>
5:18 pm - Sunday June 15, 5958

የሐኪም አበበች ሽፈራው የምርምር ውጤትንና በማሕበራዊ ሚዲያዎች የሚሠራጨውን ወሬ በተመለከተ [መጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ]

የሐኪም አበበች ሽፈራው የምርምር ውጤትንና በማሕበራዊ ሚዲያዎች የሚሠራጨውን ወሬ በተመለከተ

️ እንደሚታወቀው በዓለም ላይ የተስፋፋው ገዳይ የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ 19) በመላው ዓለም 912,572 ሰዎችን የያዘ ሲሆን 45,541 ሰዎችን ገድሏል። ዓለምን ሁሉ ያስጨነቀ ይህን ወረርሽኝ ለመግታት ሁሉም ሀገራት የራሳቸውን ምርምር እያደረጉ ይገኛሉ።
️ ከአፍሪካም በጥንታዊ የሕክምና ዕውቀት ከፍተኛ የታሪክ ደረጃ ያላት ታላቋ ክብርት ሀገራችን ኢትዮጵያ ናት። ቀደምት ኢትዮጵያውያንም በዕፅዋት፣ በእንስሳት፣ በማዕድናት ውጤቶች ሕዝቡን ከማከምና መድኃኒት ከመቀመም ዐልፈው ዓለምን ያስደነቁ በተለይ በጀርመን ተወስደው የሚመረመሩ እነ መጽሐፈ መድኃኒትን፣ መጽሐፈ ዕፀ ደብዳቤ፣ መጽሐፈ አእባንን፣ የማከምያ ጠልሰሞችን መርምረው ጽፈው አልፈዋል።  በዋሽንግተን ዲሲ በካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ አሜሪካ እንኳን በዐይኔ ያየኋቸው ወደ 400 የሚጠጉ የመድኃኒት ዝርዝር የያዙ ጥቅሎች ናቸው። እስከ ዶክትሬት ደረጃ እንደሚጠኑም አውቃለሁ።
️ ከእኛ ተወስደው ሌላውን ዓለም ሲያበለጽጉ እኛ ኢትዮጵያውያን ግን በዘመናዊ መልኩ እንደነርሱ የራሳችንን ንብረቶችና ዕውቀቶች እንዳንመረምራቸው እንዳናጠናቸው ሆን ተብሎ የተንኮል ደባ በመደረጉ የባህል ሕክምና ዐዋቂዎች ክፉ ስም እንዲሰጣቸው፣ ዕውቀታቸውም እንዳይስፋፋ ሲደረግ ኖሯል። ይኼ የራስን ዕውቀት የማስጣል ሤራ እንደ እኛ ለምሳሌ ቻይናውያን ላይም ቢደርስባቸውም በሀገር ፍቅርና በአመራራቸው ጥንካሬ ፈተናውን ተቋቁመውት የእራሳቸውን የባህል ሕክምናን ከዘመናዊው ጋር አጣምረው ታላቅ ደረጃ ላይ አድርሰውታል። ይልቁንም በዚህ ታላቅ ወረርሽኝ የቻይና የባሕል ሕክምና ጠበብት ከዘመናዊው ጋር ተቀናጅተው ታላቅ ሥራን ለሀገራቸው እያበረከቱ ይገኛሉ።
️ በተለያየ ጊዜ ወረርሽኝ ተከሥቶ ሕዝብን በሚያጠቃ ጊዜ ቀደምት የኢትዮጵያ ሊቃውንት ሕዝቡን ከአደገኞች ቫይረሶች ያክሙ እንደነበር የሚታወቅ ሲሆን ይኽን ዕውቀት ጠንቅቀው የሚያውቁት የኢትዮጵያ የሕክምና ሊቃውንት ለእዚህ ገዳይ ቫይረስ  የነበረውን ለሀገራችን አበርክተዋል። በዚህም ከፍተኛ ምስጋና ሊቀርብላቸው ይገባል። ሀገር የምትፈልገው የወሬ ኤክስፐርቶችን ሳይሆን ያላቸውን የሚያበረክቱላት ሕዝቡን በችግሩ የሚደርሱለትን ብቻ ነው።
️ በዚህ ዙርያ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር ኢንጂ.)፣ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ እንደገለጹት የኮሮና ቫይረስን በሳይንሳዊ ምርምር በተደገፈ የሀገር በቀል እውቀት ከዘመናዊ ሳይንስ ጋር በማቀናጀት ቫይረሱ ለማከም የሚያስችል የመድኃኒት ምርምር የመጀመሪያ የቤተ ሙከራ መሠረታዊ የምርምር ሂደትንና ተደጋጋሚ የቤተ ሙከራ ሞዴሊንግን በስኬት እንዳለፈ ገልጸዋል፡፡
️ የመጀመሪያ ምርምር ሂደትን በተገቢው መንገድ አልፎ ቀጣይ የእንስሳት ፍተሻ እና ክሊኒካል ፍተሻ ሥራዎች እንዲሸጋገር መደረጉን ገልጸዋል። ይህም በመንግሥት መደረጉ ታላቅና ሀገርን የሚያኮራ መሆኑን ሳናደንቅ አናልፍም።
️ መድኃኒት ተሠርቶ ለሕሙማን እስኪደርስ የግድ የሚያልፍባቸው ዓለም ዐቀፍ ሕጎችን ሊያልፍ ግድ ነውና ሌሎች ተጨማሪ የምርምሩ ሂደት መረጃዎችንም በቀጣይ የሚገለጽ መሆኑን የኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በፌስቡክ ገጹ ላይ ጽፎልናል።
️ ይህ እንዲሳካ ሁላችንም መጸለይ፣ በጎ መመኘት ሲገባ አንዳንዶች ግን በዚህ ገዳይ ወረርሽኝ ጊዜ እንኳ የፌስቡክ ሰው ለማብዛት ሲሉ የሐሰት ፌስቡክ ግሩፕ እየከፈቱ ሐኪም አበበች ሽፈራው ያላሉትን እየጻፉ ሰውን እያሳሳቱ መገኘታቸው ለዚህ መሳካት ጊዜያቸውን ዕውቀታቸውን እየሰጡ ያሉትን እያሳዘነ ይገኛል። ይልቁኑ ይህ የሐሰት ወሬ ፈጥራችሁ የምታሠራጩ ወገኖች እባካችሁን ይህ ድርጊታችሁ ተመራማሪዎችን ወደ ኋላ እንዳይጎትታቸው ማሰብ ያስፈልጋል።
️ ሐኪም አበበች ሳይሉ በሐሰት የተሠራጩ ብዙ ጉዳዮች ውስጥ ቫይረሱ ወደ ባሕር ውስጥ ከገቡት አጋንንት ካሠጠሟቸው አሣማ ነው ብለዋል የሚልና ሌሎች ውሸቶችን እየፈበረኩ የውሸት ዜና የሚያሠራጩ አሉና ከዚህ የሐሰት ወሬ በጣም መጠንቀቅ ያስፈልጋል።
️ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ብቻ የተሞከረው ሙከራ በሚመለከታቸው አካላትና በሐኪም አበበች ሽፈራው ብቻ በሕጋዊ ሚዲያዎች የሚገለጽ ሲሆን ከዛ ውጪ በየሚዲያው፣ በየፌስቡኩ የሚጻፈው ሁሉ እርሳቸውን የማይወክልና እርሳቸውም ያላሉትና የማያውቁት እንደሆነ ገልጸዋል።
️ መድኃኒቱ ተዘጋጅቶ ለአገልግሎት እስኪበቃ ድረስ ግን በሕመሙ የሚጠቁ ኢትዮጵያውያን ሕይወታቸው እንዳያልፍ ከባሕል መድኃኒት ሊቃውንት ጋር ተቀናጅቶ በሀገር ውስጥ በፍጥነት እንዲረዱ እንዲያገግሙ የሚቻልበትን ሁኔታ ግን መንግሥታችን ያስብበታል የሚል እምነት ያለን ሲሆን ሁላችንም ለዚህ መሳካት ልንጸልይበት ይገባል በማለት ጽሑፌን አበቃለሁ።
Filed in: Amharic