>

ሕዝብን ከወረራ የሚከላከልን ኃይል በአሉታዊነት የፈረጀን መንግስት!!! (ጌታቸው ሽፈራው)

ሕዝብን ከወረራ የሚከላከልን ኃይል በአሉታዊነት የፈረጀን መንግስት!!!

ጌታቸው ሽፈራው
1) በፋኖ ጉዳይ ትልቁ ችግር መንግስት በመግለጫ የሚያስመስለውና በተግባር የሚያደርገው ፈፅሞ የተለያየ መሆኑ  ነው። አዴፓ ጎንደር አካባቢ እየሆነው ባለው ላይ መግለጫ አውጥቷል። ፈጥኖ መልስ መስጠቱ ጥሩ ነው። ሆኖም አሁንም የተሸፋፈኑ ጉዳዮች አሉ። ብልፅግና ስለ ምርጫው ሲያስብ የመጀመርያ አደጋ ብሎ የፈረጀው ፋኖን እንደሆነ መሸፋፈን አያስፈልግም። ጎንደር አካባቢ በርካታ ችግሮች ሲፈጠሩ ከርመዋል። ለአብነት ያህል ህፃናት እየታገቱ ተገድለዋል። በርካታ ንፁሃን እየታገቱ ያለ አቅማቸው ገንዘብ ሲከፍሉ ከርመዋል። ይህ ሲሆን አዴፓ የረባ እርምጃ አልወሰደም። እረኞች  በስጋት ከቤት እንዳይወጡ ሲደረግ ነገ “ምረጠኝ” ብሎ ቁም ስቅል ለሚያሳየው ሕዝብ ቅንጣት ኃላፊነት አልተሰማውም። እንዲያውም ጠገዴና አርማጭሆ ድረስ ሄደው ጉዳዩን ለመፍታት የጣሩ ኮሚቴዎች ዛቻ እንደደረሰባቸው ተነግሯል። ኮሚቴው እውቅና ያገኘው በስንት ውትወታ ነው። ወደቦታው ሚዲያ ይዘው ሊሄዱ ቢጥሩም “ያጋልጡናል” ተብለው ሳይሄዱ ቀርተዋል። ህፃናት አግተው ያረዱት አረመኔዎችን የትህነግ ሰዎች እንደተቀበሏቸው እየታወቀ ለሕዝብ ግልፅ አልተደረገም። አሁንም ይህ አፋኝ ቡድን ከድርጊቱ አልተቆጠበም!
በተመሳሳይ “የቅማንት ኮሚቴ ነኝ” የሚለው አካል  የእንሰሳትና የሰውን ምላስ ሲቆርጥ ከርሟል። ምንም እንዳልተፈጠረ ከዚህ ቡድን ጋር ቁጭ ተብሎ መነጋገር ተችሏል። ይህ አረመኔ ቡድን ጋር ቁጭ ብሎ የተነጋገረ የፌደራልና የክልል መንግስት ይህ አረመኔ ቡድን ከተማ ሊያጠፋ ሲል ቀድሞ ከተገኘው ፋኖ ጋር ለመነጋገር እድሎች እያሉት  በሚገባ አልተጠቀመበትም። አዴፓም ሆነ የፌደራል መንግስቱ በመግለጫ ስለ ፋኖ መልካም ነገር የሚያወራ ቢሆንም የተያዘው አቋም ግን ተቃራኒ ነው። በመግለጫ የሚባለውን ያህል ቅንነት ቢኖር ችግሮችን መፍታት በተቻለ ነበር። የፋኖን አቅም ይበልጥ መጠቀም ይቻል ነበር።
2) ሁለተኛው ችግር ፋኖውን መጠቀሚያ ማድረግ የሚፈልግ ኃይል መበራከቱ ነው። ፋኖ በስሙ ይለመንበታል።  ከዳያስፖራ በርሮ መጥቶ “ፋኖን አደራጃለሁ” የሚል በስመ ፓርቲ የተቋቋመ ኃይል ሳይቀር ነበር። ጭራሽ ፋኖ ማዶ ተሻግሮ ከተማውን እየጠበቀ ገበያ ውስጥ በፋኖ ስም ገንዘብ የሚሰበስብ ኃይል አለ። ሌሊት ጥይት እየተኮሰ የፋኖን ስም የሚያስጠቁር ኃይል አለ። መሳርያ ስለያዘ ብቻ ከተማ ገብቶ መሬት የሚከልል አለ። በዚህ ምክንያት ጎንደር ትልቅ ችግር ውስጥ ገብታለች። ለስሙ ከፋኖ ጋር ወዳጅ መስሎ “አይዟችሁ” ብሎ ተመልሶ ፋኖ ካልጠፋ የሚለው የመንግስት አካልና ኃላፊ ቁጥር ቀላል አይደለም። ፋኖ ለአማራ ሕዝብ ምን ማለት እንደሆነ የሚያውቅ ኃይል ሁሉ በስሙ ማትረፍ ይፈልጋል። መንግስትን ጨምሮ!
 ይህም ሆኖ ቀን ከሌት የከተማው ጉዳይ የሚያሳስባቸው ፋኖዎች አሉ። በዛ ክፉ ዘመን ዱር ገደሉን የጣሱት እነ አጋዬ አድማሱን የመሰሉት የፋኖ መሪዎች ከተማ ውስጥ መሳርያ ሲወዘውዙና ሲነታረኩ አይገኙም። መታመን ያለበት ሌላው ጉዳይ ሀቀኛ ከሚባለው መካከልም አብዛኛው ከከተማ መውጣት የማይፈልግ መሆኑ  ነው።  እነ መሳፍንት ተስፉ በዚህ እድሜያቸው ከተማ ውስጥ አይገኙም። እንዲያውም በቀደም ዳባት ላይ በነበረው ስብሰባ ስራቸው ከተማ ውስጥ መሆን እንደሌለበትም መክሯል። እነ ጎቤ መልኬ ለአማራ ሕዝብ ያን ያህል መስዋዕትነት ሲከፍሉ ከተማውን ብቻ ሳይሆን ንብረታቸውን ጭምር ጥለው የሚገባቸውን ቦታ ይዘው ነው። የፋኖን ክብር ከፍ ያደረጉት ተራራና ገደሉን ወጥተው ነው።
 ፋኖ ከተማ ውስጥ በመሆኑ በስሙ እየተነገደበት ነው። ከተማ ውስጥ በመሆኑ ለጥቃት ተጋላጭ ሆኗል። ከተማ ውስጥ በመሆኑ የዲስፕሊን ጉድለቶች እንዲበራከቱ ሆኗል። ፋኖ  የከተማውን ደሕንነት የሚጠብቅ ቢሆንም መሃል ከተማ ላይ በመዋሉ ለተለያዩ ችግሮች ተጋላጭ ሆኗል።  ይህ ጉዳይ መቀረፍ አለበት። እንደ አንድ የፀጥታ ኃይል የተለየ ቦታ ተሰጥቶት ችግር ሲፈጠር ፈጥኖ የሚደርስበት አጋጣሚ ሊፈጠርለት ይገባል።  ማንም በስሙ እንዳያጭበረብር ነገሮች ሊሟሉለት ይገባል። ከምንም በላይ  እንደ አቋም የተያዘው የገዥዎች አጥፊ አቋም መቀየር አለበት!
3) ሌላኛው ችግር ያለ መረጃ የሚፅፈው፣ የሚጠቅምና የሚጎዳውን የማይለየው ፌስቡከኛ ጉዳይ ነው። በውስጥ ማጣራት የሚችለውን ሁሉ “ኧረ ምን ተፈጥሮ ነው?” ብሎ  ሕዝብ ያወዛግባል። ለስሙ ግን አወዛጋቢ ሳይሆን አንቂ ነው። ከዛም ቀጥሎ ያገኘውን አሉባልታ ይፅፋል። “እንትና ድረስለት፣ እንትና አይዞህ” እያለ ይፅፋል። በውስጥ መስመር ከወንድሙ ጋር በሚያደርገው ጭቅጭቅ፣ በአስተያየት መስጫ ከወገኑ ላይ በሚደረግ መነታረክ፣ ፌስቡክ ላይ በሚፃፍበት ቡጨቃ ከፌስቡክ ሰፈር የሚጠፋ ፈርጣጭ ሳይቀር ሊያታኩስ ሲጥር ቅንጣት ኃላፊነት አይሰማውም። “አንድ አማራ ለሁሉም አማራ ሁሉም አማራ ለአንድ አማራ” የሚል ድንቅ መፎክር እያሰማ  “በለው” ሲል ፋኖው ከአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ ጋር እንደሚገጥም ደግሞ አያስበውም።  ትልቁ የገዥዎቹ ስኬት ልዩ ኃይሉን በሕዝብ ማስጠላት ነው። ልዩ ኃይሉ የሚጠላው ደግሞ ፋኖን ከመሰለ የአማራ ኃይል ጋር ሲገጥም ነው። ይህ ሆኖ እያለ ፌስቡክ ላይ በየፊናው የፋኖ መግለጫ  እያስመሰለ ጉዳዮችን ለማባባስ የሚጥር ፌስቡከኛ  ገዥዎቹ ወደሚፈልጉት ሴራ ሰተት ብሎ እየገባ መሆኑን ሊገነዘብ ይገባል። እሱ ፌስቡክ ላይ ተደብቆ “በለው” ሲል ፋኖ ያለው የሚታወቅ አውላላ ላይ መሆኑን መገንዘብ አለበት! አንቂ ነኝ ካለ ከማወናበድ፣ ከማደናበርና ከመደናበር መውጣት አለበት!
እስካሁን መፈታት የነበረባቸው ጉዳዮች ነበሩ። አሁንም ግን ጊዜው አላለቀም! በመሆኑም:_
1) ገዥዎቹ በመግለጫና በሚዲያ እየወጡ የሚናገሩትና አዳራሽ ዘግተው የሚናገሩትን አራምባና ቆቦ አቋማቸውን ማስተካከል ይገባቸዋል። በፋኖ ጉዳይ ለካድሬያቸው የሚሰጡትን ስልጠና እና ለሕዝብ የሚሰጡትን መግለጫ ሆድና ጀርባ ሆኖ ለሕዝብም ለእነሱም መፍትሔ እንደማይመጣ ሊያውቁት ይገባል።
2) ገዥዎቹ አቋም ይዘዋል። ይህን አቋማቸውን እንዲቀይሩ ከማድረግ ባሻገር ይህን ጉዳይ በመፍታት ከገዥዎቹ በልዕልና የተሻሉ አካላት አሉ። ወለጋ ውስጥ ያን ሁሉ እየፈጠረ ያለ ኃይል፣ ባንክ የዘረፈውን ኃይልና ኦዴፓን ቁጭ ብለው እንዲነጋገሩ ሙከራ ተደርጓል።  ሕዝብን ከወረራ የሚከላከልን ኃይል በአሉታዊነት የፈረጀን መንግስት “ይህን ለምን ታደርጋለህ?” ብሎ ማፋጠጥ የእምነት አባቶች፣ የሽማግሌዎች፣ የተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ የሲቪክ ማኅበራትና የሌሎች ኃላፊነት የሚሰማቸው አካላት  ተግባርም ነው።  መታወቅ ያለበት ገዥዎቹ አካባቢውን በመከላከያ ዕዝ ስር ቢያደርጉ ያዋጣቸዋል። ችግር ሲፈጠር እንኳ የእነሱ  ልጆች ችግር አይደርስባቸውም። ችግር የሚደርስበት ሌላው ሕዝብ ነው። እስካሁን ካለፉበት ባሻገር ለራሳቸው ጠባብ ጥቅም ሲሉ፣ ማንም አይጎዳብንም ብለው ግድ የለሽ ቢሆኑ፣ ከዚህ አጥፊ አቋማቸው በተቃራኒ ቆሞ የበዛ ስልት ማሳየት ያለበት ለሕዝብ የሚጨነቀው አካል ነው።
3) ፌስቡክ ላይ ከወገኑ ጋር የማይግባባና በትንንሽ አጀንዳ ሲኳረፍ የሚውለው ፌስቡከኛ  የራሱን ወገን ለማዋጋት የሚነፋውን ፊሽካ ማቆም አለበት። ይህ ከገዥዎች ያልተለየ እብደት ነው።  ፋኖዎችንም ሆነ ሌሎች ወገኖቻችን በሕይወት እያሉ መፍትሔ ሳናመጣላቸው ሲገደሉብን የፌስቡክ ፕሮፋይል በማድረግ አንመልሳቸውም። በመሆኑም መረጃ ሳይጣራ ለሕዝባችን የማይጠቅም ጉዳይ ስንፅፍ ከመዋል በፊት መረጃ ማሰባሰብ፣ የትኛው ቢወጣ እንደሚጎዳ፣ የትኛው እንደሚጠቅም ደግመን ደጋግመን ማሰብ የግድ ይለናል።
4) ፋኖ ለሕዝብ የሚሰራ ኃይል ነው። ይህ ኃይል ለሕዝብ በሚጠቅምበት ቦታና አቅም እንዲሰራ አስፈላጊው ድጋፍ ሁሉ ሊደረግለት ይገባል።
5) ፋኖ ሕዝብን ለመከላከል የቆመው የመንግስት ኃይል ድክመት ስላለ ነው። አሁንም ድረስ አማራው ላይ ያነጣጠረ ኃይል ስላለ ነው።  ስለ ፋኖ ሲወሳ ፋኖ አማራው ላይ   ጥቃት ያደርሳሉ ብሎ የሚጠባበቃቸው ኃይሎችም ጉዳይ መታሰብ አለበት። ጉዳዩ የተነሳበትን የጎንደሩን አካባቢ ብንጠቅስ እንኳ ምላስ የሚቆርጠው፣ ከተማ ካልወረርኩ የሚለው ኃይል አሁንም መሳርያ ከመወልወልና  ከማንዣበብ አልተመለሰም። ይህ ኃይል አንድ ባልተባለበት ሁኔታ ፋኖ ትኩረት ማድረግ የአማራ ሕዝብ ላይ ያነጣጠረ እንደሆነ በግልፅ የሚያሳይ ይሆናል።
6) በፋኖ ጉዳይ እጅግ ሰከን ብለን የምናያቸው ጉዳዮች አሉ። አማራው በሌላ ኃይል እየታመሰ፣ ተከላካዩን እየገፉ ማስወጣት የሚጠቅመው ለሌላ አካል ነው። ምን አልባት ለገዥዎቹ በስሙ ለማሰርና ለማሳደድ ይጠቅማቸው ይሆናል። እንደ ሕዝብ፣ እንደ ሀገር ካሰብነው ማዳኛን መታነቂያ የማድረግ ያህል አጉል ነው። ይህ አጓጉል አካሄድ ሌላ ጣጣ እንዳያመጣ፣ ክፉ ቀን አለፍን ስንል ሌላ ክፉ ቀን እንዳይመጣ ሳንጯጯህ ሰከን ብለን ማሰብ፣ ሳንሸፋፍን ችግሮቹን መነጋገርና  መፍትሔ ከመፈለግ ውጭ ሌላ አማራጭ የለንም! አንድም!
Filed in: Amharic