>

ጌታ ሆይ እባክህን አሁን አድነን!!! (ገነት ዮሀንስ)

ጌታ ሆይ እባክህን አሁን አድነን!!!

ገነት ዮሀንስ
 
ሆሳዕና ለወልደ ዳዊት፣ ሆሳዕና በአርያም 
ዮሐ ፲፪ ÷ ፲፬ (12 ÷13 )
ታላቁ ፆም (የአብይ ፆም) በገባ በስምንተኛ  ሳምንት እሁድ ሆሳዕና ይባላል። ይህ እለት ሰንበት እሁድ የዘንባባ እሁድ ተብሎ ይጠራል። ሰዎች በሚንቋት አህያ ከአህያዋም በልጇ ሁርንጫ ጀርባ ተቀምጦ ጌታችን  ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ሳምንት በእለተ ሰንበት እሁድ ወደ ኢየሩሳሌም ገባ። ጌታችን መድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያዋ ሁርንጫ ጀርባ ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ ሕዝቡ ዘንባባ ይዘው፣ ዘንባባ አንጥፈው ተቀበሉት። “ሆሳዕና ለወልደ ዳዊት፣ ሆሳዕና በአርያም” እያሉ በመዝሙር ተቀበሉት ። ዮሐ ፲፪ ÷ ፲፫ ( 12÷13 )
የዘንባባውን እለት ዝማሬውን እና አቀባበሉን ለማስታወስ  ታላቁ ፆም በገባ በስምንተኛው ሳምንት እለተ እሁድ  “ሆሳዕና” ተብሎ ተሰይሟል ይጠራልም። ዘካርያስ በተናገረው ትንቢት መሰረት ጌታችን ትህትናውን ለመግለጥ በአህያና በውርንጫይቱ ላይ ተቀምጦ ከቢታንያ ወደ ኢየሩሳሌም ገባ። ዘካ ፱ ÷ ፱ ( 9÷9 ) ዮሐ ፲፪÷ ፲፭ (12÷15 ) ዮሐ ፳፩ ÷ ፭ ( 21÷5 )
ሆሳዕና ማለት አፅናናን፣ ጌታ ሆይ እባክህ አሁን አድነን ማለት ነው። ሆሳዕና ብዙ ትርጉም ቢኖረውም ሁሉም ወደ አንድ ሀሳብ ያዘሉ ናቸው። መዳኒት ማለት ነው። ጌታችን ኢየሱስ ሲሉት መዳኒት ሲሉት ነው። አዳኝ ማለት ነው።
 ኢያሱንም ህዝበ እስራኤል ከግብፅ ባርነት ወጥተው ወደ ተስፋው ምድር ሲሄዱ ከጠላት ጦር እየመከተ ድል እያደረገ ይመራቸው ነበርና መዳኒት ሲሉ ኢያሱ አሉት። ሆሳዕና አዳኝነቱን ሲገልፁበት ዳዊት በመዝሙሩ “አቤቱ እባክህ አሁን አድን፣ አቤቱ እባክህ አሁን አቅና” መዝ 117÷25 ብሎ በመዝሙሩ እንዳመሰገ እነሱም ጌታ ሆይ አሁን አድን፣ አሁን አቅና የሚል ተማፅኖን በዝማሬያቸው አሰምትዋል ። ህዝቡ ጌታችን ወደ ከተማቸው ሲገባ ሆሳዕና በአርያም ማለታቸው ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለምም በወዳኛው አለምም ተስፋቸው መሆኑን ሲገልፁ ነው።
የዘንባባ ትርጎሜ
ዘንባባ ተወዳጅ ዛፍ ነው። “ወደ ዘንባባ ዛፍ እመጣለሁ ጫፎቻንም እይዛለሁ” መኃ ፯ ÷ ፱ ( 7÷9 ) ጠቢቡ ሰሎሞን እንደገለፀው በሌላ መልኩ ጠቢቡ ሰሎሞን እመቤታችንን ያወደሰበት  የዘንባባ ዛፍ በቁመቱ በልምላሜው እጅግ ደስ የሚያሰኝ ስለሆነ እንድህ ሲል ተጠቅሞታል ” ይህ ቁመትሽ የዘንባባ ዛፍ ይመስላል” መኃ ፯ ÷ ፰ ( 7÷8 ) ብሏል። የጠቢቡ ሰሎሞን አባት፣ እንደ ልቤ የተባለው መዝሙረኛው ባለ በገናው ዳዊት ዘንባባ መልካም  ጥሩ ፍሬ በማፍራት አስመልክቶ “ጻድቅ እንደ ዘንባባ ያፈራል” መዝ 92÷12 ብሏል። ዘንባባ የክብር የደስታ መገለጫ ነው። ዮሐንስ በራዕዩ በበጉ በኢየሱስ ክርስቶስና በዙፋኑ ፊት የቆሙትን ጻድቃን ነጭ ልብስ ለብሰው የዘንባባ ዝንጣፊዎችን ይዘው አይቶአቸዋል። ራዕ ፯ ÷ ፱ ( 7÷9 )
ታላቅ ደገኛ አባት አብርሃም በደከመ ጊዜ እግዚአብሔር አስቦት ከመካን ሚስቱ ሳራ ይስሀቅን ሲያገኝ በደስታ ሰከረ። አብርሃም ከዘመዶቹ ተለይቶ አምላኩ ባዘዘው መንገድ ሲሰደድ፣ ከካራን ሲወጣ እግዚአብሔር ቃል ገብቶለት ነበር።  ዘርህን እንደ ምድር አሸዋ እንደ ሰማይ ክዋክብት አበዛልሀለሁ ብሎት ነበር። ቃሉ ይፈፀም ዘንድ ይስሃቅ ተወለደ። ታላቅ አባት አብርሃምም ደስታውን ለመግለፅ ለአምላኩ ምስጋናንም ለማቅረብ የዘንባባውን ጫፍ ያዘ ፣ አመሰገነም። እስራኤላውያን ከባህሎቻቸው አንዱ ዘንባባ ነው። ዘንባባ የሚይዙት እጅግ በጣም ለሚያከብሩት በዓል ነው። ከቢታንያ ወደ ኢየሩሳሌም በአህያዋ ሁርንጫ ተቀምጦ ጌታችን መድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን መግባቱን እንደወደዱትና እንዳከበሩት የገለጹበት ዘንባባ ይዘውና አንጥፈው ሲቀበሉት ነው።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር። 
አሜን
የአመት ሰው ይበለን!!!
መልካም ሆሳዕና!
Filed in: Amharic