>

የገብረክርስቶስ ደስታ 39ኛ ዓመት የሙት መታሰቢያ  (ልኡል አምደጽዮን ሰርጸድንግል)

የገብረክርስቶስ ደስታ 39ኛ ዓመት የሙት መታሰቢያ 

 

 

ልኡል አምደጽዮን ሰርጸድንግል
ቀረሽ እንደ ዋዛ
ለኢትዮጵያ እጅግ የተለየ ክብርና ፍቅር የነበረው … በኢትዮጵያ ዘመናዊ የሥነ ጥበብ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ሥፍራ የነበረው ሰዓሊና ገጣሚ ገብረክርስቶስ ደስታ ያረፈው ከዛሬ 39 ዓመታት በፊት (መጋቢት 21 ቀን 1973 ዓ.ም.) ነበር፡፡
‹‹መልስ ወደአገር ቤት፣››፣ ‹‹የካቲት 12››፣ ‹‹ያለፈው መልካሙ ጊዜ››፣ ‹‹የሐረር ገበያ››፣ ‹‹እኔ ነኝ››፣ ‹እኔ በገዛ እጄ›፣ ‹‹ጎልጎታ››፣ ‹‹ጂፕሲ ልጃገረድ››፣ ‹‹ቀይብርሃን››፣ ‹‹የድሆች ቤተሰብ››፣ ‹‹በራሪ ወፍ››፣ ‹‹በቁኤት››፣ ‹‹ጠላቂ ጀምበር››፣ ‹‹ፀደይ›› … የተሰኙት ሥዕሎቹ በኢትዮጵያ ዘመናዊ የሥዕል ታሪክ አዲስ የሥዕል ጥበብ/ስልት እንዲታይ ፋና ወጊ ከሆኑ የገብረክርስቶስ ስራዎች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
 – – –
ገብረ ክርስቶስ በይበልጥ የሚታወቀው በሥዕል ሥራዎቹ ቢሆንም በተለያዩ ጊዜያት የጻፋቸው ተወዳጅ የግጥም ሥራዎቹ በኢትየጵያ በዘርፉ ትልቅ ስም ካላቸው ሰዎች ተርታ አስቀምጠውታል፡፡ ገብረ ክርስቶስ በረቂቅ የሥዕል አቀራረቡ በኢትዮጵያ መነጋገሪያ የሆነውን ያህል፤ ግጥሞቹ የራሳቸውን የቃላት አሰላለፍ የሚከተሉና የቤት አመታታቸው ቁጥር ከተለመዱት የግጥም ቤቶች የተለዩ መሆናቸው በጥበብ ቤተሠቦች ዘንድ መነጋገሪያ መሆናቸው አልቀረም፡፡
 – – –
ገብረክርስቶስ ደስታ 60 ያህል የግጥምና የቅኔ ስራዎችን አበርክቷል፡፡ ለአገሩ የነበረውን ፍቅር ‹‹ኢትዮጵያ እናቴ›› ሲል በሰጣት ቦታ፣ የአገሩን ናፍቆት ‹‹ሀገሬ›› እና ‹‹እንደገና›› በተሰኙ ግጥሞቹ እንዲም የአገር ቁጭቱን ደግሞ ‹‹የጾም ቀን›› እና ‹‹በባእድ አገር›› በተሰኙት ግጥሞቹ ገልጿቸዋል፡፡ ከገብረክርስቶስ ግጥሞች መካከል በተለይ ‹‹ሀገሬ›› የሚለው በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅና የሚታወስ ነው፡፡
ቀረሽ እንደ ዋዛ
 (ገብረ ክርስቶስ ደስታ)
እንደ ድመቶቹ
የትም እንደሚያድሩት
እንደ ዛፍ ሐረጎች፣
እንደ ቤት ክዳኖች
ብርድ አቆራመደኝ።
ስጠብቅ —– ስጠብቅ
“ትመጫለሽ ብዬ ሳይ ማዶ፣
                            ሳይ ማዶ፣
የልጅነት ዓይኔ ሟሟ እንደ በረዶ።”
ትመጫለሽ ብዬ ደቂቃ ስቆጥር፣
ትመጫለሽ ብዬ ሰዓቱን ስቆጥር፣
ትመጫለሽ ብዬ ባዘን ሳንጎራጉር
ትመጫለሽ ብዬ በበራፍሽ ስዞር
ብርድ አቆራመደኝ።
የመንገድ መብራቶች አይተው አፌዙብኝ
ውርጩ ቀለደብኝ፣
ጨለማው ሳቀብኝ።
አለመምጣትሽን
አውቀዋል —– ያውቃሉ።
መስኮቶች ጨልመው፣
ቤቶች ተቆልፈው፣
ከተማው ሲተኛ
አይተዋል —– ያያሉ።
አለመምጣትሽን
አውቀዋል —- ያውቃሉ።
ከ”መንገድ ስጡኝ ሰፊ” የግጥም መድብሉ የተጨለፈ
Filed in: Amharic