>

ለአክራሪ ብሄር ፖለቲካ ነጋዴዎች እና ፀረ- ፍቅር ፀረ ትዳር ለሆኑ ዘረኞች አባ ዶዮ መልዕክት አላቸው !!! (ፍቅረ ማርቆስ ደስታ)

ለአክራሪ ብሄር ፖለቲካ ነጋዴዎች እና ፀረ- ፍቅር ፀረ ትዳር ለሆኑ ዘረኞች አባ ዶዮ መልዕክት አላቸው !!!

ፍቅረ ማርቆስ ደስታ

የዘር ፖለቲካ በህግ ይታገድ!

 
“አባ ዶዮን የሜጫ ኦሮሞ ህዝብ ‹‹የሰላም አባት›› እንዲላቸው ያደረገው ተግባር ጣሊያኖች በከፋፍለህ ግዛ መርህ የህዝቡን አንድነት ለመበታተንና እርስ በእርስም ለማፋጀት ያቀዱትን የዘር ልዩነት እሳት በማጥፋታቸው ነው፡፡
ይህም የኢጣሊያን ዕቅድ በእልፈታና ጀልዱ በመጠኑ ተፈጽሟል፡፡ በሜጫ ግን እርምጃ ከመወሰዱ በፊት የሃገር ሽማግሌዎች
‹‹ከባላባቱ ከአባ ዶዮ ጋር እንምከርበት›› ይሉና አባ ዶዮ ቤት ለመገናኘት ይወስናሉ፡፡ አባ ዶዮም ስለ ዕቅዱ የሰሙ ቢሆንም በቀጠሮው ይስማማሉ፡፡ ሽማግሌዎቹ ደግሞ የብልሁንና በህዝቡ የተከበሩትን የአባ ዶዮን ምክርና ድጋፍ ማግኘት እንዳለባቸው
ተማምነዋል፡፡
የቀጠሮው ዕለት ሽማግሌዎች ወደ አባ ዶዮ ቤት ሲገቡ በሩ ላይ ቆመው የሚቀበሏቸው አባ ዶዮ ሽማግሌዎቹ በስልቻ ከተቀመጠው ሰርገኛ ጤፍ እየዘገኑ እንዲገቡ አደረጉ፡፡ እንግዶች በሙሉ መግባታቸውን ሲያረጋግጡ አባ ዶዮም ገቡ፡፡ አንግዶቹ ሁሉም በእፍኛቸው ሰርገኛ ጤፉን እንደያዙ አዩ ……….
‹‹አባ ዶዮ! ምን አርጉት ብለህ ነው ሰርገኛ ጤፍ ያሳፈስከን?›› አሉ ሽማግሌዎቹ፡፡
‹‹በሉ ስብሰባችን ከመጀመሩ በፊት ነጭና ጥቁሩን ለዩልኝ›› አሉ አባ ዶዮ ኮስተር ብለው፡፡
‹‹አይ አባ ዶዮ! ትቀልዳለህ እንዴት ተደርጎ ነው ጥቅርና ነጩ የሚለየው የማይቻለውን ምነው ቀለድህብን አሉ በአንድነት፡፡
‹‹ በሉ ይቅር በሉኝ! ካስቸገራችሁ ተውት›› አሉ አባ ዶዮ፡፡
ከዚያም ሚስታቸው ያዘጋጁት ምሳ ቀረበ፡፡ አባ ዶዮና ባለቤታቸው በማስተናገዱ ተፍ ተፍ ብለው ጨዋታው ደርቶ ተበላ ተጠጣ በመጨረሻም ሞሰቡ ተነሳ፡፡
‹‹በሉ ወደ ጉዳያችን እንግባ ስብሰባችን ስለምን ነው?” አሉ አባ ዶዮ፡፡
‹‹አይ! ጣሊያን ከአማራ ነፃ የምትወጡበት ጊዜ አሁን ነው ብሎናል፡፡ እልፈታና ጀልዱ አማራን እያባረሩ የሚያንገራግሩትንም እየገደሉ ነው፡፡ እኛ ግን ከእርምጃችን በፊት ለአንተ እንንገርህ ካንተ ጋራም እንምከር ብለን ይኸው እንገናኝ አልንህ›› አሏቸው፡፡
‹‹ማለፊያ ሃሳብ ነው!›› አሉ አባ ዶዮ፡፡
‹‹ጣሊያን ከባህር ማዶ መጥቶ ከአማራ ነፃ ሊያወጣን ነዋ! ጥሩ ነው በሉ መጣው ›› ብለው ወጡና ‹‹ልጆች! አሰፋና ካሳን ባስቸኳይ ጥሩልኝ›› ብለው ተመለሱ፡፡ አሰፋና ካሳም የአባታቸውን እግር ተከትለው ከተፍ አሉ፡፡
‹‹አማራን እንግደል ብላችሁ አይደል የመጣችሁ››
‹‹አዎ!›› ሽማግሎቹ ትንሽ ግራ ተጋብተው ተያዩ፡፡
‹‹በሉ ወደ ውጭ ሳንወጣ በፊት እነዚህን ልጆቼን ቀጥለን ደግሞ እናታቸውን እንግደላቸው›› አሉ አባ ዶዮ ጎራዴያቸውን እየመዘዙ….
‹‹ምነው ጌታዬ! ለምን የአንተን ልጆች እንገላለን!›› ብለው ጠየቁ ‹‹እህ! አሁን ምሣ አብልታችሁ የወጣችው እናታቸው እኮ የመንዝ አማራ ናት፡፡ ልጆቹም በአባታቸው ኦሮሞ ቢሆኑም በእናታቸው
አማራ ናቸው፡፡ አማራን መግደል ማባረር ካለብን ከዚህ እንጀምራ›› አሉ አባ ዶዮ፡፡
‹‹ይህማ እንዴት ይሆናል አናደርገውም›› አንተስ እማናደርገውን ለምን ትጠይቀናለህ! ›› አሉ ሽማግሌዎቹ
‹‹እህ! ምን ላርግ? ቅድም ‘ሰርገኛውን ጤፍ’ ለዩ ያልኳችሁ እኮ ለዚህ ነው፡፡ አማራና ኦሮሞ እንደ ሰርገኛው ጤፍ ተቀላቅሏል ወንድሞቼ እዚህ ከናንተ ውስጥ ከአማራ ያልተጋባ ካለ ይንገረኝ? በተለይ ከሸዋ አማራ ጋር ተቀላቅለናል እኛ ኦሮሞዎች ጣሊያን የማያውቀው የማይገምተው የሚያኮራ የ‹‹ጉዲፈቻ›› እና የ ‹‹ሐርመ ሆዳ›› (ጡት መጥባት) ባህል አለን በዚህ ባህላችን ከተለያዩ ጎሳዎች ከመጡት ጋር አንድ ሆነናል፡፡ ይህ ባህላችን ከአባቶቻችን ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ የአንድንትና የአብሮ መኖር መሰረት ነው፡፡
ስለዚህ ጣሊያኖች ተለያዩ ቢሉን እኛ እንዴት መለያየት እንችላለን አሉ አባ ዶዮ ግራ ቀኙን በአይናቸው እየቃኙ፡፡ ሽማግሌዎች የአባ
ዶዮ ሃሳብ ስላሳመናቸው በፋሽስቶች የተቀነባበረው የመተላለቅ ድግስ ተበላሸ ፤ የአባ ዶዮ ምሳሌም በህዝቡ ህሊና የማይረሳ የሰላም መላ ተደርጎ እስካሁን ይታወሳል፡፡”
የመጽሐፉ ርዕስ:– ጃጋማ ኬሎ – የበጋው መብረቅ (የሕይወት ታሪክ)
የታተመበት ዓ.ም. :- 2002
የገጽ ብዛት:- 264
ከመጽሐፉ ገጾች የተወሰደ
Filed in: Amharic