>

የዕለቱ ወግ:- ዝም ብለህ ተኛ!!! (ተስፋዬ ኃይለማርያም)

የዕለቱ ወግ:-  ዝም ብለህ ተኛ!!!

 

 

ተስፋዬ ኃይለማርያም
በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጊዜ የጀርመን አውሮፕላኖች የለንደንን ከተማ በተደጋጋሚ ይደበድቡ ነበር። የአውሮፕላኖቹ ድምፅ ሲሰማ በከተማው ውስጥ ያለው የማስጠንቀቂያ ሳይረን ይጮሃል። በዚህን ጊዜ ህዝቡ እየተሯሯጠ ቦንብ ወደማያፈርሳቸው የመጠለያ  ቤቶች ይገባል። ድብደባው ሲያቆም ሁሉም ምናልባት ከድብደባው ወደተረፈው መኖሪያ ቤቱ ይመለሳል።
ብዙ ሰዎች ሮጠው ወደመጠለያው ካልገቡ መንገድ ላይና መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ይሞታሉ። ይህ የዕለት ዕለት ሩጫ የሰለቻቸው አንዲት እናት “ልሙት እንጂ ከእንግዲህ ወደ መጠለያው በየቀኑ አልሮጥም። እግዚአብሔር ከወደደ ይጠብቀኛል” ብለው ቤታቸው መተኛት ጀመሩ።
አውሮፕላኖቹ ለድብደባ ሲመጡና ሲሄዱ በህይወት የተረፉት ሰዎች ሰላም ሲባባሉ፣ እኚያ ሴትዮ ስለማይገኙ የአካባቢው ህዝብ ሴትየዋ ሞተዋል ብሎ አዘነ።
ከአራት ዓመት በኋላ ጦርነቱ ተፈጸመ። በህይወት የተረፉ የከተማዋ ነዋሪዎች እንኳን ደስ አላችሁ ሲባባሉ እኚያ ሴት መንገድ ላይ ተገኙ። ሰው ሁሉ በሴትየዋ በህይወት መኖር ተደንቆ  “እኛስ የሞቱ መስሎን ነበር። የት ከርመው ነበር?” ብለው ጠየቋቸው።
ሴትየዋም “እኔና እግዚአብሔር ተነጋገርን። እኔ በየቀኑ ለመሮጥ አቅም የለኝም። ስለዚህ እኔና አንተ ዕንቅልፍ ከምናጣ እኔ እተኛለሁ አንተ ደግሞ ጠብቀኝ አልኩት። በቃ! እኔ እየተኛሁ እሱ እየጠበቀኝ ጦርነቱ አለቀ”
ወገኔ! በዚህ በኮሮና ቫይረስና በእኛ የኑሮ ስታይል ራስህን ጠብቀህ አትችለውም። በሰላሙ ጊዜ ውኃ የሌለበት ከተማ እየኖርክ የእጅ መታጠብ ትርኢት ያሳዩሃል። እጅህን እንኳን የመታጠብ ዕድል የለህም። ስግብግብ ነጋዴ ነፍስህን የምታቆይበትን ዕድል አልሰጠህም። ስለዚህ እንደ ለንደን ከተማ ነዋሪዋ ሴትዮ አድርግ። ከአምላክህ ጋር ተስማማና እረፍ። ተኛ። አንተም አምላክህም እንቅልፍ አትጡ። “የሚጠብቅህ እሱ አይተኛም አያንቀላፋም ” ተብሎ ተጽፎልሃል።
ይህ በሽታ ካለፈ በኋላ ለመገናኘትና ለመወቃቀስ ያብቃን።
Filed in: Amharic