>

ኮሮና የሚያስከትልብን ኢኮኖሚያዊ ና ማህበራዊ ቀውስ!!! (አቶ ሙሼ ሰሙ)

ኮሮና የሚያስከትልብን ኢኮኖሚያዊ ና ማህበራዊ ቀውስ!!!

አቶ ሙሼ ሰሙ
 
አዲስ አድማስ

 – በአገራችን ሊከሰት የሚችለው የኢኮኖሚ ድቀት ውስብስብ ነው
– መንግስት በሽታውን የህልውና ጉዳይ አድርጎ ማየት ይገባዋል
– ምርጫው ሊካሄድ የማይችልበት ዕድል ከ90 በመቶ በላይ ነው
– የአርሶ አደሩን ህይወት የሚታደግ ራሱን የቻለ ኮሚቴ ያስፈልጋል

በዓለም ላይ የሰው ልጆችን እየቀጠፈ የሚገኘው የኮሮና ቫይረስ አደገኛ ወረርሽኝ፣ በኢኮኖሚም ከፍተኛ ድቀት እያስከተለ ነው፡፡ አቅም ያላቸው አገራት

የአገራቸውን ኢኮኖሚ ለማነቃቃት ከፍተኛ ገንዘብ እየመደቡ ነው፡፡ እንዲያም ሆኖ ጫናውንና ተጽዕኖውን ገና አልተወጡትም፡፡ ቫይረሱ በአሜሪካና በአውሮፓ እየታየ ባለው አቅሙ በአፍሪካ ምን ሊከሰት እንደሚችል መገመት አያዳግትም፡፡ ለመሆኑ በአገራችን ላይ ወረርሽኙ ሊያስከትላቸው የሚችላቸው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውሶች ምን ይመስላሉ? መንግስት ለአደጋው ምን ያህል ተዘጋጅቷል? ምን ማድረግስ ይጠበቅበታል? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፣ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ተንታኙን አቶ ሙሼ ሰሙ በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ዙሪያ በስፋት አነጋግሯቸዋል፡፡ ኮሮና ቫይረስ ድሮም የነበረ ነው በማለት ይጀምራሉ፡

በመጀመሪያ ደረጃ ኮሮና ቫይረስ አሁን ተስፋፍቶ ብዙ ሰው ቢያጠቃም፣ ከ1960ዎቹ ጀምሮ የነበረና የሚታወቅ ነው:: አሁን የተስፋፋበት መጠን ግን የሰዎችን እንቅስቃሴና ማህበራዊ መስተጋብር የሚገድብ ሆኗል፡፡ ማንኛውም ኢኮኖሚ ደግሞ ከሰው ልጅ እንቅስቃሴና ከገንዘብ ዝውውር ጋር የተገናኘ ነው፡፡ በተለይ አሁን አለም ባለችበት ተጨባጭ ሁኔታ ንግድ የሚካሄደው በሰዎች ዝውውርና እንቅስቃሴ ነው፡፡ የቫይረሱ ባህሪ ይሄን አስፈላጊ እንቅስቃሴ ይገድባል፡፡ ይሄ ደግሞ መሰረታዊ የኢኮኖሚ መናሮችን ያስከትላል፡፡ ሁለተኛው ጉዳይ የሥራ ሀይል ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ነው፡፡ በሥራ ላይ ሊሰማራ በሚችለው ማህበረሰብ ላይ የሚያደርሰው ጉዳት፣ የረጅምና የአጭር ጊዜ ተብሎ ሊመደብ ይችላል፡፡ በአጭር ጊዜ የሚያስከትለው ጉዳት፣ ሰዎች ተንቀሳቅሰው ሥራ ሰርተው ምርታማ ካልሆኑ ምርት አይኖርም፡፡ ምርት ከሌለ ደግሞ ኢኮኖሚው የአቅርቦት እጥረት፣ የወጪ ገቢ ንግድ ችግር ይገጥመዋል፡፡ ጉዳቱ ለረዥም ጊዜ የሚስፋፋ ከሆነ ደግሞ በርካታ የሥራ ሀይልን ሊቀጥፍ ይችላል፡፡ በእያንዳንዱ ዜጋ ላይ ምን ጉዳት ያመጣል ከተባለ፣ የኛ ሕብረተሰብ እንደሚታወቀው በአብዛኛው ከእጅ ወደ አፍ በሆነ ገቢና ድጎማ ነው የሚኖረው፡፡ እንደ ሌላው ማህበረሰብ ጥሪት ኖሮት፣ ከዚያ ጥሪቱ ላይ እየቀነሰ ሕይወቱን የሚመራ አይደለም፡፡ ዛሬ ያገኘውን ዛሬ በልቶ የሚያድር ነው፡፡ አገራዊ አቅርቦታችንም እንደዚያው ነው፡፡ መጠነ ሰፊ አቅርቦት ኖሮን፣ ያንን አቅርቦት በማያወላዳ መንገድ ወደ ገበያው ልናመጣ የምንችል አይደለንም:: ከ23 እስከ 27 በመቶ አጠቃላይ የአገራችን ምርት ከውጭ የሚመጣ ነው:: አሁን ደግሞ በቫይረስ የተነሳ አለማቀፍ እንቅስቃሴዎች እየታገዱ ነው፡፡ ነገሩ እየሰፋ ከሄደ አውሮፕላን ብቻ ሳይሆን የመርከብ እንቅስቃሴም መስተጓጎሉ የማይቀር ነው:: በኮንትሮባንድም ይሁን በሕጋዊ መንገድ የሚገቡ ምርቶች መስተጓጎላቸው አይቀርም:: ያ ደግሞ ገበያ ላይ ያለውን አቅርቦት ይገድበዋል ያሳንሰዋል፡፡ ይህ ሲሆን ገበያ ላይ ያለችውን ጥቂት አቅርቦት፣ ገንዘብ ያለው ብቻ ይጠቀምበታል፡፡ ምክንያቱም አቅርቦት ባነሰ ቁጥር ውድድር ስለሚኖር ዋጋው ይጨምራል፡፡ በመሃል ገቢው ከእጅ ወደ አፍ የሆነው መጎዳቱ አይቀርም፡፡
በሌላ በኩል፤ ፋብሪካዎችም በዚህ ቫይረስ የተነሳ ቀስ በቀስ መቆማቸው አይቀርም፡፡ ምክንያቱም በርካታ ሰው አሰማርተው የሚሰሩ እንደ መሆናቸው የንክኪ ስጋት ያይልባቸዋል፡፡ በቻይና የታየውም ይሄው አይነት ችግር ነው፡፡  የአገልግሎት ዘርፉም በዚያው ልክ ይጎዳል:: መዝናኛዎች፣ ሆቴሎች፣ የመሳሰሉት በእጅጉ ተጎጂ ናቸው፡፡ ስለዚህ በሥራቸው ያለው ሰራተኛና ራሱ ኢንዱስትሪው በእጅጉ ይጎዳል፡፡ ይሄ በእያንዳንዱ ዜጋና እንደ አገር የሚያስከትለው ጉዳት ቀላል አይደለም:: በሌላ በኩል፤ ሰው ያለችውንም ጥሪት ቢሆን በሌላ ሥራ ላይ ከማዋል ይቆጠባል:: ነገ የሚመጣውን ነገር ስለማያውቅ፣ ቤተሰቤንና ራሴን እመግብበታለሁ በሚል ጥሪቱን በሌላ ሥራ ላይ አያውልም፡፡ ያ ማለት ደግሞ በትናንሽ ደረጃ የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ ቢዝነሶችንም ከጨዋታ ውጪ ያደርጋል ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ በጉልበት ሥራ ተሰማርተው ያሉ ሰራተኞች፣ ግንባታ የሚሰሩ፣ ቀለም የሚቀቡ፣ ሽንት ቤት የሚቆፍሩ፣ ግቢ የሚያፀዱ፣ የጣራ ቆርቆሮ የሚለውጡ የመሳሰሉት ትንሽ የሚመስሉ ነገር ግን ብዙ የሰው ሀይል የሚያስተዳድሩ ሥራዎች ይገታሉ፤ ሰው ገንዘቡን መቆጠብና እነዚህን እንደ ቅንጦት ማየት ስለሚጀምር፣ የሥራ ዘርፎቹ ከገበያ መውጣታቸው አይቀርም:: ከዚህ ጋር በተያያዘ ደግሞ የኮንስትራክሽን ዕቃ በመቸርቸር የሚተዳደሩትም ከገበያ ይወጣሉ፡፡ ምክንያቱም ሰው አሁን ባለበት አስቸጋሪ ሁኔታ የሚያፈስ ቤቱን እንኳ ለመጠገን ገንዘብ ያልቅብኛል ብሎ ይፈራል:: ለሌላ ጊዜ ያሻግረዋል፡፡

ንክኪ ይቀንስ ተብሎ እርምጃ በተወሰደ ቁጥር ዝውውር ይቀንሳል፤ ዝውውር በቀነሰ ቁጥር ግብዓት ይቀንሳል፡፡ ግብዓት ሲቀንስ ኢኮኖሚ ይጎዳል፤ ይሄ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ እንዲህ ያሉ ወረርሽኞች የሚያስከትሉት ጉዳት ከድሮም ይታወቃል:: ለምሳሌ ስፓኒሽ ፍሉ የሚባለው ወረርሽኝ ተከስቶ በነበረበት ወቅት ከ3 ትሪሊዮን ዶላር በላይ ነው የአለምን ኢኮኖሚ ያደቀቀው፡፡ በቅርብ ጊዜ የተከሰቱ ወረርሽኞችም በተለያየ መጠን የኢኮኖሚ ድቀት አስከትለዋል፡፡ ይሄኛውም ጉዳቱ በግልፅ መታየት ጀምሯል:: ለምሳሌ አሜሪካ እስካለፈው ሳምንት ድረስ የአክሲዮን ገበያዋ ከ10 እስከ 15 ትሪሊዮን ዶላር ድቀት አጋጥሞታል፡፡ ከዚህ ተነስተን በአገራችን ላይ ሊደርስ የሚችለውን የኢኮኖሚ ድቀት መገመት ይቻላል፡፡ ነገር ግን በኛ ላይ ሊከሰት የሚችለው የኢኮኖሚ ድቀት እንደ ሌሎቹ ሳይሆን ውስብስብ ነው የሚሆነው፡፡ ምክንያቱም እኛ እንደ አገርም እንደ ዜጎችም በቂ ጥሪት የለንም:: እነሱ ጥሪታቸውን ተጠቅመው በድጋሚ ማንሰራራት ይችላሉ፡፡ እኛ ደሃ አገር ነን፤ በብድር የምንኖር ነን፡፡ እውነቱን እንነጋገር ከተባለ፣ ከዚህ የሰፋ ነገር በዓለም ላይ ከመጣ እርዳታ ሰጪ አገሮችም በውስጥ ጉዳያቸው ተጠምደው እጃቸውን ሊሰበስቡ ይችላሉ፡፡ ቢያንስ ለልማት ተብለው የሚሰጡ ብድሮች ሊቆሙ ይችላሉ፡፡ እነዚህን ሁሉ ስንመለከት፣ ምጣኔ ሃብቱ ላይ የሚፈጠረው ምስቅልቅል ቀላል አይሆንም፡፡ የጤናውን ችግር ለመፍታት ሲባል ሁሉም ነገር ወደ ጤና ጉዳይ መዞሩም አይቀርም፡፡ እንደኛ  ያለ ድሃ አገር ደግሞ ብዙ ነው፡፡ እንደ ሌሎቹ አገራት ገንዘብ እንኳ በድጎማ ቢገኝ፣ እያንዳንዱ ዜጋ ማግኘት አይችልም፡፡ ገንዘቡ እንኳ ቢገኝ አቅርቦቱ አይኖርም፡፡ ከዚህ አንፃር ይሄ በሽታ በጣም ትኩረትና ክትትል ሊደረግለት ይገባል፡፡ ጉዳዩ የመፍራት ያለመፍራት አይደለም፤ የመቋቋም አቅም ጉዳይ ነው:: እኛ ልንቋቋምበት የምንችልበት ሀብት በጣም ውስን ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ ጉዳይ ላይ ደግሞ ደጋግሞ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡

ከቤት ያለመውጣት እገዳ ቢተገበር፣ በኛ አገር የሚያስከትለው ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ምን ያህል ነው?

እንግዲህ ይሄ የምርጫ ጉዳይ ነው የሚሆነው፡፡ ማንኛውም እንዲህ ዓይነት ውሳኔ የጎንዮሽ ጉዳት ይኖረዋል፡፡ አጠቃላይ አገሪቱ በዚህ በሽታ ተለክፋ የሕልውና ጉዳይ ከመጣ፣ የሚወሰዱት እርምጃዎች መራር ውሳኔን የሚጠይቁ ይሆናል፡፡ የበሽታውን ስርጭት ለመግታት ደግሞ ሊወሰዱ ከሚገባቸው እርምጃዎች አንዱ እንቅስቃሴን መግታት ነው፡፡ እንዲህ ያለውን በሽታ ስርጭት ለመግታት በሚወሰደው እርምጃ በርካቶች መጎዳታቸው አይቀርም፡፡ በአዲስ አበባ ያለው አብዛኛው ለፍቶ አዳሪ፣ የክፍለ አገር ሰው ነው፡፡ ወደ አካባቢው ሄዶ ጥበቃ ተደርጎለት ምግብ ሊያገኝ የሚችልበትን መንገድ መፈለግ ይገባል፡፡ በሽታው እልቂት ከሚያስከትል የሰዎችን እንቅስቃሴ ገትቶ በምግብ ድጎማ ማቆየት ይቻላል፡፡ ለ1 ወርም ይሁን ለ20 ቀን ሰዎችን አንድ ቦታ አስቀምጦ መንግሥት ምግብ እንዲያቀርብ ማድረግ፣ ለኛ አገር ሁነኛ አማራጭ ነው:: ለወደፊት ሊከተል ከሚችል አገራዊ ቀውስም አገሪቱን መታደግ የሚቻለው በዚህ መንገድ ነው፡፡ ስለዚህ ጉዳዩ የምርጫ ጉዳይ ነው፡፡ ሰዎች በቤታቸው ተቀምጠው ምግብ የሚያገኙበትን መንገድ መዘርጋት መልካም አማራጭ ይሆናል፡፡ በጣልያን እንዲህ ያለ ቅድመ ዝግጅት ባለመኖሩ፣ ሰው የሞተን ወገኑን እንኳ መቅበር የተቸገረበት ሁኔታ ነው የተፈጠረው፡፡ ቅድመ ዝግጅት አድርገው ቢሆን ኖሮ፣ ዛሬ የገቡበት ችግር ያህል ባላጋጠማቸው ነበር፡፡ ጉዳዩ የጤና ጠንቅ ብቻ አይደለም፡፡ ዘርፈ ብዙ ነው፡፡

የዚህን በሽታ ስርጭት ለመግታት በሚወሰዱ እርምጃዎች የትኛው የህብረተሰብ ክፍል ነው የበለጠ የሚጎዳው?

በመጀመሪያ እንደ ማህበረሰብ የሚጠቃው የከተማው ሕዝብ ነው፡፡ ነገር ግን ወደ ገጠሩም መዛመቱ አይቀርም:: የገጠር ማህበረሰብ በባህሪው ተራርቆ ነው የሚኖረው፡፡ ብዙም ቅርርብ የለውም:: ሊጎዳ የሚችለው በግብዓት ወቅት ነው:: የከተማው ሕዝብ ግን በጣም ጥግግት ያለ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የከተማው ነዋሪ ከፍተኛ ጉዳት ይገጥመዋል፡፡ በዚያው ልክ ግን የከተማው ነዋሪ የሕክምና የመከላከያ ቁሳቁሶች የማግኘት ዕድል አለው፡፡ የገጠሩ ነዋሪ ይሄ ዕድል የለውም፡፡ ስለዚህ ነገሮችን በሰፊው ተረድቶና ተንትኖ ቅድመ መከላከል ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ አንዴ በሽታው ወደ ገጠር ከገባ ግን ችግሩ በጣም ሰፊ ነው የሚሆነው፡፡ በክፍለ ኢኮኖሚ ደረጃ ካየነው፣ የመጀመሪያው ተጎጂ የአገልግሎት ዘርፉ ነው፡፡ የአገልግሎት ዘርፉ በተለይ ከቱሪዝም ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አለው። በሽታውም የቱሪዝም እንቅስቃሴን ነው የሚገታው፡። ከአየር መንገድ ጀምረን፣ ሆቴሎች፣ አስጎብኚ ድርጅቶች፣ ትራንስፖርት ሰጪዎች፣ የጉብኝት ቦታዎች በሙሉ ነው ተያይዘው የሚጎዱት፡፡ የሆቴሎች ሕይወት እኮ የተመሰረተው በኢትዮጵያ አየር መንገድ ተጓጉዞ ወደ አገር ቤት በሚመጣው ቱሪስት፣ ተሰብሳቢዎችና ተጠቃሚዎች ላይ ነው:: ሆቴሎች አንዱና ዋናው ሥራቸው ከአገር አቀፍና አለማቀፍ ስብሰባዎች፣ ሴሚናሮች፣ ውይይቶች ጋር በቀጥታ የተያያዘ ነው:: እነዚህ ሁሉ ይቆማሉ፡፡ እነዚህ ነገሮች ሲቆሙ ሆቴሎች ቀጥተኛ ተጎጂ ናቸው:: ከሰላም ማጣት ጋር በተያያዘም ሆቴሎች ተጎጂ ነበሩ፤ አሁን ደግሞ ይሄ ሲመጣ ዘርፉ በጣም ነው የሚጎዳው፡፡ ስለዚህ የመጀመሪያ ተጎጂ የሚሆነው ከሰዎች እንቅስቃሴ ጋር ቀጥተኛ ተያያዥነት ያላቸው የአገልግሎት ዘርፎች ናቸው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ የሚጎዳው ኢንዱስትሪው ነው፡፡ ብዙ ሰው ተፋፍጎ የሚሰራበት ስለሆነ ትፍፍጉ እንዲቀር በሚወሰድ እርምጃ ይጎዳል:: በዚህ ሳያበቃ ትራንስፖርትና ዝውውር ከቀረ ደግሞ አቅርቦት በሌለበት ሁኔታ ኢንዱስትሪ መቀጠል አይችልም፡፡ የኛ ኢንዱስትሪ ከውጭ በሚመጣ ዕቃ አቅርቦት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ጥሬ ዕቃ ከውጭ ማምጣት የሚቻልበት ሁኔታ ሙሉ ለሙሉ እየተዘጋ ስለሆነ ኢንዱስትሪው መጎዳቱ አይቀርም፡፡ የፋብሪካ ሰራተኛውም በዚህ ቀጥተኛ ተጎጂ ይሆናል፡፡ ሌላው የውጭ ንግድ ላይ የተመሰረተው ምርት በእጅጉ ተጎጂ ነው የሚሆነው፡፡ አበባ፣ የቀንድ ከብት፣ የቡና ንግድ የመሳሰሉት እየተጎዱ ነው፡፡ የአየር ትራንስፖርት ሲቀር አበባ ንግድ በእጅጉ ይጎዳል፡፡ ግብርናው ግን ብዙም በቀጥታ ላይጎዳ ይችላል፡፡ በሌላ በኩል፤ በሽታው የግብርና አምራቹን የሚጎዳ ከሆነ ቀውሱ ቀላል አይሆንም፡፡ ስለዚህ ከወዲሁ ለአርሶ አደሩ ሕይወት መጨነቅ ያስፈልጋል። መንግሥት ለእነሱ ልዩ ትኩረት ከወዲሁ መስጠት አለበት፡፡

የውጪ ንግድ ከቀነሰ፣ አየር መንገድ ገቢውን ካጣ፣ በውጭ ምንዛሬ በኩል የሚገጥመንን ችግር እንዴት እንወጣዋለን?

ምንም በማያጠራጥር ሁኔታ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ያጋጥመናል። መንግሥት ከወዲሁ የውጭ ምንዛሬው ላይ ቁጠባ ማድረግ አለበት፡፡ እጥረቱን ለመቋቋም ከወዲሁ ሌሎች ቅድመ ሁኔታዎች መመቻቸት አለባቸው፡፡ ለምሳሌ አሁን አየር መንገድ ብዙ ዶላር አጥቷል፣ የአበባው ኢንዱስትሪውም ተጎድቷል፤ የፍራፍሬ፣ የስጋ አቅርቦትም ከገበያው እየወጡ ሊሄዱ ይችላል፡፡ ቀድሞም የውጭ ምንዛሬ እጥረት ያለብን መሆኑ ይታወቃል። ይሄ ሁኔታ ሲጨመር ደግሞ በጣም አደገኛ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ መንግሥት ወሣኝ የሆኑ እርምጃዎችን ሊወስድ ይገባል፡፡

መንግሥት እስካሁን ጉዳዩን የያዘበትን አግባብ እንዴት ይገመግሙታል?

መንግሥት ምንም እንኳን አቅሙ ውስን ቢሆንም ከዜጎቹ አቅም የተሻለ ነው:: ስለዚህ ጉዳዩን በባለቤትነት የመወጣት ሃላፊነት ሊወስድ ይገባል፡፡ ሌላ ተጓዳኝ ነገር ሊኖረው ይገባል፡፡ እስካሁን በማየው ሁኔታ ግን በመንግሥት በኩል በሽታውን የህልውና ጉዳይ አድርጎ የማየት ትኩረት አልተሰጠውም፡፡ ታጠቡ፣ ጥንቃቄ አድርጉ ተብሎ ይነገራል፤ ነገር ግን እነዚህ መረጃዎች የሚተላለፉበት መንገድ በራሱ ስጋቱን በሚገባ የሚገልፁ ናቸው ብዬ አላምንም:: አንደኛ፤ በሽታው ወደዚህ አገር ሊመጣ የሚችልበት ዕድል እንዳለ ተረድቶ መንግሥት ተገቢውንና በስጋቱ ልክ የሆነ ቅድመ ዝግጅት ሲያደርግ አልታየም፡፡ ልክ በሽታው የገባ ቀን ነው መደናገጥ የተጀመረው:: ይሄ ስህተት ነው፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ እንደ ሌሎቹ አገሮች ችግሩ ከደረሰባት በኋላ ከችግሩ ለመውጣት አቅም ያላት አገር አይደለችም፡፡ ሁሌም ቅድመ መከላከል ላይ ትኩረት መስጠት የሚገባት አገር ነች፡፡ በዚህ ዝግጁነት መሰረት አቅርቦቶች መዘጋጀት ነበረባቸው፡፡ በቂ አልኮል፣ ሳንቲታይዘር፣ ጓንት፣ የአፍ መሸፈኛ በበቂ ሁኔታ መዘጋጀት ነበረባቸው። ያ አልተደረገም፡፡ ጤና ሚኒስቴር እንኳ ሚኒስትር ሳይሾምለት ለረጅም ጊዜ ነው የቆየው፡፡ በዚህ በኩል መንግሥት በቂ ቅድም ዝግጅት አላደረገም ማለት ይቻላል፡፡ አሁንም የምናያቸው ነገሮች ለጉዳዩ የተሰጠው ትኩረት ደካማ መሆኑንና ንቅናቄ የመፍጠር ጉዳይ ገና መሆኑን የሚጠቁም ነው፡፡ በሽታው አገር ውስጥ ከገባ በኋላ እኮ በየቦታው ስብሰባዎች ይካሄዱ ነበር፡፡ በሕይወት እንኑር አንኑር ሳናውቅ፣ የምርጫ ዝግጅትና ስልጠና እንዲሁም ስብሰባዎች ሲደረጉ ነበር፡፡ ይሄ መንግሥት ሃላፊነቱን መወጣት በሚገባው ልክ እየተወጣ አለመሆኑን ነው የሚያሳየኝ፡፡ በሃይማኖት ተቋማት በኩልም፤ መንግሥት ጉዳዩን ለእነሱ አማራጭ የሚተወው መሆን የለበትም። ምክንያቱም በሽታው በአንድ በራሱ በበሽተኛው ላይ ብቻ የሚቀር አይደለም፤ አገር ሊያጠፋ የሚችል ብሄራዊ ስጋት ነው፡፡ ስለዚህ መንግሥት በዚህ ጉዳይ ላይ ቸል ከማለትና ጉዳዩን የምርጫ ከማድረግ አስገዳጅ ሁኔታዎችን መተግበር አለበት፡፡ ጥብቅ የሆነ ክትትልና ሕዝባዊ ንቅናቄ ያስፈልገዋል፡፡

ከአሁን በኋላ መንግሥት ምን ዓይነት እርምጃዎች መውሰድ አለበት ይላሉ?

አሁን እኮ ሰው በግንዛቤ እጥረት ምክንያት ውዥንብር ውስጥ ነው ያለው፡፡ በሽታው በአገር ሕልውና ላይ የመጣ መሆኑ ላይ የግንዛቤ እጥረት አለ፡፡ መንግሥት ጉዳዩን የሕልውና ጉዳይ ሊያደርገው ይገባል፡፡ ከዚህ ውጪ ምንም ሊሰራው የሚገባው ነገር ሊኖረው አይገባም፡፡ በሌላ በኩል፤ በአሁኑ ሰዓት በሽታውን ለመቋቋም ወጥና የተቀረፀ ፖሊሲ ያስፈልገናል፡፡ “አድርጉና አታድርጉ” የሚባሉት ነገሮች በግልፅና በማያሻማ መንገድ ለሕዝቡ መቅረብ አለባቸው:: ከዚሁ ጋር በተያያዘ እቅድ 2 (ፕላን ቢ) ያስፈልጋል:: ይሄ ነገር እንዲህ ቢሆን፣ ይሄን አደርጋለሁ የሚል ዝርዝር እቅድ ያስፈልጋል፡፡ ይሄን ለማዘጋጀት ደግሞ ከተለያዩ አካላት የተውጣጣ ኮሚቴ ያስፈልጋል፡፡ ከፖሊስ፣ ከደህንነት፣ ከመከላከያ፣ ከጤና ሚኒስቴር፣ ከሃይማኖት ተቋማት ከመሳሰሉት የተውጣጣ ብሄራዊ ኮሚቴ ያስፈልጋል፡፡

ሌላው አቅምን የመገንባት ጉዳይ ነው:: መንግሥት አሁን ያለችውን የውጭ ምንዛሬ ቆጥቦ፣ ሌሎች ግዢዎችን በማቆም፣ ለምግብና ለመድሃኒት ማዋል አለበት፡፡ ይሄ ገንዘብ ዛሬ የቅንጦት ዕቃ ማስመጫ ሊሆን አይገባውም፡፡ ኮስሞቲክስ፣ ሂውማን ሄር፣ መኪና ወዘተ… ማስመጫ መሆን የለበትም:: የውጭ ምንዛሪን ከነዳጅና ከመድሃኒት ውጭ ሌላ ላይ ማዋል ጥሪትን ማባከን ሲሆን፤ የበሽታውን ስጋትም አለመረዳት ነው:: የመንግሥት ተቋማት ግዢ፣ የፈርኒቸር፣ የመኪና ሌላም ሌላም ጨረታና ግዢ መቆም አለበት፡፡ ሌላው የበጀት ጉዳይ ነው:: 5 ቢሊዮን ብር መድቤያለሁ ብሏል:: ይሄ ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን አሁን ታክስ የመክፈል አቅምም እየተመናመነ ነው የሚመጣው:: ስለዚህ ከታክስ የሚፈለገውን ያህል ገንዘብ ላያገኝ ይችላል፡፡ ከዚህ አንፃር ይሄን የመደበውን ገንዘብ በአግባቡ ቆጥቦ መጠቀም አለበት፡፡ አንዳንድ አሁን አስፈላጊነታቸው ወሳኝ ያልሆኑ ፕሮጀክቶች ለአገር ህልውና ሲባል መታጠፍ አለባቸው፡፡ ገንዘቡ ለብሄራዊ ሕልውና መዋል አለበት፡፡

በሌላ በኩል፤ በሥራዎች መዳከም ምክንያት ከሥራ ውጪ የሚሆኑ ዘርፎች አሉ፡፡ ስለዚህ መንግሥት በቅድሚያ የትኛው ዘርፍ ይጎዳል?… እነማን ይጎዳሉ? የሚለውን ለይቶ፣ ከባለቤቶቹ ጋር ውይይት አድርጎ፣ የታክስ ቅናሽ መስጠት ወይም የብድር አከፋፈል ሥርዓታቸው እንዲራዘምላቸው በማድረግ፣ በሌላ በኩል እነሱ ሰራተኛውን ይዘው እንዲቀጥሉ ድርድር ማካሄድ አለበት:: እነሱ ለሰራተኛው ደሞዙን እየከፈሉ እንዲያቆዩለት፤ መንግሥት ደግሞ ታክስና የብድር መክፈያ ጊዜ ማሻሻያ ያደርግላቸው ዘንድ መደራደር አለባቸው። እነዚህን አማራጮችን ባልኩት መልኩ መፈተሽ ያስፈልጋል፡፡

ሌላው መንግሥት ውሳኔዎቹ ኮሚኔክት የሚደረጉበትን ሁኔታ ግልፅና የማያሻማ መሆኑን ማረጋገጥ አለበት፡፡ መመሪያዎቹ የአማራጭ ሳይሆን ትዕዛዝ ነው መሆን ያለባቸው፡፡ “እንዲህ ቢሆን ይሻላል” ሳይሆን “እንዲህ መሆን አለበት” የሚል አስገዳጅ  ሊሆን ነው የሚገባው። አሁን ግን እንደዚያ አይነት ነገር አይደለም የሚታየው፡፡

በሌላ በኩል፤ ገጠር ላይ ስራ መሰራት አለበት፡፡ አርሶ አደሩ የቴሌቪዥን፣ የኢንተርኔት መረጃ የለውም፡፡ ስለዚህ በትኩረት መረጃ ማድረስ ያስፈልጋል። አርሶ አደሩ በገበያ ከከተማው ጋር ይገናኛል:: ስለዚህ የግብይት ሥርዓቱን መግታት፣ ከገጠር ወደ ከተማ፣ ከከተማ ወደ ገጠር ያለውን ዝውውር መግታት ያስፈልጋል። የአርሶ አደሩን ሕይወት የሚታደግ ራሱን የቻለ ኮሚቴ ያስፈልጋል፡፡ የሚሊኒየም አዳራሽን የመሳሰሉትን ቦታዎች ከወዲሁ አዘጋጅቶ ጥቅም ላይ ማዋል ይቻላል:: መንግሥት ፈራ ተባ ያለ ውሳኔ ላይ መሆኑ፣ ሰውን ለኢኮኖሚ ተበዝባዥነት እያጋለጠው ነው፡፡ ይሄ ከሚሆን ለአንድ ጊዜ መንግሥት እንቅስቃሴዎችን ገድቦ፣ ሃብትን ከማባከን ቢቆጠብ ጥሩ ነው። ሰው ፈራ ተባ እያለ በተንቀሳቀሰ ቁጥር ለከፍተኛ ወጭ ይዳረጋል፡፡ ከዚያ ይልቅ ያለውን ቆጥቦ ራሱን ጥብቅ ክትትል ውስጥ አድርጎ፣ ለ15 ቀን በቤቱ እንዲቆይ ቢደረግ፣ ከወጪ ቁጠባ አንፃርም ጠቃሚ ነው፡፡ በሌላ በኩል፤ ሰዎች አፋቸውን እንዲሸፍኑ ለማድረግ፣ የአፍ መሸፈኛ ጭንብሎች አቅርቦትን ማሳደግና በብዛት ማከፋፈል ያስፈልጋል፡፡

ከዚህ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ የቀጣዩ ምርጫ ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን ይችላል?

መንግሥት እስካሁን ዝምታን መርጧል፡፡ ግን ከወዲሁ መወሰን ይኖርበታል፡፡ ምርጫ ይደረጋል ከተባለ ስብሰባዎች ይኖራሉ፡፡ ንክኪን የሚጠይቁ ነገሮች የግድ ይፈፀማሉ:: በምርጫ ወቅት ሰልፍ አለ፡፡ ከዚህ አንፃር ምርጫውን ለማካሄድ የማይቻልበት ሁኔታ ተፈጥሯል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ምርጫው ሊካሄድ የማይችልበት እድል ከ90 በመቶ በላይ  ነው፡፡ ምክንያቱም በዚህ ሁኔታ ማንም ሰው ካርድ ሊወስድና ለምርጫ ሊወጣ አይችልም፡፡ ሰው ከወዲሁ በጉዳዩ ላይ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው ያስፈልጋል:: ጉዳዩ ሌላ የብጥብጥ አጀንዳ እንዳይሆን ከወዲሁ ከተቃዋሚዎች ጋር ውይይቶችና ድርድሮች ማድረግ ያስፈልጋል። እኔ በሽግግር መንግሥት አላምንም፡፡ የሽግግር መንግሥትም እንዲቋቋም ፈቃደኛ አይደለሁም፡፡ ነገር ግን ከበሽታው ጋር በተያያዘ ተነጋግሮ፣ ምርጫው የሚራዘምበት ሁኔታ ሊፈጠር ይገባዋል ባይ ነኝ፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆነን ምርጫ እናካሂዳለን ማለት ግን ሌላ ምስቅልቅል መፍጠር ነው። ስለዚህ በህልውና ጉዳይ ሕገ መንግሥቱም ይፈቅዳል፤ ምርጫውን ማራዘም ያስፈልጋል፤ ይሄ በትኩረት ውይይት የሚያስፈልገው ጉዳይ ነው፡፡

Filed in: Amharic