>

"ሞተዋል ወይም በሕይወት አሉ ይበሉን'' የታጋች ተማሪዎች ቤተሰብ ! (ይድነቃቸው ከበደ)

“ሞተዋል ወይም በሕይወት አሉ ይበሉን” የታጋች ተማሪዎች ቤተሰብ !

ይድነቃቸው ከበደ
• ተለቀዋል የተባሉት ታጋቾች የት ናቸው?!
ከደንቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ለደህንነታቸው በመስጋት ወደ ቤተሰቦቻቸው እየተመለሱ በነበሩበት ወቅት ማንነታቸው ባልታወቀ ሰዎች የታገቱ ተማሪዎች ጉዳይ አሁንም ምንም መፍትሄ እንዳልተገኘለት የተማሪዎቹ ቤተሰቦች ለቢቢሲ ገልጸዋል። ተማሪዎቹ ከታገቱ ወራት የተቆጠሩ ሲሆን ወላጆች ልጆቻቸው መታገታቸውን ከሰሙ ጀምሮ ለሚመለከታቸው አካላት ልጆቻቸውን እንዲመልሱላቸው ሲጠይቁ ቆይተዋል።
ዛሬ ደግሞ ከአማራ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ለመነጋገር ባህር ዳር ተገኝተው ነበር። ወይዘሮ እንዳለች ይመር ሴት ልጃቸው እስታሉ ቸኮለ ከታገቱት ተማሪዎች መካከል አንደኛዋ እንደሆነች ይናገራሉ።
” እኔ እንዳልሰማ ቤተሰቡ ሲጠነቀቅ ነበር፤ አባትየውም ሲመላለስ ነው የከረመው። ድንጋጤውም ምኑም ተጨማምሮበት አሁን ጨጓራውን ሲታመም ነው እኔ ወደ ባህርዳር የመጣሁት። እኔ ጉዳዩን አልስማ እንጂ ልጄ ድምጿን ካጠፋች ብዙ ጊዜ ሁኗታል።” ” ይኀው መጥፋቷን ከሰማን ወዲህ ስልክ እንደውላለን፤ ምንም ነገር የለም። ያው ምን አማራጭ አለን ቤተክርስቲያን እየተሳለምን ማልቀስ ነው” ይላሉ እንባ እየተናነቃቸው።
ምናልባት ከመንግሥት አካል የተሰጣቸው ምላሽ እንዳለ የጠየቅናቸው ወይዘሮ እንዳለች ” ወደ ትምህርት ቤታቸው ተመልሰዋል። ዩኒቨርሲቲ ገብታ ትምህርቷን እየተከታተለች ነው አሉን። ብንጠብቅ ብንጠብቅ ምንም የለም፤ እስቲ አሁን መልስ ካገኘን ብለን ነው ባህርዳር የመጣነው” ይላሉ።
” በቃ ወይም ሞተዋል ወይም በሕይወት አሉ ይበሉን፤ እኛም እርማችንን አውጥተን አርፈን እንቀመጥ።”
ሌላኛው ልጃቸው እንደታገተችባቸው የሚገልጹት መሪጌታ የኔነህ አዱኛ ከደንቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ስትመለስ የታገተች ልጃቸውን በተመለከተ ከወረዳ ጀምሮ እስከ ጠቅላይ ሚንስትር ጽህፈት ቤት ድረስ መሄዳቸውን ገልጸዋል።
ወደ ባህር ዳር በመምጣት ከክልሉ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ለመነጋገር የወሰኑበትን ምክንያት ሲገልጹም “አቶ ደመቀ መኮንን በህይወት እንዳሉ፤ ታገቱ በተባለው አካባቢ ምንም ጉዳት እንደደረሰ የሚሳይ ምልክት አለመኖሩን ነግረውናል። ምከሩ ብለው በተለይ እናቶችን አበረታቱ ብለው ተመለስን። ከተመለሰን በኋላ በአጭር ጊዜ መፍትሔ ይመጣል ብለን ነበር። 35 ቀን ሆነን ውጤት ባለመገኘቱ ዛሬ ክልል መጥተናል” ብለዋል።
“ያው ይለቀቃሉ እናስለቅቃለን ተረጋጉ ነው ያሉን። መቼ እንደሚለቀቁ አልነገሩንም ፤ የተለቁቁም ያልተለቀቁም አሉ” ተብለን ነበር የሚሉት ደግሞ አቶ ላቀው ጓዴ ናቸው። ተማሪዎቹን ለመመለስ እየተሠራ መሆኑን በመግለጽ ውጤቱን እንደሚነገራቸው ቢገለጽላቸውም ምላሽ በመዘግየቱ ምክንያት አቤት ለማለት መወሰናቸውን አስታውቀዋል።
የታገቱት ተማሪዎች፡ የቤተሰብ ሰቀቀን እና የመንግሥት ዝምታ በባህር ዳር ቆይታቸውም የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ቢሮ እና ፖሊስ ኮሚሽን በመሄድ ስለጉዳዩ ምላሽ ለማግኘት ቢሞክሩም በተለያየ ምክንያት ኃላፊዎችን ሳያገኙ መቅረታቸውን ገልጸውልናል። ከሦስት ወራት በላይ የልጆቻቸውን ድምጽ ያልሰሙት ወላጆች በእነዚህ ጊዜያት ብዙ ችግሮች እንደገጠሟቸውም ነው ያስታወቁት።
የእህቷን ጉዳይ ለመከታተል አዲስ አበባ የነበረችው የታጋች ተማሪ እህት ፍቅርዓለም ቸኮለ ደግሞ በአሁኑ ወቅት በእስር ላይ እንደምትገኝም ወይዘሮ እንዳለች ይመር ለቢቢሲ ገልጸዋል። ” እህቴ ጠፋች፤ ፈልጉልኝ፤ ሰኔ ላይ ተመራቂ ናት እያለች ስትጮህ ይዘው እስር ቤት ከተቷት። መታሰሯን ከሰማን ወር ሆነው፤ ግን ከዚያም ይበልጣል። የእስታሉ ታላቅ እህቷ ነች፤ ከዩኒቨርሲቲ ከተመረቀች ሁለት ዓመት ሆኗታል። አዲስ አበባ ስራ እየፈለገችም ነበር።” የታገተችዋ ተማሪ እህት መሆኗን የሚያስረዳ ማስረጃ አቅርባ እንደምትለቀቅ ስለተነገራቸው ይህንኑ በጉጉት እየጠበቁ መሆኑን አስታውቀዋል።
” አሁን ደግሞ እህቷ ስለመሆኗ ከተወለደችበት አካባቢ ከሊቀመንበሩ አስጽፋችሁ መረጃ ይዛችሁ እንድትመጡ ተብለናል። መረጃው ሲላክ መጋቢት ዘጠኝ ትፈታለች ብለውናል። እስቲ ደግሞ ቀኑን ቁጭ ብለን እንጠብቃለን።”
መሪጌታ የኔነህ በበኩላቸው ” 95 ቀን እያለቀስን ነው፤ አዝመራ አልተሰበሰበም። እናቶች በአእምሮ እየተጎዱ ነው። እኛም እየሰራን አይደለም። ልጆቻችንን አረጋግተን ማስተማር እንፈልጋለን። ልጆቹ እኛንስ ምን ይገጥመናል? ትምህርት ምን ይጠቅመናል? ብለው አንማርም ብለው ደብተርም አላነሱም። በዚህ ተጎድተናል።”
አክለውም ” ሞተው ከሆነ ሰምተን ከዘመድ ጋር ተላቅሰን ወደ ሥራችን ተመልሰን ረጋ ብለን እንድንቀመጥ ነው የምፈልገው። ከተገኙና በህይወት ካሉ በድምጽም ቢሆን ብንገናኝ። ከሁለት አንዱን መንግሥት ቢነግረን እረፍት እናገኛለን። መንግስት በአፋጣኝ እናቶች አእምሯቸው የበለጠ ሳይዛባ እንዲስተካከሉ ቶሎ ከሁለት አንዱን ቢለይልን ነው የምፈልገው” በማለት አጠቃለዋል።
ከሰሞኑ በአማራ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ስልጠና መጠናቀቅን አስመልክቶ መግለጫ የሰጡት የአማራ ክልል የብልጽግና ፓርቲ የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ አብርሃም አለኸኝ ከተማሪዎቹ እገታ ጋር ተያይዞ የአማራ ክልል ብልጽግና ክንፍ ከፍተኛ ሥራ እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰው የተለያየ መግለጫ በመሰጠቱ የህብረተሰቡን አእምሮ ካለመያዙም በላይ አንዳንዱ መረጃ ተፋልሶ ያለበት ነበር ብለዋል።
“ፊት ለፊት መጥተን ባለመናገራችን የዘነጋነው ሊመስል ቢችልም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተነጋገርን ነው” ያሉት ኃላፊው ራሱን የቻለ ኮሚቴም መቋቋሙን አስታውቀው ነበር። “የተበጣጠሰ መግለጫ መስጠት አይገባም ብለናል። ስለዚህ ወጥ የሆነ መግለጫ በማዕከላዊ መንግስት ይሰጣል ብለን እናስባለን” ብለዋል።
Filed in: Amharic