>

እግዚአብሔር በመቅሰፍቱ ይጣራል ! (አባይ ነህ ካሴ)

እግዚአብሔር በመቅሰፍቱ ይጣራል !

 

 

አባይ ነህ ካሴ
እግዚአብሔር ከአንታርክቲክ እስከ አርክቲክ ዓለምን በአንድ ቋንቋ እያነጋገረ ነው። 
 
በአሜሪካን እስከአሁኗ ደቂቃ በኮሮና ቫይረስ 6118 ስዎች በበሽታው ተጠቅተዋል 111 ሰዎች ሞተዋል ፈጣሪ ምህረቱን ያውርድልን።
የዓለም ኃያላን ሀገራት ከአሜሪካ እስከ ቻይና ብርቱ ምጥ ላይ ወድቀዋል። እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣  ጀርመን፣  ጣልያን፣  ኢራን፣  ካናዳ፣  ደቡብ ኮሪያ . . . ጭንቅ ጥብብ ብሏቸዋል። የአፍሪካ ሀገራትም የድርሻቸውን እየዘገኑ መኾኑ ቀስ በቀስ ይፋ እየኾነ ይገኛል።
፰.፮ (8.6) ሚሊዮን ነዋሪ ያለባት የዓለም የገንዘብ ዝውውር የሚሸመንባት ኒው ዮርክ እስከ ትናንት ማክሰኞ ፱፻፳፫(923) ሰው በኮሮና ቫይረስ ተለክፎባታል። ነፍሳቸውን ይማር እና ዐሥር ሞተዋል። ይህም ከአሜሪካ ከተሞች ቀዳሚዋ ያደርጋታል። ፳ሺህ (20,000) የሆስፒታል አልጋዎች ተወግደዋል። ፫ ሐኪሞቾ በቫይረሱ ተይዘዋል።
ኒው ዮርክ፣  ሎስአንጀለስ እና ዋሽንግተን ግዛቶች ብቻ በድምሩ ከ፬ሺህ በላይ የቫይረሱ ተጠቂዎች አሏቸው። በእነዚህ ግዛቶች የመንግሥት መ/ቤቶችን ተዘግተዋል። የሕዝብ ት/ቤቶች ሙሉ በሙሉ ከትናንት ጀምሮ እንዲዘጉ ውሣኔ ተላልፏል። የግል ት/ቤቶች ቀደም ብለው ዘግተዋል።  የኒው ዮርክ ከተማ የሕዝብ ትራንስፖርት ኩባንያ በአንድ ሳምንት ብቻ ለደረሰበት ኪሣራ የ፬ ቢልየን ዶላር ማካካሻ ጠይቋል። ከ፲ (10) ሰው በላይ በአንድ ቦታ መሰብሰብ ተከልክሏል።
የሀገር ቤቱም ዜና ከቀን ወደ ቀን የተጠቂዎች ቁጥር እያሻቀበ መኾኑን ያስሰማል። የሚጠጣ ውኃ ጭንቅ በኾነባት ሀገር እጅ መታጠብ ትልቅ አጀንዳ ኾኖ መነገሩ ያስተዛዝባል። ባይኾን ሰላምታው ላይ መጠንከሩ ይበጃል።
የ፺፫ (93) ዓመቷ የእንግሊዝ ንግሥት ቫይረሱን ሽሽት ለንደንን ለቅቀው ወጥተዋል። በአሜሪካ ሥራ አጡ ወደ ፳ (20) % ከፍ ብሏል። ገንዘብ ወይም ሀብትን የማያፍር በሽታ መኾኑ የበለጸጉትን በማሸበሩ ታውቋል። የጦር ኃይል የማይረታው መኾኑ ይታወቅ ዘንድ ኒውክሌር የታጠቁትን አስገብሯል። እንደዚህ ያለው ከእግዚአብሔር እንጅ ከሰው አይደለምና ቁጣውን በትዕግስቱ መዐቱን በምሕረቱ እንዲመልስልን ዓለሙ በፊቱ ይንበርክ። መላውን የሰው ልጅ በአንድ ድምጽ እግዚአብሔር ሲጣራ መስማት ብቻ ያድናል።
Filed in: Amharic