>

ምሁር አገር እንጂ ዘርና ጎሣ የለውም !  (አሥራደው ከፈረንሳይ )

ምሁር አገር እንጂ ዘርና ጎሣ የለውም ! 

 

 አሥራደው ከፈረንሳይ 

 

ማስታወሻ :

የማሰብ ነፃነታቸውን፤ በምስር ወጥ የማይሸጡ በመሆናቸው ብቻ፤ በገዛ አገራቸው ጉዳይ ሃሳባቸውን እንዳይሰጡና እንዲገለሉ ተደርገው፤ የበይ ተመልካች በመሆን፤ በኑሮ ጫና እንዲጉላሉ ተደርገው በአገር ውስት የሚኖሩና፤ ተገፍተው የሚወዷት አገራችው ኢትዮጵያን ትተው የተሰደዱ ሃቀኛ ምሁራን፤ የአገራቸውን ሠላምና ደህንነት፤ የህዝባቸውን ክብርና ፍቅር፤ በአገር ውስጥ በሚጣልላቸው የፍርፋሪ ጉርሻ፤ ተገፍተው የተሰደዱት ደግሞ፤ በፈርንጅ አገር በሚያገኙት ቂጣ፤ የሚሸጡ ሆዳሞች አይደሉም::  

ክብር ለህሊናቸው ላደሩ፤ በሳልና ሃቀኛ ምሁራን !!

መንደርደሪያ :

    • « Il n’y a ni mauvaises herbes ni mauvais hommes. Il n’y a que de mauvais cultivateurs. » (Victor Hugo)
  • « መጥፎ ዘር ወይም መጥፎ ሰው የለም፤ መጥፎ እየዘራ  የሚያበቅል እንጂ « ቪክቶር ሁጎ
    •  La haine nous amènera plus loin que l’amour » 
  • « ጥላቻ ከፍቅር ይልቅ ረጅም ርቀት ይወስደናል  (ያጓጉዘናል)»

 

መግቢያ :

 በመጀመሪያ የምሁርነት መለኪያ መስፈርቱ ምንድነው ?

ቁና፤ ሰፌድ፤ እርቦ ፤ ስልቻ ?  ወይስ: ብርጥቆ፤ ጣሳ ፤ ገንቦ፤ እንስራ፤ ጋን ?  ወይስ: ግራም፤ ኪሎ ግራም፤ ጆንያ ? ወይስ: ገንዘብ፤ ወሲብ፤ ጎሠኝነትና ዘረኝነት፤ ስልጣን ?

በቁና የጀመርኩበት አባባል፤ የገጠሩ ድሃ ወገኔ ሊያነሳው ይችል ይሆናል ብዬ ያሰብኩት ጥያቄ ሲሆን፤ በብርጭቆ ጀምሬ በጆንያ ያበቃሁበት ደግሞ፤ የከተሜው ድሃ ወገኔ ሊያነሳው ይችል ይሆናል ብዬ ያሰብኩት ጥያቄ ነው፤ በገንዘብ ጀምሬ በስልጣን ያበቃሁበት ጥያቄ ደግሞ፤ ካለፉት 30 ዓመታት ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ በፖለቲካ ስልጣን ላይ እንደ ሙጫ ተጣብቀው፤ ሙጭጭ በማለት፤ በህዝባችን ጉሮሮ ላይ እንደ አልቅት የተጣበቁትን፤ የዘርና የጎሣ ፖለቲከኞችና ካድሬዎቻቸውን የሚመለከት ይሆናል ::

በአንዲት አገር ውስጥ አብረን እየኖርን፤ ከማህበራዊና የአብሮነት አኗኗር ባፈነገጠ መልኩ፤ ባለን ግላዊና ቡድናዊ ጥቅም፤ በስሜታዊነት በያዝነው የደነደነ የዘርና የጎሠኝነት በትር፤ በቋጠርነው የጥላቻና የቂም ከረጥት ክብደት፤ ወይም በተቃራኒው፤ ባዳበርነው የአብሮነት ስሜት፤ ባለን የባህል ትስስርና ጥምረት፤ በፈጠርነው የጋብቻ ትስስርና የቋንቋ መወራረስ፤ አብረን ያለፍንባቸው የደግና የክፉ ዘመናትን ረጅም መንገዶችና ድልድዮች ላለማፍርስ፤ ለአገራችን ልኧሏዊነት ስንል ባደረግነው ጦርነት አብረን በመቁሰል: ደማችን ተቀላቅሎ ኮለል ብሎ የፈሰሰበት ወንዝ ላለማድረቅ፤ ወይም አብረን በተቀበርንበት የመቃብር ጉርጓድ ውስጥ የተቃቀፈው አጥንታችንን ላለመለያየት፤ በጥቅሉ በምንመካበት የኢትዮጵያዊነት ክብርና  በዳጎሰው የታሪክ መድበላችን፤ ለምሁርነት የምንሰጠው የመለኪያ መስፈርት ይለያያል ::

« ከሆድ አደር ምሁር ይልቅ ገጣባ አህያ ለኢትዮጵያ ባለውለታ ነች ! » በሚለው ቆየት ያለ መጣጠፌ 

ምሁር ለሚለው ቃል ሰጥቼው የነበረውን ትንታኔ በዚህ ማስፈንጠሪያ ይመልከቱ ::

https://ethiopiazare.com/amharic/articles/34-opinion/1844-asradew

በዛሪው መጣጥፌ ባጭሩ፤ በኔ ዕይታ የምሁርነት መለኪያው ህሊና ነው ብዬ ደምድሜያለሁ::

አዎ ህሊና ! ከጊዜያዊ የሥጋ ፍላጎትና ሽንፈት፤ ስልጣንና ሸፍጥ፤ ዘረኝነትና ጎሠኝነት፤ ጥላቻና ቂም በላይ፤  ህሊና ከአድማስ ባሻገር አገራችንና ህዝባችንን የምናይበት ተፈጥሯዊ መነጥር ነው!!

ዛሬ በአገራችን ኢትዮጵያ ሁለት ዓይነት ምሁራን አሉ ::

1ኛ. ለህሊናቸው ያደሩ፤ በሳልና ሃቀኛ ምሁራንና 

2ኛ. ለሆዳቸው ያደሩ፤ ግልብ ምሁራን፤ ሲሆኑ

ሆድ አደር፤ ወይም ግልብ ምሁራን፤ ለሆዳቸው ያደሩ፤ ሃሳዊ ምሁር ተብዬዎች: ወይም የምሁርነት ጭንብል አጥልቀው ሆዳቸውን ለሚሞላላቸው ሥርዓትና ባለስልጣን እንደ ቤት እንስሳው ያደሩት ሲሆን፤ እራሱ ሳይማር፤ ግብር እየከፈለ ያስተማራቸውን ድሃ ወገናቸውን እርግፍ አድርገው ትተው፤ ለባለተረኞች ባለሥልጣናት ጭራቸውን የሚቆሉ ናቸው::

ያለፉት የ30ዓመታትና፤ የዛሬዎቹ የዘርና የጎሥ ፖለቲከኛች፤ በእጅጉ የሚጠሏቸውና የሚፈሯቸው ቢኖር፤ ለህሊናቸው ያደሩ፤ በሳልና ሃቀኛ ምሁራንን ነው ::

መለስ ዜናዊ ሃቀኛ ምሁራንን በእጅጉ ይፈራና ይጠላ ስለነበር፤ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ዓላማው እንዲመቸው፤ የወሰደው የመጀመሪያ እርምጃ፤ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በአንድ ጊዜ ከ 40 በላይ የሚሆኑ የዩኒቨርስቲ መምህራንን፤ በካድሬያዊ መስፈርቱ ብቁ አይደሉም ብሎ ማባረር ነበር ::

አገራችን ኢትዮጵያ እነዚያ ብርቅዬ ምሁራን ልጆቿን፤ ለማፍራት ከድሃ ገበሬውና ከድሃ ሠራተኛው፤ ብዙ ገንዘብና ረዘም ያለ እድሜ ፈጅታለች:: ግና መለስ ዜናዊ በአንዲት ጀንበር በትኖ የትምክህት ጎራው ተመታ ብሎ አቅራራ :: « የጨው ተራራ ሲናድ ሞኝ ይስቃል ብልህ ያለቅስል » እንዲሉ ወያኔዎችና መሰሎቻቸው ተሳለቁ፤ አገራችን ኢትዮጵያ አነባች፤ ይኸው ዛሬም ድረስ እንባዋ አልደረቀም ::

ወያኔ (ኢህአዴግ ቁጥር 1) ለሆድ አደር ምሁር ተብዬዎች ስልጣን በመስጠት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን እንዲፈርሱና እንዲበተኑ በማድረግ፤ አገራችን ከምግብ ዕጦት በከፋ ፤ የዕውቀት ረሃብተኛ እንድትሆን በማድረግ፤ አገራችን፤ ሕዝብንና ሃቀኛ ምሁራንን ተበቅሏል::

ለዚህ እንደ ምሳሌ የምትጠቀሰው ገነት ዘውዴ ነች፤ በዩኒቨርስቲያችን ውስጥ ካልጠፋ ሰው፤ ስንት በሳል አንቱ የተባሉ አባት ምሁራን እያሉ ወያኔ ገነት ዘውዴን ከዩኒቨርስቲው ውስጥ በወረንጦ ነቅሶ፤ ለትምህርት ምኒስትርነት ሲሾም፤ ትልቁ ዳቦ ሊጥ እንደሚሆን ሳይታለም የተፈታ ንበር:: 

 ወያኔ (ኢህአዴግ ቁጥር 1) ሆድ አደር ምሁራን ተብዬዎችን፤ በሆዳቸው በመግዛት፤ ሊጠቀምባቸው ሲፈልግ ይክባቸዋል፤ ያሞካሻቸዋል፤ ሲበቃው ደግሞ እንደ ሸንኮራ መጦ በመጣል፤ እንደ በርሜል እያንከባለለ ለ30 ዓመታት የእነሱን ትከሻ ተመርኩዞ አገር ዘርፏል፤ አዘርፏል :: ሰንካላ ሥርዓተ ትምህርት በመንደፍ፤ ወጣቱን የዘረኝነት ጠበል ጠምቆ፤ በጎሣ ጋቢ ዓይኖቹን በመጋረድ አንድ ትውልድ ሙሉ አምክኗል :: 

ሌላው ሊሰመርበት የሚገባ ጉዳይ፤( ኢህአዴግ ቁጥር 1 ) እና ሆድ አደር፤ ወይም ግልብ ምሁራን፤ በሳል ወይም ሃቀኛ ምሁራንን በእጅጉ ይፈሯቸዋል፤ ይጠሏቸዋልም :: ምክንያቱም ሃቀኛ ምሁራን የሆድ አደሮችን፤ ያበጠ ፊኛ የሚያስተነፍሱበት የመረቃ ዕውቀት ያላቸው ከመሆኑም በላይ፤ የተኮፈሱበትን ኩይሳ የሚንዱበት ጠንካራ የዕውቀት በትር በእጃቸው ጨብጠዋል ::

ሆድ አደር፤ ወይም ግልብ ምሁራን፤ የበሳል ወይም ሃቀኛ ምሁራንን ስም ለማጥፋት፤ በባለተረኞች ነን ባይ፤ የስልጣን አሽከርነት ስር ተወሽቀው፤ ስድብና ማናናቅ፤ ማቅለልና ማሸማቀቅን (የሚሸማቀቅላቸው ከተገኘ) እንደመሳሪያ አድርገው በመጠቀም፤ ሃቀኛ ምሁራንን ከሥራ በማፈናቀል ብሎም እንዲሰደዱ በማድረግ: ሽንፍላቸውን ለመሙልት ሲሉ ብቻ አገርን ይንዳሉ፤ ህዝብን ያደኸያሉ :: 

የሰሞኑ የኦነግ/ኦህዴድ (ኢህአዴግ ቁጥር 2) የብልጽግና ተብዬ ሆድ አደር፤ ወይም ግልብ ምሁራን፤ ስብስብ፤ ለህሊናቸው ባደሩ በሳል ምሁራን ላይ፤ እያጮሁ ያሉት ጅራፍ፤ የሁለታኛው ዙር ቀጣይ የኦነግ/ኦህዴድ (ኢህአዴግ ቁጥር 2) እቅድ መሆኑን ከወዲሁ ልንገነዘብ ይገባል::  

የመለስ ዜናዊ ትምህርት፤ ለደቀ መዝሙሩ አብይ አህመድና መሰሎቹ፤ የቆዳ ላይ ንቅሳት ነው፤ ቢፈገፍጉትም አይለቅ:: ከመለስ ዜናዊ አምልኮ: ወደ አብይ አህመድ አምልኮ፤ በብርሃን ፍጥነት ካልተለወጥክ፤ ምሁር አትባልም:: በመሆኑም በሰሞኑ የኦነግ/ኦህዴድ (ኢህአዴግ ቁጥር 2)  መስፈርት ከጎሠኝነትና ዘረኝነት፤ ከቂምና ጥላቻ፤ ለሥልጣን በሆድ ከመገዛት ባሻገር፤ ለአገር አንድነት፤ ለሰብዓዊ መብት መከበር፤ ለፍትሃዊ የአገር ሃብት ክፍፍል፤ ለዕኩልነትና ነፃነት፤ በጥቅሉ ለአብሮነት የቆምክ ከሆነ ምሁር አትባልም፤ አይደለህምም :: 

ትከሻህን ከፍ፤ አንገትህን ቀና አድርገህ፤ ለምን ? እንዴት ? በምን ክንያት ? የሚሉ ጥያቄዎችን እንዳታነሳ ከወዲሁ፤ መዋከብና መሰደብ፤ መንጓጠጥና መሸርደድ ይኖርብሃል፤ ምክንያቱም ምርጫው  ተቃርቧላ! ፈርተህ ዝም እንድትልና እንድትሸማቀቅ ያስፈልጋል:: የለመዱት የኮሮጆ ግልበጣና በመቶ ፕርሰንት( 100%) ሕዝብ መርጦን ስልጣን ይዘናል የሚሉበትን ቀን ሌት ተቀን እየቆጠሩ ነው ::

የዘርና የጎሣና ፖለቲከኞቹ በእጅ አዙር በፍጥነት ስልጣን ላይ ፊጢጥ ለማለት ተቻኩለዋል ::         

  – ለምን የአገር ሃብት የዘረፉ ሌቦች ለፍርድ አይቀርቡም ? ብለህ እንድትጠይቅ አይፈልጉም ::        

    – ለምን የጎሣና የዘር ፖለቲከኞች ህዝብን ያፈናቅላሉ ? ብለህ መጠየቅ በነሱ መስፈርት ወንጀል ነው ::

– ለምን የሕዝብ አንጡራ ሃብት የሁኑ ድርጅቶች: የቴሌኮሚንኬሽን፤ የመብራት ሃይልና፤ የአየር መንገድ….ወዘተ የመሰሉ ይሸጣሉ? ብለህ እንድትጠይቅ አይፈልጉም::                                                                                    – ለምን በጠራራ ፀሐይ ባንኮችን የዘረፉ አጋሚዶዎች አይጠየቁም ? የተጠለፉ ሴት ተማሪዎቻችን፤ እስከዛሬ ለምን ተፈልገው አልተገኙም ? ተብለው እንዲጠየቁ አይፈልጉም :: – ከግብጽ ጋር ለሚደረገው የዓባይ ወንዝ ግድብ ድርድር፤ በውሃ ሃብት ሃይል ማመንጨት፤ በኢኮኖሚ፤ በዲፕሎማሲ፤ በፖለቲካል ሳይንስና በታሪክ፤ በአገር ውስጥና ከአገር ውጪ ያሉ በሳል ኢትዮጵያዊ ምሁራን እንዲሳተፉበት ለምን አይደረግም ? ብለህ እንድትጠይቅ አይፈልጉም ……ወዘተ.

በጥቅሉ: ዝም እንድትል ከወዲሁ የህሊና ሰለባና፤ ርካሽ የካድሬዎች አለባሌና ሽሙጥ ይነዛብሃል:: በነሱ መስፈርት፤ ከአብሮነትና አንድነት፤ ከጋራ ብልጽግናና ወንድማማችነት፤ ከእኩልነትና ከነፃነት ይልቅ  የዘርና የጎሣ ፖለቲካ እያራገቡ፤ ጥላቻና ቂም በመንዛት፤ የመገንጠል ፖለትካን እንደ ገደል ማሚቶ መልሶ መላልሶ ዘወትር ማንቧረቅ ብቻ ነው ምሁርነት ::

ማሳረጊያ :

ማካፈልን የማያውቀው፤ የኦነግ/ኦህዴድ (ኢህአዴግ ቁጥር 2) የብልጽግና ተብዬ ስብስብ፤ ለ 30 ዓመታት የአገር ሃብት የዘረፉ፤ ህዝብ ያፈናቀሉና፤ የብዙ ወገኖኖቻችንን ህይወት የቀጠፉና በወህኒ ያጎሩ፤ ሕዝቡን አደህይተው እነሱ የበለጸጉበት ሥርዓት አልበቃ ብሏቸው፤ እንደገና ከያሉበት በመጠራራት፤ እነሱ ለዳግም ዘረፋና ብልጽግና፤ እኛን ለዳግም ባርነትና ድህነት ለመዳረግ፤  ጥርሶቻቸውን ስለው ዓይኖቻቸውን በጨው ታጥበው፤ ዳግም ሥልጣን ላይ ቂጢጥ ለማለት፤ ትከሻ ለትከሻ ይተሻሻሉ ::

ሌላው ሰሞኑን ያየነውና የሰማነው፤ በእጅጉ አሳፋሪ የሆነ ጉዳይ፤ ወያኔ ባደረገባቸው ወከባና እስር፤ በአገር ውስጥና በመላው ዓለም የምንገኝ ኢትዮጵያውያንና፤ ትወልደ ኢትዮጵያውያን ሠላማዊ ሰልፍ በማድረግ ድምጻችንን ከፍ አድርገን የጮህንላቸው፤ እንደ መረራ ጉዲናና በቀለ ገርባ ያሉ የጎሣና የዘር ፖለቲከኞች « ቢከፍቱት ተልባ » ሆኖ መገኘት ነው:: በተለይ የመረራ ጉዲና የጎሣና የዘረኝነት ማጥ ውስጥ ገብቶ ሲዳክር ማየት፤ በእጅጉ ያሳፍራል:: መማር: ከጎሠኝነትና ከዘረኝነት በላይ፤ የከበረ ሰብዕናን የሚያላብስ መሆኑን ዘንግቶ፤ ዘቅጦ በማየታችን፤ በእጅጉ አፈርን ::

ጎበዝ ! ምሁር አገር እንጂ ዘርና ጎሣ የለውም ! በአገር ውስጥና ከአገር ውጪ በመላው ዓለም ያሉ ሃቀኛ ምሁራን ተገዢነታቸው ለህሊናቸው እንጂ፤ ለሆዳቸው ባለመሆኑ፤ የአገራቸውን ሃብት፤ ሠላምና ደህንነት፤ የህዝባቸውን ሰብአዊ መብት መከበርና፤ የህግ የበላይነትን ለማስከበር፤ የማንንም አምባ ገነን ተመጻዳቂ መሪ ሆነ፤ የዘርና የጎሣ ፖለቲከኞችን መልካም ፈቃድ ጠያቂዎች አይደሉም፤ አይሆኑምም !!   የወያኔ (ኢህአዴግ ቁጥር 1) ለ30 ዓመታት በዘረፋት አገራችንና፤ ባደኸዩት ሕዝባችን ላይ፤ የዘርና የጎሣ ፖለቲካ አቀንቃኞች የሆኑት፤ የኦነግ/ኦህዴድ (ኢህአዴግ ቁጥር 2) ዘራፊዎች፤ ተረኛ በልጻጊዎች ለመሆን አሰፍስፈዋል :: 

በዘረፋ መበልጸግ ወንጀል መሆኑ ለማይገባቸው፤ ቁጥር1 እና ቁጥር 2 የሌቦች ስብስብ፤ ከአሁን በኋላ በአገር ውስጥም ሆነ በውጨው ዓለም ያለን ዜጎች፤ ምሁራን፤ ገበሬ፤ ነጋዴ፤ ሠራተኛ፤ ተማሪና አስተማሪዎች፤ በመተባበር፤ ለአገራችንና ለህዝባችን መብት መከበር፤ ዘብ መቆማችንን ልንነግራቸው ይገባል ::

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ !!

እግዚአብሔር ኢትዮጵያና ሕዝቧን ይባርክ !!

Filed in: Amharic