>

“ አጋዘን ሲጠግብ . . . ” (የስብሃት ተረቶች!)

“ አጋዘን ሲጠግብ . . . ” 

       የስብሃት ተረቶች!
አሰፋ ሀይሉ
 
ከመጋደም እስከ እንቅልፍ ያለው ርዝመት ትዕግሥቴን ያሳጣኛል፡፡ እገላበጣለሁ፡፡ አሁንም አላደርስህ ቢለኝ ድንገት በተኛሁበት እጄ የደረሰበትን የስብሃት ገብረእግዚአብሔርን ‹‹እግረ መንገድ ቅፅ 1-2›› መጽሐፍ ከመደርደሪያው ጎትቼ ማገላበጥ ጀመርኩ፡፡ እና ድንገት ባጋጣሚ ገጽ 191 ላይ ስብሃት የጻፋትን አንዲት ተረት አገኘሁ፡- “አጋዘን ሲጠግብ የነፍጠኛን ጎጆ ይታከካል!” ትላለች፡፡ የተረቷን ምስል ለአፍታ አሰብኩት፡፡ እና በባከነ ሰዓት… ረዥም ሳቅ! 
 
ጉድ እኮ ነው! እውነትም አንዳንዴ ጥጋብኮ የሚሠራህን ነው የሚያሳጣህ፡፡ እያልኩ መጽሐፌን አጥፌ መብራቱን አጠፋሁ፡፡ ጭለማ ፈገግታዬን ውጦታል፡፡ እንደ አጋዘኑ ያሉ… የጥጋበኞችን ጠብ-ያለሽ በዳቦ ድርጊቶች በጭለማው እያሰስኩ እያሸለበኝ ነው፡፡ “አጋዘን ሲጠግብ  የነፍጠኛን ጎጆ ይታከካል!” አለ ስብሃት? ሆሆሆ…! አይ ስብሃት… መቼም አያልቅበት፣ ይለው አያጣ መቼም እሱ…! ነፍሱ ይማራል?! በደምብ እንጂ! መጠርጠሩስ! ነፍሱን ይማርለት! አሁን በደንብ እያሸለበኝ ነው፡፡ ኧረ እንዲያውም ተኛሁ! 
 
እና ግን በመሐል እንደ ቅዠት የመሰሉ ምስሎች ውል አሉኝ፡፡ በህልሜ ይሁን በውኔ አላወቅኩም፡፡ ካልተሳሳትኩ ምስሎቹ የእነ… አብይ አህመድ፡፡ የእነ.. ለማ መገርሳ፡፡ የእነ… ብርሃኑ ጁላ፡፡ ወዘተ ወዘተ ይመስሉኛል፡፡ ብዙ ነውር አያውቁዎች አብረዋቸው ጉድ ጉድ ሲሉ ይታያሉ፡፡ በጎንደር ላይ ከእነ አዘመቱት ጦራቸው፡፡ ተዋጊዎቻቸው ግብፅን እና ጎንደርን መለየት ተስኗቸው ግራ ሲጋቡ፡፡ ጠላት የቱ ነው? ወዳጅ የቱ ነው? ሲባባሉ ውል አሉኝ፡፡ 
 
በዚያ ሰሞን “ኮሎኔል ደመቀ ና ወንዱ ና ወንዱ፣ ምነው እኚያ እናትህ ደጋግመው ቢወልዱ!” እየተባለ በየአዝማሪው ቤት መሰንቆ ሲዘገንለት የነበረው ያ ኮሎኔል ደመቀ ድንገት ብቅ ብሎ፡- “ተዉ አይሆንም ይሄ ነገር… ጉድ ሳይከሰት በመጣችሁበት እግራችሁ መሰስ ብላችሁ ከጎንደር ውጡ!” ብሎ በወገኑ ላይ የተላከውን የፈረደበት ጦር የወገን ምክሩን መክሯል — አሉ፡፡ የአሉ ዘመን… የዘንድሮ ነገር “አሉ!” ብቻ ሆኖ ቀረ ማለት ነው? ብዬ ጠየቅኩ በሕልሜ፡፡ ያገሩን ጠባይ ቢያውቀው ነው፣ ምን ያድርግ? ግራ የሚያጋባ ጊዜኮ ነው… – ብዬ እያሰብኩ ነው! በህልም ይታሰባል እንዴ? አላወቅኩም፡፡ ለጠገበ ምክር ይሰማዋል ብሎ? ለመሆኑ.. የጠገበ መስሚያ አለው?! አሁንም አላወቅኩም፡፡ “እስቲ ይሁና…!” አሉ እመት ባፈና፡፡ ማየት ነው!
 
አሁን ከሕልሜ ነቃሁ፡፡ ለመጻፍ! ጻፎችና ፈሪሳውያንን የፈጠረ አምላክ ምን ያለ ዝንጉ ነው? ፈጣሪ እንደ ኮሎኔል ደመቀ ያለውን ተኳሽ በፈጠረበት እጁ፣ እንደኔ ያለውን ሞንጫሪ…!  ተኳሽ መሆን ነበር እንጂ በዚህ ጊዜ! አነጣጣሪ! 
 
“የተኳሽ ልጅ ነኝ አነጣጣሪ
ጥይት ተኩሶ ግንባር ፈንጣሪ!
የቀስተኛ ልጅ አልሞ ወርዋሪ
በነፃነት ክብር ሁልጊዜ ኗሪ!
ባባቶቼ ነው በነገብርዬ
ባያቶቼ ነው በነእምዬ!
ደረቴ ሰፋ የቀና አንገቴ
ኢትዮጳዊ ነኝ ደፍሮ ማለቴ!” (ማለት አማረኝ!) 
 
ዳሩ ምን ዋጋ አለው? እየጻፍኩ ነው፡፡ ይሄ አማራ ግን የእውነት… እንዴት ፈረደበት?! ድሮም ሲረገጥ፣ ሲታሰር፣ ሲገደል…፡፡ አሁን የተሻለ ጊዜ መጣልኝ ሲል፣ አሁንም ያው! ጭራሽ የባሰ? ወይስ… “ማንን ታሸንፋለህ?” ቢሉት “ያው ሚስቴን ነዋ!” አለ እንደተባለው ፈሪ አባወራ መሆኑ ይሆን የዚህ “መንግሥት ተብዬው” ነገር?? “አማራው እየተረገጠ ስለኖረ፣ መረገጡን ስለለመደው፣ አሁንም እየረገጥኩት እኖራለሁ!”፣ ያለፈውን “የረግጠህ-ግዛ ሌጋሲ!” ሰጥ ለጥ አድርጌ አስቀጥላለሁ…” የሚል፣ ልክ ያጣ የጅል መፈክር… ወይ የባለጊዜ ማን-አህሎኝነት ይሆን? ወይስ እንዴት ያለ ምን-ይሉኝን የሚያውር ጥላቻ? እንዴት ያለስ ጥጋብና ንቀት? ሆሆሆ…!! ወ…ይ   ጉ…ድ?! 
 
“አጋዘን ሲጠግብ የነፍጠኛን ጎጆ ይታከካል!” አለ ስብሃት? በእርግጥም “የጠገበ አጋዘን የነፍጠኛን ጎጆ ይታከካል!” እንጂ! አጋዘኑን እያየነው?! 
 
ኧረ እርሱ ፈጣሪ ጥጋበኛውን እንዳመጣጡ ይመልስልን?! እንጂ ሌላ ምን ይባላል? 
 
እርሱ ያመጣውን እርሱ ይመልሰው!!
 
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ!
Filed in: Amharic