>
5:08 pm - Wednesday February 22, 0513

ከልማታዊ አንባገነናዊነት ወደ የብልጽግና አንባ....!!! (ያሬድ ሀይለማርያም)

ከልማታዊ አንባገነናዊነት ወደ የብልጽግና አንባ….!!!

 

 

ያሬድ ሀይለማርያም
በልማታዊ ቅዠት አገሪቱን መቀመቅ የከተተው ኢህአዴግ ከቆየበት ልማታዊ አንባገነናዊነት (developmental dictatorship) እራሱን አድሶ፣ ህውሃትን አሰናብቶ፣ አጋሮችን አሳፍሮ፣ በውህደት ተጣምሮ ሌላ የአንባ…. መንገድ ሊጀምር መዘጋጀቱን ትላንት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ምክትላቸው በይፋ አስታውቀዋል። ብልጽግናን ያለመው ይህ የገዢው ፓርቲ ጉዞ ሁለት እድሎች አሉት። ከቀድሞው የድርጅቱ አቋም ተምሮ፣ ስህተቶቹን ከልብ አርሞ፣ በውስጡ ያመረቀዘውን መርዝ ሙልጭ አድርጎ ተፍቶ እና ከልቡ ታድሶ አገሪቱን ወደ ትክክለኛ የብልጽግና አምባ ማውጣት ወይም በተሳሳተ መንገድ ገኖ ወጥቶ አንባው ላይ እራሱን አግንኖ፤ ብልጽግና ተኮር አንባገነናዊነትን (benevolent dictatorship) ማስፈን።
ህውሃት የመራችው ልማታዊ አንባገነናዊነት እፍኝ የማይሞሉ ከበርቴዎችን ፈጥሮ፣ እነሱኑ አልምቶና አደልቦ፣ ሚሊዮኖችን አደህይቶና አቆርቁዞ፣ አገሪቱን መቀመቅ ውስጥ ከቶ በዚህ ሳምንት ግብአተ ተመሬቱ ተፈጽሟል። ልማታዊው አንባገነናዊነት ቢቀበርም አብረውት ያልተቀበሩትን በሽታዎች ግን ሲያቆረቁዘው ለኖረው ሕዝብ እና ላደኸያት አገር አውርሶ ነው የሞተው። ሙስናው፣ የጎሳው ክፍፍል እና የከፋው ድህነት ዛሬም አገሪቱን ዋጋ እያስከፈለ ነው። ነገም እንዲህ በቀላሉ የሚለቀን አይመስለኝም። ከሁሉ የከፋው ግን ብሔር ተኮር የሆነው ክፍፍል ዛሬም የንጹሐንን ሕይወት እያስገበረን መሆኑ ነው።
ዛሬ የብልጽግናውን ጉዞ የጀመሩት ሰዎች ገና በጠዋቱ ለሕግ የበላይነት እና ለሰበአዊ መብቶች መከበር እያሳዩ ያሉት ዳተኝነት ይች ባቄላ ካደረች ያስብላል። የብልጽግናው ጉዞ ወደ ብልጽግና ተኮር አንባገነናዊነት እንዳይሸጋገር ብንሰጋ የሚገርም አይሆንም። ዛሬ በአገሪቱ፤ በተለይም በተወሰኑ አካባቢዎች ሥርዓት አልበኝነት ሲነግስ፣ ዜጎች የመንጋ ጥቃት ሰለባ ሆነው የመንግስት ያለህ እያሉ ሲጣሩ ጆሮ ዳባ ልበስ ማለቱ፣ የትምህርት ተቋማት ወደ ግጭት ቀጠና ሲቀየሩ ችግሩን በግዜ እንዲቆም ከማድረግ ይልግ ካልሆነ ዩንቨርሲቲዎቹን እንዘጋቸዋለን የሚል የሽሽት እና ሁከት ለሚፈጥሩት አካላት የተሸናፊነት ስሜት ማሳየቱ፣ ተማሪዎች ጥበቃ የሚያደርግላቸው መንግስታዊ አካል ጠፍቶ በየሜዳው ለማደር ሲገደዱ እና ዩንቨሪሲቲዎቻቸውን ለቀው ወደ የቤታቸው ሲመለሱ ቆሞ ማየቱ፣ የኃይማኖት ተቋማት እና ምዕመናን የጥቃት ሰለባ ሲሆኑ ምላሹ ዝምታ መህኑ የዚህን መንግስት አካሄድ ቆም ብለን እንድንመረምር ግድ ይላል።
ትንሽ ስለ ብልጽግና ተኮር አንባገነናዊነት አንዳንድ ነገር ልበል። ይህ አይነቱ ሥልጣንን የመጠቅለል እና ጉልበትን ተጠቅሞ ጎልቶ የመውጣት አካሄድ ዋነኛ እና ተቀዳሚ አላማብ አብዛኝውን የአገሪቱን ሕዝብ ወደ ኢኮኖሚያዊ ብልጽግና ማማ ከፍ ከማድረግ ትልም የሚነሳ ነው። ኢኮኖሚውን በማበልጸግ የአብዛኛውን ድሃ ሕዝብ የኑሮ ደረጃ ማሻሻል፣ ሲቀጥልም ማበልጸግ ነው ትልሙ። ብዙዎችን ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሎ ይታሰባል። ለዚህም እ.ኤ.አ ከ1944 እስከ 1980 ድረስ ዩጎዝላቪያን ያስተዳድር የነበረው እና በብዙዎች አይን ለብልጽግና የሚሰራ ተደርጎ ይቆጠር የነበረውን አንባገነን Josip Broz Tito መጥቀስ ይቻላል።
መንግስት ወደ እንደዚህ አይነቱ አንባገነናዊነት ሊሄድ ይችላል ብዮ የሰጋሁበትን ምክንያት በአጭሩ ልግለጽ እና ጽሁፌን ልቋጭ። መንግስት አገሪቱ ውስጥ ያለውን የመንጋ ሥርዓት አልበኝነት፣ የጭካኔ ግድያዎች፣ ሁከትና አለመረጋጋት፣ የትምህርት ተቋማትን ኢላማ ያደረጉ ጥቃቶችን እና ሌሎች ሥርዓት አልበኝነትን ያነገሱ ሕገ ወጥ እንቅስቃሴዎችን ለጊዜው ያላስቆመው ከአቅም ማጣት ነው ብዮ አላስብም። መንግስት ከበቂ በላይ አቅም እንዳለው እገምታለሁ። ለዛም ብዙ ማሳያዎችን ማቅረብ ይቻላል። ትልቁ ነገር እየተካሄዱ ያሉት ጥቃቶች እና አመጾች ኢላማ ያደረጉ ማንን ነው የሚለው ነው። ኢላማቸው መንግስትን እና ሥልጣን ላይ ያሉትን ሰዎች ለማጥቃት ቢሆን ኖሮ የመንግስት ምላሽ ሌላ ይሆነ ነበር።
ጥቃቶቹ መንግስትን ኢላማ ያደረጉ እና የለውጥ ኃይሉን ሥልጣን የሚፈታተኑ ነገሮች ቢሆኑ ኖሮ መንግስት ገና በጠዋቱ ያለ የሌለ ኃይሉን ተጠቅሞ አመጹን ለመቆጣጠር ይፍጨረጨር ነበር። ይሄኔ ዘፈኑም ስለ ብልጽግና ሳይሆን ሕገ መንግስታዊ ሥርዓትን ስለማስከበር ይሆን ነበር። ተመጣጣኝ ያልሆኑ ጥቃቶችን ጭምር በዜጎች ላይ ይወስድ ነበር። ለዚህም አንዱ ማሳያ የባለደራስ ማህበር እንቅስቃሴ ሥልጣኔን የሚጋፋ ነው ብለው ያሰቡት ጠቅላዩ እሳት ጎርሰው በደም ፍላት ጦርነት እናውጃለን ያሉት በአደባባይ ነበር። ምክንያቱም የባልደራስ ማህበር እንቅስቃሴ መንግስትን የሚቃወም እና የመንግስት አለአግባብ ሥልጣን መጠቀምን የሚቃወም ስለነበር። ባልደራስ ሰልፍ ጠራ ብሎ አዘጋጆቹን ማሰር፣ አባላቱን ማሰር፣ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንን ሰልፍ ማገድ እና ሌሎች ምልክቶችን ማየት ይቻላል። በተቃራኒው መንግስትን ማወደስ፣ የኖቤል ሽልማት ድጋፍ ሰልፍ ማካሄድ ደግሞ የተፈቀዱ ተገባራት ነበሩ።
እነዚህ በ ኢመደበኛ መልኩ ተደራጅተው የሚንቀሳቀሱ የመንደር ቡድኖች ትላንት ህውሃትን ሲታገሉ ቆይተው ዛሬ ፊታቸውን እንደ እነሱ ክፉ ሥርዓት ያቆረቆዘው ወገናቸው ላይ ነው። ስለዚህ መንግስት የጸቡ ተመልካች እንጂ ቀጥተኛ ተጠቂ አይደለም። ነገ ግን ነገሮች መልካቸው ሲስቱ እና መንግስት ተቆር ቅዋሜ ሲጀመር ዛሬ የወገኖችን እልቂት በትዝብት የሚያየው የአብይ አስተዳደር ያለ የሌለ ጉልበቱን ከመጠቀም ወደኃላ አይልም።
ዛሬ የሚታየው ሥርዓት አልበኝነት እና ሁከት ለብልጽግናው አንባገነናዊነት መነሻ እንደ ምክንያት ወይም ሰበብ (pretext) ሊወሰድ ይችላል። ሕዝብን ጥልቅ ስጋት ውስጥ እስኪገባ፣ ለአደጋ ተጋላጭ እሲሆን እና በሰላም ወጥቶ መግባት እስኪያቅተው ድረስ ትጠብቅ እና አንተን ለማዳን እኔ መንግስትህ የማላደርገው ነገር የለም ብለህ ዱላህን ይዘህ ትወጣለህ። ያኔ መንጋውን ብቻ ሳይሆን ተበዳዩንም አብረህ ጸጥ ለጥ አርገህ ትገዛለህ። ይህ አይነቱ ስልታዊ አንባገነናዊነት ተቀባይነት እንዲያገኝ የማድረጊያ ስልት ብዙ benevolent dictatorship ያሰረጹ አገሮች የሚጠቀሙበት ስልት ነው። ሕዝብም መንጋ ከሚያርደኝ በምንግስት ቢጫነኝ ይሻላል እያለ ከነጻነቱ በፊት ዳቦውን ያጣጥማል።
የዳቦ ነገር ሲነሳ ሰሞኑን ዜጎች እየታረዱ እና ዩንቨሪሲቲዎች እየታመሱ ባለበት በዚህ ሳምንት ውስጥ በመንግስት ሚዲያዎች አዲስ አበባ ውስጥ በሚሊዮኖች ዳቦ የሚያመርት ፋብሪካ ተከፈተ እየተባለ ሲዘፈን እና ትልቅ ፕሮፓጋንዳ ሲነዛበት ሳይ ይች ነጻነትን እያራቆተች ሆድ የምትሞላዋ የብልጽግና አንባገነናዊነት ቅርጽ ይዛ እየመጣች መሆኑ ነው የገባኝ። መንግስት ለዳቦው ፋብሪካ የሰጠውን ትኩረት ያህል በአገሪቱ ለተፈጠረው የደህንነት ስጋት ትኩረት አለመስጠቱ፣ በአገሪቱ ውስጥ እየተራባ ላለው ብሔር ተኮር መወነጃጀል ትክረት ሳይሰጥ በማhበረ ድህረ ገጽ ስለሚሰራጩ የሃሰት ዜናዎች ተጨንቆ ሕግ ወደማበጀት መሮጡ እና ሌሎች ምልክቶችን በአንክሮ ለተከታተለ benevolent dictatorship ጓዟን ጠቅላ አራት ኪሎ እየገባች መሆኑን ሊያሸት ይችላል።
ለማንኛውም የኢትዮጵያ ሕዝብ ለየትኛውም አንባገነናዊነት እራሱን አሳልፎ እንዳይሰጥ ነገሮችን በንቃት ሊከታተል ይገባል
በቸር እንሰንብት!
Filed in: Amharic