>

አምነስቲ ኢንተርናሽናል ስለታገቱት ተማሪዎች ምን ይላል?!?

አምነስቲ ኢንተርናሽናል ስለታገቱት ተማሪዎች ምን ይላል?!?

የኢትዮጵያ መንግሥት ከወራት በፊት ባልታወቁ ሰዎች ምዕራብ ኦሮሚያ ውስጥ ታግተው የደረሱበት ስላልታወቁት 17 የደምቢ ዶሎ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን ለማስለቀቅ የወሰደውን እርምጃ እንዲያስታውቅ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ጠየቀ።
የመብት ተቆርቋሪው ድርጅት ይህንን ጥያቄ ያቀረበው በመላዋ አገሪቱ ያሉ ዩኒቨርስቲዎች የኮሮናቫይረስ መስፋፋትን ለመግታት መዘጋታቸውን ተከትሎ ነው።
ባለፈው ኅዳር ወር ላይ የታገቱት የተማሪዎች ወላጆች ሰቆቃን የበለጠ የከፋ ያደረገው በምዕራብ ኦሮሚያ የስልክና የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጡ ስለልጆቻቸው መረጃ ለማግኘት የሚያደርጉትን ጥረት እንዳደናቀፈው አምነስቲ በመግለጫው ላይ አመልክቷል።
“በኮሮናቫይረስ ምክንያት በኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጠረው ስጋት፤ ተጠልፈው ከተወሰዱ በኋላ የት እንዳሉ ስላልታወቁት ልጆቻቸው መረጃ በሚፈልጉት የተማሪዎቹ ቤተሰቦች ሰቆቃን አበርትቶታል” ሲሉ የአምነስቲ ኢንትርናሽናል የምሥራቅ አፍሪካ ምክትል ዳይሬክተር የሆኑት ሰይፍ ማጋንጎ ተናግረዋል።
“የኢትዮጵያ ባለስልጣናት የተማሪዎችን ህይወት ለመጠበቅ ዩኒቨርስቲዎችን ለመዝጋት የወሰዱት እርምጃ የሚደነቅ ቢሆንም፤ ነገር ግን በተመሳሳይ 17ቱ ተማሪዎች ያሉበትን ቦታ በማወቅ ነጻ እንዲወጡ አድርገው ከቤተሰባቸው ጋር እንዲቀላቀሉ የሚያስችል ተጨባጭ እርምጃ መውሰድ አለበት” ብለዋል።
አምነስቲ ኢንትርናሽናል አናገርኳቸው ያላቸው በርካታ የታገቱት ተማሪዎች ቤተሰቦች እየከበደ የመጣ ተስፋ መቁረጥና ደጋፊ የማጣት ስሜት ውስጥ መሆናቸውን እንደገለጹ አመልክቷል።
ወደ መጡበት ሲመለሱ ከታገቱት ተማሪዎች መካከል አንዷ የሆነችው የሦስትኛ ዓመት የባዮቴክኖሎጂ ተማሪ የነበረችው ግርማነሽ የኔነህ አባት አቶ የኔነህ አዱኛ ለአምነስቲ እንደተናገሩት “ልጆቻችንን ወደ ዩኒቨርስቲ የላክናቸው የተሻለ ተስፋ ሊኖራቸው ይችላል ብለን ነበ፤ አሁን ግን የት እንዳሉና በህይወት መኖራቸውን አናውቅም” ብለዋል።
አባትየው ጨምረውም “መጠለፋቸውን ከነገረችን ዕለት ጀምሮ በለቅሶ ላይ ነው ያለነው፤ እንድንጸልይላት ነግራን ነበር፤ ቄስ እንደመሆኔ ጸሎቴን ሳሰማ ቆይቻለሁ። እናቷ በጣሙን ተጎድታለች፤ አእምሮዋ እየተነካ ነው። ከመንግሥት መንም የሰማነው ነገር የለም።”
አጋቾቹ መጀመሪያ ላይ ተማሪዎቹ ለቤተሰቦቻቸው ደውለው እንዲያናግሯቸው ፈቅደው የነበረ ቢሆንም አሁን ወላጆች ስለልጆቻቸው ከሰሙ ሦስት ወራት ተቆጥረዋል ይላል አምነስቲ።
“በምዕራብ ኦሮሚያ የግንኙነት አገልግሎት መቋረጡ ተቀባይነት የሌለውና የሰዎችን መረጃ የማግኘትና ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን የመጣስ ድርጊት ነው” ሲሉ ሰይፍ ማጋንጎ ተናግረዋል።
የተማሪዎቹን መታገት ተከትሎ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን ተማሪዎቹ ያሉበትን ቦታ የሚያፈላለግና በሰላም ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲመለሱ የሚያደርግ ከተለያዩ የመንግሥት አካላት የተወጣጡ አባላት ያሉት ግብረ ኃይል ተቋቁሙ እየሰራ መሆኑን ገልጸው እንደነበር ይታወሳል።
Filed in: Amharic