>

ክትባቱ የት ደርሷል - መድኃኒቱስ? (ደረጀ ደስታ)

ክትባቱ የት ደርሷል – መድኃኒቱስ?

 

ደረጀ ደስታ

 

ኮረና ጭንቅ ሆነና የዓለም ሳይንቲስቶች በየላቡራቶሪያቸው ከተዋል። በዚች ሰዓት እውቅና የተሰጣቸው 44 የክትባት መድኃኒት ሙከራዎች እየተካሄዱ ነው። ተስፋ ቢሞላቸውም አንዳቸውም ፍሬ አልሰጡም። ጊዜ የለምና ወዲያ እንደምታደራርጉት አደራርጋችሁ ክትባቱን ይሁን መድኃኒቱን ወዲህ በሉ ተብለው ቢገደዱ እንኳ ከሚቀጥለው ዓመት በፊት ሊያደርሱት እሚችሉት ነገር የለም እየተባለ ነው። ደረጃውን ያልጠበቀውን እንኳ መናኛ ነገር ማግኘቱ ብርቅ ሆኗል። የዓለም ጤና ጥበቃ ድርጅት እንደሚለው ከሆነ ቢያንስ ሁለት ትላልቅ የክትባት ፕሮጀክቶች ከምርመራ ወደ ሙከራ (ክሊንካል ትራያል) ተሸጋግረዋል። 42 የሚደርሱት የክትባት ግኝቶች ደግሞ እንዲሁ በያሉበት አገር እየተሞከሩ ነው። ሲደመሩ 44 ናቸው። ሙከራዎቹ መጀመሪያ በላቡራቶራዎች ውስጥ በሴሎች ላይ ይሞከራል። ከዚያ ጉዳታቸው እንስሳት ላይ ይታያል።

ወደ ሰዎች ሲሸጋገር ደግሞ በሶሰት ደረጃ ይመጣል። ሴፍቲ ቴስት በጥቂት ሰዎች ላይ ይሞከራል። ሁለተኛው ትንሽ በዛ ያሉ ሰዎች ላይ አድርጎ ተያያዥ ጉዳት (ሳይድ ኢፌክት) ካለው ይታያል። ሶስተኛው በእውነተኛ ዓለም ይሠራ ከሆነ በመቶሺዎች ላይ ይለቀቃል። ይህን ሁሉ አዋክቦ እንኳ ለማድረስ አንድ 18 ወራት ይፈልጋል። ይህ እንግዲህ ለተቀባይነቱ አሸንፎ የወጣ ከትባት ከተገኘ ነው። ከዚህ ጎን ለጎን ለሌሎች ቫይረሶችም ሆነ ሀመሞች እስከዛሬ የተሰሩትን ተቀራራቢ መድኃኒቶች እየመረጡም ሆነ እየቀየጡ መሞከር በአማራጭነት እየቀረበ ነው። መቸም ዝም ብሎ ከማለቅ ከነጉዳታቸው መሰንበት ይመረጥ እንደሆነ ለማለት ይመስላል። የህክምናው ዓለም ግን እንዲህ በጥድፊያ እሚገፉት አይደለም።

ፖለቲከኞቹ ተስፋቸው እያለቀ ሳይንቲስዎቹም ነፍሳቸው እየተጨነቀ መሆኑ ግን እየታየ ነው። ከግንባር ቀደሞቹ ከቻይናና አሜሪካ ጋር በምርምሩ እየተሳተፈች ያለቸው እንግሊዝም የጠቅላይ ምኒስትሯን ሰውነት እስከመቆጣጠር ለደረሰው ኮረና መፍትሔ ለመስጠት ያለ የሌለ ኃይሏን እየተጠቀመች መሆኑ ተሰምቷል። ፈንጠር ብላ እንደታዛቢ ተቀምጣ የነበረቸው ራሽያም አይገባበት የለው ኮረና ደራሽ ሆኖ እያጣደፋት ነው። የቻይናና የአሜሪካ መሪዎችም እየተወጋገዙም ቢሆን ለመተጋገዙ እየተደዋወሉ ነው። ዓለም አምጦ አንድ ነገር መወለዱ አይቀርም፡፤ ለነገሩ ምን ምርጫ አለ?

Filed in: Amharic