>
5:13 pm - Thursday April 19, 9325

ኢትዮጵያ፣ ሉላዊ ካፒታሊዝም የሚያተራምሳት ሀገር? (ያሬድ ጥበቡ)

ኢትዮጵያ፣ ሉላዊ ካፒታሊዝም የሚያተራምሳት ሀገር?

 

ያሬድ ጥበቡ
የዲቨንተስ የኤሌክትሪካል ቴክኖሎጂ አምራች ኩባንያን አሳዛኝ ፍፃሜና የባለቤቱን የኢንጂነር ዳንኤል ግዛውን የእስርቤት ሰቆቃ የሚያሳየውን የዘገባ ፊልም ካየሁ በኋላ ለኢትዮጵያ አለቀስኩ። ለምን እንዲህ ይሆናል ብዬም ጠየቅኩ። ወደ እእምሮዬም የመጣው የሶስት ሰዎች ምስል ነው። የዶክተር ፍቅሩ ማሩ፣ የኤርምያስ አመልጋና የኢንጂነር ዳንኤል ግዛው ምስሎች። ሶስቱንም የሚያመሳስሏቸው ነገሮች ብዙ ናቸው። ከፍተኛ ትምህርት፣ ከፍተኛ የሥራ ልምድ፣ ከፍተኛ የሃገር ፍቅርና ሁሉም በምዕራባውያን ሀገሮች አንቱ የተባሉ ሰዎች የነበሩ መሆናቸው። ሌላው ሶስቱም የሚጋሩት ደግሞ የኢትዮጵያ የሙስና ህግ ተጠቂዎች ተደርገው በግፍ በእስር መንገላታታቸው ነው።
ዶክተር ፍቅሩ ማሩ የልብ ቀዶጥገና ባለሙያ ሲሆኑ፣ አቶ ኤርምያስ የኢንቨስትመንትና ባንኪንግ ፈርቀዳጅ ነው፣ ኢንጂነር ዳንኤል ደግሞ ከ40 በላይ የፈጠራ ሥራዎችን (patents) ያስመዘገበ የኤሌክትሪካል ኢንጂነርና ባለሀብት ነበር። ሶስቱም በኢህአዴግ ባለሥልጣናት ላይ እንዲመሰክሩ ስለተፈለገ ዘብጥያ የወረዱ ናቸው። ሁለቱ ክሳቸው ተቋርጦ ሲፈቱ ኢንጂነር ዳንኤል አሁንም በባህርዳር እስርቤት በመሰቃየት ላይ ይገኛል። ሰለዳንኤል ብዙ በተናገርኩ ደስ ይለኝ ነበር። ሆኖም ከታች የተያያዘው የቪዲዮ ፋይል በብቃት ያስረዳል፣ ተመልከቱት።
ዳንኤልን ሳውቀው ድፍን 25 ዓመታት አለፉ። የታላቅ ወንድሜ ሠርግ ላይ በሚዜነት ታጭተን ነበር ቶሮንቶ ላይ የተዋወቅነው። ወንድሜ እጅግ ከሚኮራባቸውና መልካም ምግባራቸውን አንስቶ ከማይጠግባቸው ጓደኞቹ መሀል፣ ቀዳሚ ሥፍራን የያዘው ዳንኤል ነበር። ፖላንድ የድህረ ምረቃ ትምህርት ላይ በ1970ዎቹ የተገናኙ ለ40 ዓመታት የዘለቀ ጥብቅ ወዳጅነት አላቸው። ታላቅወንድሜ ስለ ዳንኤል አንስቶ ስለማይጠግብ እኔም የማውቀው ብዙ ነው። ዳንኤል ከቴክኖሎጂ ግኝት ሥራዎቹ በተጨማሪ ከሃባሻ ለየት ያሉ ነገሮችን ማድረግ ይወዳል። ለምሳሌ በአንድ ወቅት አፍሪካን በሞተር ብስክሌት ማቋረጥ ወጥኖ፣ ከአናቷ ከግብፅ ጀምሮ እስከ ደቡብ አፍሪካ እያንደቀደቀ መክነፉ ይነገርለታል። ይህ ትልቅ ጉብዝናንና ድፍረትን፣ ተነሳሽነትንና እቅድን የሚጠይቅ ፍፃሜ ነው።
የዳንኤል ጉዳይ በጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አስተዳደር ላይ ቅሬታ እንዲሰሙኝ ካደረጉ መለስተኛ ጉዳዮች አንዱ ነው። መጀመሪያ እንደተያዘ ጥረት ከዲቬንተስ ላይ የገዛውን አክስዮን በተመለከት ከሙስና ጋር የተያያዘ ነው ብለው ያንን አምኖ በነበረከት ላይ መስክሮ እንዲወጣ የሚጠይቁ ግፊቶች ይደረጉበት እንደነበሩ እንሰማ ነበር። የዲቬንተስ የሀብት ቁመና በነጻ የአካውንቲንግ ድርጅት፣ በእርነስት ኤንድ ያንግ (Ernest & Young) የተጠና ስለነበር ዳንኤል ያንን ሰነድ ለማቅረብ በመቻሉ የነበረከት ከሳሾች በዚያ መንገድ ሊገፉበት አልቻሉም። ክሱን አቋርጠው ዳንኤልን እንደመፍታት፣ አሁን መጨረሻው ሰአት ላይ ደግሞ፣ ዲቨንተስ ከጥረት የወሰደውን የኢንቬስትመንት ገንዝብ ያለበትን የባንክ እዳ ለመክፈል ስለተጠቀመበት ይህ ወንጀል ነው የሚል የአልሞት ባይ ተጋዳይ ክስ ይዘዋል። ይህም ቢሆን በቪዲዮው ላይ እንደምታዩትና የህግ ባለሙያው አቶ ዮሃንስ እንደሚከራከሩት የፍትሐብሄር ወይም የንግድ ህግ ክስ እንጂ የወንጀል ክስ ሊሆን አይችልም። ለፍትሐ ብሔር ክስ ደግሞ የድርጅቱን ባለቤት አስሮ ድርጅቱን መበተንና ከፍተኛ እውቀትና ክህሎት ያላቸውን ኢንጂነሮችና ሌሎች ሙያተኞች ከሥራቸውና ሃገራቸው እንዲፈናቀሉ ማድረግ በራሱ ትልቅ ወንጀል ነው ብዬ አምናለሁ። ስንት የታሰበለት የትልቁ ዲቬንተስ በሮች ተዘግተው ዕውቀትና ክህሎት ያላቸው ሠራተኞቹ መበታተን የሚጠቅመው የኢትዮጵያን ጠላቶች እንጂ ኢትዮጵያን ሊሆን አይችልም።
በዳንኤል ልቦናና እምነት የነገው የአፍሪካ ሳምሰንግ ሊሆን የሚችለውን ዲቬንተስ እንዲህ አድርጎ ማሽመሽመድና መበተን ይቅር የማይባል ወንጀል ነው። ይህን አድራጊው ደግሞ የአማራ ክልል ገዢ ፓርቲና የክልሉ አስተዳደር ሆነው ስናገኛቸው፣  ሀዘናችንን በአስር እጅ የበዛ ያደርገዋል። በቅርቡ የጥረት የቀድሞ ባለሥልጣን የነበሩት አቶ ወንድወሰን በኢትዮ ፎረም ቃለምልልስ ላይ ቀርበው በምስክርነት ተጠርቼ ጠቅላይ ፍርድቤት ቀርቤ ነበር ጉዳዩ የፌዴራል ክስ ሆኗል ማለታቸው፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ግፍ ለማስቆም ቀጥተኛ ችሎታ ስላላቸው፣ በኢንጂነር ዳንኤል ነፃነት የማይተማመኑ እንኳ ቢሆን፣ ለኢትዮጵያ ሲባል፣ እውቀትና ክህሎት ያላቸው የኤሌክትሮኒክስና የሶፍትዌር ኢንጂነሮች እንዳይበታተኑና ሃገር ለቅው እንዳይፈናቀሉ ለማድረግ፣ በዳያስፖራ ይህን ብካይ እያዩ ወደሃገራቸው ለመመለስ ዳተኛ የሚደረጉትን ብዙ ኢትዮጵያውያን ተስፋ ቆርጠው እንዳይቀሩ ለማገዝ፣ በነዚህ ሁሉ ምክንያቶች፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲሱን ጠቅላይ ዓቃቤ ህጋቸውን ሲሾሙ፣ ትኩረት ሰጥቶ በአፋጣኝ ሪፖርት እንዲያደርግላቸው ከሚያዙት ጉዳዮች አንዱ የኢንጂነር ዳንኤል ግዛው ነፃነት ጉዳይ መሆን አለበት ብዬ መምከር እወዳለሁ።
 ዲቬንተስን አይነት የነገ አፍሪካዊ ሳምሰንግ ማምከንና መበተን ወንጀል ነው። ይህ ሊሆን የሚችለው፣ ህዝባዊ ትግሉን አስታኮ የመጣው ለውጥ ውስጥ የኢትዮጵያን፣ የአፍሪካን፣ የጥቁር ህዝቦችን ልዕልና የማይሹት ታሪካዊ ጠላቶቻችን እጃቸውን የሚያስገቡበት ዕድል ስለተፈጠረ ነው ብሎ መጠርጠር ተገቢ ነው። ይህን በቀላሉ የምለው ጉዳይ አይደለም። ክብደት እሰጠዋለሁ። ለጥቃት የሚያጋልጥ አባባል እንደሆንም ይገባኛል። እንደተለመደው በታክስ ፍተሻ ወዘተ መዋከብ ሊያስከትል እንደሚችል አላጣሁትም። ግን ለኢትዮጵያ ዘብ ለመቆም ሲባል መባል ያለበት ነገር ነው። ይህ ለውጥ አንዱ የገጠመው ፈተና ለኢትዮጵያ ታማኝነት የሌላቸው ሃይሎች ሊያተራምሱት የሚችሉት መሆኑ ነው። አንድ የአቃቤ ህግ ባለሥልጣን ልጅህን አሜሪካ እናስተምርልሃለን፣ ወይም ሚስትህን ባንግኮክ እናሳክምልሃለን ስለተባለ የነዶክተር ፍቅሩን፣ የነ ኤርምያስ አመልጋንና ኢንጂነር ዳንኤል ግዛውን ዓይነት ሰዎች በሙስናና በህግ ሽፋን እንዲንገላቱ ሊያደርግ ይችላል። አለበለዚያ ከዳያስፖራ ገብተው መካከለኛ የምግቤት፣ የሆቴል፣ የፓርኪንግ፣ የቁፋሮ ወዘተ ሥራ ላይ የተሰማሩና ከገንዘብ በቀር የተለይ ዕውቀትም ሆነ ክህሎት የማይጠይቁ መስኮች ላይ የተሰማሩ ሰዎች ሳይነኩ፣ ዕውቀትና ክህሎት የሚጠይቁ ሃገርንም መለወጥ የሚችሉ መስኮች ላይ፣ በባንኪንግ፣ በኢንጂነሪንግ፣ በህክምና ወዘተ የተሰማሩትን እየመረጠ ጭዳ የሚያደርግ የህግ ማእቀፍ የኢትዮጵያ ብሎም የጥቁር ህዝቦች ታሪካዊና የህልውና ጠላቶች ሥራ አለመሆኑን እንዴት ማመን ይቻላል? ልናስብበትና ልንጨነቅበት ይገባል። ልንመረምረውና ልንፈትሸው ያሻል።
ሃገራችን ኢትዮጵያ ወይም ሃገረ መንግስታችን (ከተማሪው ንቅናቄ ቃላት እንድዋስ ፍቀዱልኝና) የአቀባባይ ከበርቴዎች (Comprador bourgeois) መፈንጫ እንዳትሆንና፣ ዕውቀት፣ ክህሎት፣ ሃገራዊ ፍቅርና ጨዋነት ያላቸውን ዜጎቿን (በኑሮ አስገዳጅነት፣ የሌላ ሃገር ፓስፖርት የተቀበሉትን ለኢትዮጵያ እንቅልፍ የማይተኙትን ዳያስፖራዎቿን ጨምሮ) ተራ በተራ እየመተረችና እያመከነች እንዳትሄድ ለኢትዮጵያችን ዘብ ልንቆም ይገባል።
የኢንጂነር ዳንኤል ግዛው ከአንድ አመት ህገወጥ እስር በነፃ መለቀቅም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሃገራቸው ዘላቂ ጥቅም ጋር የቆሙ ለመሆኑ አንዱ ማሳያ መንገድ ይመስለኛል። ዳንኤልን በነፃ መልቀቅም ብቻ ሳይሆን፣ በእርሱ የግፍ እስራት የተነሳ የተዘጉትን የዲቬንተስ በሮች ማስከፈትና በሙሉ አቅሙ ማምረት የሚያስችለውን የገንዘብ ድጋፍ በካሳ መልክ ሊደረግለት ይገባል ብዬ አምናለሁ። ፍትህ የዳንኤል ግዛውን ነፃነት ትጠይቃለች። የጠቅላይ ሚኒስትሩንም በር እያንኳኳች ነው። በትርፍ ጊዜው የቴክኒዮሎጂ አማካሪዎ መሆን የሚገባውን ሰው በእስር ማቆየት ግፍ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ እባክዎ ዳንኤል ግዛውን አስፈቱልን። እባክዎን!
Filed in: Amharic