>

ድምጻችን ተሰምቷል!!! ደስታና ሀዘን፣ እንባና ሳቅም ተፈራርቆብናል!!!

ድምጻችን ተሰምቷል!!!

ደስታና ሀዘን፣ እንባና ሳቅም ተፈራርቆብናል!!!

ዘመድኩን በቀለ 
አባቶቻችን ከስቱዲዮና ከሆቴል ወደ ቤተ መቅደሱ ተመልሰዋል። ይሄ ደስታችን ነው። ሀዘኑ በጦማሩ ውስጥ በጥቂቱ ብልጭ ተደርጎ ተጠቅሷል። ዝርዝሩን ነገ
እመለስበታለሁ!!!
 
★ ደስታው !!
•••
የዛሬው የምህላ ጸሎት መርሐ ግብር የቀጥታ ሥርጭት ከመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ከምሽቱ 3:00 – 4:00 ድረስ በ ADDIS TV በቀጥታ የሚተላለፍ መሆኑን ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ያገኘሁት መረጃ ነው በማለት የ EOTC TV ዝግጅት ክፍል አሳውቋል። በእውነት ደስ ይላል።
•••
እንዲህ ስንደማመጥ ከምር ደስ ይላል። አባቶቼ ቡራኬያችሁ ይድረሰኝ። ቤተ ክርስቲያን የቀጥታ ስርጭት እንዳታስተላልፍ የሚያደርጋት ለቀጥታ ስርጭት የሚሆን መሳሪያ እንደሌላት ተሰምቷል። ለወደፊቱ የመሳሪያው ዋጋ ይታወቅና ቤተ ክርስቲያን ግማሹን፣ እኛም ደግሞ ግማሹን አዋጥተን ለምነን
ቢሆን መግዛት አያቅተንም። እናም ይታሰብበት። የምን የመንግሥትን ሲለምኑ፣ ደጅ ሲጠኑም ሲቀላውጡም መኖር ነው። ኧረ ወደዚያ !!
•••
ጎበዝ አሁን ሁላችንም በጊዜ በሰዓቱ ተዘጋጅተን እንጠብቅ። ወደ ቤታችን ክትት ብለን እንግባ። ከቴሌቭዥኑ ፊት እንቁም። ምን ይደረግ እንግዲህ ለተወሰነ ቀን ግድ ነው። ደግሞ እንዲሁ ተመካክረን በቶሎ ቤተ ክርስቲያን ተመልሰን፣ የተዘጋው ተከፍቶ ዳግብ ከመንበሩ ፊት ቆመን ከቤተ መቅደሱ ገብተን በጋራ መጸለይ እስክንጀምር ድረስ ይሄንኑ አጥብቀን
እንጸልይ።
•••
ወዳጆቼ በያለንበት ዋዛ ፈዛዛውን ትተን፣ ነጠላችንን አጣፍተን፣ ከትልቅ እስከ ትንሽ ሰብሰብ ብለን ለጸሎት እንዘጋጅ። በጋራም በአንድነት እንጸልይ።
•••
ሀዘኑ….
በኢትዮጵያ ዛሬ በኮሮና የሞተ ሰው የለም። በመላው ዓለምም ጦርና የጦር ወሬም የለም። ነገር ግን ብአዴን የተባለ የካንሰሯ ህወሓት የበኩር ልጅ የኦህዴድ ወዶ ገብ አሽከር መከረኛውን፣ አሳረኛውን ዐማራውን በቅድስት ሀገር ደብረ ሮሀ ላሊበላ ሲፈጀው ውሏል።
አሳረኛው ዐማራ ከኮሮና ሳንባ ቆልፍ፣ ከብአዴን አንገት ቆልፍ፣ ከረሃብ አንጀት ቆልፍ ጋር ይተናነቅ ይዋደቅ ዘንድም ልክ፥ እንደትናንተ ዛሬም በዚህ ዘመን ተፈርዶበታል። ብአዴን ከኮሮና ቫይረስ የበለጠ ኮሌራናኮሮናም ነው። የሞቱትን ነፍስ ይማር።
•••
ብአዴን በላሊበላ የፈረደበትን አማራ ለእርድ ሲያቀርብ የግብር ወንድሙ የጉምዝ ልዩ ኃይል መተከል ላይ  ዛሬም በመላው ኢትዮጵያ ሞት የታወጀበት አማራ ላይ ቀስት እያስወነጨፈ ነው በምስሉ የምታዩት ወደ ጤና ጣቢያ ከተወሰዱት የአንዱን ነው ። በየጥሻው የወደቀውን ቤት ይቁጠረው።
እንግዲህ በዐማራ ላይ ሞት የፈረዳችሁ በሙሉ ቱ ምን አለ ዘመዴ በሉኝ መንግሥታችሁ አይጸናም። ቀጣይ ረሃብ መንግሥታችሁን ብትንትኑን እንዳያወጣው እሰጋለሁ። የከተማ ረሃብ እየመጣ ነው። ረሃብ ደግሞ ክፉ ነው። የራበው ሰው መንግሥቱን ይበላዋል። መንግሥቱን ይገለብጠዋልም።
“እምነ ረሃብ የኄይስ ኩይናት፥ ከረሃብ ጦርነት ይሻላል።”
የሚል ዜጋ ባታበዙ ይሻላችኋል። ቤት አታፍርሱ፣ ሱቅ አታፍርሱ፣ ዜጋ አትግደሉ። የሚነጫነጭ ሰው አታብዙ። ሆድ ለባሰው ማጭድ አታውሱ። እንኳንስ እናቴ ሞታ እንዲሁም አልቅስ አልቅስ ይለኛል የሚባለውን ምሳሌ አስታውሱ።
•••
የዐቢይ አሕመድ አማካሪዎች ሆይ ከተቻለ ንገሩት። የሴራ ቦለጢቃ በዚህ ሰዓት እንደማያዋጣ ንገሩት። በበሽታውም መሞታችን ካልቀረ፣ በረሃብም መሞታችንም ካልቀረ ተዋግተን ገድለን እንሙት የሚል ዜጋ እንዲበዛ ባታደርጉ መልካም ነው። ሥርዓተ አልበኞችን ህዝቡ ራሱ ይታገላቸው። አሁን የሚቀድመውን እናስቀድም። ውጊያው ከኮሮናና ከረሃብ ጋር ይሁን። ለጦርነቱ እንደርስበታለን። ጦርነቱ የት ይሄድብናል። ልማዳችንም አይደል። ክፉ ልማድ። የት ይሄድብናል? እናም አሁን ጦርነቱን አቁሙ። ረሃቡ ላይ፣ በሽታውን መከላከሉ ላይ ብትሠሩ ይበጃችኋል። ምክር ነው !!
•••
ሌላውንም እያየሁ እጨምራለሁ !!
•••
ሻሎም ! ሰላም !
መጋቢት 30/2012 ዓም
ከራየን ወንዝ ማዶ።
Filed in: Amharic