>

የመንግስት ባለሥልጣናት እንደሚገድሉት እየዛቱበት መሆኑን የፋኖ ሊቀ መንበር ሰለሞን አጠናው አስታወቀ! (ኢትኦጲስ)

የመንግስት ባለሥልጣናት እንደሚገድሉት እየዛቱበት መሆኑን የፋኖ ሊቀ መንበር ሰለሞን አጠናው አስታወቀ!

ኢትኦጲስ
 
መንግሥት የፋኖን አደረጃጀት ሙሉ በሙሉ ለማጥፈት እንቅስቃሴ ጀምሯል። እንቅስቃሴውንም የፌዴራሉ መንግሥት እና የአማራ ‘ክልል’ መንግሥት በጥምረት እያከናወኑት እንደሆነ ፋኖ አስታውቋል። እስከ መጭው መጋቢት 20 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ የፋኖ መሪዎች እጅ የማይሰጡ ከሆነ ከእስካሁኑ የበለጠ ጦር ሊያዘምትባቸው እንደሚችል ነው መንግሥት ያስታወቀው።
ለዛሬ ሀሙስ መጋቢት 17 ቀን 2012 ዓ.ም የፋኖ መሪዎችና ርዕሰ መስተዳድር ተመስገን ጥሩነህ ተገናኝተው ለመወያየት ቀጠሮ ይዘው ነበር። ይሁን እንጂ መንግሥት ሰላማዊ ድርድሩን አቋርጦ አመራሮቹ ላይ እየዛተ መሆኑን ነው ፋኖ ያስታወቀው። ፋኖ ሰለሞን አጠናው፤ የፋኖ ሊቀመንበር በተለይ ከኢትዮጲስ ጋር ባደረገው ቆይታ እንደገለፀው ከቀናት በፊት የሀገር መከላከያ ሰራዊት ጎንደር ከተማ ቀበሌ 18 ጋዜቦ ሆቴል አካባቢ በነበሩበት ዲሽቃን ጨምሮ በተለያዩ ከባድ የጦር መሳሪያዎች ጦርነት ከፍቶባቸዋል።
“ከዚህ ግድያ ከተረፍን በኋላም የመንግስት ባለሥልጣናት ስልክ እየደወሉ እጅ ስጥ፤ እጅ ካልሰጠህ ትገደላለህ” በማለት እያስፈራሩት መሆኑን ገልጿል። መንግሥት የፋኖን አደረጃጀት ለማጥፋትና በከፊል ወደ ራሱ የፀጥታ መዋቅር ውስጥ ማስገባት እንደሚፈልግም ተነግሯል። ይሁን እንጂ የአማራው ሕዝብ ጥያቄዎች ሳይመለሱ ፋኖ ትግሉን እንደማያቆም አስታውቋል። በተለይም የወልቃት፣የራያ፣የደራ እና የመተከል የአማራ ወሰኖች ወደነበሩበት ሳይመለሱ ፋኖ ትግሉን እንደማያቆም ነው ሊቀመንበሩ የተናገሩት።
“እነኝህ እና ሌሎች የአማራው ሕዝብ ጥያቄዎች ከተመለሱ ግን ፋኖ ጠመንጃ የመሸከም ሱስ የለበትም። ወደ መንግሥት መዋቅርም መግባት አንፈልግም። የሕዝብ ልጆች ነን። ከሕዝብ ነው የወጣነው። የምንመለሰውም ወደ ሕዝቡ ነው። አርሰን፣ነግደን ወይም እንደ አማራ ሕዝብ ሌሎች የሥራ አማራጮችን ፈልገን ነው የምንኖረው” ብሏል ፋኖ ሰለሞን።
ፋኖ በችግር ጊዜ አካባቢውን በማረጋጋትና ሰላም በማስከበርም አስተዋፅኦው ከፍተኛ መሆኑን ጠቁሟል። “ባለፈው መስከረም 18 ቀን 2012 ዓ.ም የቅማንት ፅንፈኛ ቡድን ጎንደር ላይ ጥቃት ሲያደርስ መንግስት አልነበረም የተከላከለው። እኛ ነን የሕዝቡን ደህንነት የጠበቅነው። በዚህ መሸለም ይገባን ነበር። መንግሥት አሁን ሊያጠፋን ሲያስብ ነው ‘ሌባ፤ ወንበዴ’ የሚለን። ፋኖ እንደሌሎች ዘራፊ አይደለም። መዝረፍ ብንፈልግ ኖሮ መስከረም 18 ብዙ ባንኮችን መዝረፍ ይቻል ነበር። የእኛ አላማ ይህ አይደለም።” ነው ያለው ሊቀመንበሩ።
ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የተፈጠረውን አለመረጋጋት በማርገብ በኩል ፋኖ ላደረገው አስተዋፅኦ ዩኒቨርሲቲው የምስጋና እና የእውቅና ደብዳቤ ሰጥቶታል። ፋኖ ይህንን አመስግኗል። የተለያዩ የፋኖ አመራሮችና አባላት በተለያዩ ጊዜያት በመንግስት አቀነባባሪት ተገድለዋል። ሺህ አለቃ ፋኖ አስቻለው ደሴን በደቡብ ጎንደር አባት፣እናትና ሕፃናትን ጨምሮ ሙሉ ቤተሰቦቹ ፊት መኖሪያ ቤቱ ውስጥ የመንግስት ታጣቂዎች በጥይት ደብድበው ገድለውታል።
ፋኖ ዘርአያቆብ አዝመራው በዳባት ወረዳ አጅሬ ጃኖራ አካባቢ በተቀነባበረ መንገድ በቅርብ ቤተሰቡ እንዲገደል ተደርጓል። በተመሳሳይ አርበኛ ጎቤ መልኬም ተገድሏል። መንግሥት ሌሎች የፋኖ አመራርና አባላትንም ገድሏል። #ሼር ይደረግ!
Filed in: Amharic