>

በረከት ምንም ሆኗል። ፍቱት! (አቤል አለማየሁ)

በረከት ምንም ሆኗል። ፍቱት!

 

አቤል አለማየሁ
በረከት ስምዖን የኢትዮጵያ ሕዝብ በዘመነ ሕወኀት ለደረሰበት አፈና፣ ዋነኛ የጭቆና ማሽን ሆኖ አገልግሏል። በምርጫ 97 ኢሕአዴግን አስደንግጦ ‘በቃኸኝ’ ያለውን የሕዝብ ድምፅ፣ ኮሮጆ አስገልብጦ በደሙ ሲነገድ ከፊት ሆኖ የመራ ፀረ-ዴሞክራሲ ሰው ነው። በመጽሐፉ (የሁለት ምርጫዎች ወግ) በተቃዋሚዎች ላይ ተሳልቋል። ብርቱካን ሚደቅሳ ላይ ለመሳለቅ የሞከረውን አያይዤዋለሁ። ዛሬ እሱ ያለበትን እና ብርቱካን ያለችበትን ስመለከት ጊዜ ደጉ እላለሁ። ይሄ ትልቅ ቅጣት ነው።
ከኢሕአዴግ ጎምቱ ባለስልጣናት ያልዘረፈ አለ ቢባል ለማመን ይከብዳል። ጌታቸው ረዳ ስለ በረከት የሙስና ክስ ሲጠየቅ እንዲህ አለ “ከበረከት ጋር ልዩነቶች አሉኝ። ነገር ግን ፓርቲ ውስጥ፣ 50 ሰው በሙስና ጠርጥረህ ብታመጣ በረከትን 49ኛ፣ እኔን 50ኛ ታገኘዋለህ።” በማለት በረከት በሙስና ስሙ እምብዛም እንደማይነሳ ተናገረ።
ይህ ማለት ግን ደረጃው ቢያንስም ያልነካ አለመኖሩን ያሳብቃል፤ ወይም ከእሱ በላይ እጅግ የመነተፉ መኖራቸውን ይጠቁማል። ዋነኞቹ መቀሌ የመሸጉት ዘራፊዎች ስላልተያዙ በረከት ነጻ ይውጣ ማለት ኢ-አመክኗዊ ነው። ነገር ግን ሌሎቹ ሌቦች እየፈነጩ፣ ውስኪ እያጋጩ፣ እየተሾሙ ባለበት አገር በረከት የእስካሁኑ እስር በቅቶት በምህረት ይፈታ ብሎ መጠየቅ (በአንፃራዊነት) ይሻላል።
የያኔው አስፈቺ ሰው ዛሬ የ”ፍቱኝ!” ምልጃ ውስጥ ገብቷል። አንዳንድ በእጁ ከበሉ ጋዜጠኞች እና አክቲቪስቶች ውጪ የሚከራከርለት ቡድን ወይም ማኀበረሰብ የለውም። ይሄ ትልቅ ቅጣት ነው።
በረከት ከመለስ ውጪ ከሕወኃቶች ጋር እንደ ነገሩ ነው። ይኸው ትዝም ብሏቸው ስሙን አንስተው አያውቁም። ፀረ አማራ ነውና የሚከራከርለት አማራ አይኖርም። ይሄ ታዲያ ትልቅ ቅጣት አይደለም?
ያ ኩፍስ ያለ ፊት ወደ ምንምነት ሲቀየር ማየት ታዲያ ትልቅ ቅጣት አይደለም? ተቃዋሚዎቹን ቃሊቲ ያጎረው ሰው ወኅኒ ወርዶ መማቀቁ ትልቅ ቅጣት አይደለም? በረከት ወደ ምንምነት ለቀየራችሁት ምስጋና ይድረሳችሁ። እንዳይነሳ አድርጋችሁ ስለጣላችሁት፤ በቃ አሁን ፍቱት፣ ለንስሀ ጊዜ ስጡት!
Filed in: Amharic