>

የግብፅ የአስዋን ግድብ እውነታዎች!!! (ቬሮኒካ መላኩ)

የግብፅ የአስዋን ግድብ እውነታዎች!!!

ቬሮኒካ መላኩ
ግብጻውያን ‹‹የአስዋን ግድብ›› ያለፈው ክፍለ ዘመን ብርቱ የድካማቸው ውጤት እና በታሪክ የመዘገቡት የሚኮሩበት እና የሚመኩበት አንጡራ ሃብታቸው እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
….
ግድቡ የተገነባው ከ1952 የግብጽ አብዮት በኋላ ነው፡፡ ግድቡ 111 ሜትር ከፍታና 3.8 ኪሎሜትር ርዝመት አለው፡፡ 10 ቢሊየን kilowatt-hours በየአመቱ  የማመንጨት አቅም ያለው ሲሆን የግብጽ ሌሊቶች ከዚህ በሚመነጭ የብርሃን ጎርፍ እየተጥለቀለቁ ከተሞቻቸው ከቀን ጸሐይ ይልቅ በምሽት መብራቶች ያብረቀርቃሉ፡፡
ለዚህ የብርሃን ጎርፍ ማመንጫ ለግድቡ የተገጠሙት 12 ተርባይኖች ያለእንቅልፍ ይሽከረከራሉ፡፡ ልብ አድርግ 95 ፐርሰንት የግብጽ ህዝብ የሚኖረው የናይል ወንዝን ተከትሎ
20 ኪሎ ሜትር እንኳን ሳይርቅ ነው፡፡
ግድቡ በ1.2 ቢሊየን ዶላር ወጪ የተገነባ ሲሆን በወቅቱ ምእራባውያን በማኩረፋቸው ገንዘቡ በቀጥታ የተገኘው ከታላቋ ሶቭየት ህብረት ነበር (እነ አሜሪካ ለምን እንዳኮረፉ በዚሁ ጽሁፍ መጨረሻ ላይ ታገኘዋለህ)፡፡
ግድቡ 33 ሺህ ስድሰት መቶ ስኩዌር ኪሎሜትር የሚሆን የምድር ስፋትን ለሚያዳርስ የመስኖ ልማት በቀጥታ ውሃ ያቀርባል፡፡ የግድቡን ሥራ በ1960 እ.ኤ.አ ያስጀመሩት  ፕሬዝዳንት ገማል አብድል ናስር ሲሆኑ የተጠናቀቀው በአስር አመት ጊዜ ውስጥ ነው፡፡
የአስዋን ግድብ መገንባት በሱዳን እና በግብጽ መካከል እጅግ ማራኪ የሆነው የናስር ሐይቅ እንዲፈጠር አስችሏል፡፡ እንዲሁም የኑቢያ ሐውልቶች ጉዳት እንዳይደርስባቸውም ተከላክሏል፡፡
የግድቡ ዋናና እጅግ ቀዳሚ የሆነው ዓላማ እኛን ተሰናብቶ እየጋለበ የሚሄደውን የአባይን (ናይል) ወንዝ እና የሚያደርሰውን ጥፋት ለማስታገስ ብሎም ዓመቱን ሙሉ በመላ የግብጽ ምድር ላይ ለሚከናወነው መስኖ ተኮር የግብርና ልማት የተመጣጠነ የውሃ ፍሰት እንዲፈጠር ለማድረግ ነው፡፡
ግድቡ የግብጽን የከርሰ ምድር ውሃ እንዲጨምርም አስችሏል፡፡ ከግድቡ የሚመነጨው ከፍተኛ መጠን ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል በምድሪቱ ላሉ በርካታ ፋብሪካዎች ለአፍታ የማይቋረጥ ጉልበት ሆኗቸዋል፡፡
ፖለቲካዊ አንድምታ ያለው የአስዋን ግድብ ያገሪቱ ህዝብ በድህነት እንዳይናወጥ ያደረገ ሲሆን በበርካታ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎቹ የግብጽን ወጣቶች የኢኮኖሚ ጥማት
የመለሰ ሲሆን የተፈጠሩ በርካታ የሥራ እድሎች የተረጋጋ እና የተሻለ ህይወት እንዲመሩ አስችሏቸዋል፡፡(ልብ አድርግ ኢትዮጵያ ውስጥ ተመርቀው ስድስት እና ሰባት አመት ስራ
ያላገኙ ወገኖች አሉህ)፡፡
በግድቡ ዙሪያ የተመጠኑ እውነታዎች 
1. ከ1970-1990ዎቹ እ.ኤ.አ ባሉት ጊዜያት የምስራቅ እና የምእራብ አፍሪካ ሀገራት በድርቅ እና በረሃብ ሲናወጡ እድሜ ለአስዋን ግድብ ግብጽ ያ ክፉ ቀን ጨረፍታውም
አልነካት፡፡(ይህንን የሚሉት እነሱ ናቸው)፤
2. ይህ ግድብ ‹‹አስዋን ሃይ ዳም›› በመባል የሚታወቅ ሲሆን የመጀመሪያው ግድብ ‹አስዋን ሎው ዳም› በ1898 በእንግሊዞች ተጀምሮ በ1902 የተጠናቀቀው ነው፤
3. የግድቡ ሥራ በእንግሊዞች ታቅዶ በራሺያዎች ተሰርቷል፤
4. 90 ሺህ ኑቢያዎች ከመኖሪያ ስፍራቸው በ45 ኪሎሜትር እንዲርቁ ተደርገዋል፤
5. ግድቡ ሲገነባ አስር አመት ወስዶበታል (በወቅቱ ቴክኖሎጂ)፤
6. በ1912 አድሪያን ዳኒኖስ የተባለ የግሪክ መሃንዲስ ተመሳሳይ ግድብ ለመስራት ሃሳብ አቅርቦ የነበር ሲሆን በወቅቱ የነበረው ንጉስ ፋሩቅ ሃሳቡን አልተቀበለውም፡፡ ይህንነ ለማድረግ የበረታው ፕ/ት ገማል አብድል ናስር ነው፤
7. ግድቡ በዓመት 10042 ጊጋዋት የኤሊክትሪክ ሃይል ያመነጫል፡፡
..
እነሱ ይህን ሁሉ ትሩፋት ከአባይ ወንዝ አግኝተው 70 ፐርሰንት በጨለማ ለሚማቅቀው እና በኩበት ጪስ ለሚጨናበሰው (ያውም የውሃው ባለቤት ሆኖ፣ ያውም በማይጎዳቸው መልክ ለመጠቀም እየተነገራቸው) ለኢትዮጵያ ህዝብ ቅንጣት ታህል ርህራሄ አለማሳየታቸው ይቀፋል፡፡
አስደማሚው ነገር ግድቡ ሊሰራ በታሰበበት ወቅት ምእራባውያን በተለይ አሜሪካና እንግሊዝ በቀዝቃዛው ጦርነት (የጂኦፖለቲካል ቀውስ) ውስጥ ከራሽያ ጋር ሲነታረኩ በነበረበት ወቅት ገማል አብድል ናስር ላቀረቡት ሃሳብ ስላልተገዛ የግድቡን መገንቢያ ገንዘብ ሲከለክሉት በቼኮዝሎቫኪያ በኩል ተራምዶ ከራሽያ ጋር በመደራደር በ2% ወለድ 1.2 ቢሊየን ዶላር ማግኘቱ ሲታወስ ነው፡፡ ያኔ አሜሪካ ቆሽቷ እርር ብሎ ነበር፡፡ (ከላይ እንዳልኩህ እነአሜሪካ ያኮረፉት በዚህ ነው)፡፡
ግድቡ ግብጾችን ጎዳቸው ከተባለ በቀንድ አውጣ ሸክም የሚመጣው <ስኪስቶሶሚያሲስ> የተባለው ፓራሳይት የሚያስከትለው ብለድ ኢንፌክሽን ብቻ ነው፡፡ ለዚህም ኪኒኒ
እየዋጡ ነው፡፡ መድሃኒቱን ደግሞ ያገኘላቸው ጅጅጋ የተወለደው የሀገርህ ልጅ ዶክተር አክሊሉ ለማ ነው፡፡ የበሽታው ሌላ ስም ቢልሃርዚያ ነውና፡፡
ሲጠቃለል፡- ውሃው የበረሃው ሙቀት ከሚበላው እኛጋ መቆየቱ ጠቃሚ እንደሆነ በ1950ዎቹ የነገራቸው የእንግሊዙ መሃንዲስ ሃሮልድ ኤድዊን ነው፡፡ እንዲሁም የህዳሴው ግድብ በናስር ሃይቅ እና በናይል ወንዝ የሚከማቸውን ደለል በመቀነስ እጅግ እንደሚጠቅማቸው ቢነገራቸውም ለማዳመጥ የፈለጉ አይመስልም፡፡
Filed in: Amharic