>

ስለ እኛ የተቀጠፉ . . . የቀያይ እምቡጦች የስንብት ደብዳቤ !!! ኦሮማይ፣ በዓሉ ግርማ

ስለ እኛ የተቀጠፉ . . . የቀያይ እምቡጦች የስንብት ደብዳቤ !!!
     (ከከፍታ ነጥብ 1702፣ ናቅፋ!)
         — ኦሮማይ፣ በዓሉ ግርማ
በአሰፋ ሃይሉ
/ለአንባቢው ማስታወሻ፡- የቀይ ኮከብ ዘመቻ ያበቃው በየካቲት ወር 1974 ነው፣ ይህ ኦሮማይ መጽሐፍ የታተመው በታህሳስ ወር 1975 ነው፡፡ ደራሲው ያየውን ለመጻፍና ለማሳተም 9 ወር ብቻ ነው የፈጀበት፡፡ ምን ታይቶት ይሆን ችኮላው? እግዜሩ ይወቅ! መልካም ንባብ!/
‹‹…. ምን ፡ ምን ፡ እንደምሸትና ፡ ምን ፡ እንደምመስል ፡ ካሁኑ ፡ ጠፍቶኛል ፡፡ ምን ፡ ምን ፡ እንደምሸት ፡ አላውቅም ፡፡ ምቾትና ፡ ሕልውና ፡ ትርጉም ፡ አልነበራቸውም ፡፡ እውን ፡ ሆኖ ፡ የሚታየኝ ፡ ነገር ፡ ቢኖር ፡ ከፍታ ፡ ነጥብ ፡ 1702 ፡ ብቻ ፡ ነበር ፡፡ እና ፡ እያንዳንዱ ፡ ሰው ፡ ወደ ፡ መጨረሻ ፡ ግቡ ፤ ወደ ፡ ተወሰነለት ፡ ጥሪ ፡ ይፈጥን ፡ ነበር ፡፡ በፍጥነት ፡ ነበር ፡ የምንጓዘው ፤ አንዴ ፡ ብቻ ፡ ነበር ፡ ለውሃ ፡ የቆምነው ፡፡ የሞቀ ፡ ውሃ ፡ እየተስማማኝ ፡ ሄዷል ፡፡ ወታደሩ ፡ በዚህ ፡ በረሃ ፡ ከቀዝቃዛ ፡ ይልቅ ፡ ትንሽ ፡ ሞቅ ፡ ያለ ፡ ውሃ ፡ ነው ፡ ጥም ፡ የሚቆርጠው ፡ ሲለኝ ፡ ይገርመኝ ፡ ነበር ፡፡ ነገሩ ፡ እውነት ፡ ሆኖ ፡ አግኝቼዋለሁ ፡፡ . . .
‹‹ የቀይ ፡ እምቡጥ ፡ ጦር ፡ አባሎች ፡ ሰውነታቸውን ፡ እንዳያጸዱ ፡ ታዘዙ ፡፡ የ17ኛው ፡ ክፍለ ፡ ጦር ፡ አባሎች ፡ አስተናጋጅ ፡ በመሆን ፡ ምግብ ፣ ውሃ ፡ ከማቅረብም ፡ ሌላ ፡ ልብሶቻቸውን ፡ ወስደው ፡ ያጥቡላቸው ፡ ነበር ፡፡ ካሜራችን ፡ ተከተላቸው ፡፡ ገላቸውን ፡ ሲታጠቡ ፡ አፋፍ ፡ ላይ ፡ ቆሜ ፡ እመለከታቸው ፡ ነበር ፡፡ ራሳቸውን ፡ ለሞት ፡ የሚያጠምቁ ፡ መስለው ፡ ታዩኝ ፡፡ ለዚህ ፡ አደገኛ ፡ ተልዕኮ ፡ እያንዳንዳቸውን ፡ ያነሳሳው ፡ ነገር ፡ ምን ፡ እንደሆነ ፡ አላውቅም ፡፡ እያንዳንዳቸው ፡ ለዚች ፡ አገርና ፡ ለዚህ ፡ አብዮት ፡ ከሌሎች ፡ ይበልጥ ፡ ተቆርቋሪ ፡ ሆነው ፡ አይደለም ፤ ወይም ፡ አይመስለኝም ፡፡
‹‹ግን ፡ አንድ ፡ ነገር ፡ ይሰማኝ ፡ ነበር ፡፡ በውስጣቸው ፡ የሕይወት ፡ እሳት ፡ የሚነድ ፡ ነፃ ፡ ሰዎች ፡ ነበሩ ፡፡ ነፃ ፡ ሰው ፡ ውብ ፡ ነው ፥ ቆንጆ ፡ ነው ፡፡ እና ፡ ሁሉም ፡ ውቦች ፥ ቆንጆዎች ፡ ነበሩ ፡፡ ልቤ ፡ በጣም ፡ አዘነ ፡፡ ጀምበሯ ፡ ከናቕፋ ፡ ተራሮች ፡ በስተጀርባ ፡ ልትጠልቅ ፡ አሽቆልቁላለች ፡፡ ሠማዩ ፡ እንደ ፡ ደም ፡ ቀልቶ ፡ ይታይ ፡ ነበር ፡፡ ቀጥሎ ፡ የሆነው ፡ ነገር ፡ ነው ፡ ይበልጥ ፡ ልቤን ፡ የነካው ፡፡
‹‹የቀይ ፡ እምቡጥ ፡ ጦር ፡ አዛዦች ፡ ለዘመዶቻቸው ፡ ወይም ፡ ለተወካዮቻቸው ፡ ወይም ፡ ለሚመለከተው ፡ ሰው ፡ የሚያስተላልፉት ፡ መልዕክት ፡ ካላቸው ፡ እንዲጽፉ ፡ ተጠይቀው ፡ ነበር ፡፡ ምን ፡ መልዕክት ፡ እንደሚተዉ ፡ ለማወቅ ፡ ፍላጎት ፡ ስላደረብኝ ፡ አንዳንዶቹ ፡ እንዲያሳዩኝ ፡ ጠይቄያቸው ፡ ነበር ፡፡ . . .
‹‹ምናልባት ፡ አደጋ ፡ ደርሶብኝ ፡ የሞትኩ ፡ እንደሆነ ፡ ያለኝ ፡ ጥሬ ፡ ገንዘብ ፡ በሙሉ ፡ ለቀይ ፡ ኮከብ ፡ ዘመቻ ፡ እንዲሰጥልኝ ፡ እጠይቃለሁ ›› የሚሉ ፡ መልዕክቶች ፡ ብዙ ፡ ነበሩ ፡፡ አሣልፈው ፡ የሚሰጡት ፡ ውድ ፡ ሕይወታቸው ፡ አልበቃ ፡ ብሎአቸው ፡ ይሆን ? በማለት ፡ ተገረምኩ ፡፡
‹‹ለሚስት ፥ ለልጅ ፥ ለወንድም ፥ ለእህት ፥ ለአባት ፥ ወይም ፡ ለዘመድ ፡ የተጻፉ ፡ ደብዳቤዎች ፡ ጥቂት ፡ አልነበሩም፡፡ አንዳንዶቹ ፡ ስለጉዞአቸውና ፡ አሁን ፡ ስለሚጠብቃቸው ፡ ተልእኮ ፡ ነበር ፡ የጻፉት ፡፡ እና ፡ አብዛኛዎቹ ፡ ደብዳቤዎች ፡ ‹‹ከዚህ ፡ በኋላ ፡ የሚሆነውን ፡ እጽፋለሁ ፡፡ ለእኔ ፡ አታስቡ ፡፡ ደህና ፡ ነኝ ፡፡ ለምንድነው ፡ የማትጽፉልኝ ? እኔ ፡ ካንቺ . . . ፡ ወይም ፡ ካንተ . . . ፡ ናፍቆት ፡ በስተቀር ፡ ሌላ ፡ አሳብ ፡ የለኝም . . . ›› በሚሉ ፡ ዐረፍተ ፡ ነገሮች ፡ የተደመደሙ ፡ ነበሩ ፡፡
‹‹ከዚህም ፡ ባሻገር ፡ ‹‹ናቅፋ ፡ ደርሰናል ፡፡ እንደ ፡ አያያዛችን ፡ ከሆነ ፡ ይህ ፡ ጦርነት ፡ ጊዜ ፡ የሚፈጅ ፡ አይመስልም ፡፡ በቅርብ ፡ ቀን ፡ እመጣለሁ ፡፡ እስከዚያ ፡ ድረስ ፡ ገንዘብ ፡ ካለ ፡ ላኪ ፡ (ወይም ፡ ላክ) ፡፡ ራዲዮና ፡ ቴፕሪኮርደር ፡ አልጌናና ፡ አፍአበት ፡ በርካሽ ፡ ዋጋ ፡ ይገኛል ፡፡›› ካሉ ፡ በኋላ ፡ ሲመለሱ ፡ ምን ፡ ለማድረግ ፡ እንዳሰቡ ፡ በዝርዝር ፡ የጻፉ ፡ ሰዎችም ፡ ነበሩ ፡፡ አንዱ ፡ ባጠራቀመው ፡ ገንዘብ ፡ ያቺኑ ፡ ማሣ ፡ እንዴት ፡ እንደሚያለማና ፡ ያቺን ፡ ጎጆ ፡ እንዴት ፡ እንደሚያቃና ፡ ይጽፋል ፡፡ ሌላው ፡ በችግር ፡ ምክንያት ፡ ያቋረጠውን ፡ ትምህርት ፡ እንዴት ፡ አድርጎ ፡ እንደሚቀጥልና ፡ እምን ፡ ደረጃ ፡ ድረስ ፡ ለመማር ፡ እንደሚፈልግ ፡ ያትታል ፡፡
‹‹ከጦር ፡ ሜዳ ፡ አያሌ ፡ ጠቃሚ ፡ ትምህርት ፡ አግኝቼያለሁ ፡፡ ተለውጫለሁ ፥ ከእንግዲህ ፡ እንዳለፈው ፡ ጊዜ ፡ ተመልሼ ፡ የምቀብጥ ፡ አይመስለኝም ፡፡ መጠጥ ፡ የሚባል ፡ ነገር ፡ ትቻለሁ ፡፡ እንደ ፡ ድሮው ፡ በትንሹም ፡ በትልቁም ፡ ነገር ፡ አልናደድም ፡፡ ጦር ፡ ሜዳ ፡ ያሰክናል ፡፡ ውዴ ፡ ሙች ፥ ቅናትም ፡ ትቻለሁ ፡፡ አሁን ፡ የምቀናው ፡ በሕይወት ፡ ብቻ ፡ ነው ፡፡ አሁን ፡ የምመኘው ፡ ነገር ፡ ቢኖር ፡ ደስታና ፡ ተድላ ፡ የሰፈነበት ፥ የሰከነና ፡ የቀዘቀዘ ፡ ኑሮ ፡ መኖር ፡ ብቻ ፡ ነው ፡፡ ወደፊት ፡ የምንኖረው ፡ ኑሮ ፡ ይታየኛል ፥ ልጄን ፡ ሳሚልኝ ፡፡ ስመለስ ፡ የበደልኳችሁን ፡ በደል ፡ ሁሉ ፡ ድርብ ፡ አድርጌ ፡ እክሳለሁ ፡፡›› በማለት ፡ የጻፉ ፡ ሌሎችም ፡ ነበሩ ፡፡
‹‹አዎ ፡ በሰው ፡ ልብ ፡ ተስፋ ፡ ምንጊዜም ፡ አይሞት ፡፡ ሕይወት ፡ ካለች ፡ ተስፋ ፡ ምንጊዜም ፡ ይኖራል ፡፡ ‹‹በማደርገው ፡ መራራ ፡ ትግል ፡ ወድቄያለሁ›› ፥ ‹‹ናቅፋ ፡ የኔ ፡ መቃብር ፥ ያብዮቴ ፡ አምባ ፡ ትሆናለች›› ፥ ‹‹ሞት ፡ አይቀርምና ፡ የሚሞቱበትን ፡ ቦታና ፡ ሁኔታ ፡ መርጦ ፡ መሞት ፡ ታላቅ ፡ ዕድል ፡ ነው ፡፡ ግን ፡ ናቅፋን ፡ አደራ ፥ እኔ ፡ የታሪክ ፡ ሰው ፡ አይደለሁም ፡፡ ተራ ፡ ወታደር ፡ ነኝ ፡፡ ግን ፡ ለኢትዮጵያችን ፡ ሕልውና ፡ ኤርትራን ፡ ወሳኝ ፡ ናት ፡ ሲሉ ፡ ሰምቻለሁ ፡፡ ለኢትዮጵያ ፡ ሕልውና ፡ ተሰውቻለሁ ፡፡ ከሕይወቴ ፡ በቀር ፡ ላገሬ ፡ የማበረክተው ፡ ሌላ ፡ ውድ ፡ ነገር ፡ የለኝም ፡፡ ወገኔ ፥ ከኢትዮጵያ ፡ ሕልውና ፡ ሌላ ፡ አደራ ፡ የለኝም ፡፡ አደራህን ፡፡ በኤርትራ ፡ ምድር ፡ የተከሰከሰው ፡ አጥንቴ ፡ በቁጣ ፡ እንዳይጮህ ፡ አደራ!›› ፡ ወዘተ ፡ የሚሉም ፡ መልዕክቶች ፡ ነበሩ ፡፡
‹‹የሚገርመው ፡ ነገር ፡ እኔ ፡ የማስተላልፈው ፡ መልዕክት ፡ አልነበረኝም ፡፡ ጨርሶም ፡ አላሰብኩበትም ፡ ነበር ፡፡ ስለሞት ፡ አስቤ ፡ አላውቅም ፡፡ የሙያዬ ፡ ባሕርይ ፥ ያለምንም ፡ ስጋትና ፡ ጭንቀት ፡ በማያቋርጥ ፡ ‹‹አሁን›› ፡ ሁኔታ ፡ ውስጥ ፡ የመኖር ፡ ልማድ ፡ አድሮብኛል ፡፡ ስለወደፊት ፡ ለምን ፡ ይታሰባል ? ትኩስ ፡ ዜና ፥ ትኩስ ፡ ሕይወት! ሞት ፡ ለኔ ፡ ምኔም ፡ አልነበረም ፥ ሆኖም ፡ አያውቅም ፡፡ ትኩስ ፡ ዜና ፡ ከማጣት ፡ አበቦችን ፡ ካለማየትና ፡ የቆንጆ ፡ ሴት ፡ እጅን ፡ ለመንካት ፡ ካለመቻል ፡ የበለጠ ፡ ስቃይና ፡ መለየት ፡ ምን ፡ ይኖራል ?! ሞት ፡ ትርጉም ፡ ሰጥቶኝ ፡ አያውቅም ፡፡ ምናልባት ፡ ዕድሜ ፡ ስላልተጫነኝ ፡ ይሆናል ፡፡ ሞት ፡ ሲቃረብ ፡ አሳቤ ፡ ምናልባት ፡ ሳይለወጥ ፡ አይቀርም ፡፡ አላውቅም ፡፡ አሁን ፡ ግን ፡ ሞት ፡ ሩቅ ፡ ሆኖ ፡ ነው ፡ የሚታየኝ ፡፡ ምን ፡ የሚያሰጋ ፡ ነገር ፡ አለ ?
‹‹ከሞትክ ፡ ሁለት ፡ ነገር ፡ ብቻ ፡ ያሰጋሃል — መንግሥተ ፡ ሠማያት ፡ ትገባለህ ፡ ወይም ፡ ገሃነብ ፡ ትወርዳለህ — እንዲህ ፡ ያለ ፡ ነገር ፡ ካለ ፡ ማለቴ ፡ ነው ፡፡ መንግሥተ ፡ ሠማያት ፡ ከገባህ ፡ ምንም ፡ የሚያሠጋህ ፡ ነገር ፡ የለም ፡፡ ገሃነብም ፡ ከወረድክ ፡ የሚያሠጋህ ፡ ነገር ፡ የለም ፡፡ ከጓደኞችህ ፡ ጋር ፡ እጅ ፡ ለእጅ ፡ ስትጨባበጥ ፡ ለሥጋት ፡ ጊዜ ፡ አይኖርህማ!›› የሚል ፡ ጥቅስ ፡ የት ፡ እንዳነበብኩ ፡ ቦታው ፡ ጠፋኝ ፡፡ ከከፍታ ፡ ነጥብ ፡ 1702 ፡ ሌላ ፡ የሚያሰጋኝ ፡ ነገር ፡ አልነበረም ፡፡ እሱም ፡ ቢሆን ፡ ምን ፡ ያሰጋል ? ይያዛል ፡ ወይም ፡ አይያዝም ፡፡ ይልቅ ፡ ጭንቀቴ ፡ ዜናውን ፡ እንዴት ፡ አድርጌ ፡ እንደማስተላልፍ ፡ ነበር ፡፡ ጭንቀቴ ፡ ምንድነው ? ዜናውም ፡ ቢሆን ፡ ይተላለፋል ፡ ወይም ፡ አይተላለፍም ፡፡ ነገ ፡ ምን ፡ ትርጉም ፡ አለው ? ሰው ፡ ለምን ፡ ይጨነቃል ? እውን ፡ ነገር ፡ አሁን ፡ ብቻ ፡ እኮ ፡ ነው ፡፡ አሁን ፡ አለሁ ፡፡ ደህና ፡ ነኝ ፡፡ እተነፍሳለሁ ፡፡ ውብ ፡ ኮኮቦች ፡ እቆጥራለሁ ፡፡ ይበቃል ፡፡ አሁን ፡ አለህ ፡ ወይም ፡ የለህም ፡፡ ጭንቀቱ ፡ ምንድነው ?
‹‹ . . . ሌሊት ፡ ሁለት ፡ ጊዜ ፡ ከእንቅልፍ ፡ ልቤ ፡ ቃዢቼ ፡ በመባነን ፡ ነቅቼ ፡ ነበር ፡፡ ሁለቱንም ፡ ጊዜ ፡ ላብ ፡ አስምጦኝ ፡ ነበር ፡፡ አንድ ፡ ጥይት ፡ በሔድኩበት ፡ እየተከታተለች ፡ ታባርረኛለች ፡፡ እንዳትመታኝ ፡ እሮጣለሁ ፡፡ ላመልጣት ፡ አልችልም ፥ ትደርስብኛለች ፡፡ ገደል ፡ አፋፍ ፡ ላይ ፡ እደርሳለሁ ፡፡ መሔጃ ፡ የለኝም ፡፡ እና ፡ ጥይቷ ፡ እየተወረወረች ፡ ትመጣብኛለች ፡፡ ባንኘ ፡ እነቃለሁ ፡፡ በሁለተኛ ፡ ጊዜ ፡ ደግሞ ፡ ከፍታ ፡ ነጥብ ፡ 1702 ፡ ላይ ፡ የወጣን ፡ ይመስለኛል ፡፡ ጠላት ፡ የለም ፡፡ ተራራው ፡ እንደ ፡ ሰው ፡ ልብ ፡ ሲመታ ፡ ይሰማኛል ፡፡ ቆይቶ ፡ የተራራው ፡ ትርታ ፡ አደንቋሪ ፡ ይሆናል ፡ ልቤ ፡ አብሮ ፡ ይሸበራል ፡፡ ነፍሴ ፡ ተጨንቃለች ፡፡ ተራራው ፡ ተጠምዶ ፡ እንደቆየ ፡ ቦምብ ፡ ድንገት ፡ ይፈነዳል ፥ ዓለም ይደበላለቃል ፥ ምጽዓት ፡ ይሆናል ፥ ጠርብ ፡ ድንጋዮች ፡ ሠማዩን ፡ ያለብሱታል ፡፡ እንደገና ፡ እያላበኝ ፡ እነቃለሁ ፡፡ . . .
‹‹ከመሰብሰቢያ ወረዳችን … ተነቃነቅን ፡፡ ቲክሲ ፡ ላይ ፡ ቶሎ ፡ ይነጋል ፡፡ ሮራ ፡ ጸሊም ፡ ላይ ፡ የንጋት ፡ ጸሐይ ፡ በሙሉ ፡ ድምቀቷና ፡ ውበቷ ፡ ስትወጣ ፡ ማየት ፡ እጅግ ፡ ያስደንቃል ፡፡ ተፈጥሮ ፡ ውብ ፡ የንጋት ፡ ትርዒት ፡ የምታሳይበት ፡ ቦታ ፡ ነው ፡ ለመጀመሪያ ፡ ጊዜ ፡ ከፍታ ፡ ነጥብ ፡ 1702ን ፡ ከሩቅ ፡ አየሁ ፡፡ የአካባቢው ፡ ትልቁ ፡ ተራራ ፡ ባይሆንም ፡ ከሌሎቹ ፡ ይልቅ ፡ ግርማ ፡ ሞገስ ፡ ተጎናጽፎ ፡ ታየኝ ፡፡ ቀጥ ፡ ብሎ ፡ ከምድር ፡ ወደ ፡ ሠማይ ፡ የተወረወረ ፡ ሹል ፡ ተራራ ፡ ነው ፡፡ … የቀይ ፡ እምቡጥ ፡ ጦር ፡ አባሎች ፡ በሙሉ ፡ አንጋጠው፡ ተራራውን ፡ በአድናቆት ፡ ይመለከቱ ፡ ነበር ፡፡ ፊታቸው ፡ ያበራል ፡፡ ያውና ፡ የመጨረሻ ፡ ግባቸው! የልባቸውን ፡ ትርታ ፡ የሰማሁ ፡ መሠለኝ ፡፡ እንደ ፡ እውነቱ ፡ ከሆነ ፡ ግን ፡ የራሴን ፡ የልብ ፡ ትርታ ፡ ነበር ፡ የማዳምጠው ፡፡
‹‹ኮሎኔል ፡ ታሪኩ ፡ ወደኔ ፡ ሲመጣ ፡ አየሁት ፡፡ አረማመዱ ፡ ሁሉ ፡ ፈጣንና ፡ ቀልጣፋ ፡ ሆኗል ፡፡ አዲስ ፡ ዩኒፎርም ፡ ለብሷል ፡፡ ተርብ ፡ መስሏል ፡፡
‹‹ዛሬ ፡ አምሮብሃል›› አልኩት ፡፡
‹‹የክት ፡ ልብሴን ፡ ነው፡፡ ብሎኝ ፥ ከሩቅ ፡ የሚታየውን ፡ ተራራ ፡ በዓይኖቹ ፡ ሲቃኝ ፡ ከቆየ ፡ በኋላ ፡ ‹‹ቆንጆ ፡ ተራራ ፡ ነው ፡፡ መቃብሬ ፡ እዚያ ፡ ላይ ፡ ቢሆን ፡ አይከፋኝም ፡፡ ለሰማይ ፡ ቅርብ ፡ ነው ፥ አይመስልህም?›› አለኝ፡፡
‹‹እኔስ ፡ ለመቃብሬ ፡ አዲስ ፡ አበባን ፡ ነው ፡ የምመርጠው ፡፡ ብዙ ፡ አበባዎች ፡ ያሉበት ፡ ቦታ ፡ ይሻለኛል›› አልኩት ፡፡
‹‹እኛ ፡ ይህን ፡ ተራራ ፡ መርጠናል›› አለኝ ፡፡
‹‹የሚሞትበትን ፡ ቦታ ፡ ማንም ፡ ሊመርጥ ፡ አይችልም ፥ ጀግኖችም ፡ ቢሆኑ›› አልኩት ፡፡
‹‹ደርሰናል ፡ እንግዲህ›› ብሎኝ ፡ ጦሩን ፡ ተከትለን ፡ ወደ ፡ ውጊያ ፡ ወረዳው ፡ እንዴት ፡ እንደምንሔድ ፡ አስረዳኝ ፡፡ ከጦሩ ፡ ኋላ ፡ መሆን ፡ ነበረብን ፡፡ …
‹‹አይዞህ ፥ ስለኛ ፡ አታስብ›› አልኩት ፡፡
‹‹እንድትሞቱ ፡ አልፈልግም ፡፡ የወሬ ፡ ስንቅ ፡ ይዛችሁ ፡ ብትመለሱ ፡ ይሻላል›› አለኝ ፡፡››
///// አበቃሁ///// አምላክ ኢትዮጵያን ይባርክ //// ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር //// ቻው ////
          — በዓሉ ግርማ፣ ኦሮማይ፣ ገጽ 315-319
Emahoy Maryam Guebrou:
Filed in: Amharic