>
6:16 am - Wednesday December 7, 2022

በዘመነ ኮሮና....  !! (ዘመድኩን በቀለ)

በዘመነ ኮሮና….  !!

ዘመድኩን በቀለ
• ኦርቶዶክስ ተዋሕዶዬ ሆይ !!  በርሽን እንዳትዘጊ። ወለል አድርገሽ ክፈቺው! እንደ ሌሎቹ በበጎቹ ላይ ጀርባሽን አትስጪ! ሙስሊሙም ጴንጤውም፣ ካቶሊኩም፣ ሶሻሊስቱም ይመጣል!  አቅፈሽ አጥምቂው! የእኔ ሐዋርያ። በርሽን እንዳትዘጊ!!!
* በዓለም እንዲህ እየሆነ ነው!!!
በዘመነ ኮሮና ሰው ባለወቀ እግዚአብሔር ባወቀ ለጊዜውም ቢሆን ዝሙት ቀረ። ተከለከለ። መላፋት፣ መዳራትም ቀረ። መጀንጀን፣ መጀናጀንም ቀረ። መላከፍ መለካከፍም ቀረ። እነ ሁሉ አማረሽም አደብ ገዙ። እነያየኋት አትለፈኝ፣ እነ ሁሉን ቀምሼም ልሙትም አደብ ገዙ። ሹገር ዳዲም፣ ሹገር ማሚም ተነፐሱ። ያዩትን ቀሚስ ሁሉ መከተልም እፉ ሆነ። ባገኙት ሥፍራ ሁሉ ባገኙት ጭን ስር መወሸቅም ሲያምርህ ይቅር ተባለ። ቤርጎ፣ ፔኒሲዮን ተዘጋ። አንጆሪ ከንፈር፣ ጉች ጉች ያለ አርቴ ጡት፣ አርቴ መቀመጫም ውኃ በላው። ተመልካች፣ ጎብኚም አጣ። የማትበላ ወፍም ሆነ። የዝሙት መንፈስ አጋንንቱ ተመታ።
•••
ኤድስ የሚመሰገንበት ዘመን መጣ። በዘመነ ኮሮና ፌስታልም፣ ኮንዶምም አያድንህም ተባለ። በዘመነ ኮሮና ማንንም አትጠጋም፣ አትጨብጥም፣ አትጎነትልም፣ አትስምም። አትዳብስም። ማሳጅ ቤት ድሪያ፣ ቡና ቤት የዝሙት ንግድም ቆመ። አትንካኝ ባዩ በዛ።
አትቅረበኝ፣ ወዲያልኝ ወጊድ ባዩም በዛ። እናም ይሄን ስታይ ኮረናዬ ቫይረስ ብቻ ሳትሆን እግዚአብሔር ለዚህች ሰዶማዊት ምድራችን አደብ ማስገዣነት የላካት አርጩሜው ናት ብለህ ለማመን ትገደዳለህ። ኮረናዬ የእኔ ኮረና እባክሽ ትንሽ ጊዜ ቆዪልን። ትንሽ ትንሽ ሳይበዛ፣ በጣምም ሳይረዝም ትንሽ ጊዜ ቆዪልን። ቶሎም አትሂጂብን።
•••
ኮሮናዬ ስንቱን አነጸች፣ አስተማረች፣ ድንበር ዘግታ፣ በረራ አስቁማ፣ ሱቅ ሱፐርማርኬት አዘግታ፣ ትምህርት ንግድ አዘግታ፣ ቤቱን በላዩ ላይ በገዛ እጁ እንዲጠረቅም፣ እንዲቆልፍ አስደርጋ ስንቱን መከረች፣ ዘከረች መሰላችሁ። ኮሮና የስንቱን የተደበቀ፣ የተሸፈነም ገመና ገለጠች። አደባይም አሰጣችው መሰላችሁ። ጀግና ነኝ ያለእኔ ወንድ የለም፣ ሞትን አልፈራም ባዩን አፈጀግና ሁላ በየጎሬው ከተተችው፣ ወሸቀችው እኮ። አንቦቆቦቆቦቀችው።  አምጰረጰረችው። ላብ በላብ አደረገችው አይገልፃትም። OMN እንኳ ባህታዊ ሲሆን? መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ ማለት እኮ ነው የቀረው።
•••
አጅሬ ኮሮና የተከሰተው በዘመነ ሁዳዴ በጾመ አርባ በዐቢይ ጾም በጾመ ኢየሱስ መሆኑን ስታይ ደግሞ የበለጠ ትገረማለህ። ሳትወድ በግድህ 14 ቀን ሁለት ሰባት ዝግ ሱባኤ ትገባለህ። ሥጋቤት የለም፣ ቁርጥ የለም። ካቲካላ ቤት፣ ሆቴል ሬስቶራንት ዝግ። ጭፈራ፣ ዳንኪራ ቤት ዝግ። ሺሻቤት፣ ጫትቤት የለም። ሴተኛ አዳሪ መሸመት ካካ ሆነ። ባለጌ ወንበር ላይ ተጎልቶ የጋለሞታ ዳሌ ቸብቸብ ማድረግ ሲያምርን ቀረ። ወንድኛ አዳሪነትም፣ ሴተኛ አዳሪነትም ከሰረ። ዘቀጠ። ተዋረደ። ሁሉም አደብ ገዛ። እንደ እኔ ዓይነቱ ዘልዛላ የሆነው ባለጌ ስዱ ሁላ የግዱን ከቤት ዋለ። ጭምትም ሆነ። እናም ይሄን ይሄን ስታይ ኮረናዬ ቫይረስ ብቻ ሳትሆን እግዚአብሔር ለዚህች ሰዶማዊት ምድራችን አደብ ማስገዣነት የላካት አርጩሜው ናት ብለህ ለማመን ትገደዳለህ። ኮረናዬ የእኔ ኮረና እባክሽ ትንሽ ጊዜ ቆዪልን። ትንሽ ትንሽ ሳይበዛ፣ በጣምም ሳይረዝም ትንሽ ጊዜ ቆዪልን። ቶሎም አትሂጂብን።
•••
ኮረናዬ ኃያላኑን ሀገራት ሁላ አስተነፈሰች። ገመናቸውንም አደባባይ አሰጣች። ላስቬጋስም ቺቺኒያም እኩል ተዘጉ። ሚኒሶታም ሱሉልታም እኩል ተጠረቀሙ። ኒውዮርክ ባዶ ሆነች። አውሮጳ ጭር አለች። የሰው ልጅ ከፈጣሪው በታች መሆኑን የግዱን አመነ። ጨረቃ ላይ ወጣን፣ አውቶሚክ ቦንብ ሠራን፣ በህክምና ሳይንስ ተራቀቅን፣ የጦር ኃይላችን አንደኛ ነው። የእድገት ደረጃችን የመጠቀ ነው ወዘተ ባዩን ሁላ ውኃ በላው። አሜሪካም ለማኝ ሆነች። ከደቡብ ኮርያ የህክምና መሣሪያ ለመነች። የቻይና እግር ላይ ተደፋች። እናም ይሄን ይሄን ስታይ ኮረናዬ ቫይረስ ብቻ ሳትሆን እግዚአብሔር ለዚህች ሰዶማዊት ምድራችን አደብ ማስገዣነት የላካት አርጩሜው ናት ብለህ ለማመን ትገደዳለህ። ኮረናዬ የእኔ ኮረና እባክሽ ትንሽ ጊዜ ቆዪልን። ትንሽ ትንሽ ሳይበዛ፣ በጣምም ሳይረዝም ትንሽ ጊዜ ቆዪልን። ቶሎም አትሂጂብን።
•••
በዘመነ ኮሮና ባል ከልጆቹ ጋር የመዋያ ጊዜ አገኘ። ሚስት የባሏን የባልነት ጣዕም አጣጣመች። አባወራው አደብ ገዛ። ቢዚ ነኝ፣ ሥራ ላይ ነኝ እያሉ እስከ እኩለሌሊት ገዳም ሰፈር፣ ዳትሰን ሰፈር፣ ቺቺንያ፣ ቦሊቪያ፣ ካዛንቺስ፣ ፒያሳ ማምሸት ቀረ። ቤተሰብ አስርቦ ገንዘብ ለጋለሞታ፣ ለመጠጥ ለአምቡላ መበተኑ ቀረ። ካለ ሆቴል ምግብ አልቀምስም ባዩ ጠብራራ ሁላ ነጭ ሽሮ ያለዘይት ይጠርግ ይልፈው ጀመር። ትእቢት ተነፈሰ። ያበጠው ጉራ ተነፈሰ። ሰከነ። አጅሬ ባል የሚስትን ስቃይና ችግር በዓይኑ በብረቱ እያየ አብሮ ተካፈለ። እናም ይሄን ይሄን ስታይ ኮረናዬ ቫይረስ ብቻ ሳትሆን እግዚአብሔር ለዚህች ሰዶማዊት ምድራችን አደብ ማስገዣነት የላካት አርጩሜው ናት ብለህ ለማመን ትገደዳለህ። ኮረናዬ የእኔ ኮረና እባክሽ ትንሽ ጊዜ ቆዪልን። ትንሽ ትንሽ ሳይበዛ፣ በጣምም ሳይረዝም ትንሽ ጊዜ ቆዪልን። ቶሎም አትሂጂብን።
•••
ኮረናዬ መቅሰፍት ናት። ያውም ሳኒታይዘር ሳሙናና ሃኪም በሽ የሆነበት ቤተ መንግሥት የምትገባ መቅሰፍት፣ እግርኳስ ተጫዋች ነው፣ ሃብታም ነው፣ ጄነራል ነው፣ እስላም ነው፣ አይሁድ ነው፣ ካቶሊክ ነው፣ ዶክተር ነው አክተር ነው የማትል መቅሰፍት። ሁሉን ትጎበኛለች፣ ሰዶማውያን ላይ ትበረታለች፣ ተንኮለኛ ሴረኛ ላይ ትበረታለች። በምድር ላይ ካሉ ሃገራት የማትጎበኘው ሃገር የለም። ሁሉአገርሽ ናት ኮሮናዬ። አታዳላም፣ ሙስና፣ ጉቦም አታውቅም። ጄነራሉንም ወዛደሩንም እኩል ትገነድሳለች። ሀብታሙንም ደሃውንም እኩል ትቀጣለች። እናም ይሄን ይሄን ስታይ ኮረናዬ ቫይረስ ብቻ ሳትሆን እግዚአብሔር ለዚህች ሰዶማዊት ምድራችን አደብ ማስገዣነት የላካት አርጩሜው ናት ብለህ ለማመን ትገደዳለህ። ኮረናዬ የእኔ ኮረና እባክሽ ትንሽ ጊዜ ቆዪልን። ትንሽ ትንሽ ሳይበዛ፣ በጣምም ሳይረዝም ትንሽ ጊዜ ቆዪልን። ቶሎም አትሂጂብን።
•••
ድሮም ሆነ አሁን በተለይ ኢትዮጵያን የነኩ፣ ያስነኩ፣ ያሴሩባት፣ የሸጧት፣ ያሸጧት፣ የዛቱባት፣ የመከሩባት፣ የዶለቱባት፣ ያስዶለቱባት ሁሉ፣ የቤት ውስጥ ቀጋ የውጭ አልጋዎቹም ጭምር የሚቀሰፉባት መቅሰፍትም ናት። ከፈለክ ሊስቱን እየው። ኢትዮጵያ ሃገረ እግዚአብሔር ናት፣ የቃልኪዳኑ ታቦት፣ ግማደ መስቀሉ፣ ያለባት የአምላክ ዙፋኑ መቅደሱ ነች። ቅዳሴው፣ ምስጋናው፣ መስዋእቱ የማይቋረጥባት የምስጋና ግምጃ ቤቱ ናት፣ የዕጣኑ ጢስ፣ ዝማሜው፣ ዝማሬው የማይቋረጥባት መቅደሱ ናት። እናም ማንም ይሁን ማን ኢትዮጵያን በክፉ የሚያይ ይቀጣል። ግብፅ ትመስክር። እናም ይሄን ይሄን ስታይ ኮረናዬ ቫይረስ ብቻ ሳትሆን እግዚአብሔር ለዚህች ሰዶማዊት ምድራችን አደብ ማስገዣነት የላካት አርጩሜው ናት ብለህ ለማመን ትገደዳለህ። ኮረናዬ የእኔ ኮረና እባክሽ ትንሽ ጊዜ ቆዪልን። ትንሽ ትንሽ ሳይበዛ፣ በጣምም ሳይረዝም ትንሽ ጊዜ ቆዪልን። ቶሎም አትሂጂብን።
•••
አሁን አሁን ኮረናዬ ከሰባኪ በላይ ተደማጭ፣ ከካህን የበለጠ ተከባሪ ሆናለች። ብዙ ሰው የግድ ማጾም ጀምራለች። ብዙውን ሰው ንስሐ እያስገባችም ነው። ለሥጋወደሙም እያበቃች ነው። ኮሮናዬ ብዙውን ሰው እየዠለጠች ወደ ቤተ መቅደስ እየነዳችው ነው። አሁን ብዙውን ሰው ሳይወድ በግዱ ዘማሪ፣ አስቀዳሽ፣ ጿሚ ጸሎተኛ መዝሙር ስብከት አዳማጭ እያደረገችው ነው። የፓትሪያርክ ስብከትና ቡራኬ ያልመለሰውን፣ እነ ዘበነና ምህረተአብ ያቃታቸውን፣ የቄስ የመምሬ ግዝት ያላመጣውን ህዝብ ኮረናዬ እያመጣችው ነው። ነጠላ መልበስ፣ ረጅም ቀሚስ፣ ቅዳሴ ውዳሴ በፈቃደኝነት ተጀመረ እኮ። እኔንም ዕጠኑኝ፣ ይባርኩኝ ይፍቱኝ አባ ባዩ በዛ። እናም ይሄን ይሄን ስታይ ኮረናዬ ቫይረስ ብቻ ሳትሆን እግዚአብሔር ለዚህች ሰዶማዊት ምድራችን አደብ ማስገዣነት የላካት አርጩሜው ናት ብለህ ለማመን ትገደዳለህ። ኮረናዬ የእኔ ኮረና እባክሽ ትንሽ ጊዜ ቆዪልን። ትንሽ ትንሽ ሳይበዛ፣ በጣምም ሳይረዝም ትንሽ ጊዜ ቆዪልን። ቶሎም አትሂጂብን።
•••
ኮሮናዬ ጀግና ናት። እነ ሁሉም ኬኛን አስደበቀች። ጃዋርን ፈሪ አደረገች። ለህዝብ አዛኝ አስደረገች። አህመዲን ጀበልን አስደበቀች። ስርቻ ከተተች። በቀለ ገርባን ድምጡን አጠፋች። መራራ ጉዲናን ማጀት አስቀረች። ዐቢይ አሕመድን ከዙረት ገላገለች። ከቤተ መንግሥት ውልፍት የለም። የሚኒሊክን ቤተ መንግሥት ውኃ አጠጪ አትክልተኛ አደረገች። ካገኘው ጋር መላፋት፣ መተቃቀፍ፣ መሳሳም አስቀረች። የፎቶ ፕሮፓጋንዳ ድራሹ ድምጥማጡም ጠፋ። እናም ይሄን ይሄን ስታይ ኮረናዬ ቫይረስ ብቻ ሳትሆን እግዚአብሔር ለዚህች ሰዶማዊት ምድራችን አደብ ማስገዣነት የላካት አርጩሜው ናት ብለህ ለማመን ትገደዳለህ። ኮረናዬ የእኔ ኮረና እባክሽ ትንሽ ጊዜ ቆዪልን። ትንሽ ትንሽ ሳይበዛ፣ በጣምም ሳይረዝም ትንሽ ጊዜ ቆዪልን። ቶሎም አትሂጂብን።
•••
ኮሮናዬ ሃይማኖቶችንም፣ ሃይማኖተኞችንም በሚዛን ላይ አስቀመጠች። መዘነችም። ዓለምን በጉልበትም በብስኩትም እናጥለቀልቃለን ሲሉ የነበሩትም ታዩ። መካ መዲና፣ ካዕባም ዝም አሉ። ምእመናን አፅናኝ አጡ። ሮምም በርሊንም ተዘጉ። ኮረና ረቂቅ ሆነች፣ ከሰው አእምሮ በላይ ሆነች። ሰውን ሁሉ ከቤቱ ከጎሬው ደበቀች። ሯጩን፣ አትሌቱን ዓለም ፍሬን አስያዘችው። በ180 ፍጥነት ጋላቢውን ሁላ አቀዘቀዘችው። ያለወታደር ቤቱ ተቀረቀረ። አልጋው ላይ ጣለችው። ኮሮና ከምር መቅሰፍት ናት። እናም ይሄን ይሄን ስታይ ኮረናዬ ቫይረስ ብቻ ሳትሆን እግዚአብሔር ለዚህች ሰዶማዊት ምድራችን አደብ ማስገዣነት የላካት አርጩሜው ናት ብለህ ለማመን ትገደዳለህ። ኮረናዬ የእኔ ኮረና እባክሽ ትንሽ ጊዜ ቆዪልን። ትንሽ ትንሽ ሳይበዛ፣ በጣምም ሳይረዝም ትንሽ ጊዜ ቆዪልን። ቶሎም አትሂጂብን።
•••
ኦርቶዶክስዬ የእኔ ተዋሕዶ እናት ዓለሜ ግን ደግ አደረግሽ። መቅሰፍት እንዴት እንደሚከለከል፣ እንዴት እንደሚመለስ ከጥንት ጀምሮ አንቺ ታውቂበታለሽና ከፊት መስመር ቆመሽልን። ወታደሩም ጀነራሉም ፈርቶ የሚሆነውን ባጣበት በዚህ ሰዓት አይዟችሁ አልሽ አትፍሩ አልሽ። ንስሐ ግቡ ልጆቼ ከእግዚአብሔር በላይ የሚሆን በሽታ የለም ብለሽ አጽናናሽን። ዕጣኑም፣ ጽናውም፣ መሰዊያውም መስዋዕቱም ያለሽ አንቺ ነሽ። አዎ ከፊት ቅደሚ። ሃገርሽን፣ ህዝብሽን አጽናኚ። እንደ ሌላው አትደበቂ፣ ፀበሉን አጠጪ፣ ቅዳሴው አይቋረጥ፣ የሰላም ጊዜ ብቻ ወታደር አትሁኚ፣ በእግዚአብሔር ቃል እንደሚሸቅጡት አትሁኚ። የሚፈራው የሚጠበቀው ሞት ቢመጣ እንኳ ገንዘሽ ቅበሪን።
•••
እሺ አሁንስ ይትነህ? አሁንም ጫት ላይነህ? እየጠጣህ ነው? ሐሺሽ ሺሻው እያጦዘህ ነው? አሁንም ትዘሙታለህ? ትሰርቃለህ? ትቀጥፋለህ? ታጭበረብራለህ? የት ነው ያለኸው? ተናገራ ምን ይለጉምሃል? ንስሐ የማትገባው ገና መቅሰፍቱ ቀርቶልኝ፣ አልፎልኝ ወደ ቀደመ አሸሼ ገዳዬነቴ እመለሰላሁ ብለህ ነው አይደል? ከጣልያን ተማር። ከስፔን ተማር። ተማር ከሩቁም ከቅርቡም ፍጥረት። ጣለው ሲጋራህን ሺሻ፣ ሐሺሽህን። ድፋው አንቡላህን፣ ትፋው ጫቱን፣ ተነስ፣ ጨክን ወስን። ንስሐ ገብተህ ተዛጋጅተህ ጠብቅ። የፈለገ ቢመጣ አትፍራ። ንስሐ ሳትገባ ሞት እንዳያገኝህ ብቻ ፍራ። “የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነውና፤ የእግዚአብሔር የጸጋ ስጦታ ግን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን የዘላለም ሕይወት ነው።” ሮሜ 6፥23። እኛ ክርስቲያኖች እንድንጸልይ እንጂ እንድንንቦቆበቅ አልተጠራንም። ሚስትህ መቁረብ እየፈለገች አንተ ገናለገና የቫይረሱ የኮረናው ዘመን አልፎ እቀብጣለሁ፣ እንደ ድሮው አለሌ እሆናለሁ ብለህ ንስሐ መግባትን ገፍተህ በባለቤትህ ላይ ለመሄድ ቀጠሮ ትይዛለህ። አንት ሌባ ትቀደማለህ ይህን ዕወቅ።
•••
እናም ይሄን ይሄን ስታይ ኮረናዬ ቫይረስ ብቻ ሳትሆን እግዚአብሔር ለዚህች ሰዶማዊት ምድራችን አደብ ማስገዣነት የላካት አርጩሜው ናት ብለህ ለማመን ትገደዳለህ። ኮረናዬ የእኔ ኮረና እባክሽ ትንሽ ጊዜ ቆዪልን። ትንሽ ትንሽ ሳይበዛ፣ በጣምም ሳይረዝም ትንሽ ጊዜ ቆዪልን። ቶሎም አትሂጂብን። ብዙም አትቆዪብን።
•••
ሻሎም !   ሰላም !  
መጋቢት 16/2012 ዓም
ከራየን ወንዝ ማዶ።
Filed in: Amharic