>

ቫይረሱን ያንቀጠቀጡ ፖለቲከኞችና ሌሎችም!! (ታምሩ ተመስገን)

ቫይረሱን ያንቀጠቀጡ ፖለቲከኞችና ሌሎችም!!!

ታምሩ ተመስገን
 
… ምስኪን የኮሮና ቫይረስ ቤት ተቀማጭ አንባቢዎቼ ዛሬ ደግሞ ቫይረሱን ስላንቀጠቀጡት ፓለቲከኞቻችን ካየሁትና ከሰማሁት አስነብባችኋለሁ።
በአገራችን ታሪክ ክፉ ቀን በመጣ ጊዜ ህዝቡን ፎጨጭ አድርጎ በመሄድ ንጉሥ ተክለሃይማኖትንና አጼ ሀይለስላሴን ‘ሚስተካከላቸው መሪ ያለ አይመስለኝም። ለዚህ ደግሞ በገጼ ላይ [አጼዎቹና የስልጣን ሿሿ] የተሰኘውን ወግ ፈልሶ ማንበብ ጥርት ያለ እውቀት ከነማስረጃው ያስጨብጣል።
ዘንድሮስ?
ዘንድሮም ነገሩ ሁሉ በአንድ ወቅት ወንድሟ ሞቶባት የመኖር አምሮቷ ጨርሶ የተሟጠጠውን የጎጃም እመቤት ግጥም አስታዋሽ ብቻ ሆኗል
“ጠበቃ ቁሚልኝ የሚለኝ ማን ነው
  ራሴን አላድን እንኳን ሌላ ሰው”
ትናንት ማምሻውን እስኪ ሰው እንደተባለው ቤቱ እየዋለ ይሆን የሚለውን ጉዳይ ለማረጋገጥ ሜክሲኮ ሄድኩ።(typical habsha)
ሜክሲኮ ያው እንደውትሮው ሸቀጧን አስፋልት ላይ ዘርራ ገበያተኛ ትጣራለች።
“አልኮሏን አልኮሏን የእጅ ማፅጃ ቫይረስ ማባረሪያ” እያለ የሚጣራ ነጋዴ ሰማሁና ሄድኩ።
ነፍ ሰዎች እየገዙት ሲያልፉ ከጎኑ ደግሞ ሌላ ነጋዴ “የአልኮል መቀነሻ በ30 ብር ብቻ” እያለ ገብያተኛ ይጣራል። #ኑ ስራ ፈጠራ እናድንቅ ወገን!
ቀና ስል ደግሞ ባልደራሱ 2 ስታዲየም የሚሆኑ ሰዎችን ሰብስቦ ሰለቫይረሱ ግንዛቤ ሲያስጨብጥ ተመለከትኩት። #በነገራችን ላይ fb ላይ “እስካሁን ማንንም ላለመጨበጥ ጥረት አድርጌ ነበር አሁን ግን ተሳሳትኩ ግንዛቤ ጨበጥኩ” ብለህ የፃፍከው ልጅ የአማኑኤል ታክሲ የትእንደማገኝ ብትነግረኝ ውለታህን አልረሳም። ይቻምሽ አባቴ!#1!
አሁንም እዛው ሜክሲኮ ነኝ። ከጀርባየ ካሉት የእጅ ማስታጠቢዎች አካባቢ የማውቀው ድምፅ ሰምቼ ስዞር ከብርሃኑ ነጋ፣ ጃዋርና ዶክተር ደሳለኝ ጋር ተፋጠጥን።
“ጓዶች እንዴት ነው በየመንገዱ እየታጠብን አመዳችን ቡን አለ እኮ። ምናለበት ከጎን ሎሽን ቢያስቀምጡልን።” ጃዋር ነበር።
ብርሃኑ ነጋ እጁን ወደ መንገደኛው እያራገፈ “ዝጋ ባክህ! ደግሞ አንተ አመዳምነት ብርቅህ ነው? ልጅ እያለህ ራሱ በጣም አመዳም ከመሆንህ የተነሳ አባትህ ራሱ ሲገርፉህ ውሃ እያርከፈከፉ አይደል እንዴ” ብሎ በመመለሱ ከፍተኛ ፀብ ተነሳ። ዶክተር ደሳለኝ በመካከል ገብቶ ሊገላግላቸው ይውተረተር ጀመር።
በዚህ መካከል ነበር አንድ ወጣት “ፊንፊኔ ኬኛ፣ ጃዋር አንደኛ” እያለ እየፈከረ ወደ ጃዋር የመጣው። ጃዋር ልጁን እንዳየው በብርሃኑ ነጋ ጀርባ እየተደበቀ “ሰውየ ርቀትህ ጠብቅ። እኔ ፊንፊኔ ላይ ህንፃ እንጂ ሰው የለኝም። በህግ አምላክ ርቀትህን ጠብቅ!” እያለ መጮህ ጀመረ።
ወዲያው ደግሞ እንደኔ ኑሮ ደህና አድርጎ የመለመለው ሌላ ወጣት “አማራነት የሰውነት ውሃ ልክ ነው!” የሚል መፈክር ተሸክሞ ትርምሱን ተቀላቀለ። ወዲያው ዶክተር ደሳለኝን ዘልየ ካልቀፍኩህ ብሎ ተገለገለ።
ዶክተር ደሳለኝ ግን “ሰውየ ስለምታወራው ነገር ምንም የማወቀው ነገር የለም! እንዳትበላሽ ርቀትህን ጠብቅ!” እያለ ከጃዋር ጀርባ ተደበቀ።
በዚህ ትርምስ መካከል አንድ ወጣት በደረቱ አንዳች መጽሀፍ ይዞ “ጌታ እንዲህ ይላል። በመጨረሻው ዘመን እኔ ላድንህ እመጣለሁ። ምንም አትፍራ አድንህ ዘንድ ይቻለኛል። አንተ ኢትዮጲያዊ ነህና በእኔ ዘንድ አፈርማቲቭ አክሽን 3% አለህ ስለዚህ ማስክ ማድረግ ጓንት መልበስ የኢሉምናቲዎች መንፈስ ነው ከአንተም ይራቅ” በማለት ተቀላቀለ።
ከትርሙሱ መካከል “አሜን የጌታ ሰው” የሚሉ ነፍ ድምጾች መሰማት ጀመሩ ይህ ወጣት ፈጣሪን እንዲህ መዳፈሩ አንድ ታሪክ አስታወሰኝ
.
… በአንድ ወቅት የበጌምድርን መሬት በሙላ ወሃ ሙላት አጥለቀልቀው አሉ። አገሬው ጎጆውን ሁሉ ወሃ ቢውጥበት ጊዜ ዛፍ ላይ ቆጥ ላይ በመንጠልጠል ነፍሱን ሊያተርፍ ይጣጣር ጀመር።
ከእነርሱ መካከል የአንድ እምነት አባት ከአምልኮ ህንፃው ጉልላት ላይ ሆነው ነፍስ ውጭ ነፍስ ግቢ ይታገላሉ። ይህን የተመለከቱ ዋናተኞች “አባ ይዝለሉ እናትርፍዎ። ህንፃውን ውሃው ልውጠው ነው ኧረ ይዝለሉ!” ቢሏቸው:-
“እኔን የሚጠብቀኝ ፈጣሪ ነው” በማለት አሻፈረኝ አሉ።
ሰው ተስፋ አልቆረጠም በሄሊኮፍተር መጥተው ሊያድኗቸው ቢሞክሩም “እምቢ እኔን የሚያድነኝ ፈጣሪ ነው” በማለት በድጋሚ አሻፈረኝ አሉ።
ደቂቃዎች ሰዓታትን ተኩ ወሃው እየጎረመሰ መጣ። ሙሉ የአምልኮ ህንፃውንና እኒያን አባት ዋጣቸው። ሞቱ።
ሞተው ፈጣሪ ፊት በቀረቡ ጊዜ ” ምነው አንድየ! ያ ሁሉ ሰው ሊያድነኝ ሲመጣ አንተ ታድነኛለህ ብየ ስፈክር ምነው ሞትን ጋትከኝ!” ብለው አማረው ጠየቁት
ፈጣሪ ግን “ምነው አባ ይድኑ ዘንድ ዋናተኛ አላኩልዎትም? ሄልኮፍተር አልሰደድሁልዎትም?” በማለት ኩምሽሽ አደረጋቸው።
……… ማይ ብራዘር ፈጣሪ ስራውን በሰው ይፈፅም ዘንድ አታውቅምን! ለምን የህክምና ባለሙያዎች ታጠብ፣ ርቀትህን ጠብቅ፣ ቤትህ ተቀመጥ ሲሉህ ፈጣሪ ራሱ ካልመጣ ብለህ ትፈታተነዋለህ። በዶክተሮች በኩል ሊያድንህ የሚሞክረው ፈጣሪ እንደሆነ እንዴት መረዳት ያቅትሃል!?….
•ርቀትዎን ይጠብቁ !
•እጅዎን ይታጠቡ  !  
•መርዝ እንደበላ ውሻ በየቦታው ክው ክው አይበሉ እዚህም እዛም አይክለፍለፉ አርፈው ይቀመጡ !’
•ከሚስትዎ አልያም ከውሽማዎ(ቱ!) እንዲሁም ከፍቅረኛዎ ከንፈር ይፁሙ!
•ለሚወዷቸው ሲሉ እራስዎታን ከኮሮና ይጠብቁ!
Filed in: Amharic