ምሁርነት በአዲሶቹ የኦፕዲኦ (ብልጽግና) ደጋፊ ምሁራን አይን ከታየ የተባለው ትክክል ነው!!!
መንግስቱ ሙሴ
* ምሁርነት በነኃይሌፊዳ በነገነት ዘውዴ ከተለካ…
ስለኢትዮጵያ ምሁራን ለታሪክ ምሁራን እተወዋለሁ። በዚያ መስክ ብዙ ባልል ከአፍ እላፊ እና አጉራ ዘለል አስተያየት ከመሰንዘር ለመቆጠብ ያህል በማለት ነው። እልፍ ሲል ደግሞ በቀድሞወቹ ካድሬወች እንዳየነውም ሆነ በህወሓት/ኢሕአዴግ ኦነግ ፈጠር ካድሬወች አይን እና አስተሳሰብ ከተጓዝን ምሁርነት የሚለካው ለመንግስት እና ለገዥወች ባደርንበት ልክ እና አይነት ነው። ከጠላት ዘመን ጀምሮ ከአባቶቻችን እና እናቶቻችን አፍ እንደሰማነው ከትምህርት ቤት እና ከታሪክ ተመራማሪወች ድርሳናት እንዳየነው በዘርአይ ደረስ፣ በዶክተር መላኩ በያን፣ አክሊሉ ኃብተወልድ እና ሦስቱም ወንድማማች ምሁራን ወዘተ ስለሀገር በእውቀታቸው ከወገናቸው ጎን ቆመው የተዋደቁ። ስለወለታ ካዴቶች እና በፋሽስት ወረራ ከልዑል እራስ እምሩ ጦር ጋር በመሆን በአርበኝነት ያበረከቱት አስተዋጸኦ ገዝፎ የወጣ የምሁራን አስተዋጸኦ ነበር። ወጣቱ ምሁር አክሊሉ ሀብተወልድ ሀገራቸው League of Nations እና በአውሮፓ መንግስታት ፊት እና አንፃር ቆመው ብቸኛ ነነበረችው ሀገራቸው የሰሯቸው ታላላቅ ስራወች የሚረሱ አይደሉም።፡
ከዚያ ዘለል ብለን ስናየው ስንመረምረው የኢትዮጵያ ምሁራን እውቀት የዕለት ጉርስ እና የአመት ልባስ የማይሰጥ ባዶነት እንዳልሆነ በአለም ዙሪያ በዘረኛው እና በአንባ ገነን ተከታታይ ስርአቶች ተገፍተው በዓለም ዙሪያ የሚኖሩትን ኢትዮጵያውያን ምሁራንን ለአፍታ በአይነህሊና መዳሰሱ ከስህተት ያድናል።፡ብዙ ስራ የሚሰሩ፣ በታወቁ አለማቀፍ ተቋማት እና በታዋቂ ኩባንያወች፣ የመንግስት መስሪያቤቶች፣ የግል ድርጅቶች ውስጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱ አሁንም በማበርከት ላይ ያሉ ብዙወችን በእንዲህ አይነት መጣጥፍ መዘርዘር ስለሚከብድ ጠቅሸው አልፋለሁ።
የዚህ መጣጥፍ አቅራቢ በቅርብ ለስራ ብሎ እንዳጸናው በኢትዮጵያውያን የግል ስራ ተዳዳሪወች በሰሜን አሜሪካ፤ ኢትዮጵያውያን ልክ እንደቻይናውያን፣ ይሁዳውያን፣ የኩባ ስደተኞች እና ሜክሲኮ ዜጎች ተርታ በራሳቸው ኮሚውኒቲወች በየሚኖሩባቸው ከተሞች የራሳቸውን ተቋማት፣ የራሳቸውን አምራቾች፣ የራሳቸውን አከፋፋዮች፣ አስመጭ እና ላኪወች ሱቆች ሸቀጦች፣ የኢንሹራንስ ኩባንያወች፣ አካውንቲንግ እና ሌሎች ምሁራዊ ሰርቪሶች በመክፈት ስራ የሚፈጥሩ ለወገኖቻቸውም አገልግሎት የሚሰጡ ናቸው። ይህን አስተዋጸኦ በየሚኖሩባቸው ሀገራት እና ከተሞች የፈጠሩት እንደሌሎች ከሁለት እና ሦስት ትውልዶች በኋላ ሳይሆን በአለፉት 30-40 አመታት ከሀገር ተሰደው ወደተለያዩ ሀገራት በሚኖሩ የመጀመሪያ ትውልድ ኢትዮጵያውያን አሜሪካ እና ሌሎች ነዋሪወች ሲሆን ከላይ ከተጠቀሱት እንደ ይሁዳውያን፣ ኩባውያን፣ ቻይናውያን ኮርያውያን ሶስት እና አራት ትውልድ ሲደርሱ ኢትዮጵያውያኑ የት ሊደርሱ እንደሚችሉ የሚገመት አይደለም። የሚገመት አይደለም የሚለው ትርጓሜ በኢኮኖሚ እና ማህበራዊ እድገት ከወዲሁ በመጀመሪያ ትውልድ ያሳዩት እድገት እና በየሚኖሩባቸው ከተሞች ያተረፈፉት ተከባሪነት። በይበልጥ የተቀበላቸው ማህበረሰብ አሜሪካውያኑም ሆነ ሌሎች እንደነሱ መጤ ህብረተሰቦች ዘንድ ያላቸው ተቀባይነት እና ከበሬታ የት የሌለ እና አስገራሚ እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል። ይህ የምሁራን ኢትዮጵያውያን ስራ ለመሆኑ ደግሞ ከግንዛቤ እንዲገባ ይገባል።
እንዴው ከተሰደዱ ኢትዮጵያውያን ምሁራን ውጤት ከሆኑ የአሜሪካን ከተሞች በምሳሌ ለማሳየት ልሞክር። በዋሽንግተን ዲሲ በ 1970 ወቹ መጨረሻ – በ 1980 ወቹ መጀመሪ በስደት ከሱዳን በአሜሪካን ኢሚግሬሽን ተባባሪነት የመጡ እና በሰሜን አሜሪካ ለትምህርት መጠው ወደ ሀገራቸው መመለስ ሳይችሉ የቀሩ ኢትዮጵያውያን አንድ የከተማውን ከፊል 18ኛው ጎዳና የተባለውን አካባቢ ያኔ እነሱ ምግብ ቤቶችን እና መገባያያ ሱቆችን ከመክፈታቸው በፊት የከተማው አስፈሪ እና አስከፊ የወንጀል ዳርቻ፤ የህገወጥ እፅ መለዋወጫ የነበረውን ከ 30 አመታት በኋላ የት እንዳደረሱት ማየት ብቻውን ለስራ ውጤቶቻቸው በቂ ማገናዘቢያ ለመሆኑ ከእኛ በላይ አሜሪካውያኑ የሚያውቁት ነው። ኢትዮጵያውያን በዚህ በአጭር ቆይታቸው በሰሜን አሜሪካ (ካናዳን እና ዩናይትድ ስቴትስ) የሀገራቸው ባህሏን፣ ወጓን፣ ልማዷን እና የሕዝቧን አኗኗር ያሳዩበት እጅግ ውብ ስራወች በተቀበላቸው ሀገራት ሕዝብ የተመሰገኑ ሲሆኑ እነዚህ ውብ ስራወች ደግሞ የኢትዮጵያውያን ልሂቃን ውጤቶች ናቸው። ለምሳሌ ጠቅላይ ሚኖስቴር አብይ አህመድ በኢሕአዴግ ያውም በማይለወጠው የዘረኛ ብሄርተኞች ስብስብ ተመርጠው ያኔ የዛሬ አመት ወደ አሜሪካ በተጓዙበት ወቅት ከዋሽንግተን ኤርፖርት እስከ ሚኒያፖሊስ ሚኒሶታ እና ሎስ አንጀለስ ካሊፎርኒያ ግዛቶች ኢትዮጵያውያኑ በክብር ተቀብለው ማንም የሀገር መሪ ያላገኘውን ታላቅ መስተንግዶ ያደረጉላቸው እዚህ ሀገር በኑሮ ባሳዩት የመንግስት እና ማህበረሰብ ክብር ጥሩ ግብራቸው የተመሰገነላቸው የኢትዮጵያ ምሁራን ውጤቶች ነው። ያ የደመቀ አቀባበል የኢትዮጵያውያን ምሁራን የስራ እና የመሪነት ውጤት መሆኑን እንዴት በዚህ አጭር ግዜ እንደተረሳ የሚያስተዛዝብ ነው። ነጻነት ያገኙ ኢትዮጵያውያን ምሁራን በየሄዱበት ክብር እና ሞገስ እንጅ የሚያስንቅ እና ሀገር እና ወገንን የሚያስገምት አንድም ነገር እንደማይሰሩ የሚኖሩባቸው ሀገራት፣ የሚሰሩባቸው ተቋማት ህያው መስክሮች ናቸው።
ከዚህስ ባለፈ
የኢትዮጵያ ምሁራን ከላይ በመግቢያ እንደጠቀስኩት የሀገራቸውን አንድነት እና የሕዝባቸውን (የሕዝቦችን አላልሁም) ነጻነት ለማስከበር ከውጭ ጠላት ተፋልመው የወደቁ እጅግ ብዙ ታሪክ የያዛቸው እንደመሆኑ እነ አርበኛ ክቡ ሐዲስ አለማየሁን፣ አርበኛ ክቡር ይልማ ደሬሳን አርበኛ ክቡር ዶክተር መላኩ በያንን ወዘተ በዚህ መጣጥፍ ማስታወስ ተገቢም ነው፡፡በሀገራቸው ለእኩልነት፣ ለነጻነት እና ለዴሞክራሲያዊ መንግስት እውን መሆን ከዘመነ መንግስቱ ነዋይ ጀምሮ እስከ አለንበት የተከፈለ መስዋዕትነት ህልቆ መሳፍርት የለውም።፡ ለዚህ ደግሞ ከነ ገርማሜ ነዋይ፣ ተስፋየ ደበሳይ እስከ እነ እስክንድር ነጋ እና መዳረሻቸው እስከ ዛሬ ያልታወቁት ጸጋየ ገ/መድህን (ደብተራው) ከአንባ ገነን መንግስት ጋር ያደረጉት ግብ ግብ እና የከፈሉት መስዋዕትነት ዛሬም እንደባውዛ ቦግ ያለ የትውልዶች ብርሀን መሆኑ እንዴት ሊረሳ፣ ሊዘለል እና ያልሆነ አስተያየት ሊሰጥባቸው ይቻላል?
የኢትዮጵያ ምሁራን እነ ሎሬት ጸጋየ ገ/መድህን፣ ኃይሉ ገ/ዮሐንስ፣ ሙሉጌታ ሉሌ፣ ብርሐኑ ዘሪሁን፣ መንግስቱ ለማ ወዘተ የዘመናዊት የኢትዮጵያዊነት ባህል ላይ አዲስ ጎዳና አመላካች ሆነው ያስጨበጡን እና ዛሬም በህይወት ያሉ በየሀገራቱ ተሰደው አለያም በሀገራቸው በዘረኞች ጉግ ማንጉግ ያው ጠቅላዩ በሚመሩት የደናቁርት መንጋ አንገት ደፍተው የሚኖሩን ሌሎቹ እንደፍየል ግልገል ሲታሰሩ እና ሲፈቱ፣ አንባገነኖች ባሻቸው በየማሰቃያ የጨለማ ቤቶች አካላቸውን ሲያጎድሉ የኖሩት ዛሬም ያሉት በድቅድቅ ጨለማ የሚበሩ ኮከቦች እንጅ እንደተባለው አላዋቂ ጉግ ማንጉግ ዘረኞች የኛ እና የእናነት ዘር ብለው የሚያጫርሱ ሕዝብ ከሕዝብ የሚያጣሉ፣ ለዘመናት ተጋብተው ተዛምደው የኖሩትን ለማፋታት፣ ለማለያየት እና የደም ንጽህና አንዱ ከሌላው አብሮ እንዳይኖር የሚያደርጉ አይደሉም። ምሁር እኛ ስናውቀው ያውም የኢትዮጵያዊው ምሁር ሞራል ከሕዝብ ፍቅር ጋር አጣምሮ የተላቭበሰው፤ ነዋይ ያልደለለው፣ ለአንባ ገነን ሸብረክ ያላለው ዛሬም በገሀዱ አለም ያውም በሀገሩ የሚኖር እንደነ ጋዜጠኛ ተመስገን አይነት እንጅ ቤተመንግስት የስልጣን ፍርፋሬ ይደርሰኛል ብሎ ደጅ የሚጠና እንዳልሆነ እንዴት አንድ የመንግስት መሪ፣ ያውም ተማሩ ከምንላቸው ተርታ ሊሰለፉ ነው ብሎ ሕዝብ ያጨበጨበላቸው አፍ ሊወጣ የማይችል አጉራ ዘለል የጅምላ እና ተራ አነጋገር ተነገረ?
የጅምላ ወቀሳ – የጅምላ አስተያየት መስጠት የጅምላ ክስ፣ የጅምላ ስድብ ሁልግዜ ስህተት ፈጣሪ ነው። ይህ ጅምላነት የሚፈጥረው ስህተት በዝቶ የሚታየው እና የሚደመጠው ደግሞ በይበልጥ ለአለፉት 50 አመታት በተካሄደው ትግል በጠባብ ብሔርተኞች እና በኋላም ህወሓት መራሽ ኦነግ መራሽ በሆኑ የፖለቲካ ፍልስፍና በተጠመቁ ግለሰቦች እና ስብስቦች ነው።፡ለምሳሌ ይህ ጸሐፊ የደርግ እና የወያኔ የፖለቲካ ትምህርት ቤቶች ያፈሯቸውን ሰወች ሁሉ በጅምላ “ሁሉም ምሁርነት የሌላቸው ደንቆሮ ለሆድ ያደሩ ካድሬወች ናቸው” በሎ ቢናገር ወይንም ቢጽፍ ብዙ ስህተት ይፈጥራል። ያውም እነዚህ ትምህርት ቤቶች ያፈሯቸው ተማሪወች በብዛት ማንነታቸው እየታወቀም ማለት ነው።፡ምክንያቱ ሁሉ ሰው አንድ አይነት አስተሳሰብ፣ ስራ እና ተግባር አይኖረውም በሚለው ትክክለኛ አስተሳሰብ በመመስረት ማለት ነው። ለምሳሌ የህወሓት/ኦነግ እምነት አራማጅ ምሁራን አማራን ጠላት፣ ኢትዮጵያን ጨቋኝ አድርገው እንደሚስሉት ማለት ነው። ያማለት ሁሉም ትግርኛ ተናጋሪ ምሁራን ሁሉም ኦሮሞኛ ተናጋሪ ምሁራን ብለን ከተፈጸምን ልክ እንደወያኔ እና ኦነግ ስህተት ያውም ትልቁን ሰራን ማለት ነው። ይህ አይነቱ አስተሳሰብ ነው ፖለቲካ ሆኖ ሀገራችንን እያፈረሰ ያለው። ይህን አስተሳሰብ ካልለወጥን ከታሰርንበት የስህተት ሰንሰለት መላቀቅ አንችልም።፡ለዚህ ነው ህገመንግሱም ይወገድ በምትኩም ሕዝብን መሀከል ያደረገ ለውይይት ቀርቦ ብዙሀኑ የሚስማሙበት ህግ እና ሀገራዊ ደንብ ይበየን የሚባለው። ህገመንግስቱም ልክ እንደገዥወቻችን ላለፉት 29 አመታት ይህችን ሀገር በብረት አገዛዝ እንደያዟት ሁሉ የጅምላ ፍርድ የሚሰጥ እና ላንዱ ብሔር ልሂቅ አካታች ሌላውን አግላይ በመሆኑ ማለት ነው የይወገድ ትግል የቀጠለው። ለማነኛውም በሀገራችን የተለመደው ነፍጠኛ፣ ትምክህተኛ ብሎ ለአንድ ብሔር የሚሰጥ፣ ጭቁን፣ የተበደለ፣ የተገፋ እያሉ ሌላውን የሚያስተዛዝን፤ ባጭሩ ሕዝብን በጅምላ የሚረግም፣ ሌላውን ወርቅ የሚያደርግ አነጋገር ይቅቁም፣ ይብቃን።