>
5:18 pm - Friday June 15, 4564

ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ የጀመራቸውን መልካም ስራዎቹን በማስቀጠል ዘላለማዊ እናድርገው!!! (አለማየሁ ገመዳ)

ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ የጀመራቸውን መልካም ስራዎቹን በማስቀጠል ዘላለማዊ እናድርገው!!!

 

 

አለማየሁ ገመዳ
የቱ ጋር መጀመር እንዳለብኝ አላውቅም። ትግል ነው ይህንን መፃፉ እራሱ። ቴዲን ለመጀመሪያ ጊዜ ያገኘሁት የዛሬ 10 አመት ገደማ ነበር – ስልክ ደውሎልኝ። በወቅቱ ለአትላንታ ከተማ አዲስ ነበርኩና፣ “ወደ ከተማችን እንኳን ደህና መጣህ። አውሮፓ መሆንህን ነበር የማውቀው። እዚህ ካለህማ አብረን ብዙ ስራዎችን መስራት እንችላለን።” በማለት ነበር መልካም ስሜት እንዲሰማኝ በ ማድረግ በስልክ ያናገረኝ።
 በኋላ የአድማስ ሬድዮ እንግዳ እንድሆን ጠይቆኝ ግብዣውን ተቀብዬ ስቱዲዮ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ በአካል ተገናኘን። በወቅቱ ሚዲያ ላይ ስቀርብ የመጀመሪያዬ ስለነበር ትንሽ ፈራ ተባ ብዬ ነበር። ቴዲ ግን ቀለል እንዲለኝ ነበር ያደረገው – ጨዋታው፣ ወንድማዊ ለዛው፣ እንዲሁም ከምንም በላይ ለማህበረሰባችን ያለውን ወገናዊነት ወዲያው ነበር የተረዳሁት። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ከቴዲ ጋር በስልክም ይሁን በአካል፣ በተለያያ አጋጣሚ በተገናኘን ቁጥር ‘boss’ እያለ ነበር የሚጠራኝ። የሆነ አበረታች ስሜት ነበረው አጠራሩ፤ የሆነ “በርታ ወንድሜ፣ በምትሰራው ሁሉ እኮራብሃለሁ!” የሚል ወንድማዊነት። አድማስ ሬዲዮ እንዲሁም ድንቅ መጽሄትን አትላንታ በነበርኩባቸው አመታት የተለያዩ መረጃዎችን ስለ ማህበረሰባችን ለማግኘት ሁሌም ብቸኛ አማራጭ እንደነበሩ አስታውሳለሁ።
ቴዲ አንድ ኢትዮጵያዊ ወገን ላይ ጉዳት ደረሰ ወይም ድጋፍ ያስፈልጋታል/ያስፈልገዋል ከተባለ ሁሌም ግንባር ቀደም ሆኖ ለሁላችን በጎነትን ሲያስተምር አስታውሰዋለሁ። በአንድ ወቅት “አንድ ሀበሻ እዚህ ስቴት ሞት፤ የሆነ ሀበሻ ደግሞ እዚህ ስቴት ጉዳት ደረሰበት የሚሉ ዜናዎችን ብዙ ጊዜ ስትሰራ በጣም ነው የሚገርመኝ” አልኩት። ምላሹም፣ “እኛ ካልሰራነው ማን ይስራው?”  የሚል ነበር።
” ቴዲ የመፍትሄ ሰው ነበር። ችግር ሲከሰት ስለችግር ዝም ብሎ ከማልቀስ ይልቅ፣ “ምን እናድርግ? እንዴት እንተባበር? ምን እናቋቁም?” የሚሉ መፍትሄ-ፈላጊ ሀሳቦችን ሲያቀርብ አውቀዋለሁ።
የዛሬ 7 አመታት ገደማ ሳውዲ አረቢያ ወገኖቻችን ላይ ደርሶ የነበረውን አስከፊ ግፍ ለመቃወም ተካሂዶ የነበረው ሰልፍ የተሳካ እንዲሆን ትልቅ ሚና ነበረው። ነገር ግን እጅግ የሚያስገርመው ነገር፣ ይህንን ለወገኑ ድምጽ ለመሆን የተዘጋጀ ሰልፍ ሲያስተባብር እንዲሁም በስፍራው ሲገኝ፣ የእናቱን ሞት ከሰአታት በፊት ተረድቶ ነበር። በወቅቱ ማመን ነበር ያቃተኝ። ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? የምል ጥያቄ ፈጥሮብኝ ነበር፤ ነገር ግን ሳናግረው ገባኝ – “ብቻዬን በእናቴ ሞት ከማዝን፣ ሀዘን ላይ ከሚገኘው ህዝብ ጋር አብሬ ባዝን ይሻለኛል ብዬ ነው ሰልፉ ላይ የተገኘሁት” ነበር ያለኝ።
 መቼም አልረሳውም ያንን ክስተት። ለሀገሩ፣ ለወገኖቹ የነበረው ተቆርቋሪነት ሰው ላይ የሚጋባ ነበር። ቴዲ አትላንታ ውስጥ ኢትዮጵያውያን በህብረት በሚያደርጓቸው በጎ ነገሮች፣ አብዛኞቹ ላይ አሻራውን ጥሏል ብል ማጋነን አይመስለኝም። ቴዲ ባሳለፍነው ቅዳሜ የሬዲዮ ስርጭት በማድረግ ላይ እንዳለ ድንገት ወድቆ ሆስፒታል መግባቱና፣ በኤምሪ ዩንቨርሲቲ ሆስፒታል ሀኪሞች ህይወቱን ለማትረፍ እየጣሩ እንደሆነ ስሰማ የተሰማኝ ድንጋጤ የተለየ ነበር።
ይህንንም ተከትሎ እሱን ለመርዳት በተከፈተው GoFundMe ወገኖች እንዴት እንዴት እንደተረባረቡ፣ የተለያየ እምነት ተከታዮች በስልክ ተገናኝተው ለቴዲ መፀለያቸውን ለሰማ ሰው ስለቴዲ ማንነት ግሩም መገለጫ እንደሆነ ልብ ይላል። ጊዜው ተሰብስቦ ለማዘን የሚመች አለሆነምና ሀዘን ባሉበት መወጣት ግድ ሆኗል። ለቴዲ ቤተሰቦች፣ ለጓደኞቹ እንዲሁም በስራው ለምታደንቁት ሁሉ የተሰማኝን መሪር ሀዘን እገልፃለሁ። ሁላችሁንም እግዚአብሄር ያፅናናችሁ። ቴዲ የጀመራቸው ወይም ያስጀመራቸው አልያም የተሳተፈባቸው በርካታ በጎ ስራዎች አሉ – አድማስ ሬዲዮ፣ ድንቅ መጽሄት፣ We Care Atlanta እንዲሁም ሌሎች ስራዎችን የቴዲን የበጎነት፣ ለወገን ተቆርቋሪነት ይዘው እንዲቀጥሉ በማድረግ ህይወቱን celebrate ማድረግ የሚገባ ይመስለኛል። ህይወት እንዲህ ናት ወገኔ፤ አለሁ ስትል የለህም። ለሌሎች መልካም ሆነን፣ በጎ አስበን፣ በጎ አድርገን፣ የሌሎች ደስታ ምክንያት ሆነን እንለፍ።
ውድ ቴዲ፣ ላሳየኸኝ መልካም ወንድምነት ከልብ አመሰግናለሁ። ስለ አርአያነትህ አክብሮቴን እገልጻለሁ።  ነፍስ ግን ይማረው ወዳጄ።
Filed in: Amharic