>
5:13 pm - Friday April 19, 4880

የኢትዮ ቴሌኮም የ994 ነፃ የስልክ መስመር አገልግሎት እና የእርካታ ጥያቄ (ከይኄይስ እውነቱ)

የኢትዮ ቴሌኮም የ994 ነፃ የስልክ መስመር አገልግሎት እና የእርካታ ጥያቄ

 

ከይኄይስ እውነቱ

 

የመደበኛ ስልክ እና መደበኛ የብሮድ ባንድ ኢንተርኔት አገልግሎትን ጨምሮ የአገልግሎት መቋረጦችንና ብልሽቶችን ለማስመዝገብ ድርጅቱ የ994 የነፃ ስልክ መስመር ሥራ ላይ ካዋለ ዓመታት ተቈጥረዋል፡፡ የተጠቀሱትን ሁለት የቴሌኮም አገልግሎቶች ከመነሻው (‘Dial up Internet Service’) ጀምሮ ተጠቃሚ እንደሆነ ደንበኛ  በአገልግሎቱ ዙሪያ ያስተዋልኩትን ጥቂት ተሐዝቦቶች እነሆ፡፡ ትኩረቴ በኢንተርኔት አገልግሎቱ ይሆናል፡፡

1ኛ/ የነፃ አገልግሎቱን መስመር አግኝቶ ብልሽት፣ የአገልግሎት መቋረጥም ሆነ ሌሎች ቅሬታዎችን ለማስመዝገብ ትዕግሥትን በእጅጉ የሚፈታተን ከመሆኑም በላይ በአማካይ ከ10-15 ጥሪዎችን ማድረግ ይጠይቃል፡፡ ከዚህም ጥረት በኋላ አገልግሎቱ ላይገኝ ይችላል፡፡

2ኛ/ የ994 መስመሩ ከተገኘ፣ አስተናጋጇ/አስተናጋጁ ሠራተኛ የችግሩን/ቅሬታውን ዓይነት በመመዝገብ መከታተያ ቊጥር ይላክልናል፡፡ እዚህ ላይ ከአስተናጋጆቹ የሚቀርብ በጣም የሚገርመኝ ጥያቄ አለ፡፡ በአገልግሎቱ (መዝግቦ ለሚመለከተው ክፍል ስለማስተላለፉ፣ ልብ በሉ ደንበኛው የኢንተርኔት አገልግሎቱ ተቋርጦበት እስኪስተካከልለት በቀጠሮ ላይ ነው የሚገኘው) ስላገኘነው እርካታ አስተያየት እንድንሰጥ እንጠየቃለን፡፡ አንባቢ ያስተውል! መመዝገብና ለሚመለከተው ክፍል ማስተላለፍ በራሱ አገልግሎት መሆኑን አጥቼው አይደለም፡፡ እርካታ ግን ከውጤት ጋር የተያያዘ ጉዳይ ነው፡፡ ድርጅቱ ባስቀመጠው ሥርዓትና ጊዜ ውስጥ ደንበኛው ችግሩ ከተፈታለት በኋላ የሚቀርብ ጥያቄ በቅድሚያ መደንቀሩ ደንበኛውን ይሉኝታ ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል፡፡ 

3ኛ/ የመኖሪያ ቤቶች መደበኛ ብሮድ ባንድ ኢንተርኔት አገልግሎት ብልሽት ድግግሞሽ (frequency of fault/interruption) ከፍተኛ ሲሆን፣ ባጠቃላይ ከተዘረጋው የቴሌኮም መሠረተ ልማት ጀምሮ ሌሎችም ከቴክኖሎጂ፣ ከሠለጠነ የሰው ኃይል እና ከአገዛዙ ጣልቃ ገብነት ጋር የተያያዙ ችግሮች ስላሉበት አገልግሎቱን ለደንበኛነት በከፈልንበት የፍጥነት ልክ አናገኝም፡፡ 

4ኛ/ ከቅርብ ወራት ወዲህ ደግሞ የኢንተርኔት ግንኙነቱም እያለ በቀን ውስጥ በተደጋጋሚ ወጣ ገባ እያለ አገልግሎቱ አለ/የለም ለማለት ተቸግረናል፡፡ እስካሁን በቅጡ ያልተፈታ ችግር ሆኖ ዘልቋል፡፡

5ኛ/ የመደበኛ የብሮድ ባንድ ኢንተርኔትም ሆነ የሞባይል ኢንተርኔት ተደራሽነትና አገልግሎት ውሱን እንዲሆን ካደረጉት ምክንያቶች መካከል ዋጋው በአፍሪቃ ደረጃም ከፍተኛ በመሆኑ አብዛኛው ሕዝባችን የመክፈል ዐቅም ስለሌለው ነው፡፡ የዐቢይ አገዛዝ ከመጣ ወዲህ (ከአንድ ወር በፊት የተደረገውን ጨምሮ) ኢትዮ ቴሌኮም በሚሰጠው የኢንተርኔት አገልግሎት የዋጋ ማስተካከያ ማድረጉ የሚያበረታታ ርምጃ ሆኖ አግቼዋለሁ፡፡ 

ለማንኛውም ኢትዮ ቴሌኮም መቼ ይሆን አገልግሎቱን አስተማማኝ የሚያደርገው? ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ኢንተርኔትን መሠረት ያደረገ የንግድ ወይም የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ማድረግ እጅግ አስቸጋሪ ይመስለኛል፡፡ ወያኔ በንቅዘት ከተጫወተባቸው ነባር ተቋማት አንዱ ቴሌ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ነውረኛውና የወቅቱ የወያኔ አለቃ ደ/ጽዮን ከበላይ ሆኖ ‹ክፍያ ኃ/የተ የግል ማኅበር› የሚል ኩባንያ ፈጥሮ ሥልጣኑን አላግባብ በመጠቀም የድርጅቱን ሕንፃዎች ሁሉ ያለክፍያ፣ ያለአንዳች ውድድር የስልክ÷ የኢንተርኔት÷ የኤሌክትሪክ÷ የውኃና የትራፊክ ቅጣት ክፍያዎችን ከሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት በጉልበት ወስዶ ከግብረ አበሮቹ ጋር ከፍተኛ ዝርፊያ ፈጽሟል፡፡ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ‹ክፍያ› የሚባለውና (በቅርቡ የተዘጋው) በውኃ፣ በኤሌክትሪክ፣ በስልክና ኢንተርኔት ደረሰኞች ላይ ስሙ የተጠቀሰው ድርጅት የመንግሥት ተቋም ይመስለው እንደነበር አልጠራጠርም፡፡ የኢትዮ ቴሌኮም ሠራተኞች ይህንን ምሥጢር እያወቁ ወያኔ ከሥልጣን ከተወገደ በኋላ እንኳን ይፋ አለማድረጋቸው እስካሁን ድረስ እንቆቅልሽ ሆኖብኛል፡፡

የቴሌኮምዩኒኬሽን ድርጅት ብሔራዊ መለያ አድርገን ከምናያቸው ተቋማት አንዱ በመሆኑ በሁሉም ረገድ ያሉበትን ችግሮች (የዐቅምም ሆነ የንቅዘት) ፈትቶ፣ አሠራሩን አዘምኖና አቀላጥፎ ለባዕዳንም ሆነ ለማንም ሳይተላለፍ አገራዊ ተቋም ሆኖ እንዲቀጥል ከሚመኙ ዜጎች አንዱ ነኝ፡፡ ቢያንስ አገር ረግቶ ሕዝብ የሚቀበለው ሥርዓት እስኪመጣ ወደ ግል የሚዛወርበት ጊዜ መተላለፍ ያለበት ይመስለኛል፡፡

አንድ ተጨማሪ በጎ ነገር ያየሁትን ላክልና ትዝብቴን ላጠቃልል፡፡ በቅርቡ የተከሠተውን ዓለም አቀፍ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ አስመልክቶ ኢትዮ ቴሌኮም በየእጅ ስልካችን የሚያስተላልፈው መልእክት ማለፊያ ሆኖ አግቼዋለሁ፡፡ አገዛዙና በዙሪያው የተኮለኮሉት ጐሠኞች አይፈቅዱለትም እንጂ ገጣሚ ታገል ሰይፉ በቅርቡ ‹ለሰው ዘር አነሰው› በሚል ርእስ ካቀረበው ጽሑፍ ‹የዘረኝነትን ቫይረስ ስርጭት ለመግታታ…› በሚል ያስተላለፋትን መልእክት ቢጨምርበት ምስጋናችን እጅግ የላቀ ይሆናል፡፡

Filed in: Amharic