>

የአንድ ተነሳሒ ጸሎት!!! (በዲያቆን ብርኃኑ አድማሱ)

የአንድ ተነሳሒ ጸሎት!!!

 

 

በዲያቆን ብርኃኑ አድማሱ
              ጌታ ሆይ ስንበድልህ ኖረናል፤ አሁንም እየበደልንህ ነው፤በሚ ታወቀን በድለንሃል እንላለን እንጂ፦በማይታወቀን ደግሞ ምን ያህል እንኳ እንደበደልንህ የምታውቀው አንተ ብቻ ነህ፡፡አሁን ግን ከሁሉም ጊዜ በላይ እየተፈተንን ነውና መውጫውን ስጠን፡፡እሥራኤል በመሥዋ ዕቱ ሳይቀር ሲበድሉህ በኢሳይያስ አድረህ፦”የመሥዋዕታችሁ ብዛት ለእኔ ምን ይጠቅመኛል? ይላል እግዚአብሔር፥የሚቃጠለውን የአውራ በግ መሥዋዕትን እና የፍሪዳን ስብ ጠግቤያለሁ፤የበሬና የበግ ጠቦት ፥የአውራ ፍየልም ደም ደስ አያሰኘኝም፤” ኢሳ፡፩፥፲፩።ብለሃቸዋል።ዳግ መኛም፦”ዓመት በዓላችሁን ጠልቼዋለሁ፥ተጸይፌውማለሁ፥የተቀደሰ ውም ጉባኤያችሁ ደስ አያሰኘኝም፤”አሞ፡፭፥፳፩።ብለህ ካስነገርህ በኋላ፦መሥዋዕት ወደማይሠዉበት ግዞት አንደላክሃቸው፤በእኛስ ላይ  ይህን ሁሉ ያመጣህብን፥በቅዳሴያችን በውዳሴያችን ጊዜ በምንፈጽ መው ግድፈትና ኃጢአት ይሆንን?
              በእውነት እኛ አንተን ያልበደልንበት ቦታና ጊዜ የት አለ? አንዳ ንዶቻችን አጸደ መቅደስህን ለሌላ  ዓላማ ተቃጠርንበት፤አንዳዶቻችን ውሰጥ ድረስ ገብተን ተነታረክንበት፥ተደባደብንበት፤አንዳንዶቻችን ከአ ንተ ከምናገኘው ጸጋ ይልቅ መቅደሱ የእኔ ነው፥የእኔ ነው በማለት ጠበቃ ይዘን ለዐመታት ተሟገትንበት፡፡አንዳንዶቻችን በነጠላችን ውስጥ ሆነን ሰለማዊ ሰልፍ ወጣንበት፡፡አንዳዶቻችንም ሰው የማያው ቃትን ኃጢአት ሠራንበት፡፡አንዳንዶቻችንም ሐፍረት ጥለን ቤተ መቅደስ ህን የፋሽን ውድድር በሚመስል ሁኔታ ተኵነሰነስንበት፡፡መቅደስህ ውስጥ ሳይቀር በስልካችን አሽካካንበት።አንዳንዶቻችንም የውበት ሳሎን አስመሰለነው፡፡በዝማሬው፥በልብሱ፥በስብከቱና በሌላውም አገ ልግሎት ከአጥቢያ አጥቢያ ተፎካከርንበት፡፡አገልጋዮችህም ጸጋ ለማ ካፈል ከሮጥነው ይልቅ ገንዘብ ለመሰብሰብ የሮጥነው በለጠ፡፡ለድኅነ ታቸው ሳይሆን ለገቢያችን ስንል ምእመናንንም እንደጠፍ ከብት ነዳና ቸው።እንደ ምርኮም ተካፈልናቸው፡፡በአንድ መቅደስ በአራት በአምስት ጻድቅ ስም ታቦት የምንደራርበውም፦ሰዉ ወደ ሌላ ቤተ ክርስቲያን እን ዳይሄድና ለእኛ ደብር ብቻ ገንዘቡን እንዲሰጥ ከመፈለግ እንጂ ለበረ ከት አይደለም።ይህንንም፦እንኳን አንተ ልብንና ኩላሊትን የምትመረም ረው ቀርቶ፥አንዳንድ ምእምናንም ታዝበው በትዕግሥት ትተውናል፡፡ በዐመት ከዐራት እስከ አምስት ታቦት በየምከንያቱ የምናነግሥበትንም ምክንያት ዛሬ ሁሉም አውቆታል።እንኳን በሌላው ጊዜ፦በዐቢይ ጾም እንኳ የምናደርገው ድለቃና ዳንኪራም አንተን ሳይሆን የእኛኑ ስሜት ለማርካት እንደሆነ ልባችን ያውቀዋል፡፡እንዲያውም ዝም ካልከን፥ከኮ ረና ያለፍንበት ብለን አዲስ ንግሥም ልንጨምር እንችላለን፡፡ አቤቱ ስን ቱን ታገሥከን?
        በዐውደ ምሕረትህ ቆመን፥በሌላው መቅደስ የተሰየመውን ካህን እያሽሟጠጥን ስንቱን ተናገርንበት፡፡ፖለቲካዊ ስሜቶቻችን ከሌላ ቦታ ይልቅ በቤተ መቅደስህ ተሰበከ፡፡ስለአንተ መድኅንነትና ጸጋ ከምንናገር ይልቅ፦እኛ በግል የወደድናቸውን ያንተ መልእክተኞች እንደሆኑ፥በግል የጠላናቸውን ደግሞ አንተ የረግምሃቸው እንደሆኑ አድርገን ስናቀርብ ስቅቅ አይለንም ነበር።ኧረ እንዲያውም አንተ በጆሯችን ሹክ እያልከን የምንናገር እንመስል ነበር፡፡በዚህና በመሳሰለው አዝነህብን ይሆን፥ ከቤተ መቅደስ እንደ ቀድሞው የማንሰበሰብበትን ጊዜ ያመጣኸው? በዚህስ ጉዳይ ማነው አፉን ሞልቶ ሊናገር የሚችል ጻድቅ? ለዘላለም ያልዘጋህብንም በእውነት ቸር ብትሆን ነው፡፡
              አዎን ጌታ ሆይ! እንደ በደላችንማ ከሆነ እንኳን ይህን ሌላስ ብታመጣ ይገባን የለምን? “የእግዚአብሔርን ልጅ የረገጠ፥ያንንም የተ ቀደሰበትን የኪዳኑን ደም እንደ ርኵስ ነገር የቆጠረ፥የጸጋውንም መን ፈስ ያክፋፋ፥እንዴት ይልቅ የሚብስ ቅጣት የሚገባው ይመስላች ኋል?”ዕብ፡፲፥፳፱።ስትል በቅዱስ ጳውሎስ እንደ ነገርከን፥ለኦሪቱ መሥ ዋዕት መርከስ ቀንተህ፦በእሥራኤል ላይ፦ለሰበዓ ዐመት ቤተ መቅደስ የማያዩበት፥መሥዋዕት የማይሠዉበት፥ምስጋና የማያቀርቡበት፥በዓል የማያከብሩበት ስፍራ ፋርስ ባቢሎን አውርደህ ከቀጣሃቸው፥እኛንማ አማናዊው የአንተ ሥጋና ደም በሚፈተትበት ቤተ መቅደስህ፦ያን ሁሉ ኃጢአት፥ፌዝና ግደየለሽነት፥የታይታ፥የይስሙላና የግብር ይውጣ አድር ገን በምንፈጽመው ነገር ብትቀጣን፥እንኳን በዚህች ቁንጥጫ መገሠጽ ቀርቶ፥እንደ ዳታን እና እንደ አቤሮን እንዳለ ከነሥጋችን ሲኦል እንኳ ብታ ወርደን ቢያንስብን እንጂ መች ይበዛብናል፡፡ነገር ግን ጌታ ሆይ! አንተ መሐሪና ይቅር ባይ ነህና፥በድፍረት የምናጠፋውን ሳይሆን በፈሪሃ እግ ዚአብሔር ሆነው ርደውና ተንቀጥቅጠው የሚያገለግሉህን ጥቂቶቹን አይተህ አኛን ብዙዎቹን ጥፋተኞች ይቅር በለን፡፡
          አዎን ጌታ ሆይ በየዕለቱ መቀደስህን መወዳደሪያና መፎካከሪያ አድርገነዋል፡፡መሥዋዕት ማቅረብ አሰልቺና አድካሚ ሥራ የመሰለን አገ ልጋዮች እየበዛን እንደመጣን እንኳን አንተ እኛም የምናወቀው ሐቅ ነው ፡፡አንድ ትልቅ ሆቴል ስንገባ የምናደርገውን ያህል ክብርና ጥንቃቄ ለቤተ መቅደስህ የማንሰጥ መኖራችንም ከአንተ የተሠወረ አይደለም፡፡ ከምእመናን ብዙዎቹም ንስሐ፥ዕርቅ፥ይቅርታና በፈሪሃ እግዚአብሔር ሆኖ ሥጋህንና ደምህን መቀበል፥ወደፊት የሚደረስበትና የማያመልጥ የሚመስለን ሞልተናል፡፡አንዳንድ ጊዜ ከካህናትም ቢሆን ምን አስቸኮ ለህ አርፈህ ቁጭ በል የምንል አንታጣም፡፡ጌታ ሆይ በዚህና በመሳሰ ሉት ምክንያቶች ቤተ መቅደስህ ተዘግቶ በጸጋ የከበሩ ብቻ የሚጠቀ ሙበት ጊዜ ብታመጣ በእውነት የተገባ ነው፤ ነገር ግን ገሥጸን አንጂ አትጣለን፥ማረን አንጂ አታጥፋን፡፡አቤቱ ጌታ ሆይ በተለይ እንደ ራሴ ንዝህላልነት ከሆነ ከቤተ መቅደስህ እንኳን ሳምንታትን ዐመታትን ብት ቀጣኝ እንደማይበዛብኝ አውቃለሁ፡፡ነገር ግን ጌታ ሆይ እንደ ቸርነትህ ነው እንጂ እንደ በደላችን አታድርግብን።ይልቁንም እኔን በጸጋ ከሁሉም የማንሰውንና በኃጢአት የምበልጠውን ይቅር በለኝ፡፡
             ጌታ ሆይ! እንኳን የሌላው ጊዜ ኃጢአት የሰሞኑ ብቻ በፊትህ ብዙ እንደሆነ አውቃለሁ፡፡ንትርካችንም ቢበዛ እንጂ አልቀነሰም፡፡ነገሩን በመንፈስ ዐይን አይተው ለንስሐቸው የሚፋጠኑትን ሁልጊዜም አታጣ ምና ሰለእነርሱ ብለህ ይቅር በለን እንጂ እኔና መሰሎቸማ ገና አሁንም እንሟገታለን፥አንነቃቀፋለን፥እንተቻቻለን፡፡በተለይ እኔማ ሲመክሩኝ የና ቁኝ፥አሳብ ሲሰጡኝም የጠሉኝ እየመሰለኝ ተቸገሬያለሁ።ከዚህም የተ ነሣ፦ሌሎች ዘንድ ስሕተት የመሰለ ነገር ፈልጌ በመተቸት፥ራሴን ነጻ ለማውጣት ብዙ ጥቅሶችን አማትርና በኋላ ላይ ግን ለድኅነቴ ሳይሆን ለክብሬ መሆኑን ሳስበው በእውነት አፍራለሁ፡፡እንዲያውም  በቅቶ በተ አምራት ቆቅ እየተያዘለት ይመገብ የነበረውን አባ መቃርስን፦”እንዴት መነኵሴ ሆኖ ሥጋ ይበላል?” እያሉ ይንቁት እንደ ነበሩት ወጣንያን መነኮሳት፥በማውቃት ብቻ ተነሥቼ በማላውቀው ሁሉ የምተቸውን አስቤ ደንግጫለሁና አትቀየመኝ፡፡ይልቁንም የአባ መቃርስን ብቃት ገልጸህ እነዚያን ተመካሂ መነኮሳት እንደ ገሠጽካቸውና እንደ መለስካ ቸው እኔን እና መሰሎቼንም አንተን ደስ በሚያሰኝ ለእኛም በሚረዳ ገሥጸህ መልሰን እንጂ አትዘንብን፡፡
              አዎን ጌታ ሆይ! ንጉሥ ቴዎዶስዮስ ከገዳሙ የተለካለትን ደብ ዳቤ መሠረት አድርጎ “አንተ እኮ አንደ ቀዳማይ ኤልያስ ነህ ሲሉ ገልጸ ውልኛል፤”ሲለው፥”ንጉሥ ሆይ! ለኤልያስ ምግቡን የሚያመጡለት ቁራ ዎች ነበሩ፥እኔ ግን ምግቤን ባሰጣው ቁራ ይወስድብኛል፤”ሲል በትሕ ትና እንደተናገረው፥እንደ ገዳማዊው አባ ኤልያስ ዘገዳመ ሲሐት፦ በት ሑታን ትደሰታለህና እንደ እርሱ ያሉትን አይተህ ባለማወቅና በትንሽ ዕውቀት የምንወዛገበውን ይቅር በለን፡፡
ጌታ ሆይ እኛም ብንሆን እንጥ ቀም ብለን እንጂ እንጉዳ ብለን አይደለምና አትቀየመን፡፡ጌታ ሆይ! አን ተን ከልብ የሚያመልኩትን ባሉበት እንደምታከብር፥ ከልብ የተመለሱት ንም ለንስሐ ጊዜ ሰጥተህ የናቁትን ሲያከብሩ፣ቸለል ያሉትን ውድነቱን ሲያውቁ፣በበደሉት ሲጸጸቱ፣ከልብ እንዲሹት አድርገህ እንደምታበቃ ቸው ሰምቻለሁና እኔንም ከእነርሱ ደምረኝ፡፡ለበቁትና በእውነት አንተን ለሚያመልኩህ፥በድፍረት ከሚቆርቡት በዕደ መላእክት በእሳት ጉጠት እየነጠቅህ በወደቁበት በረሀ እና ዋሻ እንደምታቆርባቸው ሰምቻለሁ፡፡ በመሆኑም በእነርሱ ላይ የተዘጋም የሚዘጋም ቤተ መቅደስ እንደሌለ አውቃለሁ።ለእኔ ለበደለኛው ግን አስብልኝ፥እዘንልኝ፡፡
         ዳንኤልን አንበሶች እንዳጫወቱት፥ለአቡነ አረጋዊ ዘንዶው እንደ ታዘዘ፥ለሌሎቹም ቅዱሳን ብዙ አራዊት እንደታዘዙ ሰምቼ ራሴን ሳልመ ረምር በተመካሁበት ይቅር በለኝ እንጂ አትቀየመኝ፡፡እኔ እምነት አለኝ በዬ ቤቴን እንኳ ከፍቼ አልተኛም፡፡እንኳን አንበሳ ሊያጫውተኝ ያሳደግ ሁት ውሻም አንዳንድ ቀን ይነክሰኛል፡፡ይህም ሆኖ ግን በአለማወቅ ከመናገርና በማደርገው ከመመጻደቅ አልተመለስኩም፡፡ ይህም ሁሉ ወደ ልቡናዬ ባለመመለሴ ነውና ጥፋቴን ሳይሆን ቅናቴን፥ ስሕተቴን ሳይሆን በመሳትም ቢሆን ከሰማሁት ተነሥቼ በአቅሜ በጎ ነው ብዬ መመኘቴን አይተህ ይቅር በለኝ እንጂ፦እንደ ፈሪሳዊው ቀራጩ ከአንተ ይሻላል ብለህ አታሳፍረኝ፡፡እንደሚሻል አሁን ስያዝ አስታውሻለሁ፥ከእኔ ያልተሻለ እንደሌለም ተረድቻለሁ፥ስለዚህ ይቅር በለኝ፡፡
          አዎን ጌታ ሆይ! ቤተ መቅደስህን የዘጋሁትም እኔ እንደሆንኩ አውቃለሁ፡፡ጊዜውም ቀደም ብሎ እንደሆነ አስታውሳለሁ፡፡ ቤተ ክርስ ቲያንህ ግቢ ውስጥ ቁጭ ብዬ በልቤ ከቢሮዬ ስገባ አስታውሳለሁ፡፡ ሠራዊተ መላእክቲሁ ለመድኃኔ ዓለም፥ይቀውሙ ቅድሜሁ ለመድኃኔ ዓለም እየተባለ፥እኔ ግን በልቤ ከቤትህ ወጥቼ  ከጓደኞቼ ጋር ከተማ ካለ ምግብ ቤት ስገባ አስታውሳለሁ፡፡አንዳንድ ጊዜም በኅሊናየ ተስቤ ወጥቼ ስከብር ስምነሸነሽ፥ሌላ ጊዜ ደግሞ ስሾም ስዘማነን፥አንዳንድ ጊዜ ደግሞ የተቀየምኩትን ስቀጣ ሳስቀጣ፥ሌላ ጊዜ ስማር ስመራ መር፥ስበርና ስከንፍ እውል እንደ ነበር ትዝ ይለኛል፡፡ስግዱ ላይ ሰግጄ በአሳብ ሌላ ቦታ ስባክን በሰው ተቀስቅሼ የተነሣሁበትንም አልረሳ ውም፡፡ተስጥኦ እየተቀበልኩ ከመወሰዴ የተነሣ በእግዚኦ ተሣሃለነ ፈንታ ምስለ መንፈስከ እያልኩ እስኪመልሱኝ ድረስ እንደምቸገር አልዘ ነጋውም፡፡ስለዚህ ጌታ ሆይ ከቤተ መቅደስ ሥጋየን አቁሜ ስባዝንብህ ጊዜ ነው መሰል፥የሥጋየ ማጎሪያ ብቻ ማድረጌን አይተህ በመንፈስ እስ ክመለስ ድረስ መቅደስህን ብትዘጋብኝ የሚበዛብኝ አይደለሁም።ነገር ግን ጌታ ሆይ! አንደወጣሁ አታስቀረኝ፥እባክህን ከእነ ጠፋው ልቡናየ መልሰኝ፡፡ለምን ተዘጋ? የምለውም ተጨንቄ አንጂ መከፈቱ ይገባኛል (ይደልወኒ) ብዬ አይደለምና እባክህን ጌታ ሆይ! በፈሪሃ እግዚአብሔር እንድመለስበት እርዳኝ፡፡ያን የጠፋውን በግ እንደተሸከምከው እኔንም ተሸክመህ መልሰኝ እንጂ አትተወኝ፡፡ያን ጊዜ በዋዛ በፈዛዛ ማሳለፌን ረስቼው ዛሬ አንደዋዛ መግባት ሲሳነኝ ፈራሁ፥ደነገጥሁም፡፡ትችቴን እና ነቀፋየንም የመጨነቅና ወደአንተ የመቅረብ ብቻ አድርገህ ውሰድልኝ እንጂ ጌታ ሆይ አትቀየመኝ፡፡አቤቱ ወደ ቤተ መቅደስህ እንደ ዳዊት በደ ስታ የምመጣበትን ቀን አቅርብልኝ፡፡
          አውቃለሁ ጌታ ሆይ! ቅዳሴውን ረዘመ፥አገልግሎቱንም በዛ እያ ልኩ እተች ነበር፡፡የይስሙላውን ቁመቴን አድርሼ ለሌሎች ጉዳዮች ልቤ ክንፍ አውጥቶ ይበርር ነበር፡፡ዛሬ ግን ሁሉንም እንዳቆመውና ወደ አንተ እንዳይ ስትጠራኝ ምን ያህል ጊዜ እንደበደልኩህ ሳስብ መቁጠር አቃተኝና ደነገጥኩኝ፡፡ጌታ ሆይ! በቤት መቅደስህ ውስጥ ቆሜ በዓለም ካሉት ይልቅ መበደሌን አውቄያለሁ።አቤቱ ጌታ ሆይ! መዓትህን በምሕ ረትህ፥ቁጣህንም በትዕግሥትህ መልሰህ፥ለነፍሴም ትዕግሥትንና ማስተዋልን ሰጥተህ፥በማላውቀውና በማይመለከተኝ ሁሉ ከምእመን እስከ ጳጳስ ከሚያስተቸኝ መንፈስ ነጻ አውጥተህ፥እንደ መበለቲቱ ሐና ከቤተ መቅደስህ እንዳልለይ እርዳኝ፡፡ጌታ ሆይ! በልቤ ክፋት የዘጋሁብ ህን መቅደስ በእርዳታህ ክፈትልኝና ከምሥጢራት ለምካፈልበት መቅደ ስህ አብቃኝ፡፡አቤቱ ጌታ ሆይ! ይህንንም የፈሪሳዊ ጸሎት አድርገህ አት ጸየፍብኝ፡፡ፈሪሳዊ መሆኔን አውቄ ለምኝሃለሁና።ለእኔ ዐይነቱም ቢሆን ምሕረትህ እንደማይከለከል ሰምቻለሁና።አቤቱ ፈጥነህ ማረን፥ይቅር በለንም፥ አሜን፡፡
Filed in: Amharic