>

ዓለም በቴክኖሎጂ- እኛ በጨበጣ የተጋተርነው ኮሮና!!! (ሁሴን ከድር)

ዓለም በቴክኖሎጂ- እኛ በጨበጣ የተጋተርነው ኮሮና!!!

 

ሁሴን ከድር
ዓለም በቀላሉ የማታሸንፈው ጦርነት ውስጥ ከገባች ወራት ተቆጥሯል፡፡ ጦርነቱን በበላይነት እያሸነፈ ያለው ኮረና በዳቦ ስሙ (covid 19) ነው፡፡ ይህ ቫይረስ እስካሁን ግማሽ ሚሊዮን ሕዝብን ሲማርክ ከ20ሺህ በላይ ሙት ከመቶ ሺ በላይ ቁስለኛ አድርጓል፡፡ ቫይረሱ ሰውን ከመጉዳቱ ባሻገር የዓለምን ኢኮኖሚንም አሽመድምዷል፡፡
የምዕራባውያን ሚዲያዎች የቻይናን ኢኮኖሚ ለማንገዳገድ በታለመ ስልት ወሬው እንዲናፈስ አድርገዋል የሚሉት ቻይናውያን የማንም ቤት ፈርሶ የማንም ቤት አይቀርም የተሳለቀብን ሁሉ ከጎኑ ያገኛታል ብለው ዝተው ነበር ቻይናውያን፡፡ እንዳሉትም ጣሊያን ፣አሜሪካ፣ ጀርመን፣ ፈረንሳይ፣ ስፔን፣ ኢራን አውስትራሊያ እንግሊዝ…. በኢኮኖሚም በሰው ኃይልም እጢያቸው ዱብ እስኪል ነው የተሸመደመዱት፡፡
ቻይና በአንድ ጊዜ ነው የንግድ እንቅስቃሴዋ የወደቀው፣ ታላላቅ ካምፓኒዎች ሠራተኞቻቸውን በተኑ፣ ለዓለም ለመሸጥ አዘጋጅታቸው የነበሩ ምርቶቿ መጣያ ስታጣ ወደ ቬትናም ወስዳ በርካሽ ቸበቸበቻቸው፡፡ በዓመት በ6 በመቶ ያድግ የነበረው የቻይና ኢኮኖሚ ወደ 4.5 በመቶ ማሽቆልቆሉ የአደባባይ ሚስጥር ሆነ፡፡
በአሜሪካ ደግሞ ኮሮነ እየተፌዘበት ተገልብጦ አፌያዥ ሆኖ ከች አለ፡፡ አንድ ሁለት ጀምሮ 40 ሺ ሰዎችን ሲረፈርፍ ከሁለት ሳምንት የበለጠ ጊዜ አልፈጀበትም፡፡ በካሊፎርኒያ ብቻ 56 በመቶ የሚሆነው የግዛቷ ነዋሪ በኮሮና ሊጠቃ ይችላል ሲሉ የካሊፎርኒያ ገዥ ተናግረዋል፡፡ ይህ ማለት ከ40 ሚሊየን ካሊፎርናውያን 25.5 ሚሊዮኑ መሆኑ ነው፡፡ ኒዮርክ እና ካሊፎርኒያ ድንበራቸውን ብቻ ሳይሆን ቤታቸውንም ዘግተው ወረርሽኙን እንዲቆጣጠሩ ታውጆባቸዋል፡፡ አሜሪካ በኮሮና ምክንያት የሕዝቦቼን ጉዳት ሁለት ትሪሊየን በመመደብ እታደጋችኋለሁ ብቻ እናንተ የምትባሉትን ስሙ እያለች ነው፡፡ አንሰማም ባዮቹን ‹‹ወደህ ነው?›› እያለች ወታደሮቿን በከተማ አስጥታለች፡፡ ራሺያም ‹‹ቤትህ ትቀመጣለህ ተቀመጥ እምቢ ካልክ 15 ዓመት ትመቅቃታለህ›› እያለች እያስፈራራች ነው፡፡ በነገራችን ላይ ኢትዮጵያም ‹‹ቤት ቁጭ ብላችሁ ቡና አንቃሩ›› ያለቻቸው የመንግሥት ሠራተኞች አሏት፡፡
ኮሮና ኃያላን ሀገራትን ሊቀጣ ነው የመጣው የሚሉ አፍሪካውያን አፍላፊ እስከመናገር ደርሰዋል፡፡ የዚምባብዌ የመከላከያ ሚኒስትር ኦፖአህ ሙቺንግሪያህ በማሕበራዊ መገናኛ ዘዴ ባሰፈሩት አስተያየት ‹‹እነዚያ በእኛ ላይ የኢኮኖሚ ማዕቀብ የጣሉ ኃያላን አገሮች ዛሬ አብዛኞቹ ማዕቀብ ተጥሎባቸው በቤቶቻቸው ውስጥ ታሽገዋል፡፡ በኢኮኖሚ ማዕቀብ ሳቢያ እኛን እንዳስለቀሱን እነርሱም እያለቀሱ ይገኛሉ፡፡ ትራምፕ ዘላለማዊ ፈጣሪ አለመሆናቸውን ጠንቅቀው ሊያውቁ ይገባል፡፡ እኛን በማዕቀብ ያጨናነቁን ሀገራት ዛሬ እነርሱ በኮረና ቫይረስ ሳቢያ ሲጨናነቁ ወረፋው አሁን ለእናንተው ነው›› ብለዋል፡፡ ይህ ንግግራቸው ብዙም አልተወደደላቸውም ‹‹መሐይም ሚንስትር›› አስብሏቿል፡፡
የግብጽ ከፍተኛ የጦር ጄኔራሎችን ኮሮና ለሞት ዳርጓቸዋል፡፡ አልሲሲ የግብጽ መሪም ለ14 ቀናት ዞር በሉ፣ ከሰው ተነጠሉ አስብሏቸዋል፡፡ የጀርመኗመራኄተ መንግሥት ማርኬልም ተገለሉ ተብለው 14 ቀኑ ሳይሚላ በነጻነት ለአደባባይ በቅተዋል፡፡ ልጅ አዋቂ ሀብታም ድሃ፣ ንጉስ ተራ ሰው የማይለው ኮሮና የእንግሊዙንም ልዑል ቻርለስ እንዲገለሉ አድርጓል፡፡ በርካታ ኳስ ተጫዋቾች፣ አሰልጣኞች ኮረና ነጥሏቸዋል፡፡ ዓለም በብዙው ተጎድታለች፡፡ ሲኒማ ቤቶች፣ የኮስሜዳዎች፣ የመዝናኛ ቦታዎች፣ የቱሪስት መዳረሻዎች፣ የሰማይና የውሃ ላይ ጉዞዎች፣ በአየር በሀዲስ መብረር ሁሉ እድሜ ለኮሮና ጥርቅም ብሏል፡፡ ፋብሪካዎች፣ ትላልቅ ኢንዱስትሪዎች በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞቻቸውን ‹‹ሥራ የለም ወደቤታችሁ›› ብለው አሰናብተዋል፡፡
እንደ ብሉምበርግ ዘገባ ዓለም በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ወደ 2.7 ትሪሊየን ዶላር ልትከስር እንደምትችል ተንብዮዋል፡፡ በቻይና ሊደርስ የሚችለውን አደጋ ሲዘረዝር በአውቶሞቢል ንግድ 80 በመቶ፣ በአየር መንገዷ 85 በመቶ፣ ታሽቆለቁላለች በማለት ሟርቶባታል፡፡
ድሮም ስለ ኢራን መልካሙን ማውራት የማይፈልገው የምዕራባውያን ሚዲያ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት የተጎዱባት ሰዎች መብዛታቸውንና ከቁጥጥሯ ውጪ መውጣቱን ‹‹ዘ ኒውዮርክ ታየምስ›› ሲነግረን ነበር፡፡ ሆኖም ኢራን ለቀናት ይዛው ከነበረው የሶስተኝነት ደረጃ እያሽቆለቆለች ያለማንም አለሁ ባይነት ወረርሽኙን እየተቋቋመችው መምጣቷን እያሳየች ትገኛለች፡፡ ከሰሞኑ የኢራን ዓለምአቀፍ ሚዲያ ፕሬስ ቲቪ በፌስ ቡክ ገጹ ላይ ‹‹ኢራን ብቻዋን ናት›› የሚል ጽሑፍ በአመራማሪ ካርቱን ምስል አስደግፎ ለጥፎ ነበር፡፡ የኒኩሌር ማብላያ አላት ደብቃ እያመረተች ነው በሚል በአሜሪካ ተከሳ ማእቀብ የተጣለባት ይህቺ አገር ‹‹አደጋ ላይ ናትና እንዘንላት›› ብሎ የሰብዓዊ እርዳታ እንድታገኝ እንኳ የተማጸነላት የለም፡፡ አሜሪካ ‹‹ሰብዓዊ እርዳታ አይድረስላት አላልኩም ቴዎድሮስ ራሱ ያውቃል›› ብላለች፡፡ ቴዎድስ አድሃኖምን መሆኑ ነው
የኢትዮጵያ መንግሥት በአንድ ጃፓናዊ አማካይነት ቫይረሱን ሲተዋወቅ ‹‹የዓለም ጣጣ ወደኔም መጣ ብሎ ወዲያው 300ሚሊየን በመመደብ ነበር ችግሩን ለመቋቋም ያሰበው፡፡ እየዋለ እያደር ግን ወደ ቢሊዮኖች አሳድጎታል (5 ቢሊዮን ብር)፡፡ ኢትዮጵያ ለዓለም ገበያ ታቀርባቸው የነበሩ እንደሰሊጥ ቡና ፣ቆዳና የመሳሰሉት ምርቶቿ ዓለም በገጠማት የኢኮኖሚ ወጀብ መመታቱ የማይቀር ነው፡፡ የኢትዮጵያ ችግር የኢኮኖሚ መድቀቅ ብቻ ሳይሆን የሥልጣኔም ነው፡፡ ከድህነቷ ክፋቷ እንዲሉ፡፡
ኢትዮጵያ በሽታውን ለመቆጣጠር መጋቢት 14 የእቀባና የክልከላ ውሳኔዎችን አሳልፋለች፡፡ ሰፊ ቁጥር ያላቸው ስብሰባዎችን መከልከል (ምንም እንኳ ብልጽግና ፓርቲ ሰምቶ የዝሆን ጆሮ ይስጠኝ ብሎ ክልከላውን በክልሎች ቢጥስም) ማኅበራዊ ርቀትን መጠበቅ፣ የድንበር ዝውውርን መግታት፣ እና የመሳሰሉትን፡፡ ግን ሲተገበር አይታይም፡፡ ዛሬም ሰዎች እጅ ለእጅ ተቆላልፈው፣ ትከሻ ለትከሻ ተቃቅፈው፣ እየሄዱ ነው፡፡ አዳራሾች በሃይማኖት ሰበብ ሺዎችን እየሰበሰቡ ነው፡፡ መስጊዶች በጀመዓ እያሰገዱ ነው፣ ቤተክርስቲያኖች እያሰባሰቡ ነው፡፡ አምኜ ልሙት ባዩ ኢትዮጵያዊ ችግሩ ቢገባውም ባይገባውም ግዳጅ እስኪመጣ እንዳሻኝ እሆናለሁ ባይ ሆኗል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ለቻይናዊው ባለሃብት ጃክ ማ ‹‹አፍሪካን በገንዘብህ አስባት›› ብለውት ኮሮናን ለመከላከል የሚረዳ የሕክምና መርጃ ቁሳቁሶችን ወደ ኢትዮጵያ አስገብቷል፡፡ ኢትዮጵያም በአየር መንገዷ አማካይነት ወደየ አፍሪካ ሀገራት እያከፋፈለች ትገኛለች፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህም ሳይወሰኑ ለቡድን 20 አገራት የ150 ቢሊዮን ዶላር እርዳታን ለአፍሪካ ጠይቀዋል፡፡ መጠየቃቸው ባልከፋ ይበቃል ወይ የሚለው አጠያያቂ ይሆናል፡፡ ዓለም ባንክ በበኩሉ 14 ቢሊዮን ዶላር ለአፍሪካ እሰጣለሁ ብሏል፡፡ ኢትዮጵያ 300 ሚሊዮን ዶላር ይደርሳታል፡፡ አይ ኤም ኤፍም 50 ቢሊዮን ዶላር ለሰብሰሃራን ሀገሮች አከፋፍላለሁ ብሏል፡፡
ከየአቅጣጫው የሚመጣው ገንዘብ ነፍስ ባይቀጥልም ጥሩ ነው፡፡ አሁንም ጠንከር ያሉ ችግሮች አፍጠው መጥተዋል፡፡ የችግሩን መጠን በቅጡ ያልተረዳው የአዲስ አበባ ማኅበረሰብ የተነገረውን በአንዱ ጆሮው ሰምቶ በአንዱ እያፈሰሰ ይገኛል፡፡ እስከ ሐሙስ መጋቢት 17 ቀን በኮሮና ቫይረስ 12 ሰዎች መያዛቸውንና ሁለቱ ጃፓናውያን ወደሀገራቸው መሄዳቸውን ሰምተናል፡፡ ውሎ አድሮ ቁጥሩ እንደሚባዛ ይጠበቃል፡፡ መንግሥት በየካ ኮተቤ ታማሚዎችን ለይቶ ማቆያ ማዕከልና ሌሎች የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ የሕዝቡ ቸልተኝነት የሚያስከፍለው ዋጋ በጦርነቱ ወታደሮች (ዶክተሮች) ላይ እንደሚጸና የሚጠበቅ ይሆናል፡፡
ይህንን በሽታ ለመከላከል በየካ ኮተቤ 22 ዶክተሮች ፣150 ነርሶች፣ 500 አልጋዎች ተዘጋጅተዋል፡፡ ለጊዜው ለ110 ሚሊዮን ሕዝብ በሀገር ላይ ለመጣ ወረርሽኝ በተለይ የተዘጋጀው ይኸው ነው፡፡ ውሎ አድሮ ነገሮች ይቀየራሉ ብለን እንጠብቃለን፡፡ ሆኖም እነዚህ ዶክተሮች ወደፊት የሚጭጨመሩትም ቢሆን በቂ የሆነ የሕክምና መሣርያዎች አልተሟላላቸውም፡፡ እንደ ቫይረሱ አደገኛነት ታይቶ ዓለም እየተጠቀመባቸው ያሉ ለአንድ ጊዜ ተለብሰው የሚጣሉ ጭምብል ልብሶች በበቂ የሉም፡፡ ጫማዎች፣ ኮቮሮልስ (ሙሉ ቱታ) ሆስፒታል ስክራብስ፣ ፌስ ማስክ፣ አይ ጎግል( ሰፊ መነጽር)፣ ፌስ ሼልድ፣ ግላቭስ፣ ሜካኒካል ቬንትሌተር፣ ሹ ከቨር በበቂ የላቸውም፡፡ ቻይና፣ አውስትራሊያ፣ጣሊያን…. በሕክምና ላይ ያሉ ባለሙያዎች በከፍተኛ ጥንቃቄ ታማሚዎችን እያስተናገዱ ቫይረሱ ተላልፎባቸው ለሕልፈተ ሕይወት መዳረጋቸውን አይተናል፡፡ ለመሆኑ የኛዎቹ ሐኪሞች ምንም አልባሳት፣ ወይም በቂ አልባሳት በሌለበት ምን ያህሉ ለቫይረሱ ተጋላጭ ሊሆኑ እንደሚችሉ አስበነዋል?
ይህ ባስቸኳይ ልንዘጋጅበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ ለ30 ሺህ ዜጎች አንድ ሐኪም ባለባት ሀገራችን እነዚህኑ በኮሮና ምክንያት ካጣን በማን እጅ ልንወድቅ ነው? መንግሥት ማኅበረሰብንም አስተባብሮ ቢሆን እነዚህን መገልገያ እቃዎች በአጭር ጊዜ ከየትም ሊያስመጣ ይገባል፡፡ በተፋፋመ ጦርነት ውስጥ ሠራዊቱ ጥይት አልቆበት ዛሬም በድንጋይ ታንክ እንዲመርክ እንደመጠበቅ ነው፡፡ ኮሮና አይደለም እኛን ባለኒኩሌሮቹን በቀላሉ ማርኳል፣ ሙትና ቁስለኛ አድርጓል፡፡ እኛን ተራ ወታደር (ሰፊውን ማኅበረሰብ) ብቻ ሳይሆን የጦርነቱ ጄኔራሎችን (ሐኪሞችን) ሙትና ቁስለኛ በማድረግ የዓለም መሳቂያ እንዳያደርገን ልንጠነቀቅ ይገባል፡፡
ጤና ለታመሙ፣ ሰላም ለተጠንቃቂዎች፣ ልቦና ለቸልተኞች ይስጥልን፡፡ ጥንቃቄ፡፡
Filed in: Amharic