>

ኮረና በምንቀባበለው ብር ይተላለፋል? ሶማሌ ላንድን መጠየቅ ነው! (ደረጄ ደስታ)

ኮረና በምንቀባበለው ብር ይተላለፋል?

ሶማሌ ላንድን መጠየቅ ነው!

 

ደረጀ ደስታ
አንተ ብቻ ብሩን ስጠኝ እንጂ..አይባል ነገር መከራ ነው። ባለሙያዎች አንድ ነገር ቢሉበት ጥሩ ነው። እስከዚያው ጎረቤታችንን ሶማሌ ላንድን እያነበብን እንቆይ። እንግዲህ ከሶማሊያ ተለይታ ራሷን የቻለች አገር አይደለች የራሷ ገንዘብ አላት። ያው ሽልንግ ነው። በአንድ ዶላር ሲመታ 585 አካባቢ ሽልንግ ይወጣዋል። አንድ ሺ ዶላር ሲሆን አስቡት- ያን ሁሉ ማን ተሸክሞ ይሄዳል? ኢትዮጵያ ውስጥም አንዳንድ ባለጸጎች ሰብሰብ ያለ ሰው ሲጋብዙ ከምግቡ ውድነት በላይ የሚሽከሙት ብር ብዛት ያናድዳቸዋል ይባላል።
 ሶማሌ ላንድ ግን ከዚህ ስጋት ተገላግላለች። አብዛኛው ሰው እሚጠቀመው ኢንተርኔት እንደልብ በመሆኑ ስልኩን እየመዘዘ መክፈል ነው። ሶማሌላንዶቹ ጸጉራቸውን ቢቆረጡ፣ ከታክሲ ቢቀመጡ፣ ቢበሉ ቢጠጡ፣ ቢቀበሉ ቢሰጡ፣ ሁሉ ነገር በሞባይል ስልካቸው ነው። የቻልከውን ተጠቀምበትና ሲደክምህ ተወው፣ እሚባለው ኢንተርኔት ( “አንሊምትድ ዳታ”) በወር አስራ አምስት ዶላር ብቻ ነው እሚያስወጣው። 5 ዶላር እሚያወጣም እሚበቃውን ያህል የኢንተርኔት ዳታ ያገኛል። ቤትክራይ መክፈል፣ ገንዘብ ለወዳጅ ዘመድ መላክ ቢያስፈልግ ስልክና ስልክ ቁጥር ካለ ምን ችግር አለው? አገሪቱ ጠቅላላ ኢኮኖሚዋ እሚንቀሳቀሰው በሞባይል ነው ተብሏል። ኢንተርኔት ከኮረና ባያድንም ብር የመቀባበልን ያህል ላያጋልጥ ይችል ይሆናል። በተለይ አንዲት ነገር ብድግ ለማድረግ እሚወጣው ብር ብዙ ከሆነ ከባድ ነው። ጠፍታ ጠፍታ በስንት አንድ ጊዜ እምትመጣ ብር ግን ኮረና ቫይረሱን ይዛ ባትመጣ ጥሩ ነበር። በዚህ አጋጣሚም ሁኔታዎች ቢለወጡም መልካም ነው። በሞት የተከፈለ ዋጋ ካለ የሚያስገኘው ጥቅም ቢገኝ ምን ነበረበት? (ፎቶውን ያገኘሁት ከቢቢሲ ነው)
Filed in: Amharic