>
5:13 pm - Friday April 19, 9078

በአስገራሚ ሁኔታ ከሞት የተረፈው ጋዜጠኛ ንጉሴ ወ/ማሪያም !!! (ፍጹም ንጉሴ)

በአስገራሚ ሁኔታ ከሞት የተረፈው ጋዜጠኛ ንጉሴ ወ/ማሪያም !!!

ፍጹም ንጉሴ
ሀምሌ 5 ቀን የኢህአፖ ዋና ሀፊ እና መስራች የነበረው ብርሀነመስቀል ረዳ በደርግ የተረሸነበት ቀን ነው። ይህንኑ የርሸና ዜና በኢትዮጲያ በራዲዮ ለህዝብ ሲተላለፍ ራዲዮ ጣቢያው ቅጥር ግቢ ውስጥ አንድ ድራማዊ አጋጣሚ ተከስቶ ነበር።
ለመሆኑ በኢትዮጲያ ራዲዮ ግቢ ውስጥ በወቅቱ ምን ተከስቶ ነበር? ከታች ያለውን ጽሁፍ ያንብቡ፦
ጊዜዉ በአስራ ዘጠኘ ሰባዎቹ መባቻ አካባቢ ነበር የኢትዮጲያ ራዲዮ የመዝናኛ ፕሮግራም አዘጋጅ የነበረው ጋዜጠኛ ንጉሴ ወ/ማሪያም እንደተለመደው በሱቱዲዮ ውስጥ ሆኖ ፕሮግራሙን እየመራ ነበር “ክቡራን አድማጮቻችን ከዚህ በመቀጠል አንድ ሙዚቃ እንጋብዛችኀለን” ብሎ በእስቱዲዮ ቋንቋ ተጥዶ የነበረውን ሙዚቃ ቴክኒሻኑ እንዲለቀው ምልክት ያሳየዋል  ቴክኒሻኑም ልክ ሙዚቃውን ሊለቀዉ ሲል ባስቸኳይ ለህዝብ መድረስ አለበት የተባለ መግለጫ ከደርግ ጸ/ቤት በፖስታ ታሽጎ ወደ እስቱዲዮ ይመጣል የራዲዮ ጣቢያው አመራሮችም መግለጫውን እስቱዲዮ ውስጥ የሚገኘው ንጉሴ እንዲያነበው ትዕዛዝ ይሰጡታል እርሱ የመዝናኛ ጋዜጠኛ ነው በሰአቱ በአካባቢው ሌላ ምንም አይነት ጋዜጠኛ ባለመኖሩ እንጂ የመንግስትን መግለጫዎችን የሚያነብ ጋዜጠኛ አልነበረም በወቅቱ አሰፋ ይርጉ የተባሉ አንጋፋ ጋዜጠኛ መግለጫውን እንዲያነቡ ተፈልገው በራዲዮ ጣቢያው ግቢ ውስጥ እንዲሁም ያዘወትሯቸዋል በሚባሉት ቦታዎች ጭምር ተፈልገው ባለመገኘታቸው መግለጫውን የማንበብ ግዴታ በጋዜጠኛ ንጉሴ ላይ ተጣለ።
ፓስታውን ከፍቶ መግለጫዉን ማንበብ ጀመረ መግለጫው የኢ.ህ.አ.ፓ መስራች እና አመራር አባል የነበረውን የብርሀነ መስቀል ረዳ እና የሌሎች በቁጥር 11የሚሆኑ ወጣት የኢ.ህ.አ.ፓ አባላትን መረሸን የሚገልጽ ነበር።
አስገራሚው ክስተት ከዚያ በኃላ ነው የሚጀምረው ንጉሴ መግለጫውን አንብቦ እንደጨረሰ መጀመሪያ ጥዶት የነበረውን ሙዚቃ ቴክኒሻኑ እንዲለቀው ምልክት ያሳየዋል ሙዚቃውም ሲለቀቅ የፀሀይ እንዳለ
“የሚያስደስት ነበር አፈጣጠራቸው
ዳሩ ምን ያደርጋል አፈር ባይሞላቸው”
የሚለው አሳዛኘ ሙዚቃ ነበር እንደአጋጣሚ ሆኖ የሙዚቃው መልዕክት ከመግለጫው ጋር ይጋጫል ሆን ተብሎ ለሟቿቹ በማዘን የተለቀቀ ይመስል ነበር።ይህንን የሰማው ደርግም ንጉሴን ለመያዝ ስድስት ደቂቃ አይሞላውም ነበር ታንኮችን አሰልፎ ወደ ራዲዮ ጣቢያው ሲልክ እስከ አፍንጫቸው ድረስ የታጠቁ ወታደሮችን በላያቸው ላይ የጫኑት ታንኮችም አቡነ ጴጥሮስ አካባቢ ወደሚገኘው የኢትዮጲያ ራዲዮ ደጃፍ በመድረስ ግርግር ይፈጥራሉ።
ነገሩ ያልገባው ጋዜጠኛ ንጉሴም ሀገር ሰላም ብሎ እስቱዲዮ ውስጥ በስራ ላይ እያለ ነበር በር ላይ ስለተፈጠረው ነገር ባልደረቦቹ የነገሩት ልክ እንደሰማ ወዲያው ጊዜ ሳያጠፋ በራዲዮ ጣቢያው ጀርባ በአትክልት ተራ በኩል በአጥር ዘሎ ከአካባቢው ይሰወራል ከዚያም አዳሩን ሲፈለግ ያድርና በነገለታው አ.አ ውስጥ ተይዞ ለእስር ይዳረጋል ከጥቂት ቀናት እስር በኃላ የርሸና እርምጃ ሊወሰድበት ሲል ለጋዜጠኞች ጥብቅና በመቆም የሚታወቁት በወቅቱ የደርጉ የማስታወቂያ ሚኒስተር ተጠሪ የነበሩት ሻለቃ ግርማ ይልማ ኮሎኔል መንግስቱ ኃ/ማሪያም ዘንድ በመቅረብ ስለሁኔታው አጋጣሚ እንጂ ሆንተብሎ የተፈፀመ አለመሆኑን እንዲሁም ጋዜጠኛው በእድገት በህብረት የዕውቀት እና የስራ ዘመቻ ጊዜ ዘመቻውን የሚያጅብ ሙዚቃ ሰርቶ ያበረከተ የአብዮቱ ባለውለታ መሆኑን በማብራራት ምህረት እንዲደረግለት ይማጸናሉ።
“መሄዴነው ዘመቻ መሄዴነው ገጠር
ድንቁርናን ላጠፋ ከኢትዮጲያ ምድር”
የሚለው የዕድገት በህብረት ማጀቢያ ሙዚቃ የእርሱ ነበር።
በኃላም ኮሎኔሉ የርሸናው እርምጃ እንዲነሳለት ነገር ግን ከስራው እንዲሰናበት ይወስናሉ።
ጋዜጠኛ ንጉሴም በስህተት ከመረሸን ተርፎ ከስራ ገበታው ይሰናበታል። በዚህ መልኩ ከኢትዮጲያ ራዲዮ ስራውን የለቀቀው ጋዜጠኛ ንጉሴ የራዲዮ ጋዜጠኝነቱን በጣም ከማፍቀሩ የተነሳ ሻይ ቤት ውስጥ ወይም ቡና ቤት ውስጥ ቁጭ ብሎ ራዲዮ በሰማ ቁጥር እርሱ ራዲዮን ውስጥ ባለመኖሩ የተነሳ በተደጋጋሚ ጊዜ ያለቅስ ነበር።
ከጥቂት አመታት ቆይታ በኃላ ግን ኢትዮጲያን በመልቀቅ ወደ አሜሪካን ሀገር ያቀናው ጋዜጠኛ ንጉሴ ወ/ማሪያም ከዛ በኋላ በዋሽንግተን ዲሲ እና አካባቢው የሚደመጥ የሀገር ፍቅር የሚባል የራዲዮ ጣቢያ ባለቤት ለመሆን ችሏል።
አትጥፊ ያላት ነብስ እንዲሉ !!
(ምንጭ ሀገር ፍቅር ራዲዮ)
Filed in: Amharic