>

የጸደይ ወቅት የመጀመሪያዋ የመጋቢት 30 ሙሉ ጨረቃ ሥያሜ በሌሎች ሀገራት (በመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ)

የጸደይ ወቅት የመጀመሪያዋ የመጋቢት 30 ሙሉ ጨረቃ ሥያሜ በሌሎች ሀገራት

 

 

በመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ

• ለመሬታችን ቅርብ የሆነችው ጨረቃ በተለያዩ ሀገራት የተለያየ ሥያሜ ያላት ስትሆን ለምሳሌ በቀደምት ኢትዮጵያውያን:-

1) ጨረቃ
2) ወርኅ
3) ዕብላ
4) ብናሴ
5) ኤራዕ
6) ቀመር ተብላ ተጠርታለች።
♥ በሌሎች ሀገራት ደግሞ የጸደይ ወቅት ሲገባ ለምሳሌ በዚህ ዓመት የመጋቢት 30 ሙሉ ጨረቃን “ሐምራዊ ጨረቃ” (Pink moon) ወይም “ታላቋ ጨረቃ” (Supper moon) ይሏታል።
♥ ሐምራዊ ጨረቃ መባሏም በሌሎች ሀገራት በጸደይ ወቅት የሚበቅሉት አበቦች ቀለማቸው ሐምራዊ በመሆኑ የጥንት ሕዝቦች በዚህ የጸደይ ወቅት የምትታየው ሙሉና ታላቅ ጨረቃን ሐምራዊዋ ጨረቃ ብለው ነበር የሠየሟት፨ በተለይ በጸደይ ወቅት ሙሉ ጨረቃ ከመታየቷ ጋር አበቦችን እንደገና ከመውጣታቸው ጋ በማያያዝ ዐዲስ የመሆን የመለወጥ ምሳሌ አድርገው ያስቡ ነበር።
♥ የዚህ ዓመት የጸደይ ወቅት የመጀመሪያው የመጋቢት 30 ጨረቃም ደማቅና ሙሉ ስትሆን በአንዳንድ ሀገራት ግን በከባቢ አየር ምክንያት ብዙም ባይሆን አልፎ አልፎ ቡርትካናማና ቀላ ብላም የመታየት እድል ይኖራታል።
♥ የጸደይ ወቅት የመጀመሪያዋ ሙሉ ጨረቃ በተለያዩ ሀገራት አስገራሚ ሥያሜ ያላት ሲሆን ለምሳሌ ከጸደይ እኩሌ spring equinox ቀጥሎ የሚታይና የፋሲካን በዓል ያሰሉበት ስለነበር የፋሲካ ጨረቃ (Paschal Moon) ሲሉት በተጨማሪም የዓሣ ጨረቃ (Fish Moon), የዕንቁላል ጨረቃ (Egg Moon,) እና የለምለም ሣር ጨረቃ (Sprouting Grass Moon) በመባልም ትታወቃለች።
♥ በጥንት የነበሩ ሕዝቦች በጸደይ ሙሉ ጨረቃ ጊዜ የሰዎች ጠባይ ይለዋወጣል ወንጀል ሊሠሩ ይችሉ ይሆናል የሚሉ ሲሆን ነገር ግን ይህ አባባላቸው በሳይንሱ ብዙም አይደገፍም፨ የወንጀል መርማሪዎችም ወንጀል መሥራት ከሐምራዊ ጨረቃ ሐሳብ ጋር ምንም ግንኙነት የለውም ሲሉ፤ አንዳንዶቹ ግን የጨረቃ የስበት ተጽዕኖ በሰዎች ጠባይና እንቅልፍ ላይ የራሱ የሆነ ለውጥ ያመጣል ይላሉ።
♥ ቻፊን ሚትሼል “Do full moons and supermoons really influence people and animals?” (ሙሉ ጨረቃና ታላላቅ ጨረቃ በሰዎችና በእንስሳት ላይ በእውነት ተጽዕኖ አለውን?) በሚል ርዕስ ባስነበበው ጥናታዊ ጽሑፍ ላይ የፍሎሪዳ ፓሊስ ደግሞ 5 ዓመታት ባጠናሁት ጥናት በምሉ ጨረቃ ጊዜ የሚመጡልኝ የነፍስ ማጥፋትና የጥቃት ወንጀሎች ይበዛሉ የሚል ገራሚ ሪፓርት አቅርቦ ነበር፨ ያም ሆነ ይህ ግን ጨረቃ አስደናቂ ተፈጥሮ ያላት ናትና በተፈጥሮዋ መደነቅ ይቻላል፨
♥ ስለ ጨረቃ ተፈጥሮና አጠቃላይ ጉዳይ አንድሮሜዳ መጽሐፍን በማንበብ ሰፊ ዕውቀትን ማግኘት ይችላሉ። ጨረቃን ካነሣን በዚሁ ዓመት ዐርብ ግንቦት 28 ጨረቃ በደበዘዘው ፔኑምብራ (Penumbra) በተባለው የመሬት ጥላ ውስጥ ስታልፍ እንደወትሮው የደመቀች ሳትሆን ድብዝዝ ብላ የምትታይበት “የድብዝዝ ጥላ ግርዶሽ” (Penumbral Lunar Eclipse) በኢትዮጵያ ሀገራችን በአህጉሪቱ አፍሪካ፣ አውሮፓና እስያ ይታያል።
♥ ይህንን ካየን በኋላ ደግሞ ሠኔ 14 ላይ “ቀለበታዊ የፀሐይ ግርዶሽ” ኢትዮጵያ ውስጥ ከምዕራብ አንሥቶ እስከ ሰሜን ምሥራቅ ኢትዮጵያ ስለሚታይ በሕይወት ዘመናችን ቀኑ ጨልሞ ልናየው የምንችለው ድንቅ የተፈጥሮ ክስተት ይሆናል።
Filed in: Amharic