>

የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ይታወጅ!!  በአጉል ቸልታ ህዝብን አናስፈጅ!!!! (ስዩም ተሾመ)

የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ይታወጅ!! 

በአጉል ቸልታ ህዝብን አናስፈጅ!!!!

ስዩም ተሾመ
አሁን ላይ የኢትዮጵያ መንግስት የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የሚከተለው አቅጣጫ ምንድነው?  የጠ/ሚ ፅ/ቤት ዋና ሴክቴሪያት አቶ ንጉሱ ጥላሁን ለቪኦኤ ከሰጡት አስተያየት፣ እንዲሁም የአዲስ አበባ ከንቲባ ኢ/ር ታከለ ኡማ እንደተናገሩት፣ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ለመከላከል አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ ነው።
 ነገር ግን በሀገር አቀፍ ሆነ በአዲስ አበባ ደረጃ የነዋሪዎችን እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ ለመግታት አልተወሰነም። ከዚያ ይልቅ ሁለቱም የመንግስት ሃላፊዎች እንደተናገሩት ችግሩ እየተባባሰ ሄዶ ከአቅም በላይ የሆነ ችግር ከተፈጠረ የዜጎችን እንቅስቃሴ ሙሉ ለሙሉ ለመግታት እንደሚገደዱ ገልፀዋል። ይሄ እንግዲህ ኢራን፣ ኢጣሊያን፣ ስፔን፣ እንግሊዝ እና አሜሪካን የመሳሰሉ ሀገራት ያደረጉትና በማድረግ ላይ ያሉት ነገር ነው።
ይሁን እንጂ እርምጃው የቫይረሱን ስርጫት አልገታም፣ ዜጎችን ከሞት አልታደገም። በተመሳሳይ የኢትዮጵያ መንግስት አሁን እያለ ያለው ልክ እንደ ሌሎች ሀገራት ብዙ ሰው በቫይረሱ ሲያዝና መሞት ሲጀምር የዜጎችን እንቅስቃሴ ሙሉ ለሙሉ ለመግታት አቅዷል። ስለዚህ ብዙ ሰዎች በቫይረሱ እስኪያዙና ለሞት እስኪዳረጉ ድረስ እየጠበቀ ነው ማለት ነው።
የኮሮና ቫይረስን ስርጭት ለመግታት እና የሚያደርሰውን ጉዳት ለመከላከል “መንግስት አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት እያደረገ ነው” ሲባል ምን ማለት ነው? በአጭሩ መልሱ “ምንም” ነው። ይህን ስል “መንግስት ምንም እያደረገ አይደለም” ለማለት አይደለም። ሁሉም በየፊናው የሆነ ነገር እያደረገ እንደሆነ ጠፍቶኝ አይደለም። ሆኖም ግን መንግስት የፈለገውን ነገር ቢያደርግ የቫይረሱን ስርጭት መግታት፣ በቫይረሱ የሚሞቱትን ሰዎች መታደግ አይችልም። ምክንያቱም ቫይረሱ መድሃኒት የለውም! በቃ…አለቀ ደቀቀ! ሺህ አመት ዝግጅት ቢደረግ፣ ሺህ ህንፃ በነፃ ቢሰጥ፣ ስንት ቢሊዮን ብር በእርዳታ ቢሰበሰብ አሊያም በጀት በሚመደብ በዚህ ፍጥነት ለቫይረሱ መድሃኒት ማግኘትና ዜጎችን ከሞት መታደግ አይችልም።
ለምሳሌ “የኮሮና ቫይረስ መመርመሪያ መሳሪያ ገባ” ተባለ። ነገር ግን ቫይረሱ ያለበትን እና የሌለበትን ሰው ለመለየት ካልሆነ በስተቀር ሌላ ፋይዳ የለውም። በእርግጥ “ቫይረሱ ያለበት ሰው ወደ ለይቶ ማቆያ ይወሰዳል” እንደምትሉኝ እገምታለሁ። ነገር ግን የዜጎች እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ ካልተገታ በስተቀር በየቀኑ በቫይረሱ የተያዘ ሰው ቁጥር እየጨመረ ይሄዳል። እንዲህ እያለ ሄዶ ሁሉም ሆስፒታሎች ይሞላሉ። አሁን የተቋቋሙት ግዜያዊ የህክምና ቦታዎችም በታማሚዎች ይሞላሉ። ከዛ ታማሚዎች በሆስፒታል መተላለፊያ ኮሪደሮች ይተኛሉ። በመጨረሻ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ወደ ሆስፒታል መምጣት ይተዋሉ። በየቦታው ከሚንገላቱ ቤታቸው ውስጥ መሞት ይመርጣሉ። እነዚህ ሁሉ ነገሮች የቫይረሱን ስርጭት በብዙ እጥፍ ይጨምረዋል። በዚያው ልክ የሟቾች ቁጥር በብዙ እጥፍ ያሻቅባል። ይህን ግዜ ህዝብና መንግስት በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን እና የሞቱትን ሰዎች መቁጠር ይሰለቻቸዋል። በየቀኑ በቫይረሱ የተያዙትን መቁጠር ትተው የሞቱትን በመቅበር ላይ ያተኩራሉ።
በእርግጥ ሃሳቡ በብዙዎች ዘንድ መረበሽና ሽብር እንደሚፈጥር አውቃለሁ። ነገር ግን ያልኩት ነገር በአውሮፓና አሜሪካ በእውን ሲሆን እያየን ነው። ይህ በእኛ ሀገር እንዳይሆን ምን የሚያግደው ነገር አለ? ምንም። መጀመሪያ ላይ ስለ ኮሮና ስፅፍና ስናገር “ሟርት” ይመስላችሁ ነበር። ይሄው አሁን ቫይረሱ ኢትዮጵያ ውስጥ ከገባ አንድ ወር ሞላው። በቫይረሱ የተያዙት ሰዎች ቀስ በቀስ እየጨመረ ነው። በዛሬው እለት ደግሞ ሁለት ሰዎች መሞታቸው ተገልጿል። ስለዚህ የኮሮና ቫይረስ ኢትዮጵያ ገብቷል፣ ጥቁር ወይም ነጭ ሳይል እንደሚገድል በተግባር ተመልክታችኋል። አሁንስ ምን ቀራችሁ? ጣሊያኖች፣ ስፔኖች፣ እንግሊዞች፣ ብራዚሎች፣ አሜሪካኖች፣… ወዘተ የሰሩትን ስህተት ደግመን በመስራት ሞትን ቆመን እንጠብቀው ወይስ ከእነሱ ስህተት ተምረን እንግታው?
አሁን ያሉት ሆስፒታሎች ሆኑ መንግስት በግዜያዊነት ያዘጋጃቸው ቦታዎች የመሰቃያና መሞቻ ቦታ ከመሆን የዘለለ ፋይዳ የላቸውም። ምክንያቱም ቫይረሱ መድሃኒት የለውም። በጡረታ የወጡ የህክምና ባለሞያዎችን ለግዳጅ እንዲዘጋጁ ተናገርን። ነገር ግን እነዚህ የህክምና ባለሞያዎች በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ሲሞቱ ከማየት በስተቀር ምንም ማድረግ አይችሉም። ምክንያቱም ቫይረሱ መድሃኒት የለውም። እጅግ ውድ በሆነ ዋጋ የመተንፈሻ መሳሪያ (Mechanical Ventilator) ከውጪ እያስገባችሁ ነው። ነገር ግን የመተፈሻ መሳሪያ ከተገጠመላቸው ሰዎች ውስጥ 80 ፕርሰንቱ ይሞታሉ፣ የተቀሩት 20 ፕርሰንቱ ደግሞ ከሞት የሚተርፉት የልብ. ኩላሊት እና የሳምባ በሽታ፣ እንዲሁም የስነልቦና ቀውስ ሸምተው ነው። ከዚህ በተጨማሪ ከሞት የተረፉት ሰዎች ለረጅም ግዜ የአልጋ ቁራኛ ሆነው ይቀጥላሉ።
ሌላስ? ሌላ ምን ቀራችሁ? ምንም! ምክንያቱም የኮሮና ቫይረስ ከገባ ምንም ዓይነት ምልክት ሳያሳይ በትንፋሽ እና ንግግር ብቻ ይተላለፋል። በመሆኑም በቫይረሱ የተያዘ አንድ ሰው ካለ ከሁለት ወር በኋላ መላ ሀገሪቱን ያዳርሳል። በቫይረሱ ከተያዙ ሰዎች ደግሞ የሚሞተው ሞቶ የሚድነው ይድናል። አሁን ባለው ሁኔታ ከቀጠልን የቫይረሱን ስርጭት መግታት ሆነ የሚሞቱትን ሰዎች መታደግ አይቻልም። በዓለም ላይ ያሉት የህክምና ባለሞያዎች አሁን ባለው ሁኔታ እያደረጉት ያሉት መተንፈስ አቅቷቸው ጣር ውስጥ ላሉ ሰዎች የመተንፈሻ መሳሪያ በመግጠም ስቃያቸውን ከማራዘም በዘለለ ምንም እያደረጉ አይደለም። ከማደንዘዣ በስተቀር የሚወጋ መርፌ የለም፣ የሚዋጥ መድሃኒት የለም፣ ኦፕራሲዮን አይደረግም፣…. እይን እያየ ትንፋሽ አጥሮ እየተሰቃዩ መሞት ብቻ ነው።
መንግስት አሁን የሰበሰበውን ገንዘብ በመጠቀም የዕለት ጉርስ ለሌላቸው ሰዎች ምግብና መጠጥ መግዣ ያድረገው። ከሞት የማይታደግ የመተፈሻ መድሃኒት በመግዛት፣ ሰዎች ታክመው የማይድኑበት ቦታ በማዘጋጀት በከንቱ አያባክነው። ከዚያ ይልቅ አንድ ወር የሚቆይ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ያውጅ!!!! ይህ ከመሆኑ ሁለትና ሶስት ቀናት ቀደም የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ እንደሚታወጅ፣ እያንዳንዱ ሰው ባለበት እንዲቀመጥ ትዕዛዝ ይስጥ። ሁሉም የፀጥታ ኃይሎች የአስቸኳይ እርምጃ ተግባራዊ በማድረግ ሥራ ላይ ይሰማሩ። የህክምና ባለሞያዎች በቫይረሱ የተጠረጠሩ ግለሰቦችን ከማህብረሰቡ ውስጥ እየለዩ በማውጣት ወደ ለይቶ ማቆያ ያስገቡ። አዋጁን በመፃረር መንገድ ላይ ሲንቀሳቀስ የተያዘ ግለሰብ ላይ ከፍተኛ የገንዘብ ቅጣትና እስራት ይተላለፍበት። ወደ ሀገር ውስጥ የሚደረግ ማንኛውም ዓይነት በረራ ይሰረዝ! በመጨረሻ ከአንድ ወር በኋላ ቫይረሱ ያለባቸው ሰዎች ከማህብረሰቡ ተለይተው፣ የዳነውም ድኖ፣ የሞተውም ሞት፣ ሀገርና ህዝባችንን እናተርፋለን።
እስካሁን ድረስ ቫይረሱ በከፍተኛ ፍጥነት አለመሰራጨቱ እና ሰዎች በብዛት አለመሞታቸው በዓለም ላይ በጣም “እድለኞች” ያደርገናል። ከሌሎች ስህተት ተምረን ህዝባችንን ለመታደግ ጥረት አለማድረጋችን ደግሞ በዓለም የመጨረሻ ደንቆሮዎች ያደርገናል። እንዴት ምክንያታዊ አዕምሮ ያለው ሰው በዚህ ልክ ማሰብና ማገናዘብ ይሳነዋል? ከሌላው ዓለም በተለየ መልኩ ከኮሮና ቫይረስ ህዝባችንን ለመታደግ የሚያስችል የመጨረሻ ዕድል አለን። ይህን ማድረግ ከተሳነን ግን በምድር ላይ ሞትን ቆመው የሚጠብቁ ከንቱዎች ነን።
Filed in: Amharic