>

ዶ/ር አብርሃም በላይ እና ነብዩ ስሑል ሚካኤል " የትግራይ በረከቶቻችን " (አብርሃ በላይ)

ዶ/ር አብርሃም በላይ እና ነብዩ ስሑል ሚካኤል ” የትግራይ በረከቶቻችን ”  

 አብርሃ በላይ
እኔ የብልጽግና ፓርቲ ደጋፊ አይደለሁም። የባልደራስ ደጋፊ መሆኔ ለማሳወቅ ግን ብልፅግና ፓርቲን ማንቋሸሽ አይጠበቅብኝም። ያ በሽታ የለብኝም። ለሀገሬ የሚጠቅመውን ስመሰክር እንደኖርኩት ሁሉ፣ አሁንም እመሰክራለሁ። በንፁህ ልቦና እንደምታነቡት እምነቴ የፀና ነው።
 እነ ዶ/ር አብርሃም በላይ እና ነብዩ ስሑል ሚካኤል ብልፅግና ፓርቲን በትግራይ ላይ ለመመስረት የወሰዱት እርምጃ በሌሎች ኢትዮጵያውያን እጅጉን መበረታታት አለበት ባይ ነኝ። ለምን?
1) ህወሃት ተቆጣጥሮት በኖረበት በትግራይ መሬት ላይ ተቃዋሚ መሆን በሰሜን ኮርያ እንደ ተቃዋሚ መሆን ማለት ነው። ቅጣቱ አያድርስ ነው። ብዙ ሰው ታስሮበታል፣ ተገድሎበታል፣ ለረሀብ እና ለሥራአጥነት ተዳርጓል፣ ብሎም በማህበረሰቡ ተገልሎ ለአእምሮ በሽታ ተጋልጦበታል። ህወሃት ማንኛውም ትግራዋይ ዘለአለማዊ የሎሌ ትዕግስት (servile patience) ተጠናውቶት የነሱ ፍፁም አገልጋይ ሁነህ እንድትቀር ይፈልጋሉ። እነ አብርሃም እና እነ ነብዩ ይህን ፍርሃት ሰብረውታል፣ አርአያነታቸው ወደር የለውም (Their example is groundbreaking)። ለሌላው ወጣት የድፍረት ተምሳሌት ሁነዋል።
2) ህወሃት ለሁሉም ትግራዋይ የሚያቅድለት ፕሮግራም ቢኖር ሁሉም የዘር ፖለቲካ እስርቤት ቋሚ ኗሪ ሆኖ እንዲቀር ነው። ስለዚህ የህወሃት ፍላጎት የሚደፍራቸው ወጣት እንኳ ቢነሳ ገፋ ቢል በትግራይ ብሄር ስም ከመደራጀት ውጪ ሌላ መሆን የለበትም። ትህነጎች ኢትዮጵያዊ ድርጅት መቀላቀል ነውር (taboo) ያረጉት ገና ከ40 አመት በፊት ከምስረታቸው ጀምሮ ነው። መሪዎቹ ፅንፈኛ የኤርትራ ነፃነት ተሟጋቾች ሁነው፣ ሌላው ትግራይ “ሀገሬ ኢትዮጵያ” ካለ “ዳግማይ ሽዋዊ” (ሁለተኛ የሽዋ ሰው) ወይም “ዳግማይ አምሓራይ” እያሉ ሰላሙን ይነሱታል። ትህነጎች አንድ የባንዳ ትውልድ ባፈሩበት መሬት ላይ በኢትዮጵያዊነታቸው የኮሩ ነብዩ ስሑል ሚካኤል እና አብርሃም በላይ ተወልደው አድገው የዘር ፖለቲካን በጣጥሰው ለሀገራዊ አንድነት መሰለፋቸው የጀግኖች ጀግኖች ያሰኛቸዋል። ቦታው ትግራይ ነዋ – በኢትዮጵያ ውስጥ ያለች ሰሜን ኮርያ!!!!!
ህወሃት እንደ ካንሰር የሚፈሩት ጉዳይ ቢኖር ሌላው ትግራዋይ በሀገር ደረጃ ከተደራጀ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር አብሮ ያጠፋኛል የሚል ስጋት ነው። ይህ እንዳይሆን ደግሞ እጁን ተከታትለው በመርዝ፣ በጥይት፣ በመኪና ገጭተው፣ ወይም ከፎቅ ገፍትረው ጥለው ይገድሉታል። ነብዩ እና ዶ/ር አብርሃም በላይ እና ሌሎች የትግራይ ወጣቶች በትግራይ የብልፅግና ፓርቲ አባላት ነን ብለው ያላንዳች ስጋት መንቀሳቀሳቸው ህወሃትን እንቅልፍ የነሳ ጉዳይ ሲሆን፣ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵውያን ግን እጃቸውን ዘርግተው በደስታ ሊቀበሏቸው የግድ ይላል።
Filed in: Amharic