>

ይድረስ ለቅዱስ ሲኖዶስና ለሕዝበ ክርስቲያን በሙሉ  (መ/ር ታሪኩ አበራ)

ይድረስ ለቅዱስ ሲኖዶስና ለሕዝበ ክርስቲያን በሙሉ።† 

መ/ር ታሪኩ አበራ
† አገልጋዮችን ከቤተክርስቲያን ስታሳድዱ የነበራቹ አባቶችና ሰባክያን እግዚአብሔር በእናንተን ላይ መቅደሱን ሲዘጋባችሁ ምን ተማራችሁ? †
 
† በሽታው ይመለሳል፣ መድኃኒቱም በቅርብ ይገለጣል የእናንተ ልብ ግን  ይመለስ ይሆን? 
 
† ከዚህ የባሳ እንዳይገኝህ ደግመህ አትበድል† 
 
† ሙዳየ ምጽዋት ሲቀዘቅዝና ለካህናት የሚከፈል ሲጠፋ በሩ ይከፈት ከማለታችሁ በፊት ዛሬ ልባችሁን ለእውነተኛ ይቅርታ ክፈቱ።†
 
“ጸሎቱ ለመስተቀይም ከመዘርዕ ዘወድቀ ማዕከለ አስዋክ”
 
“ይቅርታን የማያውቅ የቂመኛ ሰው ጸሎት በእሾህ መካከል እንደ ወደቀች ዘር ነች።አታፈራም።”
እግዚአብሔር ሥራው ረቂቅ ነው ፍርዱም ከአዕምሮ በላይ ነው። ዓለምን በሙሉ በአንድ በሽታ ያውም ራሱ ሰው በፈጠረው ተውሳክ  ቁጭ አድርጎ እያስተማረ ነው።እግዚአብሔር እውነተኛ መምህር ነው፣ፍጹም አይሳሳትም ሲያስተምርም  ለሰው አዕምሮ በሚመጥንና በሚረዳው መንገድ ነው ዛሬ ዓለምን አንድ ትምህርት ቤት አድርጎ እርሱ ብቻ ቆሞ እያስተማረ ነው።እግዚአብሔር እውነተኛ ዳኛ ነው።ፍርድ አያዳላም መማለጃም አይቀበልም፣ለሰው ሁሉ በእኩል ይፈርዳል።ዛሬ ዓለምን ፍርድ ቤት አድርጎ እርሱ ዳኛ ሆኖ  ለሁሉ የሚገባውን ፍርድ እየሰጠ ነው።ፈታሒ በጽድቅ ኮናኒ በርትዕ የሆነ አምላክ ነው።
ብፁዐን አባቶች ሆይ !  ትናንት ደጃችሁን ዘግታችሁ በብዙ አገልጋይ ላይ ፈርዳችሁ ነበር፣ጠርታችሁ ሳታወያዩ፣ ቀርበው እንዲናገሩ ዕድልም ሳትሰጡ፣ካሳደገቻቸው ቤተክርስቲያን፣ በጥበብ ካደጉበት ቤተመቅደስ  በግፍ አውግዛችሁ ነበር ዛሬ እግዚአብሔር በእናንተ ላይ ደጁን ዘጋባችሁ።ገብቷችሁ ይሆን? እግዚአብሔር በአንዲት በሽታ ዓለምን ሁሉ እያስተማረ ነው።
ሰባክያንና ዘማርያን ሆይ !  ትናንት አብረዋችሁ በየበረሃውና በየገጠሩ እየተንከራተቱ ወንጌልን የዘሩ፣በዝማሬ ክርስቶስን ከፍ ከፍ  ያደረጉ አገልጋዮችን ዓይናችሁ ለአፈር ብላችሁ አሳዳችሁ ከቤተክርስቲያን አስወጥታችሁ  እራሳችሁን ብቸኛ የእግዚአብሔር አገልጋይና የቤተክርስቲያን ተቆርቋሪ አስመስላችሁ ነበር የእግዚአብሔር ፍርድ ሲመጣ ግን እናንተንም አገልግሎታችሁንም ጠርጎ ከመቅደሱ አሳደደ ፣በኢሳይያስ የተነገረው ትንቢት ፍጻሜ አገኘ ” በጉባዔ መሰባሰባችሁና በዓላቶቻችሁን  ነፍሴ ተጸይፋለች።”ይሄ የእግዚአብሔር ፍርድ ገብቷችሁ ይሆን? በሽታው ምክንያት ነው ፍርዱ ግን ከሰማይ ነው።በሽታው አንድ ነው ቅጣቱ ግን ዘርፈ ብዙ ነው።
ከአንተ እምነት የእኔ እምነት ይበልጣል አንተ ፀረ ቤተክርስቲያን ነህ ብላችሁ ወንድማችሁን በአድማ፣እህታችሁን በተንኮል  አሳዳችኋል ታዲያ የእናንተ እምነት የትገባ? እውነተኛ አማኝ ከሆናችሁ መቅደሱን ዘግታቹ በየጓዳችሁ ለምን ተደበቃችሁ ? አማኝ ነኝ ካላችሁ ጸሎታችሁ ምነው መልስ አጣ? ምነውስ ጉንፋን ማጥፋት ተሳነው ? ተንኮልና ግፍ በልባቹ አለ።ፍርዱ የመለኮት ነው።
ብፁዓን አባቶች ሆይ ! ትናንት ልጆቻችሁን አቅርባችሁ ማወያየት ተጸይፋችሁ፣ አወያዩን ብለው ሲማጸኗችሁም  አፍና አፍንጫችሁን በመጎናጸፊያ ሸፍናችሁ በንቀት ታልፋ ነበር ዛሬ እግዚአብሔር የእውነት አፍና አፍንጫን አሸፍኖ የሚያሸማቅቅ ደዌ ምድራችንን ሲገዛት ፊቱን መልሰብን፤ ጸሎታችንም መልስ አጣ።ትናንት አገልጋዩን  በብጣሽ ደብዳቤ ከየሃገረ ስብከታችሁ ታሳድዱ ነበር ዛሬ እግዚአብሔር እናንተን በተራ ጉንፋን ከቢሮና ከመቅደስ አሳዶ ከሕዝብ ላያይቶ አስሮ አስቀምጧችኋል።ይህ የእግዚአብሔር ፍርድ ገብቷችሁ ይሆን?
እናንት አመጸኛ  ሰባክያንና ዘማርያን ትናንት ከአገልጋይ  ወንድምን እህቶቻችሁ ጋር ቀርባችሁ ሳትወያዩ፣መጽሐፍ ቅዱስ ዘርግታችሁ ሳትተማመኑ  ሕዝብን ለአመጻ፣ ወጣቱን ለአድማ በየዓውደ ምሕረቱ ስትቀሰቅሱ ሰንብታችኋል፣አገልጋዩንም ጾም አዳሪ አድርጋችሁ በረሃብ፣በችግር፣የቤት ኪራይ የሚከፍለው አጣቶ እንዲሰቃይ አድርጋችኋል።እግዚአብሔር  ታግሶ ዝም ቢልም አልተመለሳችሁም  ዛሬ በአንዲቷ በሽታ እናንተም ገርፏል ለአድማ የምትጠቀሙበትን ጉባዔ በትኗል፣የካሴትና የሲዲ ንግዱንም አመድ አድርጎታል፣ችግርና እጦት ምን እንደሆነ በሕይወታችሁ አሳይቷችኋል ግን ልባችሁ ያምን ይሆን?
ብፁዐን አባቶች ሆይ ! ትናንት ልጆቻችሁን መናፍቅ፣ተሃድሶ ብላችሁ አውግዛችኋል አንድም ቀን ዕድል ሰጥታችሁ ከሊቃውንት ጋር እንዲወያዩ፣መጽሐፍ ቅዱስን ዘርግተው እንዲተማመኑ ሳታደርጉ ቤተክርስቲያን አምጣ የወለደቻቸውን አገልጋዮች ሁሉ ገፍታችሁ ገፍታችሁ ለአውሬ አሳልፋችሁ ሰጥታችኋል፤ ዛሬ እናንተ ራሳችሁ ከመናፍቃንና ከሙስሊም ጋር ቆማችሁ ሳትወዱ በግዳችሁ እንድትጸልዩ ተፈርዶባችኋል።ይህ የእግዚአብሔር ፍርድ ገብቷችሁ ይሆን? ወይስ ጊዜ ያመጣው ተራ ነገር ነው ብላችሁ  እንደ ልማዳችሁ አድበስብሳችሁ ለማለፍ አስባችኋል? ከዚህ የባሰ እንዳያገኝህ አትበድል የሚለውን ቃል አስቡ።
እናንት አድመኛ  ሰባክያንና ዘማርያን ትናንት የአገልጋዮችን ስም ለማጥፋት ሲዲ እየቆራረጣችሁ፣ፎቶ እያቀናበራችሁ፣ሕዝብን ለአድማ ስታነሳሱ የነበራችሁ ዛሬ በቀጥታ ስርጭት ጳጳሳቱ ከእስላም ሼኪዎችና ከፕሮቴስታንት ፓስተሮች ጋር ቆመው ሲጸልዩ በማን ላይ ታሳድሙ ይሆን?  በማንስ ላይ ድንጋይ ታስወረውሩ ይሆን ? በማንስ ላይ ሲዲ ታቀናብሩ ይሆን ? ፍርዱ ከልባችን ጥመት ከህሊናችን ክፋት የመጣ ነውና የባሰው ፍርድ በጓዳችን ሳይገባ የበደልነውን እንካስ ያስቀየምነውን ይቅርታ እንጠይቅ።
መላው ሕዝበ ክርስቲያን ሆይ ! ልብ በሉ !በማስተዋልም ነገሮችን ተመልከቱ ትናንት በእግዚአብሔር ቤት ከባድ ግፍ ተፈጽሟል ሰባክያን በየአውደ ምህረቱ አድማ ሰብከዋል ጥላቻን ዘርተዋል፣ወጣቶች በስሜት ተነድተው ብዙዎች አገልጋዮችን ተሳድበዋል፣ደብድበዋል፣አዋርደዋል፣ማኅበራት የክስ ዶሴ አቀናብረው ብስሉን ከጥሬ፣እውነቱን ከሐሰት አቀናብረው አገልጋዮችን ለማስወገዝ በጀት መድበው በተንኮል ተንቀሳቅሰዋል፣የሲኖዶስ አባቶች በመንጋ ፍርድ ተመርተው አንድም አገልጋይ ጠርተው ሳያነጋግሩ ፣የመናገር ዕድልም ሳይሰጡ በግፍ ብዙ የወንጌል አገዮችንና ዘማርያንን አስለቅሰዋል፣ገፍተው አሳደዋል ለረሃብና ለስቃይ ዳርገዋል፣ለአውሬ ጉሮሮም ቀልበዋቸዋል።ያ የግፍ ዕንባ መሬት ፈስሶ አልቀረም፣ያ ሁሉ ሐዘን ሐዘን ብቻ ሆኖ አልቀረም የእግዚአብሔር ፍርድ በዓለም ሁሉ ላይ ሲነሳ ግፈኞችን፣አድመኞችን ጸሎተኞች ነን የሚሉ ተመጻዳቂዎችን ሁሉ  አላለፋቸውም ባዶነታቸውን እያሳያቸው ነው።እኛ ብቻ አማኝነን  አንተ መናፍቅ ነህ ብለው ወንድማቸውን ከመቅደሱ ያሳደዱ ግብዞች እምነታቸው ጉንፋን ማጥፋት አልቻለም።ሁሉም አስመሳይና ውሸታም ነው።
በመጨረሻም ፦
ብፁዐን አበው ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፣የጠቅላይ ቤተክህነት የመምሪያ ኃላፊዎች፣ሊቃውንት ጉባዔ፣ሰባክያንና ዘማርያን፣ማኅበራት፣መላው ሕዝበ ክርስቲያን እባካችሁ ከእግዚአብሔር የቁጣ በትር እኛም ትዋልዱም ፣ሀገራችንም እንድንተርፍ የበደልነውን ሁሉ ይቅርታ እንጠይቅ፣የገፋናቸውን ሁሉ ሰብስበን ለመወያየት በሰውና በእግዚአብሔር ፊት ቃል እንግባ።በአንዲት በሽታ ዓለምን ሁሉ እንደየጥፋቱ እየቀጣ ያለ ጌታ እኛንም በጥፋታችን ይዞናልና መፍትሔው ከእርሱ ብቻ ስለሆነ ነገ ሳይሆን ዛሬ ቃል እንግባ አሊያ ልባችንን አደንድነን ከእግዚአብሔር ጋር እልህ የምንጋባ ከሆነ አስከሬን መቁጠር እንጀምራለን።የእግዚአብሔር ዓላማ ግን በመረጣቸው ሰዎች ይቀጥላል።
በየአዳራሹም ተበትናችሁ ያላችሁ ወንድሞችና እህቶች እናንተም ወደ ልባችሁ ተመልሱና ከእናት ቤተክርስቲያን ጋር ቆማችሁ የዲያብሎስን ተንኮል ተቃወሙ። እናንተን ቤተክርስቲያን አልገፋቻችሁም ፣ቤተክርስቲያን አላሳደደቻችሁም ፣የገፏችሁም ያሳደዷችሁም ዛሬ እግዚአብሔር ከመቅደሱ ያሳደዳቸው ግፈኛ ሰዎች ናቸውና የእግዚአብሔርን ፍርድ ተረድታችሁ ወደ እናት ቤተክርስቲያናችሁ ለመቅረብ እናንተም ቃል ግቡና  ከቅስፈቱ ትረፋ።
እልህ ምላጭ ያስወጣል እንደሚባለው በእልህ በቅዱሳንና በቤተክርስቲያን ላይ ክፋ ቃል የምትናገሩ አገልጋዮች ንስሐ ግቡ። የዛሬ መገፋታችሁን ሳይሆን ትናንት በክብርና በሞገስ ያሳደገቻችሁን ቅድሥት ቤተክርስቲያን ተመልክታችሁ ወደ ቀደመ ፍቅራችሁ ተመለሱ።ባሳለፋችሁት አጭር ጊዜ ሁሉንም እግዚአብሔር አሳይቷችኋል  ሁሉም ተራና መናኛ ነው፣አይጠቅምም። የክብር ጸጋችሁ ያለው በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ነው፣የአገልግሎት ቅባታችሁም በዚህች ቤተክርስቲያን በክብር የሚገለጥ ነው፤ ስለዚህ እናንተም በንስሐ ወደ ቤታችሁ ተመለሱ።
ወገኖቼ እርግጠኛ ሆኜ የምነግራችሁ አድመኛውን፣ግፈኛውን፣ተንኮለኛውን እግዚአብሔር አበጥሮ ይለያል፤ ልባቸው ቅን በሆኑ አገልጋዮቹ ግን የእግዚአብሔር መለኮታዊ ዓላማ በቤተክርስቲያን ይቀጥላል።ዓላማውም ሁሉ በክርስቶስ ኢየሱስ ተጠቅልሎ ወደ እግዚአብሔር ሙላት በጸጋው እንዲያድግ ደግሞሙ የልጁን መልክ ይዞ ወረሽ እንዲሆን ነው።
ኢሳይያስ 1፥13፤ሰንበታችሁን በጉባኤ መሰብሰባችሁን አልወድድም፤ በደልንም የተቀደሰውንም ጉባኤ አልታገሥም።
14፤ መባቻችሁንና በዓላቶቻችሁን ነፍሴ ጠልታለች፤ ሸክም ሆነውብኛል፥ ልታገሣቸውም ደክሜያለሁ።
15፤ እጃችሁንም ወደ እኔ ብትዘረጉ ዓይኔን ከእናንተ እሰውራለሁ፥ ልመናንም ብታበዙ አልሰማችሁም፤ እጆቻችሁ ደም ተሞልተዋል።
16፤ ታጠቡ ሰውነታችሁንም አንጹ፤ የሥራችሁን ክፋት ከዓይኔ ፊት አስወግዱ፤ ክፉ ማድረግን ተዉ፥
17፤ መልካም መሥራትን ተማሩ፥ ፍርድን ፈልጉ፥ የተገፋውን አድኑ፥ ለድሀ አደጉ ፍረዱለት ስለ መበለቲቱም ተምዋገቱ።
ክብርና ውዳሴ ለታረደው በግ ይሁን።
ጌታ መንፈስ ቅዱስ ለሁላችንም አስተዋይ ልቡና ይስጠን።
Filed in: Amharic