>

መንግሥት ሆይ በሕገ መንግስቱ ላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማወጅ የተሰጠው ሥልጣን የገዢውን ፓርቲ የሥልጣን ህልውና ለመጠበቂያ ብቻ አይደለም!!! (ያሬድ ሀይለማርያም)

መንግሥት ሆይ በሕገ መንግስቱ ላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማወጅ የተሰጠው ሥልጣን የገዢውን ፓርቲ የሥልጣን ህልውና ለመጠበቂያ ብቻ አይደለም!!!

ያሬድ ሀይለማርያም
አገርን እና ሕዝብን አደጋ ሊጥሉ የሚችሉ የተፈጥሮ አደጋዎች እና የሕዝብን ጤንነት አደጋ ላይ የሚጥል የኮሮና አይነት ወረርሺኝም ሲከሰት አደጋውን ለመቆጣጠር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ይታወጃል። እስኪ ወግ ይድረሰን እና ይህ አንቀጽ ለመጀመሪያ ጊዜ አገሪቱ በተገቢው ሰዓት እና ቦታ ላይ ትጠቀምበት። ቀደም ሲል ገዢው ፓርቲ ወንበሩ ነቅነቅ ባለ ቁጥር የሚመዘው የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 93/1/ሀ የሚከተለውን ይላል፤ መንግስት “… የሕዝብን ጤንነት አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ ሲከሰት፤ … የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመደንገግ ሥልጣን አለው።”
መንግስት በየቀኑ በአግባቡ የማይተገበሩ መግለጫዎችን እየሰጠ ችግሩ እንዲባባስ ከሚያደርግ ኬኒያን ጨምሮ ሌሎች የአፍሪቃ አገሮች ሳይቀር እንዳደረጉት የኃይማኖት ተቋማትን ሙሉ በሙሉ መዝጋት ይኖርበታል። ትላትን ቤተክህነት መግለጫ ቢሰጥም ዛሬ በየመንገዱ ካህናት እና ምዕመናን ቫይረሱን በማጥንት እናባርራለን ብለው የማይገባ ግብግብ ሲገጥሙ ታይቷል። ጎበዝ ለእኔ ይህ አይነቱ ተግባር እግዜርንም ያለቦታው መፈታተን ነው። በዚህ ከቀጠልን ከሳምንታት በኋላ አጣኙም፣ ታጣኙም፤ ቀዳሹም፣ አስቀዳሹም፤ ሰባኪውም፣ ተሰባኪውም አይኖሩም።
መንግስት ይህን አይነት እርምጃ ለመውሰድ ከጤና ባለሙያዎች እንጂ ከኃይማኖት አባቶች ጋር አይደለም መመካከር ያለበት።
ይህ ክፉ ቀን እስኪያልፍ ጸሎት በየቤቱ ይሁን!
Filed in: Amharic