>

ኮቪድ-19 እና ዓለም፦ ከተነበቡ አሳዛኝ፣ አስገራሚ ዜናዎች...!!! (ሳምሶም ጌታቸው)

ኮቪድ-19 እና ዓለም፦ ከተነበቡ አሳዛኝ፣ አስገራሚ ዜናዎች…!!!

 

ሳምሶም ጌታቸው
ቻይና በባህላዊ መንገድ በሚዘጋጅ አንድ መድኃኒት የኮሮናቫይረስ ፅኑ ህሙማንን ማከም እንዲቻል ፈቃድ ሰጥታለች። መድኃኒቱ የሚዘጋጀው ድብ ከተባለው ግዙፍ እንስሳ ሀሞት፣ ከተፈጨ የፍየል ቀንድ እና ሌሎች 3 ዕፅዋት ነው ተብሏል። ርምጃው ፕ/ት ዢንፒንግ ባህላዊ መድኃኒቶችን ማስተዋወቅና ከዘመናዊው ህክምናው ዕኩል መጠቀም ያስፈልጋል ብለው የተናገሩትን ተከትሎ ነው። የእንስሳት መብት ተከራካሪዎች ግን በነገሩ ተቆጥተዋል። ድቦችን የሚያስፈጅ ውሳኔ ነው በሚል። ከጥንት ጀምሮ ድብ በእሲያ ሀገራት ለመድኃኒትነት በእጅጉ የሚፈለግ እንስሳ ነው። እንደሚባለው ከሆነ እግሮቹ፣ ጥርሶቹና ሀሞቱ በባህል ሀኪሞች ዘንድ በእጅጉ ይፈለጋል። በዚህም ምክንያት በቀዳሚ ዘመናት ድብ ለሀሞቱ ሲባል ይገደል ነበር። እ.አ.አ ከ1980 ዓ.ም ወዲህ ግን የድብ ሀሞት “ግብርና” በቬትናምና ቻይና በሰፊው የተለመደ ስራ ሆነ። ያ ማለት ድቡ ሳይሞት በቁሙ ሃሞቱን እየመጠጡ ለፈለጉት የመድኃኒት ስራ ማዋል ተቻለ። እንደሚባለው በድብ ሃሞት የሳምባ ምቺና የመንተፈሻ አካላት ህመሞች በቀላሉ ይፈወሳሉ። በዚህም የተነሳ ይህ የድብ ሃሞት መድኃኒት ኮቪድን ለመፋለም ተስፋ ተጥሎበታል። ቻይና በሰሞኑ ጥረቷ የቫይረሱን ተጠቂዎች ለማከም ባህላዊውን መድኃኒቶች ከዘመናዊው ማጣመሯ ነው የተነገረው።
                  ◊◊◊◊◊
ግብፆች የሀገሪቱ ቤተመንግስት ከውጭ ለሚመለሱ ዜጎች ማቆያነት እንዲውል የሚጠይቅ የትዊተር ዘመቻ ጀምረዋል ተባሏል። ሃሳቡ የተነሳው ከውጭ የሚመለሱ የሀገሪቱ ዜጎች በለይቶ ማቆያ እንዲቀመጡ ሲደረግ ወጪያቸውን ማን ይሸፍን በሚል ሙግት ነው። መንግስት በቅርቡ ከውጭ የተመለሱ ዜጎችን ሰብስቦ ሳያማክራቸው በባለ 5 ኮከብ ሆቴል ካስቀመጣቸው በኋላ ድንገት ወጪያችሁን ግን ራሳችሁ ሸፍኑ ማለቱ ቁጣ ቀስቅሷል። በዚህም ምክንያት የአል ሲሲ ቤተመንግስት [የሕዝብ ንብረት ነውና] ለይቶ ማቆያ ይሁንልን የሚል ዘመቻ ተጧጡፏል። ነገሩ ያላማራቸው ፕ/ት ሲሲ የመንግስታቸውን ውሳኔ ቀልብሰው ተመሳሳይ ወጪዎችን የሚሸፍን አንድ ፈንድ ማቋቋማቸውን አሳውቀዋል።
                  ◊◊◊◊◊
ሩሲያ ለአሜሪካ 60 ቶን የሚመዝን የህክምና ቁሳቁሶችን “በዕርዳታ” ልካለች። ፕ/ት ፑቲን፣ ከፕ/ት ትራምፕ ጋር በስልክ በተነጋገሩበት ጊዜ አሜሪካን ከኮቪድ-19 ጋር ለምታደርገው ጦርነት ሩሲያ በህክምና ቁሳቁሶች ለመርዳት እንደምትፈልግ ገልፀው፣ አሜሪካ እሺ እንድትላቸው ጠይቀዋል። ነገሩን የሰሙት ትራምፕም ሃሳቡን ተቀበሉት። ሆኖም ግን የተባለው የህክምና ቁሳቁስ በጦር ጄት ተጭኖ አሜሪካ ከደረሰ በኋላ በሁለቱም ሀገራት ዜጎች መካከል ቅሬታና ትችት አስከትሏል። አሜሪካኖቹ “ትራምፕ የዚያችን ምን እንደምታስብ የማትታወቅ አደገኛ ሀገር አካኼድ ሳይመረምር እንዴት እርዳታዋን ይቀበላል?” ሲሉ፤ በሩሲያ በኩል ያሉ ዜጎች ደግሞ መንግስታቸውን በጉረኝነት ይከሳሉ። የቫይረሱ ስርጭት በተስፋፋበት በዚህ ሰአት የሀገራችን ሀኪሞችም በቂ የህክምና አልባሳትና ቁሳቁሶች ሳያገኙ፣ ፑቲን ለታይታ ብሎ ነው ለአሜሪካ ዕርዳታ የሰጠው ሲሉ ይወቅሷቸዋል። ትራምፕ ስለተደረገው ድጋፍ ሩሲያን አመስግነው እያለ፣ ስለ ጉዳዩ የተጠየቁት ማይክ ፖምፔዎ “የምን ዕርዳታ ነው የምታወሩት? ቁሳቁሱን ያገኘነው ተገቢውን ክፍያ ከፍለን ነው” ብለው ነገሩን ሁሉ ለሰሚ ግራ አድርገውታል።
                      ◊◊◊◊◊
የፊሊፒንሱ አምባገነን ፕ/ት ሮድሪጎ በቴሌቪዥን ቀርበው፣ የኮሮናቫይረስን ለመከላከል በሚል መንግስት ያሳለፈውን ከቤት ተዘግቶ የመቀመጥ መመሪያ የማያከብሩ ዜጎች በጥይት ተጠብሰው እንደሚጣሉ አስጠንቅቀዋል። ፕ/ቱ ንግግራቸውን በመቀጠልም ወረርሽኙ እጅግ ወደ አደገኛ ደረጃ እየደረሰ ነው። ሰው ሲግራችሁ ለምን አይገባችሁም?” ሲሉ ሕዝባቸውን ተቆጥተዋል። በመቀጠልም ፖሊሶችና ወታደሮች ከዛሬ ጀምሮ ይህን መመሪያ ለማክበር የሚያመነታ ውርጋጥ ካጋጠማችሁ በጥይት ድፉልኝ!” ሲሉ አዘዋል። እንዲህ ላለው የፕ/ቱ ቁጣ መነሻ የሆናቸው ከቤት አትውጡ የሚለውን ትዕዘዝ ተከትሎ በከተማዋ ማኒላ የሚገኙ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች፣ በመንግስት በቂ የምግብ ድጋፍ እየተደረገልን አይደለም በሚል ለተቃውሞ አደባባይ ከወጡ በኋላ ነው።
                      ◊◊◊◊◊
ቻይና የህክምና ማስክ ነው ብላ የወረደ ጥራት ያለው ጨርቅ ነው የሸጠችልን ሲሉ የከሰሷትን አንዳንድ የአውሮፓ ሀገራትን ወቀሳ አስተባብላለች። ብዙ ዓይነት የጥራት ደረጃ ያለውና ለተለያየ ዓላማ የሚውል ማስክ አለ። ራሳችሁ ስትገዙ ጥንቃቄ ማድረግ ነበረባችሁ። ለምሳሌ ሆላንዶች የገዙንን ማስክ እና ያቀረቡብንን የጥራት ደረጃ መጓደል መርምረናል። ችግሩ የራሳቸው ነው። እነሱ ሲገዙ ያዘዙትና የከፈሉት ለህክምና አገልግሎት ለማይውለው ማስክ ነው። ለዚህ ማረጋገጫ ሁሉም ግዥና ሽያጭ የተካኼደባቸው ሰነዶች በእጃችን ይገኛሉ። ይሄንኑ ማስክ ለህክምና ለመጠቀም ስለሞከሩ ችግሩ እሱ ነው። ለማኛውም ተመሳሳይ ወቀሳዎች ከቀና ልብ በመነሳት ካልቀረቡ የገጠመንን አደገኛ ዓለምዓቀፍ ወረርሽኝ ለመቋቋም ያዳግተናል። እኛ የራሳችንን ችግር አቃለን፣ ቀሪውን የዓለም ሀገራት ለመርዳት ሌት ተቀን ደፋ ቀና ስንል በውሃ ቀጠነ፣ ንትርክ ውስጥ ባታስገቡን ጥሩ ነው ስትል ቻይና አሳስባለች።
                      ◊◊◊◊◊
በብዙ መከራ ውስጥ እያለፈች ባለችው ጣሊያን የምትኖር አንዲት ዩጋንዳዊት ተማሪ፣ እሷና ጓደኞቿ በረሃብ ከማለቃቸው በፊት የሀገሯ መንግስት እንዲደርስላቸው በለቅሶ ታጅባ ጥሪ አቅርባለች። ጣሊያን የምግብ ዕገዛ የምታደርገው ለዜጎቿ ብቻ ስለሆነ እኛ አስታዋሽ አላገኝንምና ድረሱልን ብላለች። የዩጋንዲ መንግስት ቤት ተዘግተው እንዲሰነብቱ ካዘዛቸው ዜጎቹ መካከል 1.5 ሚሊየን ችግረኞቹን ለይቶ 6 ኪሎ የበቆሎ ዱቄት፣ 3 ኪሎ ባቄላና ጨው እያከፋፈለ ነው። ለህመምተኞችና ጡት ለሚያጠቡ ዜጎች ደግሞ 2 ኪ.ግ ዱቄት ወተት እና 2 ኪ.ግ ስኳር ያከፋፍላል። እናም በጣሊያን የምትገኘው ተማሪ ይህንን መረጃ በመጥቀስ እኛንም መንግስታችን ይድረስልን ብላለች።
                   ◊◊◊◊◊
ከየመረጃዎቹ፣ ከየመልዕክቶቹ የሚጠቅመንን እንዴት እንለያለን? ከዓለም ኃያላን ሀገራቱ የእርስ በርስ ትንንቅ ምን እናስተውላለን? ከአፍሪካ ሀገራቱ የተሻሉ ርምጃዎችን እንዴት እንኮርጃለን? መረጃዎችን እንመርምር፣ መመሪያዎችን እናክብር። ማኅበራዊ ርቀታችንን እንጠብቅ፣ እጃችንን እንታጠብ።
Filed in: Amharic