>
5:18 pm - Tuesday June 15, 1790

የአፄ ዮሐንስ ፬ኛ 131ኛ የሙት ዓመት መታሰቢያ !!! (ልኡል አምደጽዮን ሰርጸድንግል)

የአፄ ዮሐንስ ፬ኛ 131ኛ የሙት ዓመት መታሰቢያ !!!

 

ልኡል አምደጽዮን ሰርጸድንግል
 
ኢትዮጵያን ከጥር 1864 ዓ.ም እስከ መጋቢት 1881 ዓ.ም የመሩት ታላቁ ንጉሰ ነገሥት አፄ ዮሐንስ ፬ኛ ያረፉት ከዛሬ 131 ዓመታት በፊት (መጋቢት 2 ቀን 1881 ዓ.ም) ነበር፡፡
አፄ ዮሐንስ ፬ኛ የተንቤንና የእንደርታ ባላባቶች ከነበሩት ወላጆቻቸው ሐምሌ 5 ቀን 1825 ዓ.ም. ማይ በሀ በሚባል ሥፍራ ተወለዱ። ከመንገሣቸው በፊትም ‹‹ርዕሰ መኳንንት ደጃዝማች በዝብዝ ካሳ›› በመባል ይታወቁ ነበር። በወቅቱም በትግራይ መኳንንት እግር/ዙፋን ተተክተዉ የአካባቢዉ ገዢ ሆነዉ ቆይተዋል። በሰሜን በኩል በወደቡ አቅራቢያ መገኘታቸዉ ከአዉሮፓዉያን ቆንሲሎች ጋር ወዳጅነት እየመሰረቱ መጠነኛ የትጥቅ ድጋፍ እንዲያገኙ አስችሏቸዋል፡፡
– – –
ደጃዝማች ካሳ ምርጫ የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገሥት እንደሚሆኑ እርግጠኛ ስለነበሩ ‹‹ደጃዝማች›› ከነበሩበት ግዜ ጀምሮ ራሳቸዉን ለውጭ አገራት መንግስታት በደብዳቤ ያስተዋውቁ ነበር።
ደጃዝማች በዝብዝ ካሳ፣ ከእርሳቸዉ በፊት የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት የነበሩትንና አገሪቷን ለሦስት ዓመታት ‹‹የገዙትን›› አፄ ተክለ ጊዮርጊስን ዓድዋ አካባቢ አሳም በሚባል ሥፍራ ላይ ሐምሌ 5 ቀን 1863 ዓ.ም ወግተው ድል ካደረጉ በኋላ ለበዓለ ንግስናቸው የሚያስፈልገዉን ሁሉ ሲያደራጁ ቆይተዉ ጥር 13 ቀን 1864 ዓ.ም በእለተ እሁድ በአክሱም ጽዮን ቤተክርስቲያን በጳጳሱ አቡነ አትናቴዎስ እጅ ተቀብተዉ ‹‹ሞአ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ ግርማዊ ዮሐንስ ራብዓዊ ስዩመ እግዚአብሔር ንጉሰ ጽዮን ንጉሰ ነገስት ዘኢትዮጵያ›› ተብለው ነገሡ።
– – –
ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ንጉሰ ነገስቱ በተቻላቸዉ መጠን ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግና በአንድ ማዕከላዊ መንግስት ስር የምትተዳደር አገር እንድትሆን መጣር ጀመሩ። ለሀገራቸውና ለሃይማኖታቸው ባላቸው ቀናኢነት የሚታወቁት አፄ ዮሐንስ ፬ኛ፣ አንዲት ጠንካራ አገር እውን እንድትሆን ያለ ዕረፍት ሲተጉ ኖረዋል።
– – –
አፄ ዮሐንስ ፬ኛ በተለያዩ አቅጣጫዎች ሀገር ለመውረር ከመጡት ከግብጾች፣ ከቱርኮች፣ ከጣሊያኖችና ከደርቡሾች (መሐዲስቶች) ጋር ተደጋጋሚ ጦርነቶችን አድርገው ነፃ ሀገርን ለቀጣዩ ትውልድ ያስረከቡ ታላቅ ንጉሥ ናቸው። በጉራዕ፣ በዶጋሊ፣ በጉንደትና በሌሎች ቦታዎች የተቀዳጇቸው ድሎች ለዚህ ማስረጃዎች ናቸው፡፡ በአንድ ማዕከላዊ መንግስት ስር የምትተዳደር አንዲት ጠንካራ የመገንባት እቅዳቸዉን እዉን ለማድረግም የየአካባቢ ገዢዎችን ማስገበርን የመጀመሪያ ስራቸዉ አደረጉ። በዚህም ከሞላ ጎደል ስኬታማ ነበሩ።
– – –
ሆኖም ከእርሳቸዉ በፊት የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት የነበሩት ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ አብዛኛውን ነገር በጉልበት/በኃይል እንዲሆን እንዳደረጉትና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን ምጣኔ ሀብታዊና ፖለቲካዊ አቅም በመቀነስ ማዕከላዊዉን መንግስት በዘመናዊ ጦርና አስተዳደር ለማጠናከር እንደጣሩት አይነት እርምጃን ግን አልወሰዱም። ይልቁንም ከየአከባቢዉ መሳፍንት ጋር ሰላም በማዉረድና ሀይማኖትን ዋና የፖለቲካ መሳሪያ አድርገዉ ማዕከላዊዉን መንግስት ለማጠናከር ጥረዋል፡፡
– – –
አፄ ዮሐንስ ፬ኛ እንደ ሌሎቹ የኢትዮጵያ ነገሥታት ሁሉ ሀገር ወዳድ መሪ ነበሩ። ሕይወታቸውን ያጡትም ለሀገራቸው ሉዓላዊነት በከፈሉት መስዋዕትነት ነው፡፡ በአፄ ዮሐንስ ፬ኛ የንግሥና ዘመን የኢትዮጵያን ድንበር ጥሰው እየገቡ ወረራ ሲፈፅሙ ከነበሩ የውጭ ኃይሎች መካከል ደርቡሾች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በተለይ ደግሞ ከሊፋ አብዱላሂ የደርቡሾች ንጉሥ ከሆነ በኋላ ኃይላቸው አጠናክረው በጎንደር በኩል ወረራ ፈፀሙ፤ብዙ ጥፋትም አደረሱ፡፡ ንጉሰ ነገሥት አጤ ዮሐንስ ፬ኛም ደርቡሾች በተለይም በኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች ላይ ያደረሱትን ጥፋት ለመበቀልና የአገራቸውን ድንበር ለማስከበር ‹‹መጣሁ ጠብቀኝ! እንደ ሌባ  አዘናግቶ ወጋኝ እንዳትል!›› የሚል መልዕክት ወደ ዘኪ ቱማል ላኩና ብዛት ያለውን ጦራቸውን ይዘው ወደ መተማ ዘመቱ፡፡
– – –
መጋቢት 1 ቀን 1881 ዓ.ም በዕለተ ቅዳሜ ከረፋዱ በሦስት ሰዓት ላይ ጦርነቱ ተጀመረ፡፡ ንጉሰ ነገሥት አጤ ዮሐንስ ፬ኛ ልክ እንደ ተራ ወታደር መሐል ገብተው ሲዋጉ ዋሉ፡፡ ኢትዮጵያውያን በርትተው እየተዋጉና ምርኮ በመያዝ ላይ ሳሉ አንዲት ተባራሪ ጥይት የንጉሰ ነገሥት አጤ ዮሐንስ ፬ኛ ደረት ላይ አረፈች፡፡ የንጉሰ ነገሥቱን መቁሰል ያየው ሰራዊታቸው ተደናግጦ መሸሽ ጀመረ፡፡
– – –
በጽኑ ቆስለው የነበሩት ንጉሰ ነገሥት አጤ ዮሐንስ ፬ኛም በማግሥቱ፣ መጋቢት 2 ቀን 1881 ዓ.ም አረፉ፡፡ ደርቡሾችም እየተከታተሉ የንጉሰ ነገሥት አጤ ዮሐንስ ፬ኛን አስክሬን ይዘው አትባራ ወንዝ ዳር ሰፍረው የነበሩትን ኢትዮጵያውያን መኳንንትና ወታደሮች ላይ ጥቃት በመፈፀም፣ መጋቢት 3 ቀን 1881 ዓ.ም የንጉሰ ነገሥቱን ጭንቅላት ቆርጠው ወሰዱት፡፡
– – –
የመረጃው ምንጭ፡ ‹‹አጤ ዮሐንስና የኢትዮጵያ አንድነት›› – ተክለፃዲቅ መኩሪያ 
– – – 
ፈጣሪ የንጉሰ ነገሥት አጤ ዮሐንስ ፬ኛን ነፍስ ይማር!
Filed in: Amharic