>
5:13 pm - Friday April 19, 9591

በኢትዮጵያ ኮሮናን ለመከላከል የመፍትሄ ምክረ ሀሳብ (አህመዲን ጀበል)

በኢትዮጵያ ኮሮናን ለመከላከል የመፍትሄ ምክረ ሀሳብ

አህመዲን ጀበል
በኢትዮጵያ የኮሮና ታማሚን መቁጠር በመጋቢት 4 ቀን 2012 (ማርች 13 ቀን 2020)  አንድ ብሎ  ተጀምሮ ከ25 ቀናት በኃላ በትናንት እለት ቁጥሩ 52 ደርሷል። የኢትዮጵያ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር  በየጊዜው የሚሰጣቸውን መግለጫዎች መሠረት በማድረግ ሁሉንም መግለጫዎች በጋራ በማጣመር አስልቼ እንደተረዳሁት በኢትዮጵያ ዉስጥ በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው ከተረጋገጡት መካከል የጉዞ ታሪክ የሌላቸው እና በኮሮና ከተያዘ ሰው ጋር በነበራቸው ንክኪ ምክንያት በኮሮና የተያዙት  ሰዎች ብዛት 17 ሲሆን ማለትም እስካሁን በኮሮና ከታያዙት አጠቃላይ(52 ሰዎች) ያላቸው ድርሻ 32.7%(ሰላሳ ሁለት ነጥብ ሰባት በመቶ) ነው።
 ከተለያዩ ሀገራት ወደ ኢትዮጵያ ተጉዘው የመጡና በምርመራ በሽታው የተገኘባቸው  ሰዎች ደግሞ 35 ሲሆኑ ማለትም ከአጠቃላዩ ቁጥር ያላቸው ድርሻ 67.3% (ሥልሳ ሰባት ነጥብ ሦስት በመቶ) ናቸው። ከነዚህ ዉስጥ ከግማሽ በላዮቹ ማለትም ከ35 ሰዎች ዉስጥ 18ቱ ሰዎች ወይም 51% (ሀምሳ አንድ በመቶ) የሚሆኑት ከዱባይ ብቻ ወደ ኢትዮጵያ የተጓዙ ናቸው። እነዚህ  ከዱባይ ወደ ኢትዮጵያ ተጉዘው የመጡት በሀገራችን በኮሮና ከተያዙት ከጠቅላላው አኃዝ ያላቸው ድርሻ   34.6%(ሠላሳ አራት  ነጥብ ስድስት በመቶ) ያክል ነው።
አንድ ሰው “የዱባይ ለይቶ ማቆያ ኢትዮጵያ ናት እንዴ?” ብሎ አስተያየቱን በፌስቡክ እንደፃፈው ከዱባይ ወደ ሀገር የመጡት የኮሮና ቫይረስ የተገኘባቸው ሰዎች ብዛት አስገራሚ ነው።በተለይ ደግሞ ዱባይ ስሟ ከኮሮና ጋር ጎልቶ በሚዲያ አለመነሳቱን ስናስተዉል  በዓለም ላይ መንግስታት ስለበሽታው ተጠቂዎች የሚሰጡትን መረጃ እንድንጠራጠር ያደርገነል።እንደመንግስትና ህዝብ በዱባይም ሆነ አረብ ኢምሬት ላሉት ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ልዩ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ በሚገባ መምከርና በተቻለው መንገድ ሁሉ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ማስተማርና ማገዝ ያስፈልገናል።
ከዱባይ ወደ ኢትዮጵያ ከመጡት ሰዎች ዉጭ ከሌሎች ሀገራት ወደ ኢትዮጵያ የመጡትን  ተጓዞች ስናይ ስብጥራቸው ከተለያዩ ሀገራት ሆነው  ያላቸው ድርሻም እንደሚከተለው ነው። 2ሰው ከብሪታኒያ፣ 2 ከቤልጅየም፣2 ከኮንጎ፣ 1 ከታይላንድ፣1 ከካናዳ፣1 ከአሜሪካ፣ 1 ከአውስትራሊያ፣1 ከኦስትሪያ፣1 ከእስራኤል፣1ሀገሩ ያልተጠቀሰ፣1 ወደ ብራዚል ህንድና ጅቡቲ ተጉዞ የመጣ፣1 ከሲዊዲን፣1 ከፈረንሳይ ወደ ኢትዮጵያ ተጉዘው የመጡ ናቸው። ከነዚህ መረጃዎችና በኮሮና ጉዳይ ከተለያዩ ምንጮች ካገኘኋቸው ግንዛቤ በመነሳት የሚከተሉትን የመፍትሄ ምክረ ሀሳቦቼን አቀርባለሁ።
1) በኢትዮጵያ በኮሮና ከተያዙት መካከል 67% የሚሆኑት ከውጭ ሀገራት ተጉዘው መጥተው በኢትዮጵያ ዉስጥ ሲመረመሩ ኮሮና የተገኘባቸው መሆኑን ስንረዳ የኮሮና ስርጭትን ቶሎ ለመቆጣጠር እንደመንግስት ከዉጭ ወደ ኢትዮጵያ የሚደረጉ ጉዞዎችን ሙሉ ለሙሉ ማቋረጥ በተለይ ከዱባይ ግድ ይለናል።በዚህ እርምጃ  በዉጭ የሚኖሩ ዜጎቻችን ቢያሳዝኑንም እንዲሁም  በፈለጉ ጊዜ ሁሉ ወደ ሀገራቸው መመለስ መብታቸው መሆኑን ብንገነዘብም  ሀገርንና 110 ሚሊዮን የሚሆነውን የኢትዮጵያን ህዝብ ከዚህ ከፍተኛ አደጋ ለመታደግ  ሲባል ወደ ኢትዮጵያ የሚደረግ ጉዞዎችን ቢያንስ ለ3 ሳምንት ሙሉ ለሙሉ ማቋረጥ ያስፈልጋል።
 2) ከተለያዩ ሀገራት ወደ ሀገር የሚገቡትን በሙሉ በአስገዳጅ ሁኔታ ለ14 ቀናት በለይቶ ማቆያ ጣቢያዎች ዉስጥ ማቆየቱ  በቨይረሱ የተያዙ ሰዎች ወደ ህዝቡ እንዳይቀላቀሉ በማድረግ ረገድ እስካሁን ጥሩ ዉጤት ያስመዘገ ቢሆንም፣ ምናልባትም ከብዛታቸው አንፃር ሊሆን ይችላል “በለይቶ መቆያዎቹ ዉስጥ ተገቢው ምግብና እገዛ የለም” የሚል መወራት መጀመሩ ሰዎች በተለያየ መንገድ ወደ ማቆያው ላለመግባትና የገቡትም በተለያየ መንገድ ከማቆያው ቶሎ ወጥተው ወደ ህብረተሰቡ ለመቀላቀል ጥረት እያደረጉ እንዳሉና አንዳንዶችም ወጥተው እየተቀላቀሉ አንዳሉ እየተሰማ ከመሆኑ አንፃር ለ14 ቀናት በማቆያ ከሚቆዩ በነበሩበት ሀገር ቢቆዩ ልዩነቱ እምብዛም ከመሆኑ አንፃር(በዉጭ ለመቆየት የሚቸገሩ ካሉ በዚያው የሚረዱበትን መንገድ መፈለግ ይሻላል) እንዲሁም የትናንትናዎቹን ጨምሮ ሰሞኑን በአብዛኛው ቫይረሱ እየተገኘባቸው ያሉት ከዉጭ መጥተው በአስገዳጅ ሁኔታ በለይቶ ማቆያ ዉስጥ ያሉ እንደመሆናቸው  እነርሱን ለማቆየት ፣ለመመርመርና ለማከም የሚጠይቀው አቅም ብዙ ነው።
 ከዚህ  በተጨማሪም በኮሮና ተያዙ የሚባሉትን ሰዎች  ቁጥር በነርሱ ምክንያት መጨመሩ አንድም ህብረተሰቡ ከዉጭ ለሚመጡ ሰዎች አሉታዊ እይታ እንዲኖረው ያደርገዋል ወይም ቁጥሩ ጨመረ ብሎ መስጋቱን  ያንረዋል። አልያም በማቆያ ዉስጥ በሚቆዩበት ጊዜ ከአንዱ  ወደሌላው እና  በማቆያው ዉስጥ የሚሰሩ ዜጎች ላይ የበሽታውን የመተላለፍ እድልን ይፈጥራል።
3) የተዘጋጁትን የመመርመሪያ መሳሪያዎችን፣ የማቆያ ጣቢያዎችንና የተመደበውን በጀት በእሳካሁኑ ሂደት ቫይረሱ ሊተላለፍባቸው ይችልባቸዋል ተብለው በሚጠረጠሩ አካባቢዎችና የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ ትኩረት በማድረግ በስፋት ለምርመራ ማዋል እና ድንገት የኮሮና ቫይረስ እንደተሰጋው ተሰራጭቶና ተስፋፍቶ ከተገኘም በመርመራው ላይ ተመስርቶ አፋጣኝ የመቆጣጠር እርምጃ ለመውሰድ ይቻላል።
4) በዉጭ የሚኖሩ ዜጎችስ ከዝጉ በኋላስ ምን ይሁኑ ለሚለው ጥያቄ የኔ ሀሳብ ሁሉን ነገር በመዝጋት በህብረተሰቡ ዉስጥ ተሰራጭቶ የሚገኝን የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ከተቆጣጠርን በኋላ የዓለም ሁኔታ ብዙም ለውጥ ካላመጣ ወደ ሀገር መመለስ ለሚፈልጉ ኢትዮጵያውን ብቻ በረራና ወደ ሀገር ሲገቡ በለይቶ ማቆያ ማስቀመጥን ድጋሚ በሙሉ አቅምና ከፍተኛ ጥንቃቄ በመጀመር ሌላው ህብረተሰብ ከስጋት ነፃ ሆኖ እየተንቀሳቀሰና እየኖረ መንግስት በሙሉ አቅሙ እነርሱን በማቆያ በማስቀመጥና በመመርመር ነፃ የሆኑትን ወደ ህበረተሰቡ መቀላቀል። በቫይረሱ የተያዙትንም በሚገባ ማከም ይቻላል። ይህን በማድረግ ዳግም በሽታው ወደ ህብረተሰቡ እንዳይገባ መቆጣጠር ይቻላል ብዬ አስባለሁ።
5)) በእስካሁኑ ሂደት ከኮሮና ታማሚዎች ጋር የተነካኩ የህብረተሰብ ክፍሎች ካሉ ቫይረሱ ይበልጥ እንዳይሰራጭ በመላ ሀገሪቱ ዜጎች ለሁለት ወይም ለሦስት ሳምንት ያክል ከቤት እንዳይወጡ ማድረግ። በሽታው በ14 ቀናት ምልክት ስለሚያሳይ በዚህ ጊዜ ዉስጥ የሽታው ምልክት የታየባቸውን ለይቶ በማሰስ መመርመር ይቻላል። አሁን ባለው አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያየ አከባቢዎች በከፊል እየተደረጉ ያሉ እቀባዎች የበሽታውን ስርጭት ለመከላከል ረጅም ጊዜ የሚፈጅ በመሆኑ በዜጎች ላይ  መሰላቸት፣ የኢኮኖሚ ጫና ያለው በመሆኑ አንድ ጊዜ ሁሉም እንቅስቃሴ በማቆም በአንድ ጊዜ በበሽታው የተያዙ ካሉ ለመለየት ካለማገዙ በተጨማሪም የበሽታውን ስርጭት በማስፋፋት ላይ የራሱ ሚና አለው።
6) ሙሉ ለሙሉ በሚዘጋበት ሁለት ወይም ሦስት ሳምንት ይበልጥ ሊጎዱና ለሽታውን ስርጭት ሊጋለጡ ብሎም በሽታውን ሊያስፋፉ በሚችሉትን አካላት ለምሳሌ ችግረኞችን፣ የጎዳና ተዳደሪዎችን፣ በስደተኛ ጣቢያ ያሉና በከተማ ዉስጥ በልመና ላይ የተሰማሩትን የሶሪያ ስደተኞችን ጉዳይ በልዩ ሁኔታ በማስተባበር  መፍትሄ በመስጠት ሁሉንም አይነት ትራንስፖርትና የዜጎችን እንቅስቃሴ ማገድ። በተለይ በተለያዩ አከባቢዎች ሌሊት ሌሊት በክፍተኛ ክፍያ በድብቅ ሰውን እያጓጓዙ ያሉ ተሽከርካሪዎችና ገንዘብ ተቀብለው እያሳለፉ ባሉት የፀጥታ አካላት ላይ ቁጥጥር በማድረግ ተገቢውን ጠንካራ እርምጃ በመውሰድ ማስቆም።
7) በዚህ የኮሮና ስጋት ወቅት ሰሞኑን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በርካታ ሚሺነሪዎችን አሳፍሮ ሲጓዝ በበረራ ላይ ሳለ ተቀርፆ በራሱ  በአየር መንገዱ የፌስቡክ ገፅ ላይ በማርች 30 ቀን 2020 የተለቀቀውን ቪዲዮን የተመለከተ ሰው (ከሥር ቪዲዮው ተያይዟል) አየር መንገዱ የሀገር ዉስጥና የዉጭ ሀገራት በረራዎችን ሙሉ ለሙሉ እንዲያቆም መመኘቱ ወይም ማሳሰቡ አይቀርም ብዬ አስባለሁ። ተሳፋሪዎችም ሆኑ የአውሮፕላኑ ሰራተኞች በኮሮና ምክንያት የተለየ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ሲገባቸው እንዲህ ቸልተኛ ሆነው ሳይ አስገርሞኛል።በመንግስት ዉሳኔ ለኮሮና መከላከል የሚያደርገውን የጭነት ካርጎ በረራ ሲቀር ቢያንስ ለ3 ሳምንታት  ሙሉ በሙሉ በረራ ማቆም አለበት። ዳግም በረራ ለመጀመርም በዓለምና በሀገር ዉስጥ የኮሮና ጉዳይ ላይ የሚከሰተውን ለውጥ እየታየ ሊሆን ይገባል።
8) የኮሮና ቫይረስ የፈጠረውን ስጋትና አደጋ ወደ መልካም አጋጣሚ በመለወጥ በመላ ሀገሪቱ የራስንና የአከባቢን ንፅህና በመጠበቅ ላይ በሚገባ በመስራት ንፅህናን የመጠበቅ ከፍያለ ባህል እንዲፈጠር በሃይማኖት ተቋማት፣ ሚዲያና መንግስት በጋራ መስራት ያስፈልጋል።  በኮሮና ምክንያት ንጽህናውን ለመጠበቅ በአልኮል፣ በሳኒታይዘር
እና በሳሙና እጅ መታጠብን በግድ እየለመደ ያለ፣ ከሚያስነጥስና ጉንፋን ካለበት ሰው ራሱን መጠበቅን እየተለማመደ ያለን ህዝብ ወደ ድሮው የአኗኗሩ ሁኔታ እንዳይመለስ ሁሉም ተረባርቦ በመስራት ለወደፊቱ የህዝብን ጤንነት በዘላቂነት ለመጠበቅና ጤናማ ዜጋ በመፍጠር ላይ ብቻ ሳይሆን ኮሮናንም ሙሉ ለሙሉ ለማስወገድም ጭምር ከፍተኛ ንፅህናን የመጠበቅ ባህልን መፍጠር በእጅጉ ያግዘናል።
9) ከዚህ ሁሉ ጥረትና ዱዓ(ጸሎት) ጋር አላህ አያምጣውና የኮሮና ወረርሽኝ በሀገራችን ይበልጥ ቢስፋፋ ብሎም የከፋ  ሁኔታ ቢፈጠር በሚል ታሳቢ ራስን በሚገባ ማዘጋጀት እጅግ አስፈላጊ ነው። በተለይም ሌሎች ሀገራት  እስካሁን ባለው ሁኔታ ኮሮናን ለማከም በሙከራነት  እየተጠቀሙበት ያሉትንና ስሙ በስፋት እየተነሳ ያሉትን መድሃኒቶች በብዛት መምረትና መዘጋጀት እጅግ አስፈላጊ ነው።
እንደሚታወቀው ዓለምን እያስጨነቀና የሰው ልጆችን በየቀኑ እያረገና በፍጥነት እየተዛመተ ላለው የኮሮና ወረርሽኝ ሀገራት በመከላከል እርምጃና መፍትሄ ይሆን ዘንድ እንደየአቅማቸው መድሃኒት ፍለጋ ላይ ተሰማርተዋል። በተለይም ለጥናትና ምርምር ከፍተኛ በጀት የሚመድቡ ታላላቅ ሀገራትና ድርጅቶች መፍትሄ ይሆኑ ዘንድ ለኮሮና ቫይረስ ክትባትና መድሃኒት ፍለጋ በአዳዲስና ነባር መድሃኒቶች መካከል ፍለጋቸውን ቀጥለዋል። እስከ አሁን ለተለያዩ በሽታዎች ሲባሉ ተዘጋጅተው በአገልግሎት ላይ ያሉ ሁለት ሺህ (2000) አይነት ፀረቫይስ እና ፀረ ባክቴሪያ የሆኑ መድሃኒቶችን ለኮሮና ሙከራ ተደርጓል።  የኮሮና ቫይረስን በማስወገድ ላይ ግን እስካሁን ሦስት መድሃኒቶች የተለየ ዉጤት አሳይተዋል ተብለው በተለያየ ጊዜ ስማቸው በሚዲያ ሲጠቀስ ነበር።
እነኝህ መድሃኒቶች  በ2014 በአፍሪካ  ደረጃ በተወሰኑ ሀገራት በወረርሽኝነት ተከስቶ በነበረ ጊዜ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን ለሞት ዳርጎ የነበረው ኢቦላ በሽታን በማከም ላይ ግልጋሎት  የሚውለው ሬምድስቪር (Remdsivir) ፥ ሁለት የፀረኤች ኣይ ቪ መድሃኒት የሆኑት ሎፒናቪር(Lopinnavir) እና ሪቶናቪር (Ritonavir) የተሰኙ መድሃኒቶች በጥምረት እና የፀረ ወባ (Anti Malaria) መድሃኒት የሆነው ክሎሮኪን (chloroquine)/ሃይድሮክሲሎሮኪን (HydroxyChloroquine) የተሰኙት መድሃኒቶች ናቸው።
ከነዚህ መድሃኒቶች መካከል ስሙ ተደጋግሞ እየተነሳ ያለው የፀረወባ መድሃኒት የሆነው ክሎሮኪን(chloroquine) /ሃይድሮክሲሎሮኪን(HydroxyChloroquine) ነው።
 የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ይህን መድሃኒት «ጌም ቼንጀር” ብለው በመግለፅ የአሜሪካ የምግብና መድሃኒ አስተዳደር (The US food and drug administration)(FDA)  በአስቸኳይ ጊዜ መድሃተቶቹ በአሜሪካ በኮሮና ቫይረስ ታመው ለሚገኙትና በየእለቱ እየሞቱ ላሉ አሜሪካውያን መታከምያ ይዉሉ ዘንድ ፈቃድ እንዲሰጥ ጠይቀው፣ ወትዉተው በመጨረሻም ከጋር ተያይዞ መድሃኒቶቹ በተደጋጋሚ በሚዲያ ስማቸው ሲነሳ ቆይቶ በመጨረሻም የአሜሪካ የምግብና መድሃኒት አስተዳደር(The US food and drug administration) (FDA/ኤፍዲኤ) በአስቸኳይና አጣዳፊ ጊዜ ፈቃድ በሚል መድሀኒቱ በከፍተኛ ጥንቃቄ በስራ ላይ እንዲዉል መፍቀዱ ይታወሳል።
በዚህ መድሃኒት ላይ በፈረንሳይ ማርሴይ  በኮሮና ታማሚዎች ላይ በተደረገ ሙከራ  የፀረ ወባ (Anti Malaria) መድሃኒት የሆኑት  ክሎሮኪን(chloroquine) ወይም ሃይድሮክሲሎሮኪን (HydroxyChloroquine) ከተሰኙት መድሃኒቶች አንዱን መድሃኒት እና ለተለያዩ በባክቴሪያ ለሚከሰቱ በሽታዎች የሚታዘዘውን አዚትሮማይሲን (Azithromycine) የተባለውን መድሃኒት (ይህ መድሃኒት ለሳምባምች፥ ለጨብጥ፥ወዘተ ይዉላል) በጣምራ ለኮሮና ታማሚዎች ሰጥተው ከፍተኛ ዉጤት እንዳመጡበት የፈረንሳይ ተመራማሪዎች በማርች 20 ቀን 2020 ባሳተሙት ጥናት ገልፀዋል።
 በቻይናም ክሎሮኪን ፎስፌት(ክሎሮኪን) የተሰኘውን መድሀኒት ለኮሮና ታማሚዎች በመስጠት ጥሩ ዉጤት እንዳገኙበት እየተነገረ ነው። እነኝህን መድሀኒቶች ከፍተኛ ጎንዮሽ ጉዳት ያላቸውና በተለይም ተጨማሪ ሌሎች እንደ ግፊት፣የልብ ህመም፣ የኩላሊት እና መሰል የጤና እክል ያለባቸው ሰዎች በሚዲያ ሰምተው ብቻ ያለሀኪም ትዕዛዝ እንዳይወስዱ ከማስተማር ጎን ለጎን እነኚህ በኢትዮጵያ ጭምር (በአዲግራት መድሃኒት ፋብሪካ) የሚመረቱትን መድሃኒቶች በብዛት በማምረት በአስገዳጅ ሁኔታ ሀኪሞች በኮሮና ለታመሙ ሰዎች እንዴት ሊሰጡ እንደሚችሉ ቀድሞ የሚሰጠው አቅጣጫ ላይ መዘጋጀት ያስፈልጋል።
 በአሜሪካና በፈረንሳይ ስለመድሃኒቶቹ በሚዲያ ብቻ ሰምተው በራሳቸው የዋጡና ሀኪሞች ሰጥተዋቸው ጭምር ከኮሮና ሳይድኑ የሞቱ ሰዎች እንዳሉ ስንረዳ እንደመንግስት ከአሁኑኑ በመድሀኒቶቹ ላይ ጥናት ያደረጉና ለመጠቀም እየሞከሩ ያሉትን እንደ ፈረንሳይ፣ቻይና፣ ህንድ፣ደቡብ ኮሪያና አሜሪካ ሀገራት ሀኪሞችና ተመራማሪዎች ልምድ በመውሰድ ከአሁኑኑ መዘጋጀት ያስፈልጋል። ሌሎች ሀገራት በተለይ እንደ ቻይና  ያሉት ሀገራት የተጠቀሙበትን የህክምና ዘዴ ከነርሱ በመማር ያስፈልጋል። ቻይና በወረርሽኙ ክፉኛ በተጠቃችበት ጊዜ ጭምር ሌሎች ሀገራት ወደ ቻይና የአየር በረራ ባቋረጡበት ጊዜ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ አለማቋረጡ ራሱ እንደዉለታ ይቆጠራልና  ቻይና ዉለታውን እንድትከፍል ቢጠየቅ አይከፋም። በተጨማሪም በኢትዮጵያ ዉስጥ መድሃኒቶቹም ያለሀኪም ትዕዛዝ እንዳይሸጡና ያለሀኪም የቅርብ ክትትል እንዳይወሰዱ  ጥብቅ አቅጣጫ መስቀመጥ።
10) አላህ አያድርገውና በዓለም ላይ አሁን ባለው ፍጥነትና ሁኔታ ከአሁን በኃላ ቢያንስ ለጥቂት ወራት እንኳ ድንገት ቢቀጥል  የዓለም ኢኮኖሚ፣ ፖለቲካ፣ የመንግስታት ግንኙነት፣ የህዝብና የመንግስት ግንኙነት፣ የመንግስታት የትኩረት አቅጣጫ እና መሰል ጉዳዮች ላይ በየሀገራቱ ብዙ ለውጥ መፈጠሩ አይቀርም።
በዚህ ጊዜ ሽታው በርሷ ተከስቶ ወደ ሌሎች አስተላልፋ በፍጥነት የተገላገለችው ቻይና (የሚባለው ሁሉ እውነት ከሆነ) ዜጎቿን ቶሎ ወደ ስራ አሰማርታ የኮሮና በሽታ መከላከያ ቁሳቁሶችንና መድሀኒቶችን ለሚፈልጉ ሀገራት ሁሉ በገፍ ለመሸጥ ብሎም ሌሎች ሀገራት ኮሮና ከፈጠረው የስነልቦና ቀውስ፣ የኢኮኖሚ ቀውስና የመንግስትና ህዝብ ግንኙነት ከሚፈጥሩት ተግዳሮቶች እስኪላቀቁ ድረስ ቻይና ስሟን አድሳ የመፍትሄው ዋና አካል በመሆን ዓለምን በኢኮኖሚ ልትመራ ትችል ይሆናል። ማን ያውቃል።ይህን መንግስት ግምት ዉስጥ ቢከት አይከፋም።
በዚህ ዓለም አስጨናቂ የኮሮና ስጋት ዉስጥ በገባበት ጊዜ በጠቅላይ ሚ/ር ዶ/ር አብይ አህመድና ቻይናዊው ባለሀብት የአሊባባ መስራችና ባለቤት  ጃክ ማ ከአሊባባ ግሩፕ የጋራ ኢንሼዬቲቭ ኮሮናን ለከላከልና ለመመርመር የሚዉሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ቁሳቁሶች ለ54 የአፍሪካ ሀገራት ተበርክቷል። በተጨማሪም መሰል እርዳታዎችን ለደቡብ አሜሪካ፣ ለአውሮፓና ለሰሜን አሜሪካ ሀገራት ጭምር ለኮሮና መከላከልና መመርመሪያ የሚሆኑ ብዙ ሺህ
 ቁሳቁሶችን እየረዱ ያሉበትን ሁኔታ ስናይና የቻይናን መንግስትና ህዝብ ሁኔታ የሚረዳ ሰው ይህን ማሰብ አይከብድም።
በተለይም በአሁኑ ሰዓት ሚዲያዎች ላይ እንደሚሰማው የሁሉም ሀገር ዜጋ በየቤቱ በተቀመጠበት ጊዜ ዳግም ወረርሽኙ እንዳይከሰትባት ወደ ሀገሯ የሚደረጉ  በረራዎችን አግዳ ዜጎቿ ወደሥራ መውጣት  ጀምረው የሥራ ትዕዛዛት ከየሀገሩ እየተቀበሉ ነው። ለኮሮና መድሀኒት ይውላል ተብሎ እየታመነ ያለውን ሌላው ቢቀር በኛ ሀገር ለወባ መድሃኒትነት የምንጠቀመውንና በአዲግራት መድሀኒት ፋብሪካ የሚመረተየውን ክሎሮኪን/ሀይድሮክሲክሎሮኪን እና የፊት ጭምብልን አጥተውና እጥረት ገጥሟቸው አውሮፓና አሜሪካ የአውሮፓ ሀገራት እንኳ ቶሎ የሚሸጥ ላቸውን ፍለጋ ሲሯሯጡና “ቅድሚያ ለኔ” በሚል ሲነታረኩ ስናይ ሀገራቱ በሰው ዉስጥ ራሳቸውን የሳሉበት ምስል እየደበዘዘ መሄዱ አይቀርም።
11) በዚህ የኮሮና ስጋት የሁላችንንም ስሜት ተቆጣጥሮ ይዞ በየእለቱ  በዓለም ላይ በበሽታው የተያዙትን፣የሞቱትና ያገገሙትን ሰዎች አኻዝ  ልክ እንደ የእግር ኳስ የነጥብ መግለጫ ሰንጠረዥ ወይም የዓለም የስቶክ ገበያ በሰንጠረዥ ተደርጎ በምንከታተልበት ጊዜ የአብዛኛው ሰው ስሜት ራሱን፣ሀገሩና የዓለም ህዝብን እንዴት ከዚህ በሽታ ማዳን ይቻላል? ወደሚል አቅጣጫ መሰብሰብ ችሏል።ይህ ጥሩ ስሜት ነው። እንደሀገር በአንድነት በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት ራሳችንና ህዝባችንን መታደግ የምንችለው ይህ ስሜት ከኛ ጋር መቆየት ችሎ ሳንከፋፈልና ሳንነታረክ ከፍርሃት ይልቅ ወደ ተግባራዊ እርምጃ በጋራ መሰማራት ከተቻለ ብቻ ነው። የቱንም ያክል ሀገራችንን ብንወድ፣አቅም ቢኖረን በዚህ መሰል የፈተና ወቅት ሳንደናገጥ ስሜታችንን ተቆጣጥረን በአንድነት ተገቢ በምንላቸው የመፍትሄ አቅጣጫዎች ላይ መረባረብ ስንችል ነው። ስለሆነም በተለይ በዚህ ጊዜ ከልዩነት ይልቅ አንድነት ላይ፣ ከመተቻቸትና አንዱ ሌላውን ከማጋለጥና ማሳጣት በፊት መደጋገገፍና መሞላላት ላይ ልናተኩር ይገባናል።
12) አላህ ሀገራችንና መላውን የሰው ልጆችን በቃችሁ ብሎ ኃይሉን እንዳሰየን ሁሉ መህረቱን እንዲያሳየን ራሳችንን በተውበት(ንሰሃ) እና ዱዓ(ፀሎት) ወደ አላህ እንድንዋደቅ ራሴንም እናንተንም እየመከርኩ ራሳችንና ሌሎችን በመጠበቅ ላይ ተገቢው ጥንቃቄ ሁሉ አይለየን እላለሁ።
Filed in: Amharic