>

የህንድ ፊልምን ሳይሆን የህንድ መንግስትን ተከተል!!! (በእውቀቱ ስዩም)

የህንድ ፊልምን ሳይሆን የህንድ መንግስትን ተከተል!!!

በእውቀቱ ስዩም
  የሚሆነው አይታወቅምና   ሀቅ ሀቁን ተናግሬ  ልወገድ ! 
ድሮ ኤቺ አይቪ   ባገራችን ገባ ገባ ብሎ ስታራቴጂያዊ ቦታዎችን በተቆጣጠረበት ጊዜ  ህዝቡ  ናላውን  የክህደት ሞድ ላይ አድርጎት ነበር ፤ ዋናው መተላለፍያ መንገድ  ግብረስጋ ግኑኝነት ሆኖ ሳለ ሚድያዎች  ባልተቀቀል መርፌ የመጠቀም ጉዳት  ስለሚያመጣው ጉዳት  ሲዘበዝቡ ነበር እሚውሉት  ::  እኔ ራሴ ያስራሁለተኛ ክፍል ተማሪ እያለሁ፤
“የወደቀ ምላጭ አታንሱ አትጠጉ 
መርፌ ሳይቀቀል  ይቅር  አትወጉ”
የሚል ስንኝ ያለበት የቸከ ግጥም ፅፌ ተሸልሚያለሁ:: ( በኔ እንኩዋ አይፈረድብኝም፤ በጊዜው  ስለምላጭና ስለመርፌ እንጂ ስለግብረስጋ እማውቀው ነገር አልነበረም )
 የብዙ ሰው አእምሮ ፤ግብረስጋን የመሰለ የህይወት እና የደስታ ምንጭ የገዳይ ቫይረስ መተላለፍያ ይሆናል ብሎ ለመቀበል  ዝግጁ አልነበረም ::   በተፈጥሮ   ደባሪ ሀቆችን   ባላየ እንድናልፍ ሆነን ነው የተቀናበርነው !
መንግስት ዘንበል ሲል፤ ክፉ ዘመን ሲመጣ እብሪትንና አላዋቂነትን  አስተባብረው የያዙ፤ የግዜር ወኪል ነን ባዮች መደረኩን  እንደሚቆጣጠሩት የታወቀ ነው ፤ የህዝብ ግራ መጋባትና ጭንቅ  እንደሻ ለማውራት ይመቻቸዋል !  የተሸበረ ህዝብና በጅምላ የሚሸሽ  ሰራዊት መንገድ አይመርጥም! መውጫ ብሎ ያሰበው ላይ ሁሉ ይረባረባል!
 እነሱን ትተን ስለ አሪፍ ሰባኪዎች  ብናወራ ይሻለናል፤ በጣም የማከብራቸው መርጌታ ክፍሌ  በቅርቡ በሰጡት ኦንላይን ስብከት የሚከተለውን ድንቅ ስብከት ሰብከው  አስደምመውኛል፤
“  እግዚያብሄር በየዘመኑ በተለያየ መንገድ ይሰራል፤ በሙሴ ዘመን በእጣን በእሳት ይፈውስ ነበር፤ አሁን የሚፈውሰው  በሳሙና እና  በውሃ አድሮ ነው፤   ደሞ ተበተን ከተባልክ ተበተን! እግዜር የጉባኤ ብቻ ሳይሆን የብህትውናም አምላክ ነው፤   እንጦስን ታውቀዋለህ! ብቻውን በምድረበዳ የሚኖር ባህታዊ ነበር!   እና ልጄ!
ከመሆን የህዝብ  ጦስ ! 
ተነጠል እንደ እንጦስ ! 
የህንድ ፖሊስ ትምጣብኝ!   በየቤትህ  ገብተህ ተከተት ብላ  አወጀች!   እነ ኩማር ደሞ ቤት መቀመጥ ደበረን ብለው፤ አደባባይ ላይ   በሞተር ሳይክል፤  ሽር ብትን ሲሉ ፖሊስ ከተፍ ብላ በወደላ ጨፈቃ  እያበራየች  ወደ ጎሬው  አስገባቺው ! አንዱ ህንድማ በሞተር ሳይክል መጥቶ  ዊልቼር ተመለሰ፤፤ “ በቸር እንጂ በዊልቸር ከመመለስ ይጠብቅህ” ይላሉ የህንድ እናቶች ልጆቻቸውን ሲመርቁ!   እንዲያ ነው እንጂ! ቀውጢ ዘመን ቀውጢ ውሳኔ ይጠይቃላ!
ባለፈው ፑቲን  የሞስኮብን ህዝብ አስቦክቶ  ወደ ቤቱ ለማስገባት አንበሳ ፈቶ ለቀቀ የሚል  አጉል ወሬ ሰምቼ ነበር ፤  እና አገር  ቤት ደውየ ባለንጀራየ ምኡዝን “  አብይ አህመድ  አንድ አስር አንበሶች ከነጭ ሳር ፓርክ አምጥቶ አዲሳባ ላይ ቢለቅ ምን ይፈጠ ር ይመስልሃል ?” አልኩት ፤
 “  ህዝቡ አንበሶችን አልምዶ እንደ ሀረር ጅብ ተሰብስቦ ይዝናናባቸዋል!  “
Filed in: Amharic