>

ዝምታው እስከመቼ !... ለዶ/ር ዳንኤል በቀለ  የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር (ጋዜጠኛ መአዛ መሀመድ)

ዝምታው እስከመቼ!… ለዶ/ር ዳንኤል በቀለ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር

ጋዜጠኛ መአዛ መሀመድ
* ከደንቢ ዶሎ ዩንቨርስቲ ወደ ቤተሰቦቻቸው ሲመለሱ የታገቱ 17 ተማሪዎችን ሁኔታ ምን ላይ አደረሱት? 
*
ብዙዎቻችን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዬ የተባለው ተቋም አንባገነኑን ኢህአዴግ ለማሶገድ በተደረገው ትግል የገዥዎች ህገ ወጥ የዜጎች ግድያን አንዳንዴ በዝምታ ሲያልፍ ሌላ ጊዜ ለአንባገነኖች ድርጊት “ህጋዊነት” ምስክርነት ሲሰጥ እንደነበረ ብንረዳም እርስዎ ወደ ሃላፊነት ሲመጡ የተቋቋመበትን አላማ ይወጣል የሚል እምነት ነበረን።  የሆነው ግን እንደጠበቅነው አይደለም። የታገቱ ተማሪዎችን ጉዳይ በተመለከት ያሳዩት ቸልተኝነት ስላሳዘነን እኔና ጓደኞቼ በደብዳቤና በአካል ገልፀንልዎታል።
እርስዎም ቅሬታችንን ተቀብላው ዋናው ችግር በአካባቢው ያለው ሁኔታ እንደሆነና ጉዳዩን ግን ቸል እንዳላሉት ነግረውን ነበር። ነገር ግን እስከዛሬዋ እለት ድረስ የታገቱ ተማሪዎችን በተመለከተ ይህ ነው የሚባል ውጤት አልነገሩንም።
ኮሚሽነር አሁን ላይ የሚያሳብቡበት የፀጥታ ችግር እንደተቀረፈ መንግስት ነግሮናል። ያለዎትን መረጃ ለቤተሰቦቻቸውና ለህዝብ ያሳውቁ። ስራዎትን የማያሰራ አጠቃላይ ችግር ገጥሞዎት ከሆነም ከእዚህ ቀደም በደብዳቤ እንደገለፅንልዎ ስልጣንዎትን ይልቀቁ። ከታሪክ ተጠያቂነት ሊያመልጡ የሚችሉት በዚህ ውሳኔ ብቻ ነው።
የልጅን ነገር አውቀዋለሁ። በኮሮና ወረርሽኝ ምክንንያት ለጥንቃቄ በሚል ልጄን ከዘመድ ቤት እንድታድር ወስኜ ለመላክ እንዴት እንደተቸገርኩ ሳስበው ልጆቻቸው በህይወት ይኑሩ/አይኑሩ ሳያውቁ ለአራት ወራት የተቀመጡት የታጋች ቤተሰቦች ሁኔታ ለማሰብ ይዘገንነኛል።
እባክዎትን ስለ ተማሪዎቻችን የደረሱበትን ይንገሩን።
Filed in: Amharic