>

ለሰው ዘር አነሰው!!! (ታገል ሰይፉ)

ለሰው ዘር አነሰው!!!

ታገል ሰይፉ

  “ለሰው ዘር ያንሰዋል፡፡ ኮሮና ላይ ቆመህ ዘር ይታይሃል ወይ? ኮሮና ላይ ቆመህ አፍ መፍቻህ ምንድነው? አፍ መፍቻህ ጤና ነው…. አፍ መፍቻህ ምግብ ነው… ስለዚህ የኮሮናን ጉንፋን እንኳ ተቋቁመው መጉላት ከማይችሉ የዘር ግርግሮች እራሳችንን እንጠብቅ፡፡”


             ራሱን አልፍሬድ አድለር ብሎ የሚጠራው ታላቅ የስነልቦና ምሁር “ምንድነው የመኖር ትርጉም?” ሲል ይጠይቃል፡፡ ምንድንነቱን ቁልጭ አድርገው የሚያሳዩ ሶስት መሰረታዊ ቁርኝቶች እንዳሉም አስረግጦ ይናገራል፡፡
የመጀመሪያው ቁርኝት “በዚህ ውጣ ውረድና ፈተና በበዛበት አለም ላይ ራሳችንንና ቤተሰባችንን ምን ሰርተን ነው በሰላም የምናኖረው?” ከሚል ጥያቄ ይነሳል::
ሁለተኛው ቁርኝት ደግሞ “በዙሪያችን ካሉት ሰዎች ጋር ትብብር በመፍጠር ከሚገኘው ውጤት እንዴት ተጠቃሚ መሆን እንችላለን?” ሲል ይጠይቃል፡፡
ሶስተኛው ቁርኝት፤ የሰው ልጆች በሁለት ተቃራኒ ፆታዎች ተከፍለው መፈጠራቸውን መሰረት አድርጎ ይነሳና “በነኚህ ሁለት ተቃራኒ ፆታዎች ግንኙነት በኩል፣ የሰው ዘር ቀጣይነትን የማረጋገጥ ፍላጎት በልባችን ውስጥ እንዴት ይስረፅ?” የሚል ጥያቄን ያስከትላል፡፡
ወንድማችን አድለር እንደሚለው፤ የያንዳንዱ ሰው የህይወት ትርጉም የሚወሰነው ለነዚህ ሶስት መሰረታዊ ቁርኝቶች በሚሰጠው ምላሽ ነው፡፡ፖለቲካም /እውነተኛ ከሆነ/ ለነዚህ ሶስት መሰረታዊ ቁርኝቶች የራሱን ምላሽ የሚሰጥ የፍልስፍና ዘርፍ ነው:: በተለይም የመጀመሪያውን መሰረታዊ ቁርኝት ለማሳለጥ ይተጋል፡፡ ህዝቡ ራሱንና ቤተሰቡን የሚያኖርበትን ስራ ለመፍጠር ብቻ ሳይሆን ለጤናው፣ ለምግቡና ለደህንነቱ ዋስትና ጭምር አጥብቆ ይጨነቃል፡፡
ኮሮና ቫይረስ ዋሽንግተን ከመግባቱ በፊት በተጀመረው ያሜሪካ ፣ ተፎካካሪዎች ንግግር ውስጥ በተደጋጋሚ የምንሰማቸው የምርጫ ማማለያዎችም ከዚህ መሰረታዊ ቁርኝት የመነጩ ናቸው፡፡ የመቀስቀሻ ሃሳቦቻቸው፤ የህዝቡን የኑሮ ውድነት….. የስራ አጥነት…. የጤና ዋስትና /Health care/ እና በመሳሰሉት የህዝቡ የእለት ተእለት ጥያቄዎች ላይ ያተኩራሉ፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ ከአሜሪካውያኑ በከፋ በርካታ ችግሮች ተተብትቧል፡፡ ለምሳሌ፡- የአሜሪካ ህዝብ ረሃብን የሚያውቀው በኛ በኢትዮጵያውያን በኩል ነው፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን አሁን ድረስ እንራባለን… ያልተራብነውም ቢሆን በቀን ሁለቴ መብላት ብርቃችን ነው… በቀን ሁለቴ የበላነውም ካቀረቀርንበት ገበታ “ጠገብኩ” ብለን የምንነሳው አልፎ አልፎ ነው፡፡
ያሜሪካ ህዝብ ስለ አተት የሚያውቀው ነገር የለም፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ግን አተትን ብቻ አይደለም፡፡ መተትንም ጠንቅቀን እናውቃለን /በነገራችን ላይ አተት አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት ማለት ሲሆን መተት ደግሞ መደበኛ ተቅማጥና ትውከት እንደማለት ነው/
ኢትዮጵያችን ከአተትና ከመተት በተጨማሪም ከብዙ የአለማችን ክፍሎች ከመጥፋታቸው የተነሳ ከነስማቸውም የማይታወቁ ብርቅዬ በሽታዎችም የሚገኙባት ሀገር ነች፡፡ የብርቅዬነታቸውን ያክል በዩኔስኮ ያልተመዘገቡ ብርቅዬ ህመሞች…..
ከነኚህ ብርቅዬ ህመሞቻችን አንዱ የዘር ፖለቲካ ነው፡፡ የኛዎቹ “ፖለቲከኞች” ከአሜሪካ ፖለቲከኞች በበለጠ ለህዝባቸው የምግብና የጤና ዋስትና መጨነቅና መፍትሄ ማፈላለግ በሚገባቸው ወቅት ያልበላንን ሲያኩ ሰነበቱ፡፡
የህዝቡን ችግር መፍታት ትተው የህዝቡን ትዳር በማፋታት ላይ ባተኮረ አሳፋሪ የብሄር ፖለቲካቸው ሲያናፉብን ከረሙ…
በመሀል አሜሪካን ያመሰው የኮሮና ወረርሺኝ እኛም ሃገር ገባ፡፡ ስልጡኖቹ የአሜሪካ ምርጫ ተፎካካሪዎች ኮሮና ከመግባቱ በፊት ያነሱት የፖለቲካ አጀንዳ በወረርሺኙ ምክንያት አልተገታም:: ወረርሺኙ ከመግባቱ በፊት ያነሱትን የhealth care ጉዳይ አጠናክረው ቀጠሉ እንጂ….
የኛዎቹ የዘር ፖለቲከኞች ግን በኮሮና ወረርሺኝ ትንፋሽ አጠራቸው፡፡ ምክንያቱም የዘር ፖለቲካ እንደዚህ ያሉ መሰረታዊ የህዝብ ጥያቄዎችን ለመመለስ ፍላጎቱም ዝግጁነቱም ብቃቱም የላቸውም፡፡ እንዲያውም የኮሮና ቫይረስ ኢትዮጵያዊን ከመያዙ በፊት ቀድሞ የያዘው የዘር ፖለቲከኞቻችንን አንደበት ነው፡፡
በሰሞነ ኮሮና “ወረርሺኝ ገባ” ብሎ ሆዱን የሚረሳ ሰው የለም፡፡ እንዲያውም የሆድ ጥያቄ ከመቼውም ጊዜ በላይ ያሳስበዋል:: ለዚህም ነው በሃገራችንም ሆነ በሃገረ አሜሪካ ሰዎች ከወትሮው በተለየ ዝግጁነት አስቤዛቸውን ጨማምረው መግዛት የጀመሩት፡፡
አድለር ግንባር ቀደም ሲል የገለፀው የሰው ልጅ ቁርኝትም፣ በዚህ የኮሮና ሰሞን ግንባር ቀደምነቱን ይበልጥ አስመስክሯል፡፡ምክንያቱም “በዚህ ውጣ ውረድ በበዛበት ምድር ላይ እንዴት አድርጌ እራሴንና ቤተሰቤን በሰላምና በጤና ማኖር እችላለሁ?” የሚለው ጥያቄ ይበልጥ ጎልቶ ወጥቷል፡፡ የሰው ልጅ ለምግቡና ለደህንነቱ፣ ለጤናውና ለትራንስፖርቱ አብዝቶ የተጨነቀው በዚሁ የኮሮና ሰሞን ስለሆነ…
አድለር አጽእኖት የሰጠውን ይህን የሰው ልጅ መሰረታዊ ቁርኝት አስቀድመው የተገነዘቡት የአሜሪካ ፖለቲከኞችም፤ በዚህ የወረርሺኝ ሰሞን ቀደም ሲል ሲያቀነቅኑት የነበረውን የhealth care ጥያቄ አጠንክረው በማንሳት ይበልጥ ደምቀው ታይተዋል:: ይበልጥም ተደማጭ ሆነዋል፡፡
የኛዎቹ ጉንድሽ “የምርጫ ተፎካካሪዎች” ግን ከትክክለኛው የፖለቲካ ምህዋር ከማፈንገጣቸው የተነሳ የወረርሺኙን ተፅእኖ አሸንፈው መጉላት አልቻሉም፡፡ ከኮሮና በፊት ምላሳቸውን ያስረዘሙበት የዘር ፖለቲካቸው ደበዘዘ… ፈዘዘ…
ወረርሺኙ ከመግባቱ በፊት ዋና የነበሩት የህዝባችን አንገብጋቢ ጥያቄዎች ግን የቫይረሱን ተፅእኖ አሸንፈው ይበልጥ ማንገብገባቸውን ቀጥለዋል:: ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከወትሮው በከፋ ሁናቴ ለቤተሰቡና ለጤንነቱ… ለቀለቡና ለትራንስፖርቱ በመጨነቅ ላይ ነው፡፡ ለነዚህ ውድ ጥያቄዎቹ መልስ የሌለው ፖለቲካ በነገሰበት ምድር፤ ብቻውን የሚፍጨረጨር ምስኪን ህዝብ መሆኑ ከፋ እንጂ….
በፈጣሪ ምህረት አንድ ቀን ኮሮና ቫይረስ የተፈቀደለትን የቆይታ ጊዜ አገባዶ ከሃገራችንም ከአለማችንም ይሰናበታል:: ከዚህ የሚያልፍ ወረርሺኝ የምንማረው አንድ የማያልፍ ሃቅ አለ፡፡ ይሄውም የዘር ፖለቲካ ከሰው ልጆች መሰረታዊ ጥያቄና መልስ ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌለው ነው፡፡ አድለር መሰረታዊ ቁርኝት ሲል ያቀረበልን ትንታኔም ሆነ የ21ኛው ክፍለ ዘመን የሰለጠነ ፖለቲካ የሚነግረን ይሄንኑ ነው፡፡
ለሰው ዘር ያንሰዋል፡፡ ኮሮና ላይ ቆመህ ዘር ይታይሃል ወይ? ኮሮና ላይ ቆመህ አፍ መፍቻህ ምንድነው? አፍ መፍቻህ ጤና ነው…. አፍ መፍቻህ ምግብ ነው… ስለዚህ የኮሮናን ጉንፋን እንኳ ተቋቁመው መጉላት ከማይችሉ የዘር ግርግሮች እራሳችንን እንጠብቅ፡፡
በመጨረሻም ኢትዮ-ቴሌኮም በስልክ መጥሪያችን ላይ የገጠመውን አሪፍ ማስጠንቀቂያ ላስታውሳችሁ፡-
“ጤና ይስጥልኝ… የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የእርሶም ሀላፊነት ከፍተኛ ነው…. እጅዎን በሳሙናና በውሃ ይታጠቡ… በተቀመጡበት ስፍራ በቂ አየር እንዲኖረው ያድርጉ… ትኩሳትና የሳል ምልክት ከሚያሳዩ ሰዎች ጋር ንክኪ አያድርጉ…. የህመም ስሜት ካለዎ አቅራቢያዎ የሚገኝ ሀኪምን ያማክሩ…. ባለመጨባበጥ ራስዎንና ወገንዎን ከኮሮና ቫይረስ ስርጭት ይጠብቁ…. ኢትዮ-ቴሌኮም….ፍጹም ጤና ለህዝባችን ይመኛል….”
ቴሌ ለህዝባችን ጤንነት ያሳየውን ተቆርቋሪነት ኮሮና ካበቃ በኋላም አጠናክሮ ቢቀጥል ምኞቴ ነው፡፡ እንዲህ እያለ፡-
“…..ጤና ይስጥልኝ… የዘረኝነት ቫይረስን ስርጭት ለመግታት የእርሶም ሃላፊነት ከፍተኛ ነው… ህሊናዎን በምህረትና በይቅርታ ይታጠቡ…. የተቀመጡበት ስፍራ በቂ ፍቅርና መተሳሰብ እንዲኖር ያድርጉ… የቂም ትኩሳትና የዘረኝነት ቀኬ ከሚታይባቸው ሰዎች ጋር ተመሳሳይ የተግባር ንክኪ አያድርጉ… የብሄርተኝነት ስሜት ሲጠናብዎ አቅራቢያዎ ለሚገኝ መንፈሳዊ አባት ያማክሩ… ይህ ምልክት ከሚታይባቸው ሰዎች ጋር ባለመበጣበጥ ራስዎንና ወገንዎን ከዘረኝነት ቫይረስ ስርጭት ይጠብቁ… ኢትዮ-ቴሌኮም… ፍጹም ጤናማ ሃገርን ለህዝባችን ይመኛል፡፡”
…በተረፈ ሳይለየን ያቆየን….
Filed in: Amharic