>

የምርጫ ቅስቀሳ እና የገና ጨዋታ!!! (ያሬድ ሀይለማርያም)

የምርጫ ቅስቀሳ እና የገና ጨዋታ!!!

 

ያሬድ ሀይለማርያም
* …ምረጡን ባዮች በተናገሩት ሁሉ የምንመሰጥ፣ የምንደሰት፣ የምንናደድ፣ የምንቆጣ፣ የምናለቅስ፣ ተስፋ የምናደርግ ከሆነ የምርጫ ቅስቀሳ ነገር ገና አልገባንም ማለት ነው። እነሱ ሲግሉ አብረን ግለን፣ ሲጮኹ አብረን ጮኸን፣ ሲናደዱ ተናደን፣ ሲጋጩ ተጋጭተን አንዘልቀውም…

“በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ” እንደሚባለው በጫወታው ጊዜ  በቃላት የሚገለጹ ብሽሽቆች እና ስድድቦች ሁሉ ከወዳጅ እስከ ጌታ የሚነቁር ቢሆንም የሚቆጣ አይኖርም። በገና ጨዋታ የተሰደበ ሰው ቂም አይይዝም። ተሳዳቢውም ያሻውን ተናግሮ ይሄዳል። ሆድ ያባውም፣ ነገር ያቄመውም እንዲሁ ያሻውን ተንፍሶና በስተመጨረሻም ተሳስሞ፣ አብሮ በልቶና ጠጥቶ ይለያያል።
ለምሳሌ ከገና ጨዋታ ግጥሞች ለወግ ማድመቂያ ያህል፤
‹‹ወንድ ነው ብዬ … ብሰጠው ጋሻ
ለናቱ ሰጣት ላመድ ማፈሻ
ወንድ ነው ብዬ ብሰጠው ጦር
ላባቱ ሰጠው ለቤት ማገር››
የምርጫ ቅስቀሳም እንደ ገና ጨዋታ ነው። በተፎካካሪዎች መካከል ከሃሳብ አንስቶ በማንነት ላይ ያነጣጠረ ትችት እና ነቀፌታ ይዘንባል። አንዳንዴም እስከ ስድብ ይሄዳል። በትራንፕ እና በሂላሪ መካከል የነበረውን ከልክ ያለፈ መወራረፍ ልብ ይለዋል። መነቃቀፉ እና መዘረጣጠጡ ከሞራል እና ከሥነ ምግባር እስካልራቀ ድረስ ይህ አይነቱ የተፎካካሪዎች መወራረፍ የፍጹም ነጻነት መገለጫ ነው። ማንም ማንንም ከመንቀፍ የሚያግደው ወይም የሚፈራው ነገር አይኖርም።
እንግዲህ ይህ ኮሮና የሚሉት አለምን ያስጨነቀ ቫይረስ ከፖለቲካችን ጋር ተጋብቶ ሌላ ጣጣ ካላመጣብን ለጊዜው ምርጫው በታቀደለት ወቅት ይካሄዳል ብለን ልናስብ እንችላለን። ካሰብን የምርጫ ወቅት ውስጥ ገብተናል ማለት ነው። በምርጫ ወቅት ደግሞ ፖለቲከኞች አቅላቸውን የሚጥሉበት፣ የቋጥ የባጡ የሚዘባርቁበጥ፣ በየተገኘው መድረክ ጣቃ ጣቃውን የሚቀዱበት፣ ሕዝብን በተስፋ እንጀራ አጥግበው የሚያሳድሩበት፣ በትንሽ በትልቁ በሕዝባዊ ጉዳዮች አፋሽ አጎንባሽ እንሁን የሚሉበት፣ በእያንዳንዱ ሕዝባዊ ጉዳይ ሃሳብ ሰንዛሪ፣ መላ ፈጣሪ፣ እቅድ ነዳፊ እየሆኑ በየመገናኛ ብዙሃኑ ብቅ ጥልቅ የሚሉበት ወቅት ነው።
በዚህ ወቅት ስጋት የሆነባቸውን ተወዳዳሪ ለማኮሰስ የሰራውንም፣ ያልሰራውንም እየዘረዘሩ ሃጢያቱን እንደ ተራራ አግዝፈው ሊያሳዩን ይጥራሉ። የእራሳቸውንም ብጽዕና፣ ብቃት እና ተወዳዳሪ የማይገኝላቸው ፖለቲከኞች መሆናቸውን ለማሳየት እንደየአቅማቸው የሚውተረተሩበት ጊዜም አሁን ነው።
እናማ በተናገሩት ሁሉ የምንመሰጥ፣ የምንደሰት፣ የምንናደድ፣ የምንቆጣ፣ የምናለቅስ፣ ተስፋ የምናደርግ ከሆነ የምርጫ ቅስቀሳ ነገር ገና አልገባንም ማለት ነው። እነሱ ሲግሉ አብረን ግለን፣ ሲጮኹ አብረን ጮኸን፣ ሲናደዱ ተናደን፣ ሲጋጩ ተጋጭተን አንዘልቀውም። መረሳት የሌለበት ከምርጫው መጠናቀቅ በኋላ ሁሉም ወደ እውነተኛ ማንነታቸው ሲመለሱ እኛ ሜዳ ላይ እንቀራለን። በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ፖለቲከኞች የገና ተጫዋጭ ባህሪ ነው ያላቸው። ይሸልላሉ፣ የተርባሉ፣ ይተረባሉ፣ ይሰደባሉ፣ ይሳደባሉ፣ ከእውነት ጋር ይላተማሉ፣ ይዋሻሉ፣ ይዘባርቃሉ፣ ይምላሉ፣ ይገዘታሉ፣ አንዳንዴም ይገዝታሉ።
በዛው ልክ እውነትን፣ እውቀትን እና ለሕዝብ ተቆርቋሪነትንም ይዘው አደባባይ የሚወጡ ፖለቲከኞች፤ በጠአት የሚቆጠሩ ቢሆንም አሉ። ፍሬና ገለባውን መለየት የሕዝብ ድርሻ ነው። ያን ለማድረግ ከስሜት ይልቅ በአመክንዮ፣ ከወገንተኝነት ይልቅ በእውነት ላይ ተመርኩዘን የምንመዝን መሆነ አለንብ። በተደጋጋሚ ጠቅላዩም ሆኑ ሌሎች ፖለቲከኞች ከሰሞኑ እያሳዩ ያሉት ባህሪ፣ የተደጋገመ የአፍ ወለምታዎች እና አንዳንዴም የቋጥ የባጡን መዘባረቅ ከገና ጨዋታ ብሽሽቅ የሚርቁ አይመስለኝም።
በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ እንደሚባለው ሁሉ፤ በምርጫ ቅስቀሳም ሕዝብ ተረጋግቶ አድማጭ እና ሚዛናዊ ፈራጅ ይሆናል የሚል ተስፋ አለኝ። በምርጫ ላይ የጌታ ድርሻ ያለው ሕዝብ ነውና።
በዴሞክራሲያዊ ባህል ያልተገራ ምርጫ እና ኮሮና ቫይረስ አንድ ላይ ሆነው ምን ያደርጉን ይሆን የሚለው ግን ዋነኛ ስጋቴ ነው።
ለማንኛውም ለቫይረሱ እጃችሁን በቀን ውስጥ ደጋግማችሁ በደንብ ታጠቡ፤ ለምርጫው ደግሞ (ከተካሄደ) አትኩሮታችሁን፣ የነቃ ተሳትፏችሁን እና አርቆ አስተዋይነታችሁ አይለያችው።
በቸር እንሰንብት!
Filed in: Amharic