>
5:16 pm - Saturday May 24, 0375

የመከራውን ጊዜ ለማሳጠር ምን ይደረግ? (ጸሐፊ: አፈንዲ ሙተቂ)

የመከራውን ጊዜ ለማሳጠር ምን ይደረግ?

ጸሐፊ: አፈንዲ ሙተቂ
COVID-19 የሚባለው በሽታ በዘመነ-ስፔስ እና ኳንተም ሜትሪክስ የሚኖረውን የሰው ልጅ ምጥቀት ልክ እና ገመና ገለባብጦ እያሳየን ነው።  ከመሬት በብዙ ሚሊዮን ኪሎ ሜትር ርቀው የሚገኙትን ፕላኔቶች ገጽታ እና እንቅስቃሴ የሚነግሩንና ሰለጥነናል በሚሉት ሀገራት የሚኖሩት ሳይንቲስቶችና ተመራማሪዎች በሰዎች ላይ ተጣብቃ የምትኖርን አንዲት አነስተኛ ቫይረስ ማጥፋት የሚችል ኬሚካላዊና ባዮሎጂካዊ ቀመር ለማስቀመጥ አለመቻላቸው የተፈጥሮን ሚስጢር በመሉ ለማወቅ ገና ብዙ እንደሚቀራቸው የሚያስረዳ አብነት ሆኗል። በአንጻሩ የሶስተኛው ዓለም ሀገራትን የሚመሩ መንግስታት እና የየሀገራቱ ዜጎች ባላቸው ጊዜና ሀብት ተጠቅመው ካሉበት ፈቅ ለማለት አለመትጋታቸው ወደ ትልቅ ገደል እየመራቸው መሆኑን ፍንትው አድርጎ አሳይቶናል።
—-
የኮሮና ወረርሽኝ ሁሉንም ሀገራት እየፈተነ እና ህልውናቸውን ለአደጋ እያጋለጠ ነው።  ይሁንና በሶስተኛው የዓለም ሀገራት ላይ የተጋረጠው አደጋ ከበድ ያለ ነው። የሀገራችንና የህዝባችን ሁኔታም የሚያሳስብ ነው።
ቫይረሱ ወደ ሀገራችን እንዳይገባ የነበረን ምኞት ሳይሳካ ቀርቶ ፈተናችን “አሃዱ” ብሎ ተጀምሯል። በአሁኑ ጊዜ የተመዘገቡት የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር ከስድሳ አይበልጥም። በሽታው ፈንድቶ በአውሮጳ እና በአሜሪካ እያደረሰ ያለው እልቂት እዚህ ቢደገም ግን የምንቋቋምበት ጉልበት የለንም። ስለዚህ ያለን አማራጭ የበሽታውን ስርጭት በእጅጉ መገደብ ነው።
ታዲያ ይህንን ማድረጉ ቀላል ይሆንልናል? እንዲያ እንደማይሆን ሁሉም ያውቃል። ለምሳሌ በስፔን እና በኢጣሊያ የየተገበረውን total lockdown በእኛ ሀገር በስራ ላይ ለማዋል ቢሞከር ሌላ መዘዝ ሊከተለን ይችላል። ከጠቅላላው የሀገሪቱ ህዝብ ግማሽ ያህሉ ለረጅም ጊዜ ቀርቶ ለአንድ ሳምንት የሚላስ የሚቀመስ የለውምና። በሽታውን እንሸሻለን ብለን ብዙዎችን በረሃብ መጨረስ ደግሞ ኢ-ሞራላዊ ነው።
በሌላ በኩል ይህ ክፉ አውሬ ቢስፋፋ ታማሚዎችን በየትኛው ሆስፒታል ልናሳክማቸው ነው? 450  ቬንትሌተሮችን ይዘን ነው ኮሮናን የምንጋፈጠው? ያሉን የጤና ባለሙያዎች ምን ያህል ናቸው? የICU አገልግሎት የሚሰጡ ነርሶቻችን ስንት ናቸው? ኧረ ቀጣዩ የሀገራችን እጣ ፈንታስ ምን ሊሆን ይችላል? በጣም አሳሳቢ ነገር ነው።
ሀገራችንና ህዝባችን በዚህ ወቅት መውሰድ ያለባቸው እርምጃ ከላይ የተጠቀሱትን ሁለት ተግዳሮች በጣም አነስተኛ በሆነ ኪሳራ ለመሻገር የሚያስችል መሆን ይኖርበታል ብዬ አምናለሁ። በዚህ ረገድ በራሴ ግንዛቤ እና ከሰዎች ጋር ባደረግኳቸው ውይይቶች ላይ ተመስርቼ የደረስኩበትና መፍትሔ ለማስገኘት ይጠቅማል ብዬ ያመንኩበት አንድ ሃሳብ አለኝ። ይህም የቫይረሱ ተጠቂዎች በተገኙባቸው ከተሞች ብቻ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጆ total lockdown ማካሄድ ነው።
ይህ አዋጅ የሚተገበረው በመንግስት ብቻ አይደለም። የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ሁሉ በትግበራው ይሳተፋሉ። እነዚህም አካላት መንግስት፣ የንግዱ ህብረተሰብ አባላት (ነጋዴ ግለሰቦችና ካምፓኒዎች)፣ በሀገሪቱ የሚንቀሳቀሱ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ለጋሽ ድርጅቶችና ሀገራት፣ የሃይማኖት መሪዎችና ታዋቂ ግለሰቦች፣ በውጪ የሚኖረው ዲያስፖራ እና መላው ህብረተሰብ ናቸው።
—-
በtotal lockdown ስር በሚቆዩት ከተሞች የሚከናወኑ ዋና ዋና ስራዎች የሚከተሉት ናቸው።
ሀ/በመንግስት በኩል
1. ህብረተሰቡ እጅግ አስፈላጊ ያልሆነ ጉዳይ ካልገጠመው በስተቀር ከቤት እንዳይወጣ መከልከል
2. አሁን ያለውን የምርመራ አቅማችንን በማሳደግ በከተሞቹ የሚኖረው ህዝብ በሙሉ እንዲመረመር ማድረግ
3. በበሽታው ተጠቂ ሆነው ከሚገኙት መካከል አቅማቸው የማይፈቅደው እየተለዩ በነፃ እንዲታከሙ ማድረግ
4. የገቢ ምንጫቸው ዝቅተኛ የሆነ ቤተሰቦችን ለይቶ ለኑሮ የሚያስፈልጉ መሰረታዊ የምግብና የንጽህና ሸቀጦችን ማቅረብ፣ ለዚህ ከሚያስፈልገው በጀት ቢያንስ 30% የሚሆነውን መመደብ
ለ/የንግዱ ህብረተሰብ አባላት የሚሰሯቸው
1. መንግስት በሚያቀርበው ጥሪ መሰረት በlockdown ስር በሚቆዩት ከተሞች ለሚኖሩት ዝቅተኛ ወገኖች መመገቢያና ህክምና የሚውል የገንዘብና የቁሳቁስ መዋጮና ድጋፍ ማድረግ
2. መንግስት ለሚያቀርባቸው ሌሎች ጥሪዎች ምላሽ መስጠት
ሐ/ዲያስፖራው የሚሰራቸው ስራዎች
1/መንግስት በሚያቀርበው ጥሪ መሰረት በlockdown ስር በሚቆዩት ከተሞች ለሚኖሩት ዝቅተኛ ወገኖች መመገቢያና ህክምና የሚውል የገንዘብ መዋጮ ማድረግ
2/ባላቸው እውቀትና የስራ ልምድ በዘመቻው መሳተፍ
3/የውጪ ድርጅቶችን፣ ምሁራንና ታዋቂ ግለሰቦችን ሎቢ በማድረግ ኢትዮጵያ ለዘመቻው የሚያስፈልጉ ድጋፎችን እንድታገኝ መርዳት
መ/በሀገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች
1/ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ለመመገብና ለማከም በሚከናወነው ተግባር መሳተፍ
2/ለዘመቻው የሚያስፈልጉ የህክምና ቁሳቁሶችን መለገስ
3/ በዘመቻው የሚሳተፉ የህክምና ባለሙያዎችን መመደብ
ሠ/በኮሮና ብዙ ያልተጠቁ ለጋሽ ሀገራትና ዓለም ድርጅቶች
1/የኢትዮጵያን የመከላከል ዘመቻ በገንዘብ፣ በቁሳቁስና በቴክኒክ እንዲደግፉ ማበረታታት
2. በሀገር ውስጥ የሚዋጣው ገንዘብ በቂ ሆኖ ካልተገኘ በረጅም ጊዜ የሚከፈል ከወለድ ነፃ የሆነ ብድር እንዲሰጡ ማድረግ
ረ/የሃይማኖት አባቶች እና ታዋቂ ድርጅቶች
1/ህዝቡ ከኮሮና በሽታ ራሱን እንዲከላከል ማስተማር
2/ሕዝቡ የመንግስትን የlock down ዘመቻ ዓላማ ተገንዝቦ ከቤቱ እንዳይወጣ ማስተማርና መገሰጽ
ሰ/ መላው ህዝብ
1/በሚችለው አቅም ሁሉ በዘመቻው ተሳትፎ ማድረግ (መዋጮ መስጠት፣ የህክምና ቁሳቁስ መለገስ፣ በሙያ በመሳተፍ ወዘተ)
2/ lockdown በሚታወጅባቸው ከተሞች የሚኖረው ህዝብ ከቤት አለመውጣት
3/መንግስት በሚሰጠው መመሪያ መሰረት በየጣቢያው ተገኝቶ መመርመር፣ የበሽታው ተጠቂ ሆኖ ከተገኘ ራሱን ከሌላው ህብረተሰብ መጠበቅ
4/ በኮሮና በሽታ የሚጠረጠሩትንና በመንግስት ያልተመዘገቡትን ለሚመለከታቸው አካላት መጠቆም
5/ የኮሮና በሽታን ለመከላከል የሚያስፈልጉትን ስራዎች ሁሉ በየእለቱ ተግባራዊ ማድረግ (ቤት መቀመጥ፣ እጅ መታጠብ፣ አለመጨባበጥ፣ በቂ ርቀት መጠበቅ ወዘተ)
ይህ lock down ሲተገበር ቀደም ብለው በስራ ላይ የዋሉት ስራዎች ሁሉ (ለምሳሌ ትምህርት ቤቶችና የስፖርት ውድድሮች መዘጋታቸው፣ ከጭነት መጓጓዣዎች በስተቀር በከተሞች መካከል የሚደረገው የትራንስፖርት ግንኙነት መቋረጡ፣ ወዘተ) በነበሩበት ይቀጥላሉ። ነገር ግን የገበያው ሁኔታ እጅግ መሻሻል ይኖርበታል። በሌላ በኩል በlockdown ስር በማይውሉት ከተሞችና ገጠሮች የሚኖረው ህዝብ እስከ አሁን ሲያከናውናቸው የነበሩትን የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ስራዎችን አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል።
ይህ lockdown ለረጅም ጊዜ የሚቆይ አይደለም። ከአስራ አምስት ቀን ለማያንስና ከሃያ ቀን ለማይበልጥ ጊዜ በስራ ላይ የሚውል ነው። ሌሎች ሁኔታዎችን አጥንቶ ቀኑን ማሳጠርም ሆነ ማስረዘም ይቻላል። መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በስራ ላይ በሚውልበት ጊዜ ብቻ ተግባራዊ የሚሆን ደንብና መመሪያ ማውጣት ይጠበቅበታል (አዋጁ በሚተገበርበት ጊዜ አስፈላጊ የምግብ ግብአቶችን ደብቆ እጥረት እንዲፈጠር በሚያደርጉት እና የመሸጫ ዋጋ በሚጨምሩት ላይ የሚጣል ቅጣት ተደንግጎ ይወጣል)።
እዚህ ላይ መሰረታዊውን ነጥብ እንዳትስቱ ይፈለጋል። የlock down እርምጃ የሚታወጀው የቫይረሱ ተጠቂዎች በተገኘባቸው ከተሞች ላይ ብቻ ነው። ሌሎች ከተሞችና ገጠሮች በሽታውን በመከላከል ላይ ቢሳተፉም በlockdown ስር አይካተቱም።
 ከላይ የተጠቀሱት ባለድርሻ አካላት ይህ በተወሰኑ ከተሞች ላይ የሚተገበር የአጭር ጊዜ lockdown ቢቀርብላቸው ይደግፉታል የሚል እምነት አለኝ። ለምሳሌ ካለፉት ሁለት ሳምንታት ጀምሮ አብዛኞቹ የሀገራችን ነጋዴዎች ስራቸውን እየሰሩ አይደለም። በዚህም የተነሳ ወጪ እንጂ ገቢ የላቸውም።
እነዚህ ነጋዴዎች በየቀኑና በየወሩ የሚከፍሏቸው ክፍያዎች አሉ። እያንዳንዱ ነጋዴ ለግሉና ለቤተሰቡ የሚያወጣቸው ብዙ ወጪ ያወጣል። ለንግዱ ለሚያስፈልጉ ግብአቶች (የቤት ኪራይ፣ የመብራትና የውሃ፣ እና ሌሎች ) ወጪዎችን ያወጣል። ለመንግስት የሚገብረው ግብርም አለ። የባንክ እዳ ወስዶ ከሆነ ለእርሱም ያስባል። እነዚህን ሁሉ ማሟላት የሚችለው እንደልቡ መንቀሳቀስ ሲችል ነው። አሁን በምናየው ሁኔታ ግን ወጪዎቹ ናላውን አዙረውት በዓመታት ልፋት ያፈራው ጥሪት ሊያልቅበት ይችላል። ስለሆነም ለአጭር ጊዜ ለሚተገበረው total lockdown ዘመቻ የሚችለውን እንዲያዋጣ ቢጠየቅ ይህንኑ አድርጎ ወደ ስራው መመለስ ነው የሚፈልገው። ስለሆነም ሃሳቡ ተቀባይነት የለም ብሎ ከመሞከር መቦዘን አያስፈልግም።
እንግዲህ ጠቃሚ የመሰለኝን የመፍትሔ ሃሳብ አቅርቤአለሁ። እልቂትና ረሃብን ማስቀረት የሚቻለው በእንዲህ ዓይነት ዘዴ ነው የሚል እምነት አለኝ። እንዲህ ካልተካሄደበት በቀር አሁን ባለው መንገድ የትም መድረስ የሚቻል አመስልም። በዚህ ላይ መወያያትና ጉዳዩ ሃሳቡን ወስዶ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ወገኖች ማቅረብ ይቻላል።
Filed in: Amharic