>
5:13 pm - Sunday April 19, 4246

ድህረ-ኮሮና እና የአማራ ህዝብ ዕጣ ፈንታ (ዴቭ ዳዊት)

ድህረ-ኮሮና እና የአማራ ህዝብ ዕጣ ፈንታ

ዴቭ ዳዊት
ዓለም ስለኮሮና ወረርሽኝ እያወራ መሽቶ በሚነጋበት፣የሀገራት የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እንደ አርክቲክ በረዶ በቀዘቀዘበት በዚህ ወቅት የሮዝሻይልድ መንበር በሆኑት ኑዮርክ፣ፍራንክፈርት እና ለንደን ማህፀን ውስጥ የድህረ-ኮሮና ዓለማቀፍ ዕጣ ፈንታን የሚወስን ፅንስ እየተገላበጠ ይገኛል። ደግሞም በቅርቡ ይወለዳል።
 በፋይናንስ ተቋማት ቀውስና በኢኮኖሚ መጫጨት (Economic shrinkage) መዳህ (crawling) ጀምሮም መንግስታትን እስከማፈራረስና ከዚያ ሲከፋም ሀገራትን እስከመበታተን ይሄዳል። ይህ ሊመጣ ያለው እውነት ነው!
ይህ የኢኮኖሚ መፋፋት-መጫጨት ዑደት (Boom and Bust Cycle) አዲስ ክስተት አይደለም። ከኢኮኖሚ ፋይዳው ይልቅ ከዘመናት በፊት የምዕራብ ሀገራት መንግስታትን ምርኮኛ ያደረጉ ጥቂት የተመረጡ አለማቀፍ ገንዘብ አታሚዎች (የሀያላኑን ሴንትራል ባንክ የሚዘውሩ ባለፀጎች! ለምሳሌ የአሜሪካንን የመገበያያ ዳላር የሚያትመው የ13 ግለሰቦች ንብረት የሆነው ፌደራል ሪዘርቭ የተባለው ተቋም ሲሆን ከዚህ ውስጥ የ56% ባለቤትነት ድርሻ ያለው አጠቃላይ ሀብታቸው በትሪሊየን ዳላር የሚቆጠረው የሮዝሻይልድ ቤተሰብ ነው) ፖለቲካውን ከሚዘውረው ስውር እጅ ጋር በመቀናጀት ይህንን አለም ወደሚፈልጉት ቅርፅና አቅጣጫ የሚቀይሩበት የፖለቲካ መሣሪያ ነው። ከዎተር-ሉ ጦርነት እስከ ሳራዬቮው ግድያ፣ ከኦቶማን ኢምፓየር መበታተን እስከ ኦስትሮ-ሀንጋሪ ኢምፓየር መፍረስ፣ከእስራኤል መመስረት እስከ ኮሪያ መከፈል፣ከራሺያ አብዮት እስከ ሂትለር መነሳትና መውደቅ፣ከሶቭየት መውደቅ እስከ አረብ ስፕሪንግ /የአረብ አብዮት/ ካሉ አለማቀፍ ክስተቶች ጀርባ የነበረው ይኸው ዑደት ነው።
የኢትዮጵያ መንግስታትም የዚህ ዑደት ሰለባ ሆነው በታላቅ መውደቅ ተሰባብረው አልፈዋል። ለምሳሌ የሀይለስላሴን መንግስት እንዲሽመደመድ የወዲያው-ምክንያት (immediate factor) ከሆኑት ዋነኛ ምክንያት አንዱ የአረብ-እስራኤል የዮምኪፑር ጦርነትን ተከትሎ የአረብ ሀገራት በነዳጅ ምርት አቅርቦት ላይ ያደረጉት ማዕቀብ በአጠቃላይ አለማቀፍ ኢኮኖሚው ላይ ያሳደረው ጫና ኢትዮጵያንም ሰለባ ስላደረጋት ያንን ለመቋቋም በሚል የንጉሡ አስተዳደር በነዳጅ ዋጋ ላይ ያደረገው የዋጋ ጭማሪ እና የኑሮ መናር የንጉሡን የግማሽ ክፍለዘመን መንግስት ግብዓተ መሬት አፋጥኖታል።
የደርግ ውድቀትንም ሰፋ አድርገን ከአለማቀፍ ሁኔታዎች አንፃር ብንፈትሸው የዚሁ ዑደት ሰለባ ሆኖ የፈረሰ መንግስት ነው። እንደሚታወቀው ደርግ የሶቭየት ኅብረት ሳተላይት ጥገኛ መንግሥት ነው። ወደስልጣን በመጣ በአራተኛው ዓመት የሶቭየት መንግሥት አሜሪኖች ባጠመዱለት የአፍጋኒስታን ጦርነት ራሱን ማገደ። ያ በሆነ ማግስት አሜሪካ በጦር መሣሪያ፣ ሳዑድ አረቢያ ሙጃሂድኖችን መልምሎ በማቅረብ ለሶቭየት ቀዩ ጦር የእግር እሳት ከመሆን አልፈው ከዎልስትሪት የተነሳው የፋይናንስ ተቋማት ቀውስና የኢኮኖሚ መጫጨት የነዳጅ ዋጋን ቁልቁል አወረደው። አብዛኛው ገቢዋን ከነዳጅ የምታገኘው ሶቭየት ኢኮኖሚዋ ሲደቅ  ከአፍጋኒስታን በሽንፈት ከመውጣት አልፎ ከምስራቅ ጀርመን እስከ መንግሥቱ ሀይለማርያም ድረስ ያሉ ሳተላይት ወዳጆቿን አየር ላይ ጥላ በራሷ ጉዳይ ተጠመደች። ከብሬዥኔቭ ሞት በኋላ የተተኩትና ሞት በየተራ የወሰዳቸው ዩሪ አድሮፖቭም ይሁኑ ኮንስታንቲን ሼርኔንኮ እንዲሁም ለውጥ ብለው ጀምረው በሀገር ማፍረስ የደመደሙት ጎርባቾቭ ለደርግ መንግስት ጀርባቸውን ስለሰጡት ጠንካራ አለማቀፍ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ድጋፍ አጥቶ፣ ይይዝ ይለቀውን እንደሻተ ሲወዛገብ በአንፃሩ እንደ አማራ አቆጣጠር እስከ 1980 ዓ.ም ድረስ እዚህ ግባ የሚባል  ድል አስመዝግቦ የማያውቀውን ይልቁንም ባንክ በመዝረፍ ወንጀል ተሰማርቶ የነበረውን የትግሬ ቡድን የአሜሪካ መንግስት አደራጅቶ እና ነፍስ ዘርቶበት በሶስት ዓመት ውስጥ ለምኒልክ አልጋ አበቃው።
አንድ ሊሰመርበት የሚገባው ጉዳይ ቢኖር በሁለቱም መንግስታት ውድቀት ዋዜማም ይሁን ማግስት የአማራ ህዝብ ዓለማቀፋዊውን ሁኔታ ገምግሞ ከራሱ ነባራዊ እውነታ ጋር በማጣጣም ወደፊት እንዲራመድ የሚያስችለው አደረጃጀትም ይሁን ንቃተ ህሊናን ባለማዳበሩ ከፍተኛ ዋጋ ከፍሏል።
ዛሬ ደግሞ ሌላ ገፅታ ያለው በመከራ የሚወለድ ዓለም እየመጣ ነው። እንደ ዓይን ጥቅሻ ቅፅበታዊ ሳይሆን አዝጋሚ ነው። በ2008 በፍራንክፈርት እና ኑዮርክ የጀመረው የፋይናንስ ቀውስ ወደ ኢኮኖሚ መጫጨትና ፖለቲካዊ ቁስ አድጎ የአረብ አብዮትን ለማስጀመር ሁለት ዓመት ፈጅቶበታል። የድህረ-ኮሮና ቀውስም ልክ ከባህር ወለል በታች በመሬት ንጣፎች መካከል እንደሚከሰት የቴክቶኒክ መንሸራተት ያለ ነው። ያ ርዕደ ንጣፍ አሁን ተከስቷል። ዛሬ እየሆነ ያለው ርዕደ ንጣፉን ተከትሎ ራሱን ለትልቅ ጥፋት እያሳደገና እያዘጋጀ ያለው የሱናሚ ማዕበል እያደገ በአስፈሪ ፍጥነት መምጣት ነው። እኛም ዛሬ ላይ ሆነን ልንጠይቅ የሚገባን በዛሬው ቁመናችን የአማራ ህዝብ ለእንዲህ አይነት ቀውስ ዝግጁ ነው ወይ? የሚለውን ነው።
ትግሬና ኦሮሞ በሀይለስላሴ መንግሥት መውደቅ ዋዜማ የተሻለ ራሳቸውን የማወቅና የብሔርተኝነት ግንዛቤ ነበራቸው። በዚህም እርሾ ላይ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ካፒታላቸውን እያሳደጉ ሄደው በደርግ ሥርዓት መውደቅ ዋዜማ የሀገሪቱን ዕጣ ፈንታ በመወሰን ረገድ የተደራጁ ወሳኝ ሀይሎች ሆነው ብቅ አሉ። በሂደቱም ዛሬም ድረስ የሚመፃደቁበትን ፖለቲካዊ ድል ከማግኘታቸውም በላይ በታሪክ የእነሱ ያልሆኑ ይዞታዎችን ተቀራምተው ሰፋፊ ግዛቶችን ወረሱ። በአንፃሩ  የአማራ ህዝብ ወጣት ልጆቹን በደርግና በኢህአፓ ጥይት ከማጣቱም በላይ በትርፍ የከተማ ቤት አዋጅና መሰል ህጎች መቆርቆዙ ሳያንስ ፥ በድህረ ደርግ ማግስት በወያኔ ትግሬ መሪነት በአራቱም አቅጣጫ ተወጥሮ በእሳት ዠንዠር ሲገረፍ እነሆ ለሶስት አስርታት ጥቂት-ጉዳይ ሆኖት ሌላ አስፈሪ ዓለማቀፍ ማዕበል ከፊቱ እየመጣ ነው።
በድህረ-ኮሮና ማዕበል ምክንያት  ለወትሮው አንድ ሐሙስ የቀረው የማዕከላዊ መንግስት፥በዚህ ደረጃ የሚከሰት የኢኮኖሚ ቀውስና ለዘመናት ሲብላላ የኖረው የፖለቲካ ተቃርኖ የሚፈጥረውን ንዝረተ-ሞገድ /Shockwave/ የሚቋቋምበት አቅም ይኖረዋል የሚል እምነት የለኝም። ለዚህ መነሻ የሆነኝ ደግሞ በስልጣን ላይ ያለው ፋሽስታዊው የኦሮሞ መንግስትም ይሁን በሰሜን አድፍጦ ያለው የአማራ ሕዝብ የምንጊዜም ጠላት የሆነው ወያኔ ትግሬ የሁለት ሀገረ-መንግስት እሳቤን ስሌት ቀምረው ብዙ የተጓዙ በመሆኑ በውጤቱ አትራፊ እንጂ ለኪሳራ የማይዳረጉበትን መደላድል በመፍጠራቸው ነው።
በተቃራኒው ብአዴንና ለብአዴን ዕድሜ መራዘም ትልቁን አስተዋጽኦ እያበረከተ የሚገኘው በጭምብልና በግላጭ ያለው የዳያስፖራ ከዳሚ ካድሬ የአማራን ሕዝብ የስንግ ይዘው በጎጥ በመከፋፈል ህዝባዊ አንድነቱን በመሸርሸር፣ የብሔር ንቃተህሊናውን እንዳያዳብር በማሸማቀቅ፣ ማህበራዊ ስክነት አግኝቶ ዛሬን እየኖረ ስለመፃዒ ዕድሉ እንዳይመክር ጦር ሰራዊት ከእነብረት ለበስ ተሽከርካሪው ሰፍሮበት መንግስታዊ ሽብር እየተፈፀመበት ይገኛል። የእነዚህ ነገሮች ድምር ውጤት በድህረ-ኮሮና በሚፈጠረው ዓለም ውስጥ አማራን በካርታ ላይ ፈልጎ ማግኘት ወደማይቻልበት ደረጃ እንድንደርስ የሚያደርግ ነው። ስለ አማራ ህዝብ ይመለከተኛል የሚል ግለሰብም ይሁን ቡድን አልያም አደረጃጀት ይህንን ጉዳይ በቸልታ ሊያየው አይገባም። በአማራዊ አንድነታችን ላይ ብዙ መስራት ይጠበቅብናል፤ ድህረ-ኮሮና ይዞ የሚመጣውን ማዕበልና መመሰቃቀል እንዴት መሻገር እንዳለብን በስክነት መምከርና መዘጋጀት አለብን። ብአዴንና ወደረኛ ካድሬዎቹንም ጥግ ማስያዝ የምንችለው፥ ስለ አንድ አማራ ህዝብ ይመለከተናል ብለን የምናምን እኛ በዚህ ረገድ ብዙ ርቀት መጓዝ ከቻልን ብቻ ነው።
ከነገው ማዕበል እንደ ህዝብ ለመትረፍ ዛሬ ላይ ሆነን ነገአችንን እንስራ!!!
አማራዊ አንድነት ይለምልም!
Filed in: Amharic