>
12:25 am - Thursday December 1, 2022

የጨርቅ ማስክ በሚጠቀሙና በማንጠቀም ህዝቦች መሀል ያለ ሰፊ ተጋላጭነት ልዩነት! (ቅዱስ ማህሉ)

የጨርቅ ማስክ በሚጠቀሙና በማንጠቀም ህዝቦች መሀል ያለ ሰፊ ተጋላጭነት ልዩነት! 😷 

ቅዱስ ማህሉ
 
* ልማድን ያስቀራል፤ የኮሮና ቫይረስን ስርጭት ይቀንሳል!
 
«የድሆች አመጽ ያስፈራው የጣሊያን መንግስት!»
የኢትዮጵያ መንግስት የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎቹ በኩል በፍጥነት አምርቶ የሚታጠብ የጨርቅ ማስክ ነገ ዛሬ ሳይል ለህዝቡ ያዳርስ። ጊዜ የለም። የኢትዮጵያ መንግስት ማድረግ የሚችለውን ሁሉ ሳይሆን በማድረግ ከፍተኛ ውጤት የሚያስገኘውን አሰራር ብቻ ይከተል። የባህርዳር፣የኮምቦልቻ፣የአዋሳ፣የአዲግራት ወዘተ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች ቢያንስ በከተማዎቹ ለሚኖሩት ነዋሪዎች በራሳቸው ወጭ የጨርቅ ማስክ ሰርተው ቢያድሉት ብዙ ህይወትን ከማትረፍ ባለፈ በክፉ ቀን ማህበራዊ ግዴታቸውን መወጣት የሚችሉበትን አጋጣሚ ስለሚጠቀሙበት ዛሬ ነገ ሳይሉ ይተግብሩት። ማስክን የመጠቀም ውጤታማነት ለማሳየት ምሳሌ የምናደርጋቸው ሃገራት አሉ።
 ጃፓን(ጣሊያን ሁለተኛ ናት) በዓለም ላይ ብዙ አረጋዊያን የሚኖሩባት ሃገር ናት። የመጀመሪያው የኮሮና ቫይረስ ተጠቂ በጃፓን የተመዘገበው Jan 14 ነው። እስካሁን በጃፓን የኮሮና ቫይረስ የተያዘ ሰው 1,953 ሲሆን የተመዘገበው ሞት ግን 56 ብቻ ነው።
  ጣሊያን ደግሞ የመጀመሪያዋን የኮሮና ተጠቂ ሪፖርት ያደረገችው ጃኑዋሪ 29 ሲሆን እስካሁን የተያዙት 101,739 ሲሆን 11,591ሽ ሰዎች በሞት ተለይተዋል።
 ጃኑዋሪ 19 ቀን ደቡብ ኮሪያ የመጀመሪያውን ሰው ሪፖርት ያደረገች ሲሆን እስካሁን 9,786 ሰው ኮሮና ቫይረስ እንዳለበት ሲረጋገጥ 162 ዜጎቿ ደግሞ ሞተዋል።
በአሜሪካ የመጀመሪያው ተጠቂ ሪፖርት ከተደረገበት ጃኑዋሪ 20 ጀምሮ 164,248 ሰዎች በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን እስካሁን 3,164 ሰዎች ሞተዋል።
ስፔን ጃኑዋሪ 30 አንድ ብላ መቁጠር ጀምራ ዛሬ ላይ 87,956 ዜጎቿ ኮሮና ቫይረስ እንዳለባቸው ያረጋገጠች ሲሆን 7,716 ዜጎቿን ደግሞ በሞት ተነጥቃለች።
 ፌብሩዋሪ 29 የመጀመሪያውን ሰው ሪፖርት ያደረገች ቼክሪፐብሊክ  እስካሁን 3001 ሰዎች በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው ስታረጋግጥ 23 ሰዎችን ደግሞ በሞት ተነጥቃለች።ቼክ ሪፐብሊክ ከማርች 18 ጀምሮ ማስክ ማድረግ ግዴታ እንዲሆን አድርጋለች። በዚህም በከፍተኛ ሁኔታ የአዲስ ተያዦች ቁጥር መቀንሱ ታውቋል።የእኔ መልዕክትም ማስክ በማድረግ ብዙ ኢትዮጵያዊያንን በኮሮና ቫይረስ እንዳያዙ በቀላሉ መከላከል እና ስርጭቱን እንዳይስፋፋ ማድረግ ይቻላል። በፍጥነት ከተገበርነው ማለቴ ነው።
 ማስክ በማድረግ ብዙ ክፍት ገበያዎች ላይ ያለውን ትፍፍግ፣ በአንድ ቤት ለብዙ የመኖር ባህል፣ ገበያ ላይ በቅርበት የሚደረጉ የቀንስ አትቀንስ ክርክሮች፣በጣት ምላስ እየነኩ ብር መቆጠር፣ አፍ ላፍ ገጥሞ ወሬዎች፣ የቡና ወግ እና ሌሎችም ብዙ ማህበራዊ መስተጋብርን የሚያጠናክሩ ስር የሰደዱ ልማድ እና ባህል ባለበት ሃገር ማህበራዊ መራራቅ፣ ሰላምታ አለመለዋወጥ እና  የእጅ መታጠብ ጉዳይ  ወዘተ ችግሮች  ማስክ በማድረግ መቀንስ ይቻላል። አፉ ላይ ማስክ አድርጎ ገበያ የሚሄድ ሰው ገንዘብ ሲቆጥር ወደ ምላሱ ሲሄድ ከተሸፈነበት ምላሱን አይነካም። ሰው ሰላም ቢልም አፉን አይነካም። ከባዱን እና ባንዴ መተው  የሚከብደውን እና ለማስፈጸምም የማይቻለውን ልማድ ከማቆም በዚያ ምክንያት ሰውየው እጁን ወደ አፉ እንዳይወስድ ማድረግ ይቀላል። ማስክ በማድረግ!  እጅ መታጠብ ሲናገሩት ቀላል እና ተራ ነገር ይመስላል። በኢትዮጵያ ግን እንኳን በገጠር ለከተማው ነዋሪ ራሱ  ፈታኝ ነው።
 መንግስትም ይህን አቅርቦት የማድረግ አቅም የለውም። በዚያ ላይ በየእለቱ ካልሰራ የማይበላ ብዙ ነው። በር ዘግተህ ተቀመጥ ሲባል “ምን ልብላ?” ብለው የሚጨነቁ ሚሊዮን ነፍሶች አሉ። በነዚህ ላይ በር እዘጋለሁ ማለት ሌላ መዘዝ ሊያስከትል እንደሚችል ከወደ ጣሊያን እያየን ነው። ድሆች የሚበዙበት ደቡባዊ ጣሊያን በቂ ምግብ የለንም ካሁን በኋላ እቤታችን አንቆይም በሚሉት ዜጎቿ ቁጣ እያየለ መምጣቱን ተከትሎ ማፊያዎች ሁኔታውን መጠቀሚያ ለማድረግ አመጽ እየቀሳቀሱ መሆኑ ያሳሰበው የጣሊያን መንግስት ለደቡባዊ ግዛት አስተዳደሮች የሚከፋፈል 4•3ቢሊዮን ዩሮ ገንዘብ አጽድቋል። በሲሲሊ መንግስት ከወዲሁ ወታደሮችን አሰማርቷል። የፓሌርሞ ከንቲባ አካባቢው በአመጽ ከመናጡ በፊት “መንግስት መፍጠን አለበት፤ እጅግ በጣም መፍጠን አለበት።” ሲሉ አሳሳቢነቱን ገልጸዋል።  ስለዚህ እንደ ኢትዮጵያ እና እንደ አቅማችን መፍትሄ እንወጥን። የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል መርሆቹን የሚተገብሩ፣ አቅሙ እና ችሎታው ያለቸው ሁሉ ጥረታቸውን ይቀጥሉ። ለሁሉም ግን ማስክ ወሳኝ ነው። ማስክ በመላው ኢትዮጵያ ለማረሚያ ቤቶችም ጭምር በፍጥነት ለህዝቡ ይዳረስ።
ከዚያ መንግስት ማስክ ሳያደርጉ መንቀሳቀስ ይከልከል። ለነገሩ ህዝቡ ራሱ ያን ተፈጻሚ ማድረግ ይችላል። ይህን ጉዳይ ክልሎችም ሆናችሁ ወረዳዎች ወይም ከተማዎች በፍጥነት ተግብሩና ለሌላው ሞዴል ሁናችሁ አሳዩት። ቢያንስ ሌላውን ጥንቃቄ ሁሉ ማድረግ እስክንችል፣  ልማድ አድርገን እስክናዳብረው እና ዝግጁነቱ እስኪኖረን ድረስ በዚህ መንገድ የቫይረሱን ስርጭት መግታት እንችላለን።
Filed in: Amharic