ጅምላ ጨራሽ መሣሪያዎች!!!
ዶ/ር እንዳለማው አበራ
ሁላችንም እንደምናውቀው የጦር መሣሪያዎች በሁለት ይከፈላሉ፡፡ እነሱም መደበኛ (Conventional) እና ጅምላ ጨራሽ (Weapons of Mass Destruction [WMD]) የሚባሉት ናቸው፡፡ መደበኛ የሚባሉት እነ ጠመንጃ፣ መድፍ፣ ታንክና የመሳሰሉት ሲሆኑ ጅምላ ጨራሾቹ ደግሞ በሦስት ይከፈላሉ፡፡ ለአጠራር እንዲመች በሚመስል መልክ ቀደም ባለው ጊዜ በእንግሊዝኛ ABC Weapons ይባሉ እነደነበር እናስታውሳለን፡፡ A = Atomic, B = Biological, C = Chemical መሆኑ ነው እንግዲህ፡፡
ከእነዚህ ጅምላ ጨራሽ መሣሪያዎች መካከል ዙሪያቸው በምስጢርና በሴራ ትንተና የተተበተበው ባዮሎጂካል መሣሪያዎች ይመስሉኛል፡፡ ስለእነሱ ጥቂት እናውጋ፡፡
1. የእነዚህ መሣሪያዎች ዒላማ ምንድነው?
ባዮሎጂካል መሣሪያዎች የጠላትን ሰው፣ እንስሳት ወይም አዝመራ ለመጉዳት ጥቅም ላይ ይውላሉ፡፡ በቀላል አነጋገር ሰውን ወይም እንስሳትን ለመግደል፣ ወይም ዕፅዋትን ለማጥፋት ጥቅም ላይ ሊውሉ ይችላሉ፡፡
2. ጎልተው የሚጠቀሱ ክስተቶች
• ጣልያኖች ከአድዋ ጦርነት በፊት ሁለት በደስታ በሽታ (Rinderpest) የተያዙ ከብቶችን በምፅዋ በኩል አስገብተው በሽታው ከአገራችን አልፎ በሌሎችም የአፍሪካ አገሮች ለመዛመቱ ምክንያት ሆነዋል፡፡ ይህ ታስቦበት የተደረገ ነው የሚሉ አሉ፤ በስህተት ነው ያሉም አልታጡም፡፡ ያደረሰው ጉዳት ግን በቁጥር ለመተመን የሚከብድ ነበር፡፡ ከአገራችን የቁም እንስሳት ግማሽ ያህሉ እንዳለቁ፣ አልፎ ተርፎም የዱር አራዊት ሳይቀር በበሽታው እንደረገፉ ተዘግቧል፡፡ በነገራችን ላይ ይህ በሽታ በምፅዋ በኩል ገብቶ እስከ ደቡብ አፍሪካ ድረስ እንደተዛመተ አንብበናል፡፡
• ጃፓኖች በሁለተኛው የዓለም ጦርነት በቻይና ላይ በፈፀሙት ባዮሎጂካል ጥቃት ከ200ሺህ በላይ ቻይናዊያን እንደተገደሉ ተመዝግቧል፡፡ (በነገራችን ላይ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከተጠናቀቀ በኋላ ጃፓኖች በዘመኑ ለፈጸሙት ግፍ በበቂ ሁኔታ ይቅርታ አልጠየቁም፣ ተገቢውን ካሣም አልከፈሉም ተብለው ይወቀሳሉ፡፡)
• በደቡብ አፍሪካ የእውነት አፈላላጊና እርቅ ኮሚሽን ሲስሰሙ ከነበሩት ዘግናኝ ታሪኮች አንዱ ከባዮሎጂካል መሣሪያዎች ጋር የተያያዘ ነበር፡፡ ይኸውም የአፓርታይድ መንግሥት ጥቁሮችን ለይቶ የሚያጠቃ መሣሪያ ለማግኘት ምርምር ያካሂድ እንደነበር የተገለጸበት ነው፡፡
• በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት አሜሪካ የኩባን የአንድ ዓመት ሸንኮራ አገዳ ምርት እንዳወደመችባት እንሰማ ነበር፡፡ የስኳር ምርት የኩባ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ስለነበረ አገሪቱን ለማሽመድመድ የተወሰደ እርምጃ ይመስለኛል፡፡
• (ዕፅዋትን በተመለከተ የሚታወቅ ሌላ ዘመቻ አለ፡፡ አሜሪካ በቪየትናም ጦርነት ጊዜ የቪየትኮንግ ተዋጊዎች ከለላ ያገኙበትን ደን ለማውደም ኬሚካል መሣሪያዎችን ተጠቅማለች፡፡ የዚያ ጣጣ እስካሁንም አልለቀቀም፡፡)
3. መሣሪያው ምንድነው?
የተለያዩ ባክቴሪያና ቫይረሶች ባዮሎጂካል መሣሪያ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ ጃፓኖች ኮሌራን፣ ታይፎይድንና ሌሎችንም ጀርሞች ሞክረዋል፡፡ አሜሪካ ውስጥ ከመስከረም 1 ቀን 1994 (September 11, 2001) በኋላ በቁርባ (Anthrax) ባክቴሪያ ጥቃት ሊፈጸም ይችላል ተብሎ ተሰግቶ ነበር፡፡ እንደ ፈንጣጣ ቫይረስ ያሉ ጀርሞችም ወደፊት ጥቅምላይ ሊውሉ ይችላሉ ብለው የሚሰጉ ወገኖች አሉ፡፡
የዘረመል ምህንድስና እየረቀቀ በሄደ ቁጥር አዲስ አይነት ጀርም የመሥራት አቅምም የዳበረ ፡፡ ይህ አቅም በክፉ ሰዎች እጅ ከገባ ሊያስከትል የሚችለውን ውድመት ማሰብ ራሱ ይሰቀጥጣል፡፡
4. ባዮሎጂካል መሣሪያ ስትጠቀም…
ደጋግመን እንደሰማነው አንድ ወገን የባዮሎጂካል መሣሪያን ለመጠቀም ከፈለገ ማድረግ ያለበት ጥንቃቄ አለ፡፡ ይኸውም በአንድ በኩል ጥቃቱ/መሣሪያው ወገንንም የማይነካ መሆኑን ማረጋገጥ፡ ከዚህ አልፎ ደግሞ ለወገን ሕዝብ የመሣሪያውን ማርከሻ (ክትባት ወይም መድኃኒት) ማዘጋጀት ነው፡፡ የጠላትን ወገን እፈጃለሁ ብሎ የለቀቀው ጀርም መልሶ የራሱን ሕዝብ ካጠቃ ውጤቱ ተያይዞ ማለቅ ይሆናል፡፡
5. በኤችአይቪ ዘመን
በኤችአይቪ ዘመን የግንዛቤ ማበልጸጊያ ስልጠና ብለን ባዘጋጀን ቁጥር በውይይት ሰዓት ብዙ ጊዜ ከሚወስዱብን ጥያቄዎች መካከል አንዱ ይህ ነበር፡፡ የገባንን ያህል በማስረዳት እናልፈዋለን፡፡ የራሳቸውን ሕዝብ መከላከል የሚያስችል ዘዴ ሳያዘጋጁ እኛን ለማጥቃት የፈጠሩት መሣሪያ ነው ብሎ ለማመን ይከብዳል፡፡
6. ኮቪድስ?
ይህን ቫይረስ ቻይና ሠራችው ወይስ አሜሪካ የሚል መካሰስ እንሰማለን፡፡ በተለይም የአሜሪካ ቀኝ አክራሪ ሚዲያ ተቋማት ቻይናን ተጠያቂ ለማድረግ ይሞክራሉ፡፡ በስህተት የተለቀቀ የሚለው መላምት በኤችአይቪም ዘመን ስንሰማው የነበረ ነው፡፡ በበኩሌ ይህን ለማመን ይከብደኛል፡፡
7. እና ምን ይሻላል?
እዚህ ላይ በኤችአይቪ ዘመን የቀድሞው የዛምቢያ ፕሬዚደንት ኬኔት ካውንዳ የተናገሩትን ጠቅሰን ማለፍ ብቻ ይበቃል፡፡
“ኤችአይቪ ከየትም ይምጣ ከየት የሚሄደው ግን እኛን ወደማጥፋት ነው፡፡ ስለዚህ ራሳችንን ከዚህ በሽታ መጠበቅ አለብን፡፡”
በኮቪድም እንደዚያው ነው፡፡
እጃችንን እንታጠብ ፣ አካላዊ እርቀታችንን እንጠብቅ፡፡