ የሚሆን ለም መሬት። የሚኖርበት ቤት ለእርሻ ስራ የሚያገለግሉ ሙሉ መሳሪያዎች ያለ አንዳች ክፍያ ይሰጠው ነበር። አሁን ደግሞ ሊቢያውያን በዚህ መሬት ላይ በየደቂቃው ይገደላሉ።
እንዲህ እንደዛሬው ለሊቢያውያን መኪና ቅንጦት ከመሆኑ በፊት አንድ ዜጋ የፈለገውን አይነት መኪና መንዳት ከፈለገ የመኪናው ዋጋ ግማሹ የሚሸፈንለት በሃገሪቱ መንግስት ነበር። እድሜ በጥላቻ ላበዱ ጭፍን ተቃዋሚዎች  ዛሬ በሊቢያ አዲስ ጫማም ብርቅ ነው።
ዛሬ አንዲት የሊቢያ እናት የምታስበው በየጎሳ አለቆች በየደቂቃው በሚተኮስ አዳፍኔ ከነ ልጇ ሳትሞት በሰላም ከአራስ ቤት እንድትወጣ ነው የምትመኘው ምክንያቱም ከወለደችበት ሆስፒታል በአበባ ጉንጉን ተቀብሎ ስለወለደች ብቻ አምስት ሺህ ዶላር የሚሸልማት የጋዳፊ መንግስት የለም።
ዛሬ ለሊቢያውያን ህክምና የሚሰጡ ሆስፒታሎች ወደ መሳሪያ መጋዘንነትና ወደጦር ካምፕነት ተቀይረው ሊቢያውያን የሚታከሙበት ቦታ ከማጣታቸው በፊት አንድ የሊቢያ ዜጋ ከታመመ ከአረቡ አለምና ከአፍሪካ ተወዳዳሪ በሌለው የሊቢያ ሆስፒታሎች ታክሞ ጤንነቱ ሊመለስ ካልቻለ መንግስት ሙሉ ወጭውን ሸፍኖ በውጭ ሃገራት የሚያሳክመው ሲሆን በህክምና ላይ ባለበት ወቅትም በወር 2300 ዶላርና አንዳንድ ቦታዎች የሚንቀሳቀስበት መኪና ይመደብለት ነበር። አሁን እድሜ ለአሜሪካንና ለቀሽም አብዮተኞች ቀላል በሽታን ኣንኳን ለመታከም አበሳ ነው።
በሊቢያ ሚዲያዎች መንግስት ምን ያህል ነዳጅ ወደ አለም ገበያ እንዳቀረበ ሲዘገብ ሁሉም ዜጋ ካልኩሌተር አውጥቶ ወደ አካውንቱ ምን ያህል ብር እንደገባለት ከመንግስት ጋር ይተሳሰባል ምክንያቱም የሊቢያ መንግስት ለውጭ ገበያ ከሚያቀርበው እያንዳንዱ በርሜል ነዳጅ ሽያጭ ከሚገኘው ገቢ ላይ በእያንዳንዱ የሊቢያ ዜጋ የባንክ አካውንት ውስጥ በየጊዜው ይገባለት ነበር። እድሜ ለሰይጣናዊቷ ሃገር አሜሪካ ይሁንና ዛሬ  በሊቢያ ጥያቄው ተቀይሯል.. አሁን የሊቢያ ዜጎች መሰረታዊ ፍላጎት መኖር ብቻ ሆኗል.. ዛሬን እተርፍ ይሆን ነው ስጋታቸው ..።
Filed in: Amharic