
ተመረመርኩ!!!

( በእውቀቱ ስዩም)
ወደ አሜሪካ የተመለስኩት ትራምፕ ከግብፅ ጋ ተሞዳሙዶ ኢትዮጵያን አስገድዶ ለማስፈረም በዛተበት ቀን ማግስት ነው:: ብዙዎቻችሁ ኢትዮጵያውያን እንዲህ ባለ የጭንቅ ቀን ጥለሃት መሄድህ ክደት ነው በማለት በኢንቦክስ ወቅሳችሁኛል: : የወጣሁት ለታክቲክ ነው! እንደኔ እንደኔ ያሜሪካን ከውስጥ ሆኖ ለመታገል ከዚህ ጊዜ የተሻለ አጋጣሚ የለም::
እና ስም አይጠሬው እንዴት እያረጋችሁ ነው? ከአምቡላንስ ሰብሮ ያመለጠው ትኩሳታም ዜጋ ፤ ሲረሸን ላይቭ የሚተላለፈው መቸ ነው? ለመሆኑ ዛፓዎች አስፈላጊው ፍተሻ አድርገውበታል ? እንደኔ እንደኔ ኤርፖርት ላይ በመሳርያ ሲዳብሱት ትኩሳቱ ያሸቀበው፤ በቫይረሱ ምክንያት አይመስለኝም:: የሆነ በዱባ ቅጠል ጠቅልሎ የዋጠው ኮኬን ሳይኖር አይቀርም!! አለበለዝያ ሰው እንዴት የጤና ድጋፍ ሸሽቶ ያመልጣል?
እኔማ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ሳረግ ቆይቻለሁ:: ፊትህን አትንካ ተብሉዋል ፊቴን አልነካም:: መንገጭላየ ግድም ሲበላኝ ፤ እንደ ዳንግሌ በግ የግድግዳውን ጠርዝ በመታከክ ጥሜን አረካለሁ:: ማንኛውንም አይነት የበር እጀታ አልጨብጥም:: ትናንት ያንዱን ሚኒማርኬት በር እንደቻክኖሪስ በርግጫ ከፍቼ ስገባ ዘበኛው ተናዶ በጥፊ ሊያጮለኝ ከቃጣ በሁዋላ፤ ለቅድመ ጥንቃቄ በሚል በጠረባ ጣለኝ::
በቀደም ለት፤ ወደ ቤቴ እየሄድኩ አንዱ ከጀርባየ አስነጠሰ:
ዞር አልኩና ” ሶየ .. በህግ አምላክ እንዳትንቀሳቀስ ! “
“ምነው?”
ያነጠስክበት ቦታ ከኔ ጋ ያለውን ርቀት ልለካው ነው !!! ከሶስት ሜትር ካነሰ ወደ ጤና ጣቢያ እደውላለሁ”
በተቻለኝ መጠን ቅድመ ጥንቃቄዎችን ሳደርግ ቆይቻለሁ፤ ጉሮሮ መድረቅ የለበትም በተባለው መሰረት ውሃ ካጠገቤ አይለይም :: አሜሪካ ውስጥ የውሃ ችግር የለም፤ ከፈለግሽ ትራስሽ አጠገብ ቧንቧ ማስገጠም ሳይቀር ትችያለሽ :: እዚህ አገር በፈረቃ እሚመጣ ጥም እንጂ በፈረቃ እሚመጣ ውሃ የለም ! ድሮ አንድ ጣሳ ውሃ ከጠጣሁ በመላው ሰውነቴ ሲንሸራሸር ሰንብቶ፤ ሁለመናየን አፅድቶ በሁለተኛው ቀን ነበር ተረፈ ምርት ሆኖ የሚወጣው:: እንዲያውም አንዳንዴ ሳምንት የማልሸናበት ጊዜ ነበር፤
አሁን ገባ ብርጭቆው ካፌ ሳይወርድ፤ የምጠጣው ነገር በቀጥታ ስርጭት ወደ ፊኛየ ይሄዳል:: “ከበውቄ ጋራ መጠጣት እኮ ውሃ በወንፊት ውሃ እንደ መቅዳት ነው “ ይላሉ አብሮ ቀምቃሚዎቼ! ደሞ አንድ ብርጭቆ ውሃ ጠጥቼ አንድ ማድጋ የምሸናበት ምሲጢር አይገባኝም ፤ የሆነ ለጡሮታ የተጠራቀመልኝ ሽንት ሳይኖር አይቀርም ::
ችግሩ ፤ ምኝታ ቤቴ ከሽንት ቤቴ በጣም ይርቃል:: በዛ ላይ ያሜሪካ ሽንት ቤት በጣም ፅድት ያለ ስለሆነ በቀላሉ እሺ ብሎ አይወርድልኝም :: የመጣው ሌሊት ከሆነ ደግሞ አባብየ ወይም ጨቁኘ አሳድረዋለሁ፤
ከትናንት ወድያ በተከታታይ በእሩምታ ማስነጠስ ጀመርኩ ፤ ብዙም ሳልደናገጥ 911 ደወልኩና “ መጥታችሁ ትወስዱኝ ወይስ መደዳውን ልበክል?” አልኳቸው፤ በታንክ የታጀበ አምቡላንስ ልከው ወሰዱኝ::(ከኢትዮጵያ መምጣቴን ስለሰሙ ሰብሮ ያመልጣል ብለው ሰግተው ነው)
ዶክተሩ መርምሮኝ ሲያበቃ
“ ጥሩ እና መጥፎ ዜና አለኝ” አለ፤
“ከጥሩ ጀምር!”
“ ኮረና የለብህም:: ግንባርህ ላይ ነጥሮ ተመልሷል::”
“ተመስጌን . .መጥፎው ዜናስ ምንድነው?”
“ ሁለተኛው የምርመራ ውጤት እንደሚያሳየው ፊኛህ ላይ ችግር ተከስቷል”
“ፊኛየ ምን ሆነ?”
‘’ ፊኛህ ሽንት በማቆር ብዛት የተነሳ ተለጥጦ የላም ጡት መስሏል፤”
“ እና ምንድነው እሚሻለኝ?” አልኩ በጭንቀት::
“ አለም በወረርሽኝ በሚዋከብበት ዘመን ያንተን ፊኛ ስራ ፈቶ እሚያክም የለም! እዛው አገርህ ገብተህ እንድትሞት ሪፈር ፅፈንልሃል ! “